በኢንጂነር ታከለ ኡማ ከንቲባነት የሚመራው የአዲስ አበባ አስተዳደር አመራር ላይ ከመጣ ወዲህ በበርካታ መስኮች የታችኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ያማከለና ተጠቃሚ ያደረገ እርምጃዎችን ወስዷል።
ተማሪዎች በትምህርት ቤታቸው በነጻ እንዲመገቡ ማድረግ የቻለ፤ የትምህርት ቤት ዩኒፎርማቸውን አሰፍቶ ያለበሰ የተማሪዎችን የምግብ ወጪ ሸፍኖ እንዲመገቡ ማድረግ የቻለ፤ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተል የመጀመሪያው የአዲስ አበባ ከንቲባና አስተዳደር በመሆኑ ምስጋናችን የላቀ ነው።
ከተማሪዎች ውስጥ ምግብ ይዘው ትምህርት ቤት ለመሄድ የማይችሉ፤ ሲርባቸውም የሚወድቁ፤ ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል ያልቻሉም እንደነበሩ ይታወቃል። የተማሪዎችን የምግብ ወጪን መሸፈን፤ ዩኒፎርም በአስተዳደሩ ወጪ ማልበስ እጅግ የሚደነቅ የሚበረታታ ዘለቄታነት ሊኖረውም የሚገባ ተግባር ነው። በዚህም ክቡር ከንቲባውንና የሚመሩትን አስተዳደር እናመሰግናለን። ከዚህ ቀደም ይሄን አስቦ ያደረገው የለም።
መኖሪያ ቤት ለሌላቸው እቅመ ደካማዎች ቤት መሰጠቱ፤ የበጎ ሰብእና ማሳያና የሚወደስ ተግባር ነው። ዳቦ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መሰረታዊ ነው። ነጋዴዎች ዋጋን በማናርና ሕብረተሰቡን በማማረር ግራም በመቀነስ የሚጫወቱትን ደባ ለመስበር በከተማው አስተዳደር ታቅዶ የተጀመረው ብዙ ሺህ ዳቦዎችን ለማምረት የሚችል የዳቦ ፋብሪካ ግንባታ ስራው በመጀመሩ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ይታመናል። ለዚህም ክቡር ከንቲባውንና አስተዳደሩን እናመሰግናለን።
በከተማዋ የተሰሩት ስራዎች የብዙሃኖችን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ ናቸው። ለጥቂቶች ብልጽግናን ለብዙሃኑ ጉስቁልናን የሚያመጡ አይደሉም። ሁሉም አብሮ እንዲያድግ የሚያደርጉ ናቸው። ወደ ስራ የገቡት ቀጣይነት እንዲኖራቸው፣ ያልተጠናቀቁትም ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ባለሀብቱ እና መላው ህብረተሰብ እንደራሱ ፕሮጀክት ሊመለከታቸው ይገባል። ለመንግስት ብቻ ከመተው ይልቅ ሁሉም ባለው አቅም ሊደግፍ ይገባል። ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ እውቀት ያለውም በእውቀቱ እየደገፈ ቀጣይነታቸውን ሊያረጋግጥ ይገባል።
የከንቲባ ታከለ ኡማ አስተዳደር በእስከአሁኑ ጉዞው ድሀውን የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለ በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል። ለዚህ ያለንን ጥልቅ አድናቆትና አክብሮት እንገልጻለን።፡ የዚያኑም ያህል የአዲስ አበባ ኢኮኖሚያዊ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ረዥም ዘመናትን ያስቆጠሩና ውስብስብ ናቸው። በቀበሌ የአስተዳደር አመራርና አገልግሎቶች፤ በጤና ጣቢያና ክሊኒኮች፤ በመሬት ዘርፍ፤ በኮንስትራክሽንና ግንባታ፤ በመንገድ ላይ ሕገወጥ በሆነ ሁኔታ ላስቲክ እየዘረጉ የሚካሄደው ህገወጥ ንግድ ሁሉ ሕግና ስርአት ሊይዝ ይገባል።
የአዲስ አበባ ችግር ዘርፈ ብዙና ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። በአንድ ጀምበር የሚፈታ የሚቀረፍ አይደለም። አይታሰብም። ሊሆንም አይችልም። ይሄንን መጠነ ሰፊ የኖረ ችግር ለመፍታት ሕዝብና መንግስት ተደጋግፈው ተማክረው ተደማምጠው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
በአሁኑ ሰዓት አቅም በፈቀደ መጠን ከንቲባውና አመራራቸው የታችኛውን የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ ችግር ፈቺ እርምጃዎችን እየወሰዱ ስላሳዩን ይህ በየትኛውም ዘመን ያልታየ ለሕዝብ የሚጠቅም አካሄድ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል። ድጋፋችን አድናቆታችንም ከዚሁ ለሕዝቡ እየተደረጉ ካሉ በጎ ስራዎች ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ቤት አልባዎች፤ ረዳት አልባዎች፤ ጎዳና አዳሪዎች፤ ረዳት አልባ ሕመምተኞች በብዛት የሚገኙባት ከተማ ናት አዲስ አበባ። ወገናችሁን ለመርዳት ላሳያችሁት ቅን ልቦናና ለሰጣችሁት ቅድሚያ ደግመን ደጋግመን እናመሰግናለን።
ከተማዋን ወደ ገጠር መንደርነትን ለማሳነስ እየደፈሩ ያሉ አላዋቂዎች በጨዋ ደንብ ተው ሊባሉ ይገባል። የወንጀለኞችና የነፍሰገዳዮች የተቀናጀ ስውር ሴራ የአዲስ አበባን ነዋሪ ክፉኛ እያስመረረው ስለሆነ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ወንጀለኞችን ለሕግ በማቅረብ የሕዝብ አጋርነቱን ደጋግሞ ሊያረጋግጥ የከንቲባው ጽህፈት ቤትም የችግሩን ጥልቀት ተረድቶ ሊያመክነው ይገባል። አስተዳደሩ በብዙ መልኩ በሰራቸውና ሕዝብ ዘንድ በደረሱ ተጨባጭ ስራዎች ሕዝባዊ ፍቅርና ድጋፍን በማግኘቱ ደግመን እናመሰግናለን። ቀሪዎቹን ለማሳካት እንዲተጋ በዚሁ እንዲቀጥልም እናበረታታለን! እናመሰግናለን ክቡር ከንቲባ !
አዲስዘመን ጥር 14/2012