ኤች አይ ቪን መከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ ያስፈልጋል፤ በዚህ ረገድ በተለይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የኪነት ሰዎች እና የእምነት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው። ሰሞኑን በካፒታል ሆቴል ኤች አይ ቪ /ኤድስ እያስከተለ ባለው ሀገራዊ ችግሮች መደረግ በሚገባው የመከላከል ሥራ ዙሪያ አርቲስቶችን እና የጥበብ ባለሙያዎችን ጨምሮ “አሁንም ትኩረት ለኤች አይ ቪ መከላከል” በሚል በዋፋ እና በፌዴራል ኤች አይ ቪ /ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ትብብር ውይይት ተደርጎ ነበር፤ በውይይቱም ታዋቂና አዳዲስ የጥበብ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የውይይቱ ተሳታፊና የኪነጥበብ ባለሙያዋ ወ/ሮ ውዳላት ገዳሙ በሰጡት አስተያየት “ባለቤት ካልጮኽ ጎረቤት አይደርስም” ይባላልና የኤች አይ ቪ ጉዳይ በመንግሥት፣ በሚዲያ እና በጽ/ቤቱም በኩል በሚገባ ካልተነሳ የጠፋ እስኪ መስል ድረስ ከፍተኛ መዘናጋት እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል። አክለውም የኤች አይ ቪ ጉዳይ ቀላል ስላልሆነ ወደ ፊት ሰፋ ባለመልኩ በተመቻቸ እና በቂ ጊዜ ተሰቶት የኪነጥበብ ባለሙያዎችን በማሳተፍ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ በሀገራችን ሁኔታዎች ባልተመቻቹበትም ሁኔታ ከፊት ቆመው የሚሠሩ መሆናቸውን እና አሁንም ለመሥራት ዝግጁነቱ መኖሩንም ተናግረዋል። ሁላችንም የቆምነው ለሀገራችንና ለህዝቧ ደህንነት ነው። ስለዚህም የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይገባናል፤ ኢትዮጵያ ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍል ወጣቶችና የሀገሪቱ የነገ ተስፋዎች ያሉባት ሀገር ስለሆነች እንዲሁም ኤች አይ ቪ ትልቅ ስጋት በመሆኑ ጉዳዩን በዝምታ መመልከት ተገቢ አይሆንም።
በሌላ በኩል ኤች አይቪን በመከላከሉ በኩል የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ በቅድሚያ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው እና በየማሳጅ ቤቶች፣ ሺሻ እና የመጠጥ ቤቶች እድሜያቸው ያልደረሱ ልጆችን ማየት፣ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ያመላክታሉና ጥብቅ ቁጥጥር ቢደረግበት የሚል ሃሳብ በውይይቱ ተሰንዝሯል። በመሆኑም የሀገር ተረካቢውን ወጣትና ታዳጊ ካሁኑ በማህበረሰቡ በሚገባ መቅረጽ ያስፈልጋል። የኪነጥበብ ሰው እንዲሁም ወላጅ ተሳትፎበት በየትምህርት ቤቱም አቅራቢያ ያሉ ዳንስ ቤቶችና ጭፈራ ቤቶች እንዲሁም ቀስቃሽ የሆኑ ሱስ ቤቶች ላይ ቁጥጥር ካልተደረገ ታዳጊ ወጣቶችን መታደግ ከባድ ይሆናል የሚል ሀሳብ ተነስቷል።
የኢትዮጵያን ታዳጊ በትክክለኛ ስነምግባር እየቀረጽን፣ ባለፉት ጊዜያት የነበሩ እሴቶቻችን፣ ባህሎቻችን በትክክል እየተላለፉ መሆኑም ጥያቄ ውስጥ ያለ ነው፤ በተለይ በዚህ ጉዳይ ጽ/ቤቱም በሚገባ ስራዎችን ካልሰራ ስለ ጉዳቱ መጠን ቸልተኝነቱ ሊባባስ ይችላል። ለህጻናትና ለወጣቶች ደህንነት ሲባል ባህሎቻችን ሲጣሱ፣ ዲሲፕሊን ሲበላሽ፣ እሴቶቻችን ሲበላሹ ዝም ማለት ተገቢ ስላልሆነ ማህበረሰቡም ዝም ብሎ ማየት የለበትም፤ የኪነጥበብ ባለሙያዎችም ከጽ/ቤቱ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸው ተነስቷል።
በውይይቱ ተሳታፊ የነበረው ንብረት ገላው የተባሉ ሌላኛው የጥበብ ባለሙያ በሰጡት አስተያየትም በራስ ተነሳሽነት በተዘጋጀው ድራማም እሮብ ታህሳስ 17 ቀን 2011 ዓ.ም፣ በኤች አይቪ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ ማዘጋጀታቸውን እና በዚህም የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ነግረውናል። ከአጋርነታቸው ባሻገርም ታዋቂ ሰዎችና የኪነጥበብ ባለሞያዎች በኤች አይ ቪ/ኤድስ ዙሪያ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ በሚለው ፕሮግራም ሁሉም የኢትዮጵያን የኪነጥበብ ባለሙያዎች በምን መልኩ ተወክለው የበኩላቸውን ሃላፊነት እየተወጡ እንደሆነ ግልጽ መሆን አለበት። ሁሉም የመንግስት መስሪያቤቶች፣ የግል ድርጅቶች፣ እንዲሁም የሰው ኃይል የሚገኝባቸውና በተለይ ጥበብ ተግባራዊ ሊደረግባቸው የሚገባ ተቋማት በሙሉ ላይ ትልቅ ሥራ መሠራት ይኖርበታልም ብለዋል።
ኤች አይ ቪ/ኤድስ እድሜ፣ ጾታ፣ ሃይማኖት፣ ብሄር የማይልና የሁሉም የጋራ አጀንዳ ነው። ስለዚህ አብዛኛው የፈጠራ ክህሎት ያላቸው አርቲስቶች ዝግጁ ሆነው ሳለ የገንዘብ እገዛ ተደርጎላቸው የይድረስ ይድረስ ሳይሆን ወጥ በሆነ መልኩ ለለውጥ ሥራ መቆም እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል። በመሆኑም የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪውን በተገቢው ሚዛን ላይ በመመዘን መጠቀም መቻል አለብን ብለዋል።
ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊም እንዳሉት “አርቲስቶች ወይም የጥበብ ባለሙያዎች በተለይም የቅኔ ባለሙያዎች ብዙ ጆሮ አላቸው፤ ሀገሪቱ የስነምግባርና የሞራል፣ የሃይማኖት ሀገር፣ እንዲሁም እግዚአብሄርን የሚፈራ፣ ሰውን የሚያፍር፣ ህሊናውን የሚያዳምጥ ህዝብ ያለበት ሀገር ነች። በኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው በአንድ እምነት ስር ያለ ነው። ውስጥ 98 በመቶው ሙስሊም ወይ ኦርቶዶክስ ነው ወይም ደግሞ ፕሮቴስታንት ስለሆነ ከጥበብ ባለሙያው ይልቅ መስጊድ እና ቤተክርስቲያንን በመጠቀም ማስተማር ይበልጥ ውጤት ያመጣል። ስለዚህ ፓስተሮቹን፣ መነኮሳቱን፣ ካህናቱን፣ ኡስታዞቹን በመጠቀም መከላከል ከዝሙት ሃጢአትም ጭምር እንዲርቁ ስለሚያግዝ ይበልጥ ስኬታማ ያደርጋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
አክለውም ድሮ በነበረው ባህላችን እጮኛሞች በተለያየ ታክሲ ተቀጣጥረው አንድ ቦታ ይገናኙ ነበር፤ አሁን ግን እንደስልጣኔ በየአደባባዩ እየተጓተቱ መሄድ የሞራል ውድቀት ወይም ዝቅጠት እየሆነ በመምጣቱ ድርጅታችሁ ከነዚህ ከእምነት ተቋማት ጋርም ያለውን ፕሮግራም አጠናክሮ አብሮ መስራት አለበት ብለዋል።
በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችም ኢትዮጵያዊ መልክ የላቸውም፤ በአማርኛ የሚሰራው ለፈረንጆች የሚሰራ ይመስላል። «እነ ፀጋዬ ገ/መድህን ሙተው እየተናገሩ እኛ ግን ቆመን እየሞትን ነው» በማለት እሴቶቻችንን ይበልጥ መጠበቅ እንዳለብን አሳስበዋል።
ደሳለኝ የተባሉ ሌላው የጥበብ ባለሙያ ከዋፋ በሰጡት አስተያየት ዋፋ ከፌደራል ኤች አይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ጋር በመሆን ብዙ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ከነዚህም በጥቂቱ የመድረክ፣ የተጓዥ፣ የምርምር፣ የሚድያ፣ የህትመት ስራዎች እንዲሁም በርከት ያሉ ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል። በዚህም ፣ዋፋ ድርጅት ማህበራዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ምናልባት ጨረታ ወጥቶ ወይ የግል ድርጅቶች ቢሳተፉበት በብዙ ገንዘብ ይተመን የነበረውን በጥሩ ሙያ ብዙ ስራዎች እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኤች አይ ቪን በመከላከል ስራ ላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ለማግኘት የሚኬድበት ሁኔታም፤ በየማህበራቱ በተደራጁበት በመሄድ ለምሳሌ የትያትር፣ የሙዚቃ፣ የደራሲ እና የሰዓሊ ማህበር እየተባለ በዚህ መንገድ የጥበብ ባለሙያዎችን እንደሚያገኙም ጠቅሰዋል። በብዛት ታዋቂዎችን የጥበብ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን፣ በአንድም በሌላም መንገድ በኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ስራዎች ተሳታፊ የሆኑ፣ የሬድዮ ወይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ፣ ማስታወቂያዎች፣ የመድረክ ስራዎች ላይ ወይም ሌሎች ላይ የተሳተፉ ተተኪ ባለሙያዎችንም ማሳተፋቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም ለውጥ ለማምጣት በሚቀጥለው በዚህ አይነት ትኩስ ጉልበት ጋር ሁሉም በጋራ በሀላፊነት ሃገር እና ትውልድ የማዳን ስራውን የማስቀጠል ሂደት ላይ ማተኮር አለብን ሲሉም አሳሰበዋል።
ወደፊትም በሚኖሩት ልዩ ልዩ ስራዎች በርካታ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ እና በህብር እና በፍተሻ የሚሰሩ ስራዎች እንደሚኖሩ እና ከዚህ በፊትም እንደነበረው የድብቅ ድራማ ስራዎች ይሰራሉ። በትምህርት ቤት ድረስ ለሚኒሚድያዎች የሚቀርቡ ሳይቀር እየቀረጽን እያስተላለፍን ነው። በዚህም ጥሩ ውጤት እያመጣንበት በመሆኑ የሚቀጥል ይሆናል። አሁንም ሁላችንም ቢሆን ከጽ/ቤቱም ጋር ከዋፋም ጋር ሆነን ስራዎችን ለመስራት በኪነጥበብ ባለሙያዎችም በኩል ቅንነት አለ። በመሆኑም የትኛውም የኪነጥበብ ባለሙያ ዋፋ ጋር ቢመጣ በተቻለው መጣን አቻችለን አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የፌዴራል ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የእቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ነፃነት ሃኒቆ በበኩላቸው በውይይቱ የተነሱ ሃሳቦች ተገቢ ናቸው ብለዋል። አጠቃላይ በሚዲያ የሚተላለፉ መልእክቶች የሃገራችንን ባህል፣ እምነት፣ ወግ አስጠብቆ እየሄደ አለመሆኑ ተቀባይነት አለው። የሃይማኖት ተቋማትን በአግባቡ መጠቀም አለብን በሚለውም ላይ ትክክለኛና የማያወላዳ በመሆኑ በስፋት እንደሚሰራበት ጠቁመዋል።
በተደጋጋሚ የተነሳው አባባሽ ነገሮችን የማስቆም ጥያቄም ትክክል ሆኖ አባባሽ ሁኔታዎችን ከማስቆም አንፃር ጉዳዩ የሃገር ጉዳይ፣ ትውልድን፣ ወጣትን የመታደግ ጉዳይ በመሆኑ ቢሮውን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ትልቅ የቤት ስራ እንደሚጠበቅ ነግረውናል። በሌላ በኩል የህብረተሰቡ እንዲሁም የወጣቱ ፍላጎትን በተመለከተ በተለይ ወጣቱ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የተለያዩ ፍላጎቶች ይኖሩታል። በመሆኑም የወጣቱ ፍላጎት እየታየ ስራ መስራት ላይ ብዙ ይቀራልም ብለዋል።
በማጠቃለያም በተለይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከኤች አይ ቪ ኤድስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ጋር እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ለመስራት በሚደረገው ጥረት በራችን ክፍት ነው። ባለን አቅም አሁንም አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል።
የገንዘብ አቅምን በተመለከተ ጽ/ቤቱ ከ90በመቶ በላይ ገንዘብ ለመድሃኒት ግዢ እንዳዋለና መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነ ገልጸው ሁሉም ባለድርሻ ባለው አቅም እንዲሰራ ጽ/ቤቱም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።