መረጃ ማግኘት የሁሉም ሰው መብት ነው። እዚህ ላይ ግን ምን ዓይነት መረጃ የሚለው ከፍተኛ የሆነ ትኩረትን የሚሻ ጥያቄ ይሆናል። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ መረጃዎች ሁሉ ጠቃሚ የማይሆኑበት ሁኔታ ስላለ። ሌላው ምን ዓይነት መረጃ እንፈልግ ወይም እናግኝ ከሚለው ባለፈ የመረጃው ምንጭ ማነው የሚለውንም ማጥራቱ ያሥፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በተለይ አሁን አሁን እንደምናየው የተዛቡና የተዘበራረቁ መረጃዎችን እያገኙ በጭፍን ከመፍረድና እርስ በእርስ ያልሆነ ችግር ውስጥ ከመግባት ያድናል።
በቀደመው ጊዜ መረጃ በተለይም ደግሞ አገራዊ ሁኔታን የሚያትቱ ዜናዎች ይሰራጩ የነበረው ከተወሰኑ በውል ከሚታወቁና በህግም ተጠያቂነት ካላቸው ተቋማት ነበር፤ ዛሬ ላይ ደግሞ እድሜ ለቴክኖሎጂ የዜናዎቹ ምንጭ ብዙ ከመሆኑም በላይ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚሰራጨው ወሬም የተለያየ እየሆነ ህብረተሰቡ የቱን መስማት እንዳለበት በከፍተኛ ሁኔታ እየተቸገረ ስለመሆኑ ምስክር መቁጠር አያሻም። በተሳሳቱ መረጃዎች ምክንያትም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡
በተለይም በአሁኑ ወቅት ሀይ ባይ ያጡት እንደ ማህበራዊ ድረ ገጾች ያሉ የተቋቋሙበትን አላማ ወደጎን ትተው ያልተጣራ ወሬን የሚነዙ ግለሰቦችና ተቋማት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የህዝቦች ትስስርና አብሮ የመኖር የቆየ ታሪክ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና እያሳደሩ በመሆኑ አሁንም የሚመለከተው አካል ሀይ ሊላቸው ይገባል።
እዚህ ላይ ግን ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃን ለህብረተሰቡ እንዲያስተላልፉ በህግ የተፈቀደላቸው “ጋዜጠኞችም “ ሳይቀሩ ስሜታዊ በመሆንና በማዳላት አንዱን ወገን ሲጠቅሙ ሌላውን ሲጎዱ እንዲሁም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ተጠቅመው ያልተገባ ድርጊትን ሲፈጽሙ ይስተዋላል። ይህ መስተካከል አለበት፡፡ ሚዛናዊና ትክክለኛ መረጃ የማቅረብ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል። ህዝቡም መረጃዎችን እያጣራ መጠቀም አለበት፡፡
ይህንን ሁኔታ ይከላከላል በሚል የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ ረቂቅ አዋጅ፤ የጥላቻ ንግግርና የሃስተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ስምረት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሃገራዊ አንድነት፣ ለሰብአዊ ክብር፣ ለብዝሃነትና ለእኩልነት ጠንቅ መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል። በዚህም መሰረት መሰረታዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በሕግ የተደነገጉ፣ በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውን አላማ ለማሳካት አስፈላጊ የሆኑ፣ ተመጣጣኝና በጠባቡ የተበጁ መሆን እንዳለባቸው ደንግጓል። ይህ ደግሞ ትክክለኛና የተጣራ መረጃ ለህዝቡ እንዲደርስ ያግዛል።
የተወሰነ ቡድን ላይ ያነጣጠረ፣ ብሄርን፣ ብሄረሰብንና ህዝብን፣ ሀይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር በሞራልም በህግም በፍጹም የተከለከለ ቢሆንም አሁን የምናየው ሁኔታ ግን ‹‹የአንተ ብሔር የእኔ ብሔር እንዲሁም ሀይማኖት ›› እየተባለ ያልተጣሩ ወሬዎችን ይዞ በማራገብ አገርን ያህል ትልቅ ነገርም ማመስ ላይ ትኩረቱን አድርጓልና መረጃ አለን ብላችሁ የምታሰራጩ ሰዎች ለምትሰሩት ስራ ኃላፊነት ሊሰ ማችሁ ይገባል።
የሃሰት መረጃና መረጃውን ሃሰት መሆኑን በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን ሃሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል በቂ ምክንያት እያለ የሚሰራጭ ሀሰተኛ መረጃ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ከዚህ ተግባር መቆጠብ አለበት፡፡ ተጠያቂነትን የሚያስከትም መሆኑንም ማወቅ ይገባል:: መንግስትም የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት የሀሰት መረጃ በማሰራጨት በተሰማሩ ተቋማት ሆኑ ግለሰቦች ተገቢውን እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡
አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን በተለይም ደግም “መገናኛ ብዙሃን” ተብለው በህግ ፈቃድ የተሰጣቸው አካላት የሚያሰራጩት ዘገባ እውነትን እንዳይስት አንዱን በዳይ ሌላውን ተበዳይ እንዳይሆን ፈቃድ የሰጠውም አካል ይሁን ሌላው የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል።
ይህንን ማድረግ ሳንችል በቀረን ቁጥር ግን እንደ አገር በርካታ ነገሮች በተዛቡ መረጃዎች ምክንያት መበላሸታቸው፤ ብዙዎችም በተንጋደደ መንገድ እንዲሄዱ እንዲሁም ባልጠራ ወሬ ተገቢ ያልሆኑ የህዝብ ለህዝብ ቅራኔዎች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄን ማድረግ ይገባል። በመሆኑም በሀሰተኛ መረጃና ሚዛኑን ባልጠበቀ ወሬ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እና ስርዓት ለማስያዝ ህዝብና መንግስት ተባብረው ሊሰሩ ይገባል፡፡ በዚህም መረጃን አጣርተን ጥቅም ላይ እናውል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 13/2012