አንዳንድ ገጣሚያን ነብይ ናቸው። ግጥሞቻቸው ደግሞ ትንቢት፡፡ ሌሎች ደግሞ ዘጋቢዎች ይሆናሉ፡፡ ግጥሞቻቸውም ታሪክ፡፡ ይህን ያስባለኝ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “ሞት ማለት” በሚል ርዕስ በ1967 ዓ.ም የጻፉት ግጥም ነው:: የክርስትና እምነት ተከታዮች ዳግም በተወለዱበት የጥምቀት በዓል ማግስት ሞትን አጀንዳ ማድረጌ ቀፎኛል፡፡ ግን እየሆነ ካለው ነገር በላይ አይቀፍም በሚል ርዕሰ ጉዳዩን ጉዳዬ አድርጌዋለሁ፡፡ ፕሮፌሰሩ ሞትን ከገለጹባቸው ስንኞች ጥቂቶቹን ወስጄ ቀደም ሲል የነበረው የሞት አረዳድ ታሪክ ሆኖ መቅረቱን ያለንበትን ዘመን ዋቢ በማድረግ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ሞት ማለት አሉ ፕሮፌሰሩ ከ45 ዓመታት በፊት …
አለመናገር ነው ጭው ያለ ዝምታ ፤
የመቃብር ሰላም የሬሳ ጸጥታ ፤
ደሃ በሰሌኑ ሳጥን ገብቶ ጌታ ፤
የውሸት ልዩነት ተጋድሞ በተርታ ፤
አይመሽ ወይ አይነጋ ጠዋት የለ ማታ ፤
ሀዘን የለ ለቅሶ ደስታ ፈገግታ ፤
ዘፈኑና ለቅሶ የምስጥ ሹክሹክታ፡፡
የዛሬን ሞት ለመግለጽ እነዚህ ስንኞች ተገቢ ቃላትን አልያዙም፡፡ ጭው ያለ ዝምታና የመቃብር ሰላም ድሮ ቀርቷል፡፡ ዛሬ የመቃብር ቦታዎች በግሬደር እየታረሱ በምትካቸው የንግድ ሱቆች እየተገነቡ ነው። የውሸት ልዩነት የሚባል ነገርም የለም፡፡ በቤተ እምነቶች ደሃና ሐብታም የሚለዩት እንደቀድሞ በሰሌንና ሳጥን መሆኑ ቀርቷል። ዝቅተኛ ከሚባለው አምስትና ስድስት ሺ ብር አንስቶ እስከ መቶ ሺ ብር ድረስ መክፈል የሚችል ብቻ በእምነት ተቋማት በተያዙ የመቃብር ቦታዎች ይቀበራል፡፡ እንደመኖሪያህ ግቢህ ሁሉ የመቀበሪያ ቦታህ ስፋት የሚወሰነው በመክፈል አቅምህ ልክ ነው፡፡ ቅንጡ መብራቶች በተገጠሙላቸው ውድ የመቃብር ስፍራዎችም ሟች በወታደሮች እየተጠበቀ ይመሻል ፤ ይነጋል። የምስጥ ሹክሹክታም ከአፈር ሽታ ጋር ሽታ ሆኖ ቀርቶ ፉካ ውስጥ በእምነበረድ ትዝታው በርዷል፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች መጽሔቶች ላይ ከፎቷቸው ስር በሚያሰፍሯቸው ሀሳቦች ተገርማችሁ አታውቁም ? ተማሪዎቹ ከፎቷቸው ስር የሚያሰፍሩትን ሀሳብ ጽፈው ለመጽሔት አዘጋጅ ኮሚቴ የሚሰጡት ከምርቃታቸው ቀን ቀድመው ነው። የመቃብር ላይ ጽሑፎችንም ሟቾች ከመሞታቸው በፊት እንዲጽፏቸው ቢደረግ በርካታ አስተማሪ ፣ አስገራሚና አዝናኝ መልዕክቶች ይተላለፉባቸው ነበር። ሟቾች በሕይወት እያሉ ያጡትንና ያገኙትን፣ የተረዱትንና ያልተረዱትን፤ የተደነቁበትንና የበሸቁበትን እንዲሁም የተደሰቱበትንና ያዘኑበትን በሕይወት ለቀሩት የሚያጋሩባቸው ሰሌዳዎች ይሆኑ ነበር፡፡ ዘላቂ ማረፊያዎች መሆናቸው ቀርቶ የነገዎቹ ሟቾች የሚያዘወትሯቸው ዘላቂ መኖሪያዎች ይሆኑ ነበር፡፡ የምሬን ነው እኮ ! ምነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥሩ ሁኔታ የተያዙ አንዳንድ የመቃብር ቦታዎች ላይ ሠርግና ልደት መደገስ ተጀምሮ የለ እንዴ፡፡
መምህርና ገጣሚ ደበበ ሰይፉ በመቃብሩ ላይ የሚሰፍረውን መልዕክት ተናዞ እንደሞተ ይነገራል፡፡ ደበበ የመረጠው “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” በተሰኘ የግጥም መድብሉ ገጽ 72 ላይ የሰፈረችውን “ለምን ሞተ ቢሉ” የተሰኘች አጭር ግጥሙን ነበር። ምናልባትም ግጥሟን ለመጻፍ ሲነሳ በሐውልቱ ሰሌዳ ላይ እንድትሰፍር ሳያጫት አይቀርም፡፡ እንዲህ ትነበባለች፡፡
ለምን ሞተ ቢሉ
ንገሩ ለሁሉ
ሳትደብቁ ከቶ
“ከዘመን ተኳርፎ ከዘመን ተጣልቶ”፡፡
ደበበ አንድ ጊዜ ብቻ በሚሞትበት ዘመን ስለሞተ ነው ይህችን ግጥም የመረጠው። የዛሬ ሟቾች ግን መቃብራቸው ላይ የሚጻፈውን መልዕክት የመምረጥ ዕድል ቢሰጣቸው “በምድር ላይ ሁሉ ነገር ውድ ነበር ፤ መቀበሪያ ቦታ ጭምር፡፡” ብለው የሚጽፉ ይመስለኛል፡፡
አንዳንድ የእምነት ተቋማት የቦታ ጥበት ሳይኖር ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ምዕመናንን ሰባት ዓመት የሞላቸውን የቤተሰቦቻቸውን አጽሞች እንዲያነሱ አሊያም ገንዘብ ከፍለው ለተጨማሪ ሰባት አመታት እንዲያድሱ ይጠይቃሉ፡፡ ገንዘቡ የተከፈለለት አጽም በነበረበት ለሰባት ዓመታት ይሰነብታል። ገንዘብ የሚከፍልለት የሌለው ደግሞ ቦታውን ለከፋይ ይለቃል፡፡ የቦታ ጥበት ሳይኖር በክብር ያረፉ አጽሞች በሰባት ዓመት እንዲነሱ የሚደረጉ ከሆነ “ዘላቂ ማረፊያ” የሚለው መጠሪያ ጊዜያዊ ማረፊያ አሊያም መጠለያ ተብሎ መቀየር አለበት፡፡
ዶክተር ዳዊት “አለመኖር” በተሰኘ መጽሐፉ በአንድ ገጸ ባህሪው በኩል እንዲህ ይላል፡፡ የሰው ልጅ የሞት ፍርሃቱን በሶስት መንገዶች ያሸንፋል፡፡ ልጆች በመውለድ ፤ በሃይማኖት (ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ በማመን) እና ስሙ የሚጠራበትን ስራ ሰርቶ በማለፍ፡፡ ታዲያ ቀንቶት በሶስቱም መንገዶች አለመኖርን መፍራት ያቆመ (የቀነሰ) ሰው እንኳን ሞቱን ሲያስብ ምቾት አይሰማውም፡፡ እንግዲህ እዚህ አስቀያሚ ስሜት ላይ ነው የትና እንዴት እቀበራለሁ የሚል ሀሳብ የሚጨመረው፡፡
ፕሮፌሰሩ ግን
ሞት አለመስጋት ነው የግዴለሽ ዓለም ፤
ድንጋይ ተሸክሞ በውሃ ላይ መቆም ፤
…ማንም አይጎዳ ማንም አይጠቀም፡፡ ይላሉ፡፡
በአንድ ወቅት የዕድሮች ህብረት ተቋቋመ ሲባል ለፖለቲካ ተልዕኮ መስሎኝ ነበር፡፡ አሁን ሳስበው ግን እድሮቹ ህብረት የፈጠሩት “በተናጠል የቀብር ቦታ ዋጋን መሸፈን የማንችልበት ጊዜ ይመጣል” ብለው በመስጋት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለአንድ የቀብር ስነስርኣት የሚጠየቀውን ገንዘብ ከየት ያመጣሉ ? የቀብር ቦታ ዋጋ እየናረ መሄድ ያሳሰባቸው አንዳንድ ዕድሮች ከመደበኛ ወርሃዊ ክፍያ ውጪ መዋጮ በመጠየቅ በደህና ጊዜ በያዙት ይዞታ ላይ ቤቶች ሰርተው ለማከራየት ግንባታ እያካሄዱ ነው፡፡
የቀብር ቦታ ጭንቅ የሆነባት አዲስ አበባ ከ90 በላይ የቀብር ስፍራዎች አሏት:: ከእነዚህ የቀብር ስፍራዎች ውስጥ 81 በእምነት ተቋማት የተያዙ ሲሆኑ 11 የቀብር ስፍራዎች ደግሞ በመንግሥት ይዞታ ስር የሚገኙ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውበት መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የዘላቂ ማረፊያ ልማትና አስተዳደር “ማንኛውም ዜጋ የመቀበር መብት ስላለው መሬት በነፃ ያገኛል፡፡ የባይተዋርና የመደበኛ የቀብር አገልግሎትም በራሴ ቦታዎች ላይ ያለክፍያ እሰጣለሁ” ቢልም በእነዚህ ቦታዎችም በማህበር የተደራጁ “ቀብር አስፈጻሚዎች” ዳጎስ ያለ ክፍያ ይጠይቃሉ፡፡
መንግስት በስሩ ባሉት ዘላቂ ማረፊያዎች ቀብር ያለ ምንም ክፍያ እንዲፈጸም ማድረግ አለበት፡፡ አማራጭ አጥቶ ወደነዚህ የቀብር ስፍራዎች የሚሄድ ደሃን ባደራጃቸው “ቀብር አስፈጻሚዎች” ማስጨነቁን ይተው:: ለመቃብር ስፍራነት መሬት ጠይቀው ለሌላ ዓላማ የሚያውሉትንና አጽም እየለቀሙ ትናንሽ መርካቶዎችን የሚገነቡትን የእምነት ተቋማትም አደብ ያስገዛ፡፡ ምዕመናንም በክብር ያረፉ አጽሞች እየተነሱ ቤተ እምነቶች በንግድ ተቋማት መከበባቸውን ተቃወሙ። የእምነት ተቋማትም ተከታዮቻችሁን በማስተባበር እንደማንኛውም አልሚ መሬት በሊዝ ወስዳችሁ ገቢ ማግኛ ህንጻዎችን ለመገንባት ብትንቀሳቀሱ መልካም ነው፡፡ አሟሟታችንን ብቻ ሳይሆን ቀብራችንንም ያሳምርልን !
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 13/2012
የትናየት ፈሩ