ማልዶ ከቢሮው የተገኘው የፖሊስ መኮንን የዕለት ስራውን ከመጀመሩ በፊት ከጠ ረጴዛው ያገኛቸውን መዝገቦች ማገላ በጥ ይዟል። ሰሞኑን ለክፍሉ በርካታ ጥቆማዎች መድረሳቸውን ያውቃል። የድብደባና ቤት ሰብሮ ስርቆት እየተበራከተ ነው። ለነዚህና ለሌሎችም ችግሮች ነዋሪውን፣ ማወያየት ግድ ይላል። ለፍርድ ቤት የሚተላለፉና ጉዳያቸው የሚመረመር ቀሪ ፋይሎችም የእሱን ውሳኔ የሚሹ ናቸው።
በአንዳንድ ስፍራዎች ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፊያ የሚፈጽሙ ቀማኞች የተለየ ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል። ለወንጀሎች መበራከት ምክንያት የሆኑ የአንዳንድ ሺሻና ጫት ቤቶች ጉዳይም ትኩረት ሊነፈገው አይገባም። ፖሊሱ መደበኛ ስራውን ከመጀመሩ አስቀድሞ የትናንትናውን ውሎ መለስ ብሎ መቃኘት ጀመረ። በሀሳብ ውጣ ውረድ ተጉዞ ቀና ከማለቱ ግን በዕድሜው ለጋ የሚባል አንድ ታዳጊ ፊት ለፊቱ መቆሙን አስተዋለ።
መኮንኑ ለማለዳው እንግዳ በእጁ ወንበሩን ጠቁሞ አረፍ እንዲል ጋበዘው። ታዳጊው የፖሊሱን ፊት ካየ በኋላ ገፅታው ላይ የተለየ ድንጋጤ መነበብ ጀመረ። በሚንቀጠቀጡ እጆቹ አፉን ለመያዝ እየሞከረ ጥቂት ቃላቶችን ለማውጣት ታገለ። ሁኔታውን ያስተዋለው አዛዥ እንዲረጋጋ ነግሮት በትዕግስት ጠበቀው።
ልጁ እንደምንም ከራሱ ታግሎ ወስጡን ለመቆጣጠር ሞከረ። ጥቂት ቆይቶም ሆነ ያለውን ሁሉ አንድ በአንድ እየዘረዘረ ማስረዳት ጀመረ። በሁኔታው የተደመመው የፖሊስ መኮንን ከታዳጊው አንደበት የሚሰማውን አስገራሚ ጉዳይ አንድም ሳያስቀር በማስታወሻ ደብተሩ ላይ ማስፈር ጀመረ።
ከዓመታት በፊት
መንግስቱ ተወልዶ ያደገው ከአንድ ገጠር ቀበሌ ውስጥ ነው። ወላጆቹ ልጆች ወልደው ከማሳደግ የዘለለ ‹‹እዚህ ግባ›› የሚባል ሀብት የላቸውም። ይህ መሆኑ ደግሞ መንግስቱን ጨምሮ ሌሎች እህትና ወንድሞቹ እንደልጅ የሚገባቸውን ሳያገኙ እንዲያድጉ ግድ አለ። መንግስቱ ዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር እንደእኩዮቹ ትምህርት ቤት ገብቶ ለመማር መጓጓቱ አልቀረም።
የእሱ የተለየ ፍላጎት ግን ብቻውን መፍትሄ አላመጣም። የወላጆቹ እጅ ማጠር ለእሱም አቅም ማጣት ምክንያት ሆኖ ትምህርት ናፋቂውን ብላቴና ከቤት አውሎ የከብቶች እረኛ እንዲሆን አስገደደው። መንግስቱ የከብቶች ጭራ እየተከተለ የህጻንነት ዕድሜውን አጋመሰ። ጥቂት ከፍ ማለት ሲጀምር ግን ልቡ ከፍ እንዳሉት ያገሩ ልጆች አርቆ ማሰብ ያዘ። ጋሞጎፋን ለቆ ወደአርባ ምንጭ ከተማ ሲጓዝ መተዳደሪያውን አላጣም። ከአንድ ሆቴል በአስተናጋጅነት ተቀጥሮ ለኪሱ ገንዘብ ቋጠረ።
አርባምንጭ ያገኛቸው ጓደኞቹ አዘወትረው የሚያወሩት የአዲስ አበባን ህይወት ነበር። የመንግስቱ ጆሮዎች ይህን በሰሙ ጊዜ ይበልጥ ተሳቡ። ልቡ በተለየ ተስፋ ተሞልቶም ስለከተማዋ ቀን ከሌሊት አሰበ። አብዛኞቹ እንደነገሩት በዚህች ከተማ ማንም ጦሙን አያድርም። በኑሮ ፈጥኖ ለመለወጥም ምርጫዎቹ የበረከቱ ናቸው። ብዙ ሲሰማ የቆየው መንግስቱ ልቡ በእውን ወደማያውቃትና ዘወትር ወደሚናፍቃት አዲስ አበባ ርቆ ሸፈተ። የአርባምንጭ ቆይታውን አጠናቆም ወደ አዲስ አበባ ገሰገሰ።
አዲስ አበባ
ከአርባ ምንጭ ወደ አዲስ አበባ ያቀናው መንግስቱ እግሩ ከመኪና እንደወረደ ያገሩን ልጆች አገኛቸው። ይህ መሆኑ የእንግድነት ስሜት ሳይኖረው ከተማውን ለመላመድ ረዳው። ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ከአንድ ታዋቂ ሆቴል በዓሣ ጠባሽነት ተቀጠረ። ውሎ ሲያድር የእጁን ሙያ ያደነቁ የሆቴሉ ደንበኞች ዓሣውን ደጋግመው ተጋበዙለት።
መንግስቱ በሆቴሉ ቆይቶ የጎደለውን ኪሱን በገንዘብ ሞላ። ሌሎች ያገሩን ልጆች በቅርበት እያገኘም ብቸኝነቱን ቀረፈ። አንዳንዴ ገጠር ያሉትን ቤተሰቦች ሲያስብ የልጅነት ልቦናው ርብሽ ይላል። ጥቂት ቆይቶ ወደስራው ሲመለስ ግን ሁሉን ረስቶ ከብዙዎች ሲጫወት ይውላል።
አንድ ቀን መንግስቱ ባልንጀሮቹ አዘወትረው የሚውሉበትን ስፍራ እያሰበ የእሱን ብቸኝነት አስታወሰ። አሁን ያለበት ዓሣ ቤት ተወስኖ የሚውልበት በመሆኑ እንደሌሎቹ ለመውጣት መግባት አያመቸውም። በአንድ ቦታ ዓሣ ብቻ ሲጠብስ ከመዋልም ንጹህ አየር እያገኘ ያሻውን መስራት እንደሚችል ካሰበበት ቆይቷል። ይህን እያሰላሰለ ስራውን ለመልቅቀ የወጠነውን ዕቅድ እውን አደረገው።
መንግስቱ አትክልት ተራ አካባቢ የጀመረው አዲሱ ስራ ተመቸው። ሁሌም ማልዶ እየወጣና አትክልት እየተሸከመ ወደ ታክሲ ተራ ያደርሳል። ረፈድ ባለ ጊዜም በስፍራው የሚደርሱ እናቶችን እየተከተለ በጉልበቱ ያግዛል። በሰራው ልክ የሚሰጠው ክፍያ ደግሞ ለዕለት ጉርሱ በቂው ሆኗል። በአካባቢው ለእሱ አቅም በሚመጥን ክፍያ ምግብ ከሚያዘጋጁ ሴቶች ያሻውን ገዝቶ ይመገባል።
እሱን ጨምሮ ሌሎች ታታሪዎች በአነስተኛ ገንዘብ የሚያገኙትን ሻይ ቡና ፉት እያሉ ትኩስ ድንችና ዳቦ፣ አምባሻና ጢቢኛን ይገምጣሉ። በዚህ ስፍራ ሰርቶ የሚሮጥ ሁሉ ለሆድ የተባለውን አያጣም።
መንግስቱ የአትክልት ተራ ውሎው ሲጠናቀቅ ለአዳሩ ርቆ አይሄድም። ሌሎች እንደሚያደርጉት ሁሉ በአካባቢው ካሉ መጋዘኖች በአንዱ ደርሶ ጎኑን ለዕንቅልፍ ያሳርፋል። ነግቶ የቀጣዩን ቀን ስራ እስኪጀምርም የቀን ድካሙን አሳልፎ በአዲስ ጉልበት ይነሳል። ይሄኔ የትናንትናው ጎዶሎ ላይ የዛሬን አክሎ ነገን ሙሉ ለማድረግ የያዘውን ዕቅድ ያስበዋል ወዲያው አብሮት ያደረው ድካሙ ጥሎት ይሸሽና ውስጡ ለሞቀ የስራ መንፈስ ይነሳሳል።
መንግስቱ አካባቢውን ይበልጥ ሲያውቅ የቋጠረውን ጥቂት ጥሪት ስራ ላይ ለማዋል አሰበ። ወዲያውም ከአትክልት ተራ ያሻውን እየገዛ በትርፍ መሸጥ ጀመረ።ይህኛው ስራም ይበልጥ ተመቸው።በየቀኑ እየገዛ በደህና ዋጋ የሚሸጠው አትክልትም አትራፊ ሆነለት።
መንግስቱ አትክልት ተራ ላይ ስራ ከጀመረ ወዲህ በርካቶችን አውቋል። በተለይ ግን ያገሩን ልጆች ባገኘ ጊዜ ደስታው ወሰን አልነበረውም። በዚህ ስፍራ በርከት የሚሉ የጋሞ ወጣቶች እንደሱ ሰርተው ያድራሉ። አብዛኞቹ በዕድሜ የሚበልጡት ቢሆንም በተለየ ቅርበት አብሯቸው መዋልን ለምዷል፡
የአትክልት ተራና አካባቢው ሁሌም በግርግር ውሎ ያድራል። አብዛኞቹ ሲደክሙ ውለው አረፍ ሲሉም የሚቀማምሱትን አያጡም። የተቀቀለ ዕንቁላል፣ ድንች በዳጣ፣ ዳቦ በሚጥሚጣና ሌላም ቁርስና ምሳቸው ሆኖ በፍቅር ይመገቡታል።
ሚያዚያ 18 ቀን 2010 ዓም
ዕለተ እሁድ ማለዳ መንግስቱ በተለመደ ስራው ላይ አርፍዶ ሲደክም ቆይቷል። ገበያው ጋብ ሲልና ስራው ቀለል ሲልም ሁሌም ጎራ ብሎ ቁርስ ከሚቀምስበት ቦታ ላይ ተገኝቷል። በዕለቱ ሁሌም በቦታው ሻይ ቡና የምታፈላው ደንበኛው በተለ የ ብስጭት ውስጥ ነበረች።
መንግስቱ ከስፍራው መድረሱን ያስተዋለችው ወይዘሮ ቦታ ይዞ ያሰበውን ከማዘዙ በፊት የስድብ መአት አወረደችበት። ጥቂት ቆይታም ለጆሮ የሚከብድ አስደንጋጭ እርግማን አሸከመችው። ጉዳዩ ያልገባው መንግስቱ የሆነውን ለመረዳት ሌሎችን ለመጠየቅ ሞከረ።
ከስፍራው የነበሩ አንዳንዶች ከእሱ ያገር ልጆች አንደኛው በትልቅ ድንች ወርውሮ እንደመታትና በዚሁ ብስጭት እሱንና ሌሎችን እየተራገመች መቆየቷን አስረዱት። በሁኔታው የተጨነቀው መንግስቱ ደንበኛውን ጠጋ ብሎ ሊያረጋጋት ሞከረ። በንዴት የጦፈችው ሴት በቀላሉ መመለስ አልቻለችም።
መንግስቱ ጥቂት ቆይቶ ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለውን በቀለን መፈለግ ያዘ። በቀለ ከእሱ በዕድሜ የሚልቅ ያገሩ ልጅ ነው። መንግስቱ አጠገቡ ደርሶ የፈጸመው ድርጊት ሁሉ ተገቢ እንዳልሆነ ሲነግረው በንዴት መጦፍ ጀመረ። ታናሹ መንግስቱ ግን ከእሱ በሀሳብ በልጦ ሴትዬዋን ይቅርታ ሊጠይቃት እንደሚገባ ደጋግሞ አስጠነቀቀው።
በቀለ የመንግስቱን ልጅነትና የተናገረውን መዝኖ ድርጊቱን ከድፍረት ቆጠረው። ይህን ሲናገር ሌሎች በመስማታቸው ተናዶም በጩኸት አምባረቀበት። በዚህ ብቻ አላቆመም። በእጁ ያጠለቀውን የሹራብ ጓንት አውልቆ ደጋግሞ በቦክስ ነረተው። ምቱን መቋቋም የተሳነው ታዳጊ በተማጽኖ እንዲተወው ለመነው። የዕድሜያቸውን ልዩነት ያስተዋሉ ሌሎችም ከመሀል ገብተው ሊገላግሉ ሞከሩ።
ግልግሉ የበዛበት በቀለ ይበልጥ እልህ እየገባው ሄደ። ይባስ ብሎም የመንግስቱን ሱሪ በላዩ ሸርክቶ ሌሎች እየሳቁ እንዲሳለቁበት አደረገ። መንግስቱ በሆነው ሁሉ አፍሮና ተሳቆ የተቀደደውን ሱሪ ለማሰፋት ሮጠ። በቀለ ግን ርቆ ከመሄዱ በፊት ከኋላው ደርሶ ክፉኛ እየደበደበ አሰቃየው።
ብስጭት
መንግስቱ በበቀለ የተፈጸመበትን ድርጊት ፈጽሞ መርሳት አልቻለም። በተለይ ሱሪውን በላዩ ላይ ቀዶ በሌሎች ያሳቀበትን አፍታ ደጋግሞ ባሰበው ጊዜ እልህና ብስጭት ይንጠው ያዘ። አንገቱን ደፍቶ መሬት እየቆረቆረ የቀን ውሎውን አሰበው። እጅግ ከባድና አሳፋሪ ሆነበት። በቀለ በፈረጠመ ክንዱ ያሳረፈበት ከባድ ዱላ መላ ሰውነቱን እየጠዘጠዘ ሲያሳቃየው ቆይቷል። አሁንም እጅና እግሮቹን እያሻሸ ደጋግሞ አለቀሰ። ጎረምሳው ባለ በሌለ ሀይሉ ያደረሰበትን ጥቃት በቀላሉ መርሳት አልቻለም።
ሌሊት 8፡00 ሰዓት
ውሎውን በለቅሶና ትካዜ ያሳለፈው መንግስቱ ምሽቱንም ከሀዘን ሳይርቅ ከወዲያ ወዲህ ሲል ቆይቷል። ከለመደው የአዳር ቦታው ሌሊቱን አጋምሶ ለአፍታ ሲነቃ ግን በቀለና ጓደኞቹ እሱ ካለበት አካባቢ ከሚገኝ አንድ መጋዘን ውስጥ ስለመኖራቸው አወቀ። ይሄኔ ነገር ሲያብሰለስል የቆየው አዕምሮው በአንድ ጥያቄ ተወጠረ። ጥያቄውን ለራሱ ብቻ ይዞ ማቆየትን አልፈለገም። ፈጥኖ ወደተባለው መጋዘን ተንደረደረ።
በቀለና ጓደኞቹ በአትክልት መጋዘኑ ከሚገኝ የተሞላ ማዳበሪያ ላይ ብርድ ልብስ ደርበው አረፍ ብለዋል። ሌሊቱ ከመጋመስ ቢያልፍም የያዙት ጨዋታ ለዕንቅልፍ የጋበዛቸው አይመስልም። ድንገት የመንግስቱን መድረስ ሲመለከቱ ግን ሁሉም ጨዋታቸውን አቁመው ወደእሱ አፈጠጡ።
መንግስቱ ቀን የዋለበት እልህና ቁጭት እንዳልተወው ያስታውቃል። ቂሙን ስላልረሳ ሰውነቱ እየተንቀጠቀጠ ነው። ከፊት ለፊቱ በቀለን ባየው ጊዜ ውሎውን አስታውሶ ድርጊቱን ለምን እንደፈጸመበት ጠየቀው፤ ሁኔታውን ያየው በቀለ አሁንም በድፍረቱ ተገርሞ ሊሳለቅበት ሞከረ። አብረውት የነበሩትም በሳቅ አጅበው ዳግመኛ ያፌዙበት ያዙ።
መንግስቱ እነሱ እንዳሰቡት ትንሽነቱን ሊያስመሰክር አልፈለገም። ከወዲያ ወዲህ ሲንከራተቱ የነበሩት ዓይኖቹ ከአንድ የብረት መኮትኮቻ ላይ እንዳረፉ በእጁ አፈፍ አድርጎ ወደ በቀለ ጭንቅላት አነጣጠረ። መኮትኮቻው ዒላማውን አልሳተም። የበቀለን ራስ ለሁለት ከፍሎ ከመሬት ላይ ጣለው። በድርጊቱ የደነገጡት ባልንጀሮቹ ተሯሩጠው ሊይዙት ተነሱ። ፍጥነቱን አልቻሉትም ሮጦ አመለጣቸው።
የፖሊስ ምርመራ
በዕለት መዝገቡ የወንጀሉን ድርጊት ያሰፈረው የአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ከሁለት ቀናት በኋላ የተጎጂው ህይወት ማለፉን አረጋገጠ። ድርጊቱን የፈጸመውን ለመያዝም ቡድን አዋቅሮ አሰሳውን ቀጠለ። በመርማሪ ኢ/ር ሲሳይ ተሾመ መሪነት የተጀመረው የፖሊስ ምርመራ በመዝገብ ቁጥር 1277/10 በተከፈተው ፋይል ላይ የዕለት ሁኔታዎችን እየመዘገበ ተጠርጣሪውን መፈለጉን ቀጠለ።
ከቀናት በኋላ ከጋሞጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አንድ የስልክ ጥሪ የደረሰው ፖሊስ ተጠርጣሪው ታዳጊ መንግስቱ ዳኜ በራሱ ፈቃድ እጁን ለህግ መስጠቱን በመግለጽ በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉን አስታወቀ።
ወደኋላ ….
የፖሊስ መኮንኑ የማለዳውን እንግዳ ቃል ተቀብሎ ካጠናቀቀ በኋላ የመንግስቱን ገጽታ አጥንቶ ፍጹም የሆነ ሰላም እንደሚነበብበት ገመተ። መንግስቱ በቀለ መጎዳቱን እንጂ መሞቱን አላወቀም። ሌሊቱን ከስፍራው አምልጦ እንደወጣ ወደ ትውልድ አገሩ ጋሞጎፋ ገሰገሰ። ሁኔታውን ለቤተሰቦቹ አስረድቶም በቀለን አሳክሞ የሚድንበትን ገንዘብ ማሠባሰብ ጀመረ። ጥቂት ቆይቶ ግን የመሞቱን መርዶ ሰማ፤ ለቀናት ከራሱ ጋር ሲሟገት ቆይቶም አንድ ቀን ማለዳ እራሱን ለህግ አሳልፎ ሰጠ።
ውሳኔ
ጉዳዩ በፖሊስ ሲመረመር የቆየው የመንግስቱ ጉዳይ መዝገቡ ተጠናቆ ለዓቃቤ ህግ እንዲተላለፍ ሆኗል። ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ተከሳሹ በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጦ እንዲከላከል ዕድል ሰጥቶታል። ሆኖም መንግስቱ ጥፋቱን ሙሉ በሙሉ በማመኑ በዕለቱ ለመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ቀርቧል። ፍርድ ቤቱ በዋለው ችሎትም ተከሳሹ ይማርበታል ያለውን የአስራ ስምንት ዓመት ጽኑ አስራት በይኖ መዝገቡን ዘግቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
መልካምስራ አፈወርቅ