የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ በተድላና በደስታ ለመኖር የሚፈልገውን ያህል ሲሞትም በክብር ማረፍን ይመኛል፡፡ እድር የሚባለው ማህበራዊ ተቋም የሚመሰረተውም ለዚህ የችግር ጊዜ ማለፊያ ታስቦ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በተለይ በከተሞች አካባቢ በእድር የማይሳተፍ ቤተሰብ ብዙም አይስተዋልም፡፡ ከዚህም ባሻገር ሰዎች እንደየእምነታቸው በአካባቢያቸው በሚገኙ የእምነት ተቋማት ውስጥ በመታቀፍ ከህልፈት በኋላ ለሚኖረው ዘላቂ ማረፊያ ከወዲሁ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡
በሌላም በኩል የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ በምድር ላይ እያለ የመኖር መብት እንዳለው ሁሉ ከሞተ በኋላም ግብአተመሬቱ እንዲፈጸምለት ማድረግ ሰብአዊ መብቱ ግዴታ ነው፡፡ ከሞራልም ሆነ ከህግ አኳያ የሰው ልጅ ከሞት በኋላ በተገቢው ሁኔታ ስርአተ ቀብሩ ሊፈፀም ይገባል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን አሁን በአንዳንድ የእምነት ተቋማት ከቀብር ስፍራዎች ክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከቀብር ስፍራዎች ጋር ተያይዞ እስከ 90 ሺህ ብር ድረስ ለቀብር ስፍራ መክፈል እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ መብትን የሚጋፉና የሰው ልጅ ከሞተ በኋላ ሊያገኝ የሚገባውን ክብር የሚያሳንሱ ናቸው፡፡ ይህ የተጋነነ የቀብር ማስፈፀሚያ ገንዘብ ከሞት በኋላም ደሃና ሃብታም እንዲፈጠር ልዩነትን የሚፈጥሩ ከመሆናቸውም በላይ አጠቃላይ የእምነትን መርሆዎች የሚቃረን ነው፡፡
የእምነት አባቶች እንደሚሉት ሰዎችን እኩል ከሚያደርጉ ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሞት ነው፡፡ አሁን እየተፈጠረ ያለው የቀብር ስፍራዎች ዋጋ መለያየት ግን ይህንን የእኩልነት መንፈስ የሚያዛባ ሲሆን፤ ሰዎች ለእምነት ተቋማት ያላቸውን እምነትም የሚሸረሽር ነው፡፡
በእርግጥ በአሁኑ ወቅት በተለይ በአዲስ አበባ ካለው የህዝብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና ከቦታ ጥበት ጋር ተያይዞ የቀብር ስፍራዎች በየጊዜው እየጠበቡ መሄዳቸው እውን ነው፡፡ በከተማዋ ያሉትን የቀብር ስፍራዎች የተመለከተ ሰው ምን ያህል የሞት መበራከት እንዳለ በቀላሉ ሊገነዘብ ይችላል፡፡
እነዚህ የቀብር ስፍራዎች ቶሎ ቶሎ የመሙላታቸውን ያህል የመሬት እጥረትም እንዳለባቸው ይታወቃል። ሆኖም ሰው ከሞተ በኋላ መሬትን የሚገዛ መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ ይልቅ ያለውን መሬት እንዴት በአግባቡ በቁጠባ መጠቀም ይቻላል የሚለውን መለየትና ከሞት በኋላ ለመቀበሪያ ፍትሃዊ አገልግሎት የሚገኝበትን ሁኔታ መፍጠር ከሃይማኖት አባቶች ይጠበቃል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በከተማዋ ከ90 በላይ የቀብር ስፍራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ የቀብር ስፍራዎች ውስጥ 81ዱ በእምነት ተቋማት የተያዙ ሲሆኑ 15ቱ ደግሞ በመንግሥት ይዞታ ስር የሚገኙ ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የዘላቂ ማረፊያ ልማትና አስተዳደር “ማንኛውም ዜጋ የመቀበር መብት ስላለው መሬት በነፃ ያገኛል። የባይተዋርና የመደበኛ የቀብር አገልግሎትም በራሴ ቦታዎች ላይ ያለክፍያ እሰጣለሁ” ቢልም በእነዚህ ቦታዎችም በማህበር የተደራጁ “ቀብር አስፈጻሚዎች” ክፍያ መጠየቃቸው አሳሳቢ ነው፡፡
ይህ ጉዳይ ግን ሊታሰብበት የሚገባው ነው፡፡ በተለይ በመንግስት ተቋማት ስር የሚገኙ ተቋማት ከእንዲህ አይነት አባዜ ወጥተው ሰዎች አገልግሎቱን በነፃ የሚያገኙበትን እድል መፍጠር ይገባቸዋል።
ከዚህም በሻገር በእምነት ተቋማትም ቢሆኑ እንዲህ አይነት የዋጋ ልዩነቶችና የተጋነኑ ክፍያዎች በአንድ በኩል ከሞራልም ሆነ ከማህበራዊ እሴት እንዲሁም ከእምነት ተቋማት አስተምህሮ አንፃር ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ አልፎ አልፎ ለመቃብር ስፍራነት መሬት ከመንግስት ወስደው በቦታው ላይ ህንጻ የሚገነቡትንም የእምነት ተቋማት መቆጣጠርና መሬት በአግባቡ ለተገቢው ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ መንግስት ሆነ የእምነት ተቋማት ለሰው ልጆች ዘላቂ ማረፊያ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 15/2012