ጊራና በቀድሞ አጠራር ወሎ ክፍለ ሀገር የጁ አውራጃ በሃብሩ ወረዳ የምትገኝ የገጠር መንደር ነች። ይህች መንደር ጥቅጥቅ ባለ ደን የተከበበችና ምንም አይነት መሰረተ ልማት ያልተዘረጋባት ብትሆንም ቅሉ ከትግራይ፥ ከአፋር፥ ከወልዲያና ከላሊበላ ድርስ እየመጡ በርካታ ሰዎች ለ500ዓመታት ሲገበያዩባት የቆዩባት የገበያ ማዕከል እንደነበረች ይነገራል። ይህች የገጠር ቀበሌ ካፈራቻቸው ብርቱ ኢትዮጵያዊያን መካከል አቶ አብዱራህማን አህመዲን አንዱ ናቸው። በ1960ዓ.ም በዚህች መንደር የተወለዱት እኚህ ግለሰብ ታዲያ እንደማንኛውም የአካባቢው ነዋሪ ከፊደል ጋር የተዋወቁት በቅዱስ ቁርዓን ትምህርት ቤት ነው።ዘመናዊ ትምህርትን የተቀላቀሉትም በመንደሯ ስም በተሰየመው 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ከስድስተኛ ክፍል በኋላ ግን በአካባቢው መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ውርጌሳ ከተማ ሄደው ለመማር ተገደዱ። በውርጌሳም 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደሴ በሚገኘው ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተከታተሉ።
በነበራቸው ቅልጥፍናና ጉብዝና ምክንያት በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ የ1ኛ እና የ2ኛ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፤ በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ገብተው በማኔጅመንት ትምህርት መስክ ዲፕሎማቸውን አገኙ። ትምህርታቸውን በ19 ዓመታቸው እንዳጠናቀቁ የንግድ ሚኒስቴር ተቀጣሪ ሆኑ። በሚኒስቴሩ የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዋና ክፍል ረዳት ሆነው እየሰሩም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው ክፍለ ጊዜ ገብተው በሶሾሎጂ ትምህርት ክፍል ለሦስት ዓመት ከተከታተሉ በኋላ አቋርጠው ደግሞ በፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግኑኝነት ትምህርት ክፍል ገብተው ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ። በዚህም አልተወሰኑም በህግ ዲፕሎማ እና በኢኮኖሚክስ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል። ግብርና ግብዓት ባለስልጣንና ከተማ ፕላን ኢንስቲትዩትና ቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ከሰሩባቸው የመንግሥት ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በፖለቲካው መስክ በቀደሙት ዓመታት ስማቸው ጎልተው ከሚጠሩት አንዱ የሆኑት እኚሁ የዛሬ እንግዳችን ታዲያ ኢዴፓን በወጣትነታቸው ከመሰረቱት ሰዎች አንዱ ሲሆኑ ፓርቲው ከቅንጅት ጋር ሲዋሃድም በማዕከላዊ ኮሚቴው አባል ሆነው የድርጅቱን ማኒፌስቶና ሰነዶችን በማዘጋጀት የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል። በአገርአቀፍና በአዲስ አበባ ምርጫ ተወዳድረው በአዲስአበባ እንዲሁም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ገብተው አገልግለዋል። ከ2002 ዓ.ም በኋላ ግን ከፖለቲካው ራሳቸውን አገለሉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በአማካሪነት እየሰሩ ይገኛሉ።እንዲሁም በተለየዩ ጋዜጦችና ማህበራዊ ሚዲያዎች ያላቸውን ሃሳብና ፖለቲካዊ ትንታኔ በመስጠት እየተሳተፉ አፅተዋፅኦ እያበረከቱ ነው። እንግዳችን አቶ አብዱራህማን አህመዲን በተለያዩ ወቅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር እንዲህ ቆይታ አድርገዋል።
አዲስ ዘመን፡- ፖለቲካውን የተቀላቀሉበትን አጋጣሚ ያስታውሱን እና ውይይታችን ብንጀምር?
አቶ አብዱራህማን፡- ወቅቱ 1991 ዓ.ም አካባቢ ነው፤ በዚያን ጊዜ እኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተማርኩ እያለሁ አንድ ጓደኛዬ ከአቶ ልደቱ አያሌው ጋር አስተዋወቀኝ። በወቅቱ እኔ በጋዜጦች ላይ እፃፅፍ ስለነበር በአገር ጉዳይ ላይ ከልደቱ ጋር ውይይት እናደርግ ስለነበር ይበልጥ እየተቀራረብን መጣን። በዚያን ጊዜ ደግሞ እነ አቶ ልደቱ ከመአአድ ወጥተው የግል ፓርቲያቸውን ለማቋቋም ጥረት እያደረጉ ነበር። ከዚያም በውይይት መግባባት ላይ በመድረሳችን በጋራ ኢዴፓን ወደ መመስረት ሄድን። እናም ኢዴፓን ጥቅምት 20 ቀን 1992 ዓም መሰረትን። የሚገርምሽ ኢዴፓ እንደተመሰረተ የመጀመሪያውን ጋዜጣዊ መግለጫ በፅሁፍ አርቅቄ ያዘጋጀሁትና የመራሁት እኔ ነበርኩኝ።
በዚያው በተቋቋምንበት ዓመት በነበረው አገር አቀፍ ምርጫ ተወዳድሬ በማሸነፌ አዲስ አበባ ክልል ምክር ቤት አገልግያለሁ። በምርጫ 97 ደግሞ የተሳተፍኩት በተወለድኩበት ሰሜን ወሎ አካባቢ ሲሆን በዚያም ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን ችያለሁ። ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2002 ዓ.ም እንደወጣሁኝ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ወጣሁኝ። እኔ ለነገሩ በመጀመሪያም ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ስገባ በአባልነት ለአሥር ዓመታት ብቻ የማገልገል እቅድ ነው የነበረኝ። በእቅዴ መሰረትም በ11ኛ ዓመቴ ላይ ፓርቲውን ለቅቄያለሁ። ከዚያ በኋላ ግን በአገሬ ጉዳይ ላይ አሁንም በተለየዩ መድረኮች ላይ እየቀረብኩ አስተያየት በመስጠትም የተለያዩ ፅሁፎችን በማዘጋጀትም መንግሥት በሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች ላይ በመገኘትም እሳተፋለሁ። ትንታኔዎችን እሰጣለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በወጣትነት ኢዴፓን ከመሰረቱት አንዱ እንደመሆንዎ ፓርቲው ሲመሰረት የነበረው አለማ ምን ነበር? እንደመስራችነትዎ በወቅቱ ፓርቲው ስሙ ልቆ የመውጣቱ ሚስጥር ምንነበር ይላሉ?
አቶ አብዱራህማን፡- እንደነገርኩሽ ኢዴፓ የተመሰረተው በ1992 ነው። በዚያ ወቅት ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ አልነበረም። ይህም ኢዴፓን ገና ሆኖ እንዲወጣት ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ህብረብሄራዊ ሆኖ መውጣቱ ነው። ህዝቡም በዚያን ወቅት ለብሄር ድርጅቶች ፍላጎት አልነበረውም። እንግዲህ ያ ክፍተት በነበረበት ሰዓት ነው ኢዴፓ የተወለደው። ሁለተኛው የኢዴፓ የጥንካሬ ምንጭ የፓርቲው አባላት አቅም፥ ይዘናቸው የተነሳናቸው አጀንዳዎች ማንም ነክቷቸው የማያውቁ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ እንኳ ብጠቅስልሽ የባህር በር ጉዳይ የህዝብ አጀንዳ ቢሆንም እስከዚያ ጊዜ ድረስ ይህንን ጥያቄ የትኛውም ፓርቲ ይዞት አልተነሳም ነበር። እናም ኢትዮጵያ የባህር በሯን እንድታገኝ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥረት እናደርጋለን የሚል ትልቅ አጀንዳ ነበረን። በተጨማሪም በደርግና በኢህአዴግ የተወረሱ ንብረቶች እንዲመለሱ እናደርጋለን የሚል ሃሳብም አንስተናል።
ሌሎችም ትልልቅ ኦኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ነበሩን። ዛሬ ብልፅግና ፓርቲ የወሰዳቸው ብዙዎቹ አጀንዳዎች ያኔ ኢዴፓ ሲያቀነቅናቸው የነበሩ ናቸው። ለምሳሌ ከአንድ ቋንቋ በላይ ብሄራዊ ቋንቋ እንዲኖር ማድረግ የሚለውን አጀንዳ ኢዴፓ በዚያ ወቅት ሲያቀነቅነው የነበረ ነው። በተለይም በአዲስ አበባ ላይ በአሥሩም ክፍለከተሞች ቢያንስ በኦሮምኛ ትምህርት የሚሰጥበት ሁኔታ መኖር አለበት ብሎ ኢዴፓ ያምን ነበር። ስለዚህ ኢዴፓ በዚያ ወቅት እነዚህን የመሳሰሉ አጀንዳዎችን ይዞ መነሳቱ ለፓርቲው ገናነት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቶታል ብዬ አምናለሁ። ሌላው ኢዴፓ በዚያ ወቅት የነበሩት ወጣት መሪዎች ታዋቂነት ባይኖረንም ይዘናቸው የመጣናቸው ሀሳቦች ጠንካራ ስለነበሩ ያለምንም ፍርሃትና በልበ ሙሉነት ኢህአዴግን እንተች ስለነበር በህዝቡ ልቡና በቀላሉ መግባት ቻልን። በወቅቱ ህዝቡ በየቤቱ እየተንሾካሸከ በቁጭት የሚያነሳቸውን ጉዳዮች እኛ አደባባይ መናገራችን፤ ኢህአዴግ በየቦታው የሚያደርጋቸውን ጥፋቶች ነቅሰን በማውጣት ማጋለጥ መቻላችን ከፍተኛ አድናቆት አስቻረን። በአጠቃላይ እነዚህ ሂደቶች ኢዴፓን ገናና እንዲሆንና ተሰሚነት እንዲኖረው ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ይመስሉኛል። ዛሬ ኢዴፓ የነበረው ራዕይ መስመር እየያዘ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- መስመር እያየዘ ሲሉ በራሱ በኢዴፓ ነው ወይስ በሌላ ፓርቲ?
አቶ አብዱራህማን፡- ዞሮ ዞሮ ራዕዩ ዘመናዊ የፖለቲካ ስርዓት እንዲኖር ማድረግ ነው። ዛሬ ገዢው ፓርቲም ራሱን አርሞና የፖለቲካ ፕሮግራሙን ጭምር አስተካክሎ ህብረብሄራዊ ነትን ይዞ ወጥቷል።ይህም የትግል ውጤት ነው። በሌሎችም ፓርቲዎች እንደዚሁ ጎራ እየተፈጠረ ነው። ስለዚህ ዘመናዊ የፖለቲካ ስርዓት በአገራችን እንዲመጣ የሚለው አስተሳሰብ እና የጥላቻ ፖለቲካ እየቀረ የሚሄድበት አቅጣጫ እየመጣ ነው። በሌላ በኩልም የመገዳደል አቅጣጫ እና ጫካ ገብቶ በጦርነት ትጥቅ ትግል አድርጎ የመምጣት ሂደት እየቀረ ነው። ዛሬ የትጥቅ ትግል የሚያደርግ ፓርቲ የለም። ከዚህ ቀደም የትጥቅ ትግል አጀንዳ የነበራቸውና በውጭ የነበሩ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ዛሬ ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል። ስለዚህ ይሄ የኢዴፓ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ፓርቲዎች አላማና አስተሳሰብ ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- ከ1997 ወዲህ ደግሞ ፓርቲው እየተዳከመ መጥቷል፤ በእርሶ እምነት ለመዳከሙ አብይ ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ አብዱራህማን፡- እንደሚታወቀው እንግዲህ ኢዴፓ በ1992ዓ.ም ተመስርቶ በዚያው ዓመት ባደረገው ውድድር አዲስ አበባና በዙሪያዋ ተወዳድሮ ነበር። በወቅቱ ሰበታ ላይ ባያሸንፍም በአዲስ አበባ ላይ ካቀረብናቸው 50 የሚደርሱ እጩዎች 16ቱ አሸንፈዋል። ሁለቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ቱ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት አልፈው ነበር። ልብ በይ እንግዲህ ፓርቲው ይህንን ያደረገው በተመሰረተ በሰባት ወራት ውስጥ ነው። ይህንን ቁጥር እያሳደግን ብንሄድ በሁለትና በሦስት ምርጫዎች የአገሪቱን የአመራር ቦታ መያዝ እንችላለን የሚል ራዕይም ነበረን። በ1997ቱም ምርጫ አዲስ አበባና ከተሞች ላይ እንደምናሸንፍ እርግጠኞች ነበርን። በተጨማሪም በተለያዩ ክልል ምክርቤቶች ላይ መጠኑ ሰፋ ያለ የምክርቤት አባላት ይኖሩናል የሚል ራዕይ ነበረን።ይሁንና በ1993 ዓ.ም ላይ የአዲስ አበባ ከተማ የወረዳና ቀበሌ ምርጫ ከተሳተፍን በኋላ ኢህአዴግ ከባድ ጫና ያደርግብን ጀመር። በርካታ አባሎቻችንና አመራሮቻችን ታሰሩ። ተንገላቱብን። በተለይም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ረብሻ ማካሄዳቸውን ተከትሎ በረብሻው ተሳትፋችኋል፤ እናንተ ናችሁ ያቀጣጠላችሁት በሚል በርካታ የፓርቲው አመራሮች ታሰርን።
አዲስ ዘመን፡- ግን እናንተ በረብሻው አልተሳተፋችሁም ነበር?
አቶ አብዱራህማን፡- እኛ በፍፁም አልተሳተፍንም! ቦታውም አልነበርንም። በዚያ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አባልም አልነበረንም። ደግሞም አቅማችንም ያን ያህል የተደራጀም አልነበረም። ገና ተመስርተን በሺዎች የሚቆጠሩ አባል እንኳ ማፍራት የምንችልበት ሁኔታ አልነበረም። እነሱ በእንጭጫችን ሊያጠፉን ስለፈለጉ ነበር ያንን ጫና ሲያደርሱብን የነበረው። እነዚህ ነገሮች በውስጣችን ፍርሃት እየፈጠሩብን ሁኔታ ቢኖርም ተቋቁመን መውጣት ችለን ነበር። ከዚያ በኋላ ሌላውና አንዱ አላማችን የተበታተኑትን ፓርቲዎች አንድ ማድረግና ማዋሃድ የሚል ነበርና ከኢዲዩና ከኢህዴግ ጋር ተዋሃድን። ውህደቱን ስኬታማ በሆነ
መንገድ ካካሄድን በኋላ ለ1997 ዓ.ም ምርጫ ከሁለት ዓመት አስቀድመን መዘጋጀት ጀመርን። በዚያ መሰረትም ጥልቅ ይዘት ያላቸውን የፓርቲውን ማብራሪያ ሰነዶች አዘጋጀን። እነዚህ ሰነዶች በኢኮኖሚ፥ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ነገሮችን ያካተቱ ነበሩ። እኛ በዚያ ወቅት ይህንን የመሰለ ሰነድ ማዘጋጀት መቻላችን ዛሬ ድረስ ያስገርመኛል። ምክንያቱም ኢህእዴግ እንኳ መንግሥት ከሆነ በኋላ ነው ያዘጋጀው። ደግሞም አሁንም ድረስ እንደዚህ አይነት ሰነድ ያለው ፓርቲ የለም።
ያንን ሰነድ ካዘጋጀን በኋላ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጥምረት መስራት የሚል ነገር መጣ። በ1996ዓ.ም ህብረት የሚባል ነገር ተፈጠረና ህብረት ውስጥ ገባን። እኛ በወቅቱ ወደ ህብረቱ የገባነው «ወይ ተባበሩ፤ ወይ ተሰባበሩ» የሚል ግፊት ከህብረተሰቡ ስለመጣብን ነው። ይሁንና ህብረቱ ውስጥ ያሉ በውጭ የሚገኙ ሃይሎች ትጥቅ ትግል እናደርጋለን የሚሉም ጭምር ስለነበሩ ከእነሱ ጋር አንድ ላይ ሆኖ መስራቱ ሊያስኬደን አልቻለም። ኢህአዴግም ደግሞ በአንድ እግራችሁ ሰላማዊ መንገድ በአንድ እግራችሁ ትጥቅ ትግል ነው የምታካሂዱት የሚል ነገር ያመጣብናል የሚል ስሜት ስላደረብን ከዚያ ህብረት ወጣን። ከዚያ ህብረት ስንወጣ በኢህአዴግም በኩል በሌሎችም ፓርቲዎች በኩል ከባድ ቅስቀሳ ተካሄደብን። «ፀረ ህብረት ናችሁ» የሚል ነገር መጣ። በዚያ ሁኔታ ላይ እያለን ቅንጅት ውስጥ እንግባ የሚባል ነገር ሲመጣ በተለይ እኔና የተወሰንን አመራር አባላት መግባት የለብንም ብለን ተከራክረን ነበር። አንድም ሆነ ሁለት መቀመጫ እናግኝ ግን ብቻችንን እንሂድ የሚል አቋም ያዝን። በተለይም በዚህ ጉዳይ ላይ እኔ ክርር ያለ አቋም ነበረኝ። ምክንያቱም እዚያ በኩል የነበሩትን ሃይሎች ከፊሎቹ ከእኛ ጋር በአስተሳሰብም፤ በአመለካከትም ልዩነት ስለነበራቸው ነው። አንዳንዶቹ ከተገኘ የትጥቅ ትግሉንም ቢሆን የሚጠሉ አልነበሩም። ስለዚህ ከእነዚህ ሃይሎች ጋር ሥራ መስራት ያስቸግረናል የሚል አቋም ነበረኝ። በቅርብ ጊዜ እንዳውም አቶ ልደቱም በሰጠው ቃለምልልስ በዚያን ጊዜ መግባት የለብንም ያልነውን ሰዎች ይቅርታ ጠይቆናል።
ይሁንና በወቅቱ እንዳልኩሽ የህብረተሰቡ ግፊት ስለነበር ከዚያኛው ህብረት ወጥተን ቅንጅትንም እምቢ ብንል ተፅእኖው የበለጠ ይበረታብናል የሚል ከባድ ክርክር ፈጥሮብን ነበር። እናም ፓርቲውንም ወደ መከፋፈል ይዘን ከምንሄድ የብዙሃኑ ሃሳብ እንቀበል ብለን ብዙዎቻችን ተቀበልንና ቅንጅቱ ተመሰረተ። በነገራችን ላይ ቅንጅቱ ሲመሰረት አራት ተግባራትን ለማከናወን ብቻ ነበር። አንደኛው በአንድ የምርጫ ወረዳ ሳንደራረብ በጋራ እጮዎችን ለማቅረብ ሲሆን ሌላው ደግሞ በጋራ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ተስማምተን ነበር። ሦስተኛው ስምምንታችን ሥራ በጋራ ፋይናንስና ሌሎች የህዝብ ግኑኝነት ስራዎችን እንሰራለን የሚል ሲሆን አራተኛውና የመጨረሻው ሥራ የሆነው ተቀናጅተን በምንሰራቸው ሦስት ስራዎች በምንፈጥረው መልካምና ጠንካራ ግኑኝነት ላይ ተመስርተን ወደ አንድ ፓርቲ እንመጣለን የሚል ነበር። በነገራችን ላይ በወቅቱ ቅንጅት የራሱ የሆነ አላማና ራዕይ ያለው ፓርቲም አልነበረም። በኋላ ኢዴፓ ያዘጋጀውን ማኒፌስቶ ነው የቅንጅት ማኒፌስቶ የሆነው። ከዚያም ከአራቱ ፓርቲዎች አራት፤ አራት ሰዎች ተመርጠው ቅንጅቱን እንዲመሩ ተደረገ። እነዚህ ሰዎች ታዲያ ውሳኔ የሚወስኑት በምርጫ ሳይሆን በመግባባት ላይ ተመስርተው ነበር። አብሮ ከመስራት ባለፈ ውህደት ባልተፈጠረበት ሁኔታ ለህዝቡ ውህደት እንደተፈጠረ አድርገን መግለፃችን ከሰራናቸው ስህተቶች አንዱና ዋነኛው ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በቅንጅት ውስጥ የነበሩት ፓርቲዎች በምርጫው ወቅት ሳይዋሃዱና እውቅና ሳያገኙ ነው ወደ ቅስቀሳ የገቡት እያሉኝ ነው?
አቶ አብዱራህማን፡- አልተዋሃዱም፤ ምንም ውህደት አልነበረም። እንዳልኩሽ አራቱን ጉዳዮች ለመስራት ተቀናጀን እንጂ አንድ ፓርቲ አልነበርንም። እንዳውም ምርጫው ሲያልቅ ቅንጅቱ እንደሚከስም ነው ደንቡ የሚገልፀው። ይህ የተፈራረምንበት ደንብ አሁንም እጄ ላይ ይገኛል። ምርጫውን ያበቃው ግንቦት ላይ ነው ከዚያ በኋላ ቅንጅት ፈረሰ። ከዚያ በኋላ ነው እንደገና ወደ ውህደት ለመምጣት ጥረት ሲደረግ የነበረው። መስከረም 14ቀን 1998 ዓ.ም ላይ እንደገና ውህደት ተመሰረተ ተባለ። በዚያ ወቅት ግን እኛ ኢዴፓን ይዘን ስንሄድ አሁንም እነዚያ ሰዎች በውህደት ሊያሰሩን እንደማይችሉ ስለገባን በስልት ነው ወደ ውህደቱ የገባነው። አስቀድመን ባደረግነው የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ፓርቲያችንን የምናከስመው ውህዱ ፓርቲ በሁሉም ክልል በወረዳ ደረጃ ሲያዋህድ ነው እንደሆነ አቋም ያዝን። ያ ባልሆነበት ሁኔታ ሰርተፍኬታችን መልሱና ፓርቲያችሁን አክስሙ ሲሉን የጉባኤያችንን ውሳኔ ማክበር ስለነበረብን አልተቀበልናቸውም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በመጀመሪያ ደረጃ እናንተ ፓርቲያችሁን ሳታከስሙና ሰርተፍኬታችሁን ሳትመልሱ ወደ ውህደት መምጣት እንደማትችሉ አታውቁም ነበር?
አቶ አህብዱራህማን፡- እናውቃለን። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ጠቅላላ ጉባኤያችን ውሳኔ የምንከስመውና ሰርተፍኬታችንን የምንመልሰው ግን ውህዱ ፓርቲ እሰከታች ድረስ ውህደት መፍጠሩን ስናረጋግጥ ነው የሚል ነበር። አዲስ አበባ ላይ ብቻ ማዕከላዊና ጠቅላላ ጉባኤ ስለተካሄደ ውህደት ተፈፀመ ማለት አይደለም ብለን ስንከራከር እነሱ ግን ሊቀበሉን አልቻሉም።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ የእናንተም ፓርቲ ቢሆን ከልብ ውህደቱን የሚፈልግ ከሆነ እስከታች የማውረዱን ሥራ አብሮ መስራት አልነበረበትም ?
አቶ አብዱራህማን፡- አብረን እንስራ አልናቸው፤ እነሱ ግን አልተቀበሉንም። እነሱ በሩጫ የሚፈልጉት የፓርቲያችንን መክሰም እንጂ ውህደቱን አልነበረም። እኛም እንግዲያውስ ሦ ስቱ ፓርቲዎች ውህደታቸውን ቀጥሉ ብለን ፈቀድንላቸው። የእነሱ አላማ ግን ኢዴፓን ማክሰምና እኛን ከፖለቲካ መድረክ ማባረር ነበረ፤ እኛም ይህንን ስለተረዳን ኢዴፓን ይዘን ቀጠልን። ፓርላማም ገባን።
አዲስ ዘመን፡- ለቅንጅት መፍረስ ከሚሰጡ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ኢዴፓ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ አመራሮች የስልጣን ጥማት ስለነበራቸው መሆኑ ይነሳል። በሌላ በኩልም ኢህአዴግም እጁን ማስገባቱን ይጠቀሳል። እርሶ እነዚህን ሃሳቦች ይቀበላሉ?
አቶ አብዱራህማን፡- ፖለቲካ ውስጥ ሆኖ የስልጣን ጥመኛ መባል በእውነቱ ነውር ነው። ታዲያ ምን ልናደርግ ነው ፓርቲ ውስጥ የገባነው? መንግስተሰማያት ልንገባ ነው? ልናስተምር ነው የገባነው?። ፖለቲካ እኮ ስልጣን የሚገኝበት ቦታ ነው፤ ሌላ ነገር የለውም። ፓርቲ ማለትም መሪዎች ማፍሪያ ስፍራ ነው። እነዚያ መሪዎች ደግሞ ስልጣን ይይዛሉ። እኛም አላማ ስለነበረን እኮ ነው የገባነው። አላማችን ልናስፈፅም የምንችለው ደግሞ ስልጣን ስንይዝ ነው። ስለዚህ የስልጣን ጥመኛ የሚለው ቋንቋ ግልፅ አይደለም። ሌሎቹስ አልተጠሙም ነበር?
አዲስ ዘመን፡- ግን በጠቅላላው የቅንጅት አባላት ዘንድ ሳትመረጡ ነው ወደ ስልጣን መምጣት አለብን የምትሉት?
አቶ አብዱራህማን፡- አይደለም፤ ነገር ግን ኢዴፓ ለሰባት ዓመታት በፓርቲነት ሲታገል የቆየ ነው። መኢአድም ከአሥር ዓመት ያላነሰ ጥረት ሲያደርግ የነበረ ፓርቲ ነው። ኢድሊና ቀስተዳመና ግን ትናንትና የተፈጠሩ ናቸው። ውህደት ሲፈጠር ግን የተደረገው ነገር ከሁለቱ ፓርቲዎች ከእያንዳንዳቸው 12 ሰው፥ ከሁለቱ ደግሞ ከእያንዳንዳቸው 18 ሰው ይመረጥ ተባለ። በዚያ መሰረት እኛም 18 ሰው አዋጥተናል። ከዚያ ሊቀመንበር ኢንጅነር ሃይሉ ሻወል ሆኑ። በእርግጥ እሳቸው ሊቀመንበር በመሆናቸው ቅሬታ አልነበረንም። ምክንያቱም ነባርና በእድሜም የበሰሉ ናቸው። ቀጥሎ ግን ኢዴፓ መሆን ነበረበት። ይሁንና ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አባል ከሆነች ከአንድ ወር በኋላ ነው የፓርቲው ምክትል ተቀዳሚ ሊቀመንበር የሆነችው። ይህ መሆን ነበረበት?
አዲስ ዘመን፡- በምርጫ አይደለም ወደ ስልጣን የመጣችው እያሉኝ ነው?
አቶ አብድራህማን፡- ሦስቱ ፓርቲዎች ተመሳጥረው ባደረጉት ጥረት ነው ወይዘሪት ብርቱካን ያሸነፈችው። ምርጫውን ሆን ብለው ተጣምረው በሴራ ለብርቱካን ሰጧት። ነገር ግን አቶ ልደቱ ነበር በዚያ ቦታ ላይ መሆን የነበረበት። የማይካደው ነገር ያንን ሲያሳጡን አኩርፈናል። ደስተኞችም አልነበርንም። ያንንም ብለን ግን አልወጣንም። ይሁን ብለን ተቀብለነዋል። እንዳልሽው ግን የስልጣን ጥማት ቢኖረን ኖሮ መውጣት ነበረብን አይደል? ግን አልወጣንም፤ ፓርቲውን ይዘን ቀጠልን። የተሰራው ሥራ ትክክል እንዳልነበረ ግን ይታወቃል። አሁን አሁን እኮ ብዙዎቹ ትክክል አለመሆኑን እየተናገሩ ነው ያሉት። በወቅቱ ሴራ መሰራቱን እያመኑ ነው። ስለዚህ ከስልጣን ጋር ተያይዞ የተነሳው ነገር ዝም ብሎ ስማችንን ለማጥፋት እንጂ እውነታውን መሰረት ያደረገ አይደለም። ስልጣን ብንፈልግ ኖሮ ወዲያውኑ እንወጣ ነበር። እኛ ግን አልወጣንም ፤ምክንያቱም ቅንጅቱ እንዲኖር እንፈልግ ነበር።
አዲስ ዘመን-ስለዚህ ለቅንጅት መፍረስ የኢዴፓ አመራሮች ተጠያቂ አይደሉም ?
አቶ አብዱራህማን፡- በፍጹም አይደሉም።በነገራችን ላይ ፓርቲውን እነመኢአድ ሊያፈርሱት ሲሉ እኛ ነን ያዳነው። ስለዚህ እኛን የስልጣን ጥመኞች ናችሁ የሚለው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ማየት ትችያለሽ። ዝም ብሎ የተለጠፈብን ስም ነው። የቅንጅት አመራር የነበሩትና ከኢድሊ ቀስተደመና መኢአድ የመጡ ሰዎች እኛ ከመጣን እንደማናሰራቸውና ጥያቄ እንደምናነሳባቸው ስለገባቸው እኛን ሊያገሉን ፈለጉ። እኛም ያለ ፓርቲ እርቃናችንን ሊያስቀሩን እንደሆነ ስለገባን ተጠነቀቅን። ፈርሰን መቅረት የለብንም ነው። ሰባትና ስምንት ዓመት የለፋንበትን ፓርቲ በትነን እኛም ተበትነን መቅረት አልነበረብንም። እንዳልኩሽ እኛ ከመጀመሪያውኑ መውጫ መንገዳችንን አመቻችተን ነው የወጣነው። ይሄ መታወቅ ነበረበት። ስለዚህ ነው ራሳችንን ያላከሰምነውና ሰርተፊኬታችንን ለምርጫ ቦርድ ያልመለስነው።
አዲስ ዘመን፡- ለቅንጅት መፍረስ የኢህአዴግ ሚና አልነበረውም?
አቶ አብድራህማን፡- ኢህአዴግን ዝም ብለን ሰበብ ማድርግ የለብንም። ኢህአዴግ ግፊት ሊያደርግ ይችላል። ቅንጅት ቢፈርስለት ደስታውን አይችለውም። እንድንኖር አይፈልግም። ኢህአዴግ ለግልም ሆነ ለቡድን ፓርቲዎች ተኝቶ አያውቅም። ግን ለመፍረሳችን ምክንያት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ቅንጅት በምርጫ 97 በምርጫ አሸንፎ እያለ አዲስ አበባን አለመረከቡ አሁን ላይ ሲያስቡት ትክክል ነበር ይላሉ?
አቶ አብዱራህማን፡- በእውነቱ ትክክለኛ እርምጃም፤ ውሳኔም አልነበረም። ቅንጅት ትልቁ የተሳሳተው ስህተት ያ ነው። እንደኢዴፓ ግን እኛ የወሰንነው ውሳኔ ለቅንጅቱ ምክር ቤት አቅርበናል። በመጀመሪያም በአዲስ አበባ ደረጃ ምርጫውን እንደምናሸንፍ እንደ ኢዴፓ እርግጠኞች ነበር። በፌዴራል ደረጃ ግን ጥርጣሬው ነበረን። ሌሎቹ አባላት ግን በጣም በተጋነነ መልኩ በፌዴራል ደረጃ መቀመጫ እናገኛለን ብለው አምነው ነበር። ነገር ግን ስህተት የሆነ ግብ ነበር። እኛ እንዳልነውም ኢህአዴግ ባህሪው አምባ ገነን ስለሆነ ምርጫው ተጭበረበረ። እኛም ብንሆን ከከተማ ውጭ የሆነው ህዝብ ለመድረስ እጮዎችን በሚገባ ማቅረብ አልቻልንም ነበር። ግን አዲስ አበባን አሸነፍን። በኋላም ፤ምክር ቤት እንግባ፤ አንግባ የሚል ውዝግብ በመካከላችን ተፈጠረ።
በወቅቱ ቅንጅቱ የሚመራው በጋዜጦችና በአክቲቪስቶች ስሜት ስለነበር መግባት የለብንም የሚል ውሳኔ ላይ ደረሰ። እንደኢዴፓ ግን ይህንን ስሜት መከተል እንደማይገባ ስንሟገት ነበር። በኋላ ላይ እንዳውም ሄደን ወረዳ እንነጋገር የሚል ነገር መጣ። እኛ ግን የማወያየቱንም ሃሳብ አልተቀበልነውም ነበር። አንድም ውይይት ላይ ኢዴፓ አልተሳተፈም። በሁለተኛ ደረጃ በእኛ በኩል የአዲስ አበባን መቀመጫ እንረከብ የሚል ሃሳብ ነበረን። ባገኘናቸው የክልል ምክር ቤቶችና የተወካዮች ምክርቤት መቀመጫዎች ላይ ባለን የምርጫ ዘመን የዚህን መንግሥት አምባገነንነት ለህዝቡ እናሳይ እንታገል ብለን ነበር። እነሱ ግን በጋዜጣ ይመሩ ስለነበር የእኛን ሃሳብ ሊቀበሉ አልፈለጉም። ፓርቲ ወይም የፖለቲካ መሪ ማለት የህዝብን ስሜት ገርቶ የሚመራ እንጂ ህዝብን እየተከተለ የሚሄድ አይደለም። በዚያ ውቅት ግን ቅንጅቱ የህዝብን ስሜት የሚከተል እንጂ ህዝብን የሚመራ አልነበረም። እኛንም ጭራሽ እንደካሃዲ፥ ከወያኔ ጋር እንዳበርን፥ የመሳሰሉትን ስም ወደ መቀጠል ውስጥ ነው የተገባው።
አዲስ ዘመን፡- ግን እናንተ ከኢህአዴግ ጋር አላበራችሁም? በተለይም ይህ ሁኔታ አመራሮቹ አሁን ድረስ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ለማጣታችሁ ምክንያት አይደለም ይላሉ?
አቶ አብዱራህማን፡- በማበር ከሆነ ከነበረከት ስምኦን ጋር ውስኪ ሲጠጣ የነበረው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ነው እንጂ ልደቱ አያሌው አይደለም። አቶ ልደቱ ከ100 ቀናት በላይ በመኪና ሲከታተሉትና ሲያሰቃዩት ነበር። የሚበላውና የሚጠው እስኪያጣ ተንገላቶ ነበር። በእስርቤት ሲማቅቅና ባዶ እግሩን እስኪተላ ድረስ ሲደበደብ የነበረ ሰው ነው። እስኪ አንዳቸው ታስረው ያውቃሉ? ስለዚህ አምስት ሳንቲም ከኢህአዴግ የተቀበለ የኢዴፓ አመራር እንደሌለ እመሰክራለሁ። እኔም ተቀብዬ አላውቅም፤ አነጋግሮኝም የሚያውቅ የኢህአዴግ አባል የለም። እኔ እንግዲህ ኢዴፓን ወክለን በቅንጅት ውስጥ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ አንዱ ነበርኩ። አነጋግሮኝ የሚያውቅ አንድም ባለስልጣን አልነበረም። ሌሎቹንም ጓደኞቼን አውቃቸዋለሁ እንደዚህ የሚያደርጉ ሰዎች አይደሉም። በተለይም አቶ ሙሼ ሰሙን በቅርበት ስለማውቀው ይህንን የሚያደርግ ሰው አልነበረም። በአጠቃላይ ከኢህአዴግ ጋር አብረዋል የሚባለው ነገር ውሸት ነው። የተነዛብን አሉባልታ ነው። ብንሄድ እንደምንበልጣቸው ያወቁና የፈሩን ሰዎች ናቸው ስማችንን ያጠፉት።
አዲስ ዘመን፡- ፓርቲያችሁ አሁንም ውዝግብ ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል፤ በተለይ የተወሰነው አካል ከኢዜማ ጋር መቀላቀሉን ተከትሎ ጉዳዩ ወደ መክስም እያመራ መሆኑን ሰምተናል። እርሶ እነዚህን ሁኔታዎች ከውጭ ሆነው እንዴት ታዘቡት?
አቶ አብዱራህማን፡- መቼም እኔም ብሆን መስዋትነት የከፈልኩበት ፓርቲ ነውና ህልውናው ቀጥሎ ለውጤት ቢበቃ ደስታውን አልችለውም ነበር። ምክንያቱም የለፋሁበትና የወጣትነት ጊዜዬን ያሳለፍኩበት ፓርቲ በመሆኑ ነው። ሆኖም ግን ቅንጅቱ ጋር የነበረው ኢዴፓን የማጥፋት ዘመቻ አሁንም ቀጥሏል። ያ በመሆኑ ነው ከ22 ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አራት ሰዎች ብቻ ከኢዜማ ጋር የተቀላቀሉት። 18ቱ አሁንም ኢዴፓ ውስጥ ናቸው። ፊርማ አሰባስበው ለምርጫ ቦርድ አቅርበው ነው ፓርቲው አሁንም ህልውናውን ይዞ መቀጠል የቻለው። ስለዚህ በ1998 ዓም አልፈርስ ያላቸውን ኢዴፓ አሁንም ለማፍረስ ነው እየተጣረ ያለው።ይሄ አይጠቅምም። ኢዴፓ የሌለበት ኢዜማ ጠንክሮ ሊወጣ አይችልም። ስለዚህ ኢዴፓን የማፍረስ ትግል ውስጥ ከሚገቡ የራሳቸውን ማጠናከር ነበር የሚገባቸው። ኢዴፓ በኩል ግን አሁንም ጠንክረው እየወጡ ያሉ አዳዲስ ወጣቶች ገብተዋል። እነዚህ ወጣቶች እኛ ልክ ኢዴፓን ስንመሰርት የነበረን ጉልበትና አቅም ነው ያላቸው። በነገራችን ላይ ምን ጊዜም አስተሳሰብን መቅበር አይቻልም። አስተሳሰብን ማፍረስ አይቻልም። ኢዴፓም በመሰረቱ ዝም ብሎ የሚፈርስ ፓርቲም አይደለም። ኢህአዴግን ሲታገል የነበረ ፓርቲ በሌሎች ፓርቲዎች ትግል ይፈርሳል ማለት ዘበት ነው። ባይሞክሩት ይሻላቸዋል።
አዲስ ዘመን- እርሶ በዕቅድዎ መሰረት ከፓርቲው በ11ኛው ዓመትዎ መውጣቶዎትን ነግረውኛል፤ ነገር ግን የወጡበት ወቅት ውዝግብ የነበረበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፈሪ አያስቆጥሮትም?
አቶ አብዱራህማን፡- አይ አይደለም፤ እኔ የወጣሁት ከውዝግቡ በኋላ ነው። እንዳውም በ2002 ዓም ብዙ ሥራ ሰርቼ ነው የወጣሁት። በነበረው ምርጫም ከፍተኛ ድምፅ እንዲያገኝና ስሙን መልሰን ነው ከፓርቲው የለቀቅነው።
አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ተከትሎ ለፖለቲከኞች ምህዳሩ ሰፍቷል ብለው ያምናሉ?
አቶ አብዱራህማን፡- እንግዲህ በተለይ ዶክተር አብይ ስልጣን ከያዙ በኋላ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ተለውጧል። የፖለቲካ ሃይሎች ሃይል አሰላለፍም እየተለወጠ ነው ያለው። የሃይል አሰላለፉን ትልቁን ለውጥ እንዲመጣ ያደረገው ደግሞ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው የአደረጃጀት ለውጥ ነው። ኢህአዴግ በፊት የብሄር ፓርቲዎች የመሰረቱት ድርጅት ነበር አሁን ግን ህብረብሄራዊ ሆኗል። ከዚያ መውጣቱ የአገሪቱን የፖለቲካ አስተዳደር ለውጦታል። ለምሳሌ ኢዴፓ ወይም ቅንጅት ውስጥ የነበሩት ፕሮግራሞች አሁን ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ ሰዎች እያቀነቀኗቸው ነው። ስለዚህ የሃይል አሰላለፉ መለወጡ ትልቅ ለውጥ በአገርም ደረጃ ያመጣል ብዬ አስባለሁ። ሌላው ሁለተኛው ጎራ ከዚያው ከኢህአዴግ የተከፈለው በሕወሃት ስር እየተሰባሰበ ያለ ሌላ ሃይል አለ። እንደምታውቀው ለራሳቸው የፌዴራሊስት ኃይሎች የሚል ስም ሰጥተዋል። እሱም ጥሩ ነገር ነው። እንዳውም ብልፅግናን ፓርቲ የሚፈታተን ጠንካራ ሃይል ቢሆን ጥሩ ነው። ምክንያቱም ሕወሃት ላይ ብቻ እንዳይቀር ስጋት አለኝ። ሌሎች የብሄር ፓርቲዎችም እዛው ጎራ ላይ ተጠናክረው ቢወጡ ጥሩ ነው። ይህም ሚዛኑን እንዲጠብቅ ያደርጋል። ሦስተኛው ሃይል በተቃዋሚው ጎራ በኢዜማ ዙሪያ የተሰባሰቡ ህብረብሄራዊ የሆኑ ፓርቲዎች ደግሞ እንዲሁ ጠንከር ብለው አንድ ላይ ቢሰባሰቡ ጠቃሚ ነው። አራተኛው ጎራ እንደ ኦነግና በኦሮምያ ላይ የሚሰሩ ፓርቲዎችም እንደዚሁ ጠንከር ብለው የተበተነ ሃይላቸውን ማደራጀት ይገባቸዋል። በዚህ መልኩ ቢሰባሰቡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሦስት አራት አማራጭ ሆነው ይቀርባሉ። በቅርብ ጊዜ በሚደረገው ምርጫ ብዙዎቹ ነገሮች ጠርተው የሚወጡበትና የሚከስሙት ከስመው ጠንካሮቹ ጎልተው የሚወጡበት ሁኔታ ነው የሚኖረው።
በነገራችን ላይ በቅርቡ ከሚደረገው ምርጫ ብዙ መጠበቅ የለብንም። በአንድ ምርጫ ብቻ በአንድ አገር ላይ ዴሞክራሲ ሊሰፍን አይችልም። በአሜሪካ 250ዓመት የቆየ የዴሞክራሲ ስርዓት ነው ያላቸው። ይህንን ሁሉ ዓመት አሳልፎ እንኳ አሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ጤናማ የሆነ ምርጫ አካሄድ አለ ማለት አይቻልም። አንዳንድ ጊዜ ምርጫ ይጭበረበራል። ስለዚህ ምርጫ የትም አገር የተሟላ ሆኖ አያውቅም። እኛም ጀማሪዎች እንደመሆናችን ስርዓቱን እያሻሻልነውና እያጠራነው እንሄዳለን እንጂ በአንድ ምርጫ ፍፁም ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሂደት መጠበቅ አግባብ አይደለም።የሚሳካም ነገርም አይደለም። እንኳን እንደኛ መቶ ሚሊዮን አመል ያለው መቶ ሚሊዮን ህዝብ ይዘን እንደጅቡቲ አይነት አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ህዝብ ያላቸው አገራት እንኳ ምርጫ ቢካሄድ መጭበርበሩ የማይቀር ነው። እናም በመጪው ምርጫ ብዙ ነገሮች የሚጠሩበት ሁኔታ ይኖራል እንጂ ፍፁም የሆነ ሂደት መጠበቅ የለብንም ባይ ነኝ። በተለይ የፓርቲዎች አደረጃጀት ጥርት ብሎ የሚያልቅበት ሁኔታ ይፈጠራል ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ እንደህዝብ ተሳትፎ እናድርግ፤ ፖለቲከኞችም ደግሞ በሚገባ ስራቸውን መስራት አለባቸው። ጎራዎቹን መለየት አለባቸው። በየመንደሩ ጓደኛሞች እየተሰባሰቡ ፓርቲ ሟቋቋና ለህዝብ አማራጭ ነን ብሎ በህዝብ ስም መማልና መገዘት መቆም አለበት። በኢትዮጵያ ህዝብ መቀለድ የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- ያንን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለ ብለው ያምናሉ?
አቶ አብዱራህማን፡- አዎ አለ፤ ምንአልባት እንደዕይታችን ሁኔታ ሊለያይ ይችላል። በኢህአዴግ በኩል ጥርት ብሎ ወጥቷል። በህውሃት በኩል የተወሰኑ ሃይሎች ለመሰባሰብ እየሞከሩ ነው። ያ ቢጠናከር ጥሩ ነው።በተቋዋሚዎች ጎራ ገና ሽኩቻነው እያየን ያለነው። በእርግጥ እንደ ኢዴፓና ኢዜማ ያሉ ፓርቲዎች በየግላቸው ከሌሎች ጋር ጥምረት እየፈጠሩ ነው ያሉት። ግን እነዚህ ነገሮች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። አሁን እነዚህ የቤት ስራዎች ሳይሰሩ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አይነት መሆን የለበትም። በእኔ ግምገማ ግን ፖለቲከኞች ስራቸውን እየሰሩ አይደለም። ይህንን ካልሰሩ ደግሞ ምርጫው ላይ ዝም ብሎ ተራ ፉክክር ውስጥ እንዳይገቡ ስጋት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አስቀድመው ሲገልፁ ብልፅግና ፓርቲ ህብረብሄራዊ ነው ብለውኝ ነበር። አንዳንዶች ግን አህዳዊ ስርዓት መልሶ ሊያመጣ ነው እያሉ ይሞግታሉ። በእርሶ እይታ ይህ የሚሆንበት እድል አለ?
አቶ አብዱራህማን፡- እኔ ይቅርታ አድርጊልኝና ይህንን ፍረጃ ያመጣው ሕወሃት ነው። ምክንያቱም ሕወሃት ፓርቲዎችን በመፈረጅ ትታወቃለች። ይህ ኮምዩኒስታዊ ባህሪዋ ነው። ይህንን በማለታቸው ደግሞ እኔ አይገርመኝም። ብልፅግና ፓርቲ አህዳዊ ስርዓት ላምጣ ቢል እንኳ በተቋዋሚው ጎራ የተሰለፉ ሃይሎች አይቀበሉትም። እነኢዜማ ህብረብሄራዊ ናቸው። አህዳዊ ፓርቲን አይፈልጉም።
አዲስ ዘመን፡- ግን እነዚህን ፓርቲዎች ህብረብሄራዊ የሚያሰኛቸው ነገር አለ?
አቶ አብዱራህማን፡- ህብረብሄራዊ ፓርቲ ማለት እኮ ባሉበት የፓርቲ አመራር ሆነው የሚደራጁበት ፓርቲ ማለት ነው። ስለዚህ የእነዚህም ፓርቲዎች አደረጃጀት የሚያሳየው ህብረብሄራዊ መሆኑን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ማለት አንድ የአማራ ክልል ተወላጅ ኦሮምያ ክልል፤ወይም የኦሮሞ ተወላጅ አማራ ክልል ሄዶ ይመራል እንደማለት ነው?
አቶ አብዱራህማን፡- አይደለም! ብዙ ሰው መረዳት ያልቻለው ይህንን ጉዳይ ነው። ለምሳሌ አሜሪካ 50 ግዛቶች ቢኖራትም እያንዳንዱ ፖለቲከኛ የሚወዳደርው ባለበትና በኖረበት ግዛት ነው። እኛም አገር ላይ ተመሳሳይ ነው የሚሆነው። አንድ ሰው በኖረበት ወረዳ ነው የሚመረጠው። ኦሮምያ ክልል የምክርቤት አባል የሚሆኑ ሰዎች (ክልሉ ኦሮሚያ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ) በክልሉና በወረዳው የተመረጠ ሰው ነው ሊያስተዳድር የሚችለው። ስለዚህ እንዴት አድርጎ ነው ከአማራ ክልል መጥቶ ሊያስተዳድራቸው የሚችለው? ሰዎች እንደዚህ አይነት ውዥንብር ሊፈጠርባቸው አይገባም። ምንም አይነት ተአምር ቢመጣ ይህን አይነት ነገር አይከሰትም። የኢትዮጵያ ህዝብ ሊቀበለው የሚችለው ነገር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አስቀድመው በህውሃት ስር የፌዴራሊስት ሃይሎች መጠናከር አለባቸው የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል፤ ይህ መሆኑ ግን ህውሃት የነበረውን አምባገነናዊ ስርዓት ዳግም እንዲመልስና እንዲያንሰራራ እድል ይሰጠዋል የሚሉ ስጋቶች ይደመጣሉ። እርሶ ይህ ስጋት አያሰጋዎትም?
አቶ አብዱራህማን፡- ይህ የሚወሰነው በህዝብ ነው። አስተሳሰብን በጉልበት ማፍረስ የለብንም። ያ አስተሳሰብ ህዝብ በምርጫ ይጣለው። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስፈልገኝ እንደዚህ አይነት አደረጃጀት ነው ብሎ ከመረጣቸው እሰየው ነው!። አላስፈላጊ መሆኑን እያሳየን እንደገና መታገል ነው የሚገባን። ደግሞም ህዝቡ 27 ዓመት አይተነዋል አንፈልገውም ካለ በምርጫ እንደሚጥላቸው እርግጠኛ ነኝ። እንደ አደረጃጀት ግን አመለካከቱ መፍረስ የለበትም፤ መበተንም የለባቸውም፤ ይህንን ስል ሕወሃቶች ጠቃሚ ናቸው እያልኩኝ አይደለም። እኔን ብትጠይቂኝ አንዲት ድምፄን ለማን እንደምሰጥ አውቀዋለው። ለእንደዚህ አይነት አደረጃጀት ድምፄን ሰጥቼ ዳግም መሰቃየት አልፈልግም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ይጠቅመኛል ባለው መልኩ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች ስለሚኖር ሊያሰጋን ሊያስፈራንም አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የትጥቅ ትግል የሚያነሳና የጥላቻ ፖለቲካ የሚያራምድ ፓርቲ የለም ብለውኝ ነበር። እናንተ እና እኛ እየተባበሉ መገዳደልና መፈናቀል ባለበት ነባራዊ ሁኔታ ይህንን ማለት ከእውነታው ማፈንገጥ አይሆንም?
አቶ አብዱራህማን፡- በእኔ እምነት በአዋጅ አውጆ የትጥቅ ትግል አካሂዳለሁ ያለ ፓርቲ ያለ አይመስለኝም። በቀደሙት ዓመታት ግን ነበር። ኦነግ ፥ኦብነግና ግንቦት ሰባት በግልፅ በትጥቅ ትግል የሚምኑና የሚታገሉ ነበሩ። በዚያ ደረጃ የትጥቅ ትግል አደርጋለሁ የሚል እስካሁን አላጋጠመኝም። ሽፍታ ግን እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለ ያልሰለጠነ ማህበረሰብ ባለበት አገር ይቅርና በሰለጠኑት አገራትም ሽፍታ አይጠፋም። አሁንም እንደዚህ አይነት ባህሪ ያላቸው በጎንደርም፤ በትግራይም፤ በምዕራብ ወለጋም አሉ። ወደፊትም ይቀጥላሉ። የሚጠበቁም ናቸው። መካለከያ ሃይሉ ነው ይህንን ሁኔታ ሊያስተነፍስ የሚችለው። ነገር ግን ፖለቲካዬን ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ የለም ብሎ ወደ ትጥቅ የሚገባ የለም። እንደኢሀፓ ያሉ በቀይሽብር ሊጠየቁ የሚችሉ ሰዎች ሁሉ መጥተው የፖለቲካ ትግል እያካሄዱ ነው። ነግር ግን ልሸፍት የሚል እብድ ከመካከላችን አይጠፋም። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ እብዶቻችንን እየመከርንም እየገሰፅንም መመለስ አለብን። ይህን ሁኔታ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚጠቀሙበት አይጠፉም ማለት ግን አይደለም። በተለይም ሕወሃት ብልጥ ፖለቲከኛ ነች። እንኳን ያበደና የተደራጀ ሃይል አግኝታ ሌላውም እንዲሸፍት ገፋፍታ ጠበንጃ ሰጥታ የምትልክ ነች። ምክንያቱም የቀረባት ነገር አለ። የበላይነቷ ስለቀረ መፈራገጧ አይቀርም።
በሁለተኛ ደረጃ ያነሳሽው የጥላቻ ፖለቲካ ነገር በእያንዳንዳችን ስሜት ውስጥ ያሉ ነገሮች ናቸው። ከጥንት ጀምሮ ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ጠላቴ ነው ማለት የተለመደ ነገር ነው። ስለዚህ በርቀት መታየትና መፈራረጅ በባህላችንም ያለ ነው። ይህ ሁኔታ ግን እያደገ ሄዶ በደመኝነት በጥላቻ የሚያስተያየን ከሆነ አደጋ ነው።ይህ ጉዳይ ጥንቃቄ የሚፈልግ ይመስለኛል። በየቦታው የምናየው ጥላቻ የማን ጥላቻ ነው? የሚለው ነገር መለየት አለበት። በእኔ እምነት ይህ ጥላቻ ያለው ህብረተሰቡ ውስጥ አይደለም። እነዚህ አክቲቪስቶች ፥ የተማሩ የሚባሉት ሃይሎችና ፖለቲከኞች ጋር ግን በስፋት ታያለሽ። ሁሉም ማለት ባይሆንም ፅንፍና ፅንፍ ላይ የቆሙ አሉ። ስለዚህ ሁልጊዜ አንድአይነት ነን ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ከሌሎች አገሮች አኳያ ስናየው ግን ይህን ያህል ጠንክሮ የወጣ ፅንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲ አለ ብሎ መውሰድ ይቸግረኛል። የእኛ አገር ፅንፈኝነት በውስጥ ለውስጥ፤ በገደምዳሜ ነው እንጂ የሚሄደው ጎልቶ የወጣ አይደለም። እነዚህን ግን ሌሎቹ የፖለቲካ ሃይሎች ማርገብ ይጠበቅባቸዋል። ህዝቡም ሊያወግዛቸው ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በመንግሥት በኩል ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ አብዱራህማን፡- በገዢው ፓርቲ በኩል በተለይ ዶክተር አብይ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ፓርቲውን በዚህ ደረጃ መለወጥ በራሱ ለእኔ ትልቅ ለውጥ ነው።ኢህአዴግ እንዲህ እንዲሆን እፈልግ ነበር። ምንም አይነት አላማ ቢኖረው በዘር መደራጀት አገሪቱን ሊያጠፋ መሆኑን ተገንዘቦ ፓርቲውን በዚህ ደረጃ ማደራጀት መቻል ትልቅ ለውጥ ነው። ዶክተር አብይ እሳቸው በሚመሩት አመራር ይህ ለውጥ በመምጣቱ እድለኛም ናቸው። በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ስማቸውን በበጎነት እያሰመሩ እያለፉ መሆኑን አይቻለሁ። ዶክተር አብይ ከዚህ በኋላ ምንም ባይሰሩ እንኳን እስካሁን የሰሩት በቂያቸው ነው ባይ ነኝ።
በእርግጥ አሁንም ግን የሚቀሩ ነገሮች አሉ። ሕወሃት መራሹ ኢህአዴግ በነበረበት ጊዜ በርካታ ሰዎች ያለአግባብ ይታሰሩ ነበር። ብዙዎቻችን ብዙ ቀምሰናል። አሁንም ደግሞ የተወሰኑ ወገኖች ተመርጠን ታስረናል የሚሉ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው። በተለይ ከሕወሃት አካባቢ ብዙ ሰዎች እስር ቤት አሉ፤ ለፍርድ አልቀረቡም የሚባል ነገር አለ። ይህም የተደረገው ትግሬ በመሆናቸው እንደሆነ ይነሳል። ይህንን ዶክተር አብይ ማጣራት አለባቸው። ወይም የፍትህ ስርዓቱ ይህንን ኦዲት ማድረግ አለበት። በተጨባጭ ያለአግባብ የታሰሩ ሰዎች ካሉ መታየት አለበት። ከአንድ ዓመት በላይ ምንም አይነት ውሳኔ ሳይሰጣቸው የታሰሩ መኖራቸውን እኛም እናውቃለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ በማሰር ብቻ ሳይሆን የቁም እስርም ሊኖር ይገባል። ሁሉንም ማሰር ላይገባን ይችል ይሆናል። እስርቤት ውስጥ አስቀምጠን በሞራልም፤ በአካልም ከምንገላቸው በውጭ ሆነው ክሳቸውን መከታተል የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለውይይታችን መቋጫ የሚሆን ጥያቄ ላንሳ፤ እርሶ በአሁኑ ወቅት ፓርቲ ውስጥ የመግባት እቅድ የሎትም?
አቶ አብዱራህማን፡- እኔ አስቀድሜ እንዳልኩሽ ፓርቲ ውስጥ ስገባ አምስት ዓመት አገለግላለሁ ነው ያልኩት። ነገር ግን ቢያንስ ሁለት የምርጫ ዘመን ማገልገል አለብህ ስለተባልኩኝ ነው አስር ዓመት የቆየሁት።ከዚህ በኋላ ፖለቲካ ውስጥ የመግባት ሃሳብ የለኝም። ግን ደግሞ የሰው ልጅ የፖለቲካ እንሰሳ ነው። ከፖለቲካ ሊገለል አይችልም። ያለ ፖለቲካ ውሎ ማደር አይቻልም። ምክንያቱም ፖለቲካ ውሳኔ መስጠት አገር ማስተዳደር ነው። ስለዚህ አሁን እኔ ወደ ሽምግልና እየሄድኩኝ ስለሆነ ሰዎችን መምከርና ማማከር ነው ስራዬ መሆን ያለበት።ሌሎችም እኔን አርዓያ ማድረግ አለባቸው ብዬ አምናለሁ። በተለይ በእኔ እድሜ ያሉ ፖለቲከኞች የጡረታ ጊዜያቸውን በፖለቲካ ማሳለፍ አለባቸው ብዬ አላምንም። አሁን ደግሞ ለባለተሮቹ ወጣቶች መተው ይገባቸዋል። ልንሰራበት በምንችለው ጊዜ ነው መስራት ያለብን። ይህ ማለት ግን አገሬን አላገለግልም ማለት አይደለም። መንግስት አምኖብኝ በሚመድበኝ ቦታ ሁሉ ገብቼ ደመወዜንም ቀንሼም ቢሆን ለማገልገል ፍቃደኛ ነኝ። ግን አገሬን ለማገልገል የግድ ፖለቲከኛ መሆን የለብኝም። እኔ በአጠቃላይ አሁን የፓርቲ ባርያ ሆኜ መስራት አይደለም የምፈልገው። በቀሪ ህይወቴ በፓርቲ የመታቀፍ ፍላጎት የለኝም። እነልደቱ ራሱ ለወጣቱ አስረክበው እንዲወጡ ነው የምመክራቸው። አገር በቅብብሎሽ ነው የሚመራው ነውና።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
ማህሌት አብዱል