ጫካ ውስጥ ባለችው አነስተኛ ጎጆ የሚኖር አንድ ድሃ ነበር። ጎጆዋ እጅግ አነስተኛ ከመሆኗ የተነሳ ከእርሱና ከሚስቱ በስተቀረ ሌላ ሰው ለማስተኛት አትበቃም። በአንድ ሌሊት ዶፍ ዝናብ እየጣለ አንድ ሰው የጎጆዋን በር አንኳኳ። ባል «በዚህ ዝናብ መንገድ የጠፋበት ሰው ሳይሆን አይቀርም አውሬዎች እንዳይበሉት ቶሎ ክፈቺለት» አላት ሚስቱን። «ቦታ የለም እኮ የት ልናሳድረው?» በማለት ጠየቀች ሚስት።
ባልም በጥያቄዋ ተገርሞ እንዲህ አለ «ይህ እኮ የቦታ እጥረት ያለበት ቤተመንግስት አይደለም፤ ይህ የድሀ ጎጆ ነው የቦታም ገደብ የለበትም፤ ለሁለት ይተኙበታል፣ ሶስት ሆነው ይቀመጡበታል፤ ቦታ አይጠፋም፤ ቦታ እንፈጥራለን ቶሎ በሩን ክፈችለት» ሚስትየውም በሩን ከፈተች፤ በዝናብ የራሰው እንግዳ አመስግኗቸው ወደጎጇቸው ገባ።
ለመተኛት ቦታው ለሶስት ስለማይበቃ ቁጭ ብለው የባጡን የቋጡን ማውራቱን ተያያዙ። ታሪክ፣ ተረት፣ የሰሙትን ያዩትን እያወጉ ሌሊቱን አሳለፉ። በዚህ መሀል እንደገና በሩ ተንኳኳ፤ በሩ አጠገብ የተቀመጠው አዲሱ እንግዳ ነው። ወዳጄ በሩን ክፈተው ሌላ መንገድ የጠፋበት እንግዳ እያንኳኳ ነው አለ የቤቱ ባለቤት። እንግዳው «ቦታ የለም እኮ» አለ። «ሚስቴም አንተ ስታንኳኳ ቦታ የለም ነበር ያለችው፤ እሷ የምትለውን ብሰማ ኖሮ ይህን ጊዜ ጫካ ውስጥ በአራዊት ተበልተህ ነበር። ደግሞም መተኛታችንን ትተን የተቀመጥነው ባንተ ምክንያት መሆኑን አትርሳ። ይልቅ በሩን ክፈት ሶስት ሰዎች ተመችቷቸው ከተቀመጡ አራት ሰዎች ደግሞ ባይመቻቸውም ተጠጋግተው መቀመጥ አያቅታቸውም። ተጠጋግተን ስንቀመጥ ትንፋሻችን ያሞቀናል፤ብርድም አያገኘንም» አለው አባወራው።
እንግዳው ሰውዬ እያመነታ በሩን ከፈተ። አንድ ሰው ገባና አመስግኖ ተቀመጠ። ተጠጋግተው ተቀምጠው ወሬአቸውን እየጠረቁ ሳለ ብዙም ሳይቆይ በሩ ባልተለመደ መልኩ ተንኳኳ። ሚስትየውና ሁለቱ ሰዎች አባወራው አሁንም በሩን ክፈቱ ይላል ብለው በፍርሀት ፀጥ አሉ። እንዳሰቡትም «በሩን ክፈቱ ማን እንደሚያንኳኳ አውቃለው አህያዬ ነው፤ በዚህ ሰፊ ዓለም ብቸኛው ጓደኛዬ እሱ ነው፤ እንጨቴን ወደ ገበያ ይዞልኝ የሚሄደው ባለውለታዬ እንዴት ውጪ ሆኖ በዝናብ ይደብደብ። እንኳን እርሱ እናንተም ገብታችኋል ክፈቱ በሩን» አላቸው።
ሁሉም «አህያው የት ሊቆም ነው?» በማለት ተቃወሙ። «አልገባችሁም ይሄ የድሀ ጎጆ ነው፤ መቼም ቢሆን ቦታ አይጠፋም አሁን ተቀምጠናል አህያው ሲገባ ደሞ ሁላችንም እንቆማለን፤ እሱም ይሞቀዋል ምን ያህል እንደወደድነውም ይገባዋል» አለ አባወራው። እንግዶቹ እየተናደዱ በሩን ሲከፍቱ በዝናብ የራሰው አህያ ገባ።
የደሀው ሰው የህይወት መርህ «መስጠት የፈለገ የሚሰጠው አያጣም» ነውና ከጎደሎው እየሰጠ በደስታ ብዙ ዓመት ኖረ። ሰውየው «ይህ የደሀ ጎጆ ነው የቦታ እጥረት የለም እናብቃቃዋለን» እንዳለው አብቃቁት፣ ውጪ ዝናብ እየዘነበ ነው ፡፡እነርሱ ውስጥ እየተጫወቱ ነው፤ ሞቋቸዋል ሌሊቱ ውብ በሆነ መልኩ አልፏል። ቢሆንም ያለን ነገር ማካፈል ደስታው ለሰጪው ነው። «ባይኖርህ እንኳን ከፈለክ የምታካፍለው ነገር አታጣም» ይህን የኦሾ አስተምህሮን ስናስታውስ በሁላችንም አዕምሮ ውስጥ አንድ ነገር መመላለሱ አይቀርም።
ስንቶቻችን ነን ከትርፋችን ሳይሆን ከጎዶሏችን ለሌሎች የምናስበው፤ የምናካፍለው? ስንቶቻችንስ ነን ካለን ላይ የተወሰነችውን በማካፈላችን የምንደሰተው? ነገ የገና በዓል ነው ለበዓሉ የሚሆን ብዙ ድግሶችን ደግሰን የቀኑን መድረስ በጉጉት እየጠበቅን ይሆናል። ዶሮውን፣ በጉን፣ ቅርጫውን በአንድ በኩል አሰናድተን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጠላው፣ ጠጁ አልበቃ ብሎን ውስኪ ለማውረድ የተዘጋጀን እንኖራለን።
ያለውን፣ የሞላውን፣ የተትረፈረፈውን ለመጋበዝና ስጦታ ለማዥጎድጎድ የምንበረታውም ብዙዎች ነን። መንገዳችን ላይ ወይም በራችን ላይ ወድቀው ጠኔ የሚያላትማቸው ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሰብ እንዳለብን ልነዘነጋ አይገባም። በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በድንኳን ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እንዳሉም አንዘንጋ።
«ያለው ጠመቀና ያለውን ጠቀሰው…» እንዲሉ ያለው ላለው የሚሰጠውን ያህል ባይሆንም እንኳ፤ እጅግ በጥቂቱ ለተቸገሩ፣ በዓሉን ተደስተው ለማሳለፍ ለማይችሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ ብንችል ደስታችንን እጥፍ ድርብ ይሆንልናል።
አዲስ ዓመትን ስንቀበል «የአዲስ ዓመት ስጦታ ለእናት ሀገሬ» ብለን ራሳችን ለራሳችን የገባነው ቃል ነበር። እናት ሀገራችን በአንድ ቀን ስጦታ አትደሰትም። እርሷ የምትደሰተው በጉያዋ ያሉት ሁሉም ዜጎቿ ሰርክ ሲደሰቱላት፣ ጠግበው ሲያድሩላት፣ ተካፍለው ሲበሉላት፣ እርዛት ሲርቃቸው ነው። ዛሬም ድረስ ቃላቸውን ጠብቀው ዛሬም ድረስ ከትርፋቸው ሳይሆን ከጎዶሏቸው የሚያካፍሉ እንዳሉ አይካድም። በአንፃሩ የአንድ ወቅት ዘመቻ ሆኖባቸው ለታይታ የፈጠኑት ዛሬ ላይ የት እንዳሉ የማይታወቁትም ብዙ ናቸው።
ለመስጠት ከፈለግን የምንሰጠው አናጣም። ምክንያቱም ለአንዳንዶች ትራፊ የሆነው ለሌሎች መሰረታዊ ፍላጎት ይሆናል። እናም አቅመ ደካሞችን፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንንና ህፃናትን በማጉረስ አለንላችሁ እንበላቸው።ሁሉጊዜም በምንኮራበት ባህላችን ተጠቅመን፤ ያለንን ለሌላቸው አካፍለን ደስታችንን እናጋራቸው። መልካም የገና በዓል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011