አዲስ አበባ፡- በአራት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የእናቶችና ህፃናት ልዩ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ አስታወቀ፡፡
ልዩ ሆስፒታሉ ትናንት ተመርቆ አግልገሎት መስጠት ሲጀምር የሆስፒታሉ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር ወንድምአገኝ ገዛኸኝ በሁለት ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ሆስፒታል ባአጠቃላይ አራት መቶ ሃምሳ ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን አራት መቶ ሃምሳ አልጋዎች ያሉት ሲሆን ለእናቶችና ህጻናት የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ግልፀዋል፡፡
በአገሪቱ በርካታ የእናቶችና የህፃናት ህክምና ማዕከላት ቢኖሩም ይህ ልዩ ሆስፒታል በእናቶችና ህፃናት ላይ ራሱን ችሎ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ከሌሎቹ የተለየ እንደሚያደርገው ዋና ፕሮቮስቱ ተናግረዋል፡፡
ከመደበኛ የጨቅላ ህፃናት ህክምና በተጫማሪ እስከ ልብ ቀዶ ህክምና ድረስ የዘለቁ ሙሉ የህፃናት ህክምና አግልግሎቶችን እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል። ለእናቶችም የማዋለድ አገልግሎትን ጨምሮ የሴቶች የካንሰር ህክምና፣ የጡትና የማህፅን በር ጫፍ ካንሰር ልየታ አገልግሎቶችንም ሙሉ በሙሉ ራሱን ችሎ የሚሰጥ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ሆስፒታሉ አስራ ሶስት የቀዶ ህክምና፣ አስራስድስት አልጋዎችን የሚይዝ የህፃናት ከፍተኛ እንክብካቤ ማዕከል ያለው ሲሆን በእናቶች ጤና ላይ ተጨማሪ ስድስት አልጋዎችን ያቀፈ መሆኑንም ገልጸዋል። ይህም ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት እየሰጠ ያለውን የእናቶች ህክምና እና የህፃናት ቀዶ ህክምና አገልግሎትን እንደሚሳድገው አመልክተዋል፡፡
የጤና ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ በበኩላቸው የሆስፒታሉ ግንባታ ጥራቱን የጠበቀና የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችል የእናቶች፣ ሴቶችና ህፃናት ተኮር የሆነ ተቋም ከመገንባት አኳያ ተጀምሮ ዛሬ እውን መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የተመረቀው የእናቶችና የህፃናት ሆስፒታል የሚሰጠው አገልግሎት ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆንና ህንፃውም አሁን ያለውን ገፅታ ይዞ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ በርካታ ስራዎች እንደሚጠበቁም አሳስበዋል:: በቀጣይም የጤና ሚንስቴር እንዲህ አይነቱን የእናቶችና ህፃናት ተኮር ሆስፒታሎች ግንባታ ላይ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ልዩ ሆስፒታሉ በቀን ከሁለት ሺ አምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ እናቶችና እስከ ሶስት መቶ ለሚጠጉ ጨቅላ ህፃናት የህክምና አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚገመት ሲሆን በእለቱ የስነ ተዋልዶ ጤና ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ተጥሏል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 10/2012
አስናቀ ፀጋዬ