ከጥቂት ቀናት በፊት፤ ጠዋት በማለዳ ላይ፤ የተገዳደረኝን ፈታኝ ክስተት ከአሁን በፊት ተጋፍጬ የማውቅ አይመስለኝም። ተገዳዳሪዬ ደግሞ ብርቱ ጉልበተኛ ወይንም ጦረኛ አልነበረም። በዕድሜም ሆነ በዕውቀት፣ በችሎታም ሆነ በብስለት በልጦኝም አልነበረም። በሀብትና ዝናም ብልጫ አልነበረውም። የጠየቀኝን ፍልስፍናዊ ጥያቄ ባለመመለሴ ግን ለራሴ የተሸናፊነት ስሜት ተሰምቶኛል። ጥያቄው በቀን ውሎ ብቻ መልስ ተሰጥቶት የሚረሳ ሳይሆን ዕድሜ ልክ አብሮ ሳይመለስ ሊኖር የሚችል ሞገደኛ ጥያቄ ነው። እስከ ግባ መሬቴ ሳስታውሰው የምኖርም ይመስለኛል። ቢሮዬ እንደደረስኩ ሳላስበው የሥራ ጠረጴዛዬ ላይ አንግቴን ደፍቼ ለረጂም ደቂቆች ተክዣለሁ። ለመልስ ያዳገተኝንም ጥያቄ መላልሼ አመንዥኬዋለሁ። በዚህ መካከል ነበር ሳላስበው ተገዳድሮ ላሸነፈኝ ሃሳብ “በእንባ ዘለላ አጅቤ” አሜን ብዬ የገበርኩት።
“ወንድ ልጅ ተከልሎ ነው የሚያልቅሰው!” የሚለው የጋሽ ጸጋዬ ገ/መድኅን አባባል የበለጠ ፉርሽ የሆነብኝ ከዚያን ዕለት በኋላ ነው። “ለምን?” ቢሉ ለሌሎች ወዳጆቼ ታሪኩን ባጋራሁ ቁጥር ስሜቴ እየተናወጠ “እንባ እንደሚታገለኝ” ባልናዘዝ ዋሾ እሆናለሁ።
እነሆ የገጠመኜ ሙሉ ታሪክ፤
ዕለቱ ደመናማና ጨፍጋጋ ነበር። በማለዳ ወደ ሥራዬ የምገሰግሰው በሠፈሬ አካባቢ በሚገኝ አንድ ትልቅ አደባባይ ላይ በድርብርብ ጥግግት እንደ ምልምል የወታደር ሠራዊት ሰልፋቸውን አሳምረው ወረፋ የያዙ ትራንስፖርት ጠባቂዎችን ግራና ቀኝ እያማተርኩ ነው። የሰልፈኞቹ ቁጥር ከአንድ ባታሊዮን ጦር ቢተካከል እንጂ አያንስም። አንዳንዴ በመኪናዬ እንድጭናቸው የሚቁለጨለጩ ዓይኖች ሲበዙብኝ ከሦስት የማይበልጡ ህጻናትንና ወጣት ተማሪዎችን መርጬ “ሊፍት በመስጠት” እተባበራቸዋለሁ። እነርሱን ማስቀደሜ ትምህርት ቤት እንዳይረፍድባቸው በማሰብ ነው። ለሦስት ተመራጮች ሃምሳ እጩዎች ተሽቀዳድመው መኪናዬ ውስጥ ሊገቡ ሲታገሉ ማስተዋል እንደምን ልብን እንደሚሰብር መገመት አያዳግትም። አንዳንዱም ቀድሞ ለመግባት በሚፈጠረው ግፊያና ግርግር መካከል የመውደቅ አደጋም እንደሚያጋጥም እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም ትብብር ሲያደርጉ የሚደርሰውን ጉዳት ደጋግሜ አስተውያለሁ። የከተማችንና የሀገራችን የትራንስፖርት ችግር መቼና እንዴት እንደሚቀረፍ አዋቂው እግዚሃሩ ብቻ ነው። በእኛ ዘመን ለማየት ከታደልን ግን ለፈጣሪ ሀገራዊ “የግምጃና ጧፍ” ስዕለት ለማቅረብ ብንሳል ክፋት የለውም።
በዚያ ጣጠኛና ጨፍጋጋ ማለዳ በትራንስፖርት ጥበቃ ሰልፍ ላይ ከእናቱ ጋር የነበረ አንድ የአምስት ዓመት ሕጻን መኪናዬን ከሩቅ እንዳየ የእናቱን እጅ መንጭቆ በማምለጥ መሃል መንገድ ላይ በመቆም እንድጭነው ምልክት አሳየኝ። የሩጫው ፍጥነት ለአደጋም የሚያጋልጥ ዓይነት ነበር። አልጨከንኩበትም። ቆሜ ከእናቱ ጋር አሳፈርኳቸው።
ልክ መኪናው ውስጥ እንደገባ ለሙያው እንደተጣደፈ ጋዜጠኛ በጥያቄዎች ያጣድፈኝ ጀመር። ስሜንና የቤቴን አካባቢ ጠየቀኝ። እኔም በአክብሮት መለስኩለት። የእነርሱ ሠፈር ከእኔ መንደር ትንሽ ራቅ እንደሚል እናትዬው ነግራኛለች። ጥያቄውን አላቋረጠም ሥራዬንና ሙያዬን እንድነግረው አፋጠጠኝ፤ አለሳልሼ መለስኩለት። በእርሱ የዕድሜ ደረጃ ላይ ላሉ ሕጻናት መጽሐፍ መጻፌን ስነግረውማ የምርመራ ያህል ይሞግተኝ ገባ። መጸሐፌን እንድሰጠውም በኮልታፋ አንደበቱ ትዕዛዝ አወጀብኝ። አልከፋኝም።
የሕጻኑ እናት ተሳቃ ይመስለኛል “ሰው አታድርቅ!” ብላ በሳሳ ጥፊ ዳበስ አደረገችው። እንዳልጎዳችው እኔውም እመሰክራለሁ። ልጁ ግን ምርር ብሎ ያለቀሰው ልክ እንደተጎዳ በመቁጠር ነበር። ያስለቀሰው ጥፊው ሳይሆን ከውይይቱ ስላናጠበችው ይመስለኛል። “ፊት ከሰጡት እርሱ አይቻልም። ልብ አድርቅ ነው።” የታዘብኩት መስሏት እንደሆነ ገብቶኛል። “ተይው ይጫወት አታሳቅቂው!” የእናትየውን ጭንቀት ለማርገብ ሞከርኩ።
ሕጻኑን ማረጋጋትና ልቅሶውን ማስቆም ግድ ስለነበር ብልሃት ያልኩትን ዘዴ በመጠቀም ልክ እሱ እንዳደረገው ስሙን ዕድሜውንና የት እንደሚማር ጠየቅሁት። “ስሜ ቤቢሾ ነው። ዕደሜዬ አምስት አመት ነው።” በማለት ራሱን አስተዋውቆ የሚማርበትን ሙዓለ ሕጻናት ስም እየተፍነከነከ በአግባቡ መለሰልኝ። ትንሽ ኮልተፍ ስለሚል ማር ከአፉ ጠብ የሚል ይመስላል። “ቤቢሾ” መደበኛ ስሙ እንዳልሆነ ገብቶኛል። ልጅነት ቅንነትም አይደል፤ የነገረኝ የቤት ስሙን ነበር።
ጥያቄዬን ስጀምር ለቅሶውና ኩርፊያው ከመቅጽበት እንዴት እንደተገፈፈ ገርሞኛል። ልጁ ብልህና ንቁ ነው። ያውም ከእድሜው በላይ። የእኔን መረጃ በሙሉ ከወሰደ በኋላ ጥያቄውን ከጎኔ ወደ ተቀመጠችው ባለቤቴ አዙሮ ስሟንና የት እንደምትሰራ ለማወቅ ምርመራውን ጀመረ። የእናቱ የመሳቀቅ ስሜት ስለገባኝ ነፃ እንድታደርገው ደግሜ ትዕዛዝና የማረጋጊያ ሃሳቤን ሰንዝሬ አደብ አስገዛኋት። ቤቢሾ የልብ ልብ ተሰምቶት ጥያቄውን አጠንክሮ ባለቤቴን አፋጠጣት። ስሟን በአግባቡ ከመለሰችለት በኋላ ሥራዋን አድበስብሳ ሳትነግረው አለፈች።
በውይይታችን መካከል የFM 97.1 ሬዲዮ የማለዳ ዜና እወጃ ሰዓት ደርሶ ስለነበር የሬዲዮኑን ድምፅ ከፍ አድርጌ ማዳመጥ ጀመርኩ። ቤቢሾ ማውራቱን አላቆመም። የዜናው እወጃ ከተጠናቀቀ በኋላ “ዛሬ ፀሐይ ከጠዋቱ 12፡13 ደቂቃ ወጥታ ከምሽቱ 12፡17 ደቂቃ ትጠልቃለች።” የሚለው መረጃ ተላለፈ።
ይሄን ጊዜ ቤቢሾ በመኪናው መስታወት ውስጥ ወደ ሰማይ እያንጋጠጠ ፀሐይዋ በሰማይ ላይ መኖር ያለመኖሯን ማጣራት ጀመረ። ግራና ቀኝ እየተገላመጠና ወደ ላይ እያንጋጠጠ ፀሐይዋን እንደሚፈልግ በፊት ለፊት መስታወት እየተከታተልኩት ነበር። ሰማዩ በጨፍጋጋ ደመና ተሸፍኖ ስለነበር እንኳንስ ፀሐይዋ ልትታይ ቀርቶ ማለዳው ራሱ በአግባቡ ፈገግ አላለም ነበር።
የቤቢሾን የኮልታፋ አንደበት ጨዋታ ወድጄው ስለነበር፤ “ለምን ዝም አልክ ተጫወት እንጂ” ብዬ ከሃሳብ ቀሰቀስኩት። የመገረም ገጽታ እየተስተዋለበት በመስታወት ውስጥ ግራና ቀኝ እያንጋጠጠ “ሴትዮዋ አሁን በሬዲዮ ውስጥ ለምን ፀሐይዋ ወጣች ብላ ዋሸች። የእኛ ፀሐይ መች ወጣች? ውሸታም ነች!” ጥያቄው ቁጣም የተቀላቀለበት ነበር።
“አየህ ቤቢሾ ፀሐይዋ የወጣችው . . .” ብዬ ሳይንሳዊ ትንተና ልሰጠው ስሞክር ሃሳቤን ከቁብ ሳይቆጥር “ሬዲዮኑ ውሸታም ነው። የእኛ ሠፈር ፀሐይ አልወጣችም።” ብሎ የመልስ ምት አቀመሰኝ። “አየህ ቤቢሾ ቀኑ ደመናማ ስለሆነ ነው እንጂ ፀሐይዋ እኮ ወጥታለች። ለእኛ እንዳትታይ የጋረዳት ጭጋጉና ደመናው ነው።” ማብራሪያዬ እንኳንስ ለሕጻኑ ቤቢሾ ቀርቶ ለአዋቂዎችም የሚመጥንና የሚጥም ስላልመሰለኝ ግራ እንደተጋባሁ ምን እንደምመልስለት ማሰላሰል ጀመርኩኝ።
“ውሸት ነው። የእኛ ሠፈር ፀሐይ አልወጣችም።” እየተወራጨ አቋሙን አስረግጦ ነገረኝ። መልስ አልነበረኝም። ባለቤቴ ትንፍሽ ሳትል የሕጻኑን ሁኔታ የምትመለከተው በአግርሞት ነበር። መሸነፌን አምኜ ተረታሁ። ያ ጨፍጋጋ ዕለት ከማይጋፉት ባላጋራ ጋር ስላገጣጠመኝ በራሴ ተሸናፊነት ራሴው ተሳቀቅሁ። ሽንፈቴን ዋጥ አድርጌ ክርክሩን ለማስለወጥ ሙከራ ማድረግ እንዳለብኝ ማሰላሰል ጀመርኩኝ። ሕጻኑ ያለዕድሜው የበሰለ ጉድ መሆኑን ተረድቻለሁ። ፍቅሩም ውስጤ ጠልቆ ሲገባ ተሰምቶኛል።
“ቤቢሾ እስቲ ትምህርት ቤት ስለ ፀሐይ ከምትዘምሩት መዝሙር አንዱን ዘምርልኝ?” ሌላ ጣጣ እንዳያመጣብኝ እየተጠነቀቅሁ ሃሳብ ለማስለወጥ ስል ጥያቄዬን ሰነዘርኩ። ጥያቄዬ ውስጥ “ፀሐይ” የሚል ቃል መኖሩን ያስተዋልኩት ከአፌ ከወጣ በኋላ ነበር። ሌላ የጥያቄ ዶፍ እንዳያዘንብብኝ ሰግቻለሁ።
ቅኑ ቤቢሾ ለጥያቄዬ መልስ ለመስጠት አልዘገዬም። ጥያቄውን ሳያስጨርሰኝ ፈጠን ብሎ፤
“ፀሐዬ ደመቀች፣
ብርሃኗን ለእኛ ማለት አወቀች።
ፀሐይ ብርሃን ፈንጥቃ፣
ከአድማስ ወደ እኛ መጥቃ፣
ጊዜው ደረሰ ጠራ ሰማይ፣
በእናት ሀገር በእማይ።”
“ትንሹ መልአክ ቤቢሾ” በኮልታፋ አንደበቱ፣ በሚማርክ ዜማ ከመላእክት ዜማ ጋር በሚስተካከል ቃና መንፈሳችንን እያረሰረሰ አዜመልን። እርሱ አሳምሮ የሸመደደውን ዜማ እያዳመጥኩ ሌላ ስሜት ውስጥ ጭልጥ ብዬ ገባሁ። ይህንን መዝሙር መስከረም 5 ቀን 1973 ዓ.ም የዝዋይ ሕጻናት አምባ በጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና በሃንጋሪው ፕሬዚዳንት በይፋ ተመርቆ ሥራውን በጀመረ ዕለት የዘመሩት የያኔዎቹ የሕጻናት አምባ ታዳጊ ሕጻናት የዛሬዎቹ ጎልማሶች ነበሩ። የሙያ ባልደረባዬና ወዳጄ ሽመልስ ኃይሌ ከያኔው ዘማሪያን ሕጻናት መካከል አንዱ ነበር። ዛሬ እርሱም በልጆች ተባርኮ አባባ የመባል ወግ ደርሶታል። እንዲያውም በቅርቡ አያት ልትሆን ነው እያልኩ አቀልድበታለሁ።
በእነዚያ ትንታግ ባለ ብሩህ ተስፋ የሕጻናት አምባ ልጆችና በተቋሙ ላይ የኢህአዴግ አገዛዝ ስለፈጸመው ኢሰብአዊ ግፍ ወደፊት ጊዜው ሲመቻች ዝርዝሩን እመለስበታለሁ። መዝሙሩን የደረሰውን ሰለሞን ታደሰ ሰንደቁን እና የማስተባበሩን ስራና መዝሙሩ ለሚዲያ እንዲበቃ ያመቻቸችው አንጋፋዋ አርቲስት አለምፀሐይ ወዳጆ ላደረጉት ጥረት በያሉበት የባዕድ ሀገር አክብሮቴ ይድረሳቸው። ይህንን ተስፋ አቀጣጣይ ዘመን ተሸጋሪ ዜማ ባዜሙት የያኔዎቹ ሕጻናት ላይ ጨካኙ ሥርዓት “ፀሐያቸውን ያጨለመ ቢመስለውም” አብዛኞቹ የአምባው ልጆች ዛሬ ከራሳቸው ተርፈው ለሀገር ትልቅ ውለታ እየዋሉ እንዳሉ ስራቸው ምስክር ነው።
የቤቢሾን “ፀሐዬ ደመቀችን” መዝሙር ከኮልታፋ አንደበቱ ሰምቼ ሳልጠግብ ትምህርት ቤቱ በራፍ ላይ ስለደረስን በእናቱ አስታዋሽነት መኪናውን ዳር አሲዤ ሳወርዳቸው መንፈሴና ልቤ ከብላቴናው ጋር ቀርቶ ነበር።
“የእኛ ፀሐይ አልወጣችም ውሸት ነው። የሠፈራችንን ፀሐይ አሳየኝ። ጋዜጠኛዋ ውሸቷን ነው፤ የእኛ ሠፈር ፀሐይ አልወጣችም።” የቤቢሾ ጥልቅ ሃሳብ ደጋግሞ ውስጤን አናወጠው። በእዘነ ኅሊናዬም እያቃጨለ እረፍት ነሳኝ።
ስለ እውነት “የልጆቻችን የተስፋ ፀሐይ” ደምቃ ወጥታለች?
ቤቢሾ ከዘመናት መከራ ሊገላገል ያልቻለውን ምስኪን የሀገሬን ሕዝብ በሙሉ በነፍሱ ውስጥ ሰብስቦ የያዘ የሀገሬ ምሳሌ መስሎ ታየኝ። በፍልስፍና የታጨቁት ጥያቄዎቹ ደግሞ የሀገሬን ጭጋጋማ ፖለቲካ አስታወሱኝ።
ፖለቲከኞች ነን ባይ ግራ ገቦች ተስፋ በማይስተዋልበት ጨፍጋጋ ፍልስፍናቸው የፈነጠቀውን የዴሞክራሲ ፀሐይ ሊጋርዱ ሲያጠሉበት እየታወሰኝ በቁጣ ውስጤ ሲተረማመስ ታውቆኛል። ቤቢሾ “ጋዜጠኛዋን ውሸታም ነች!” ብሎ በልጅነት ልቡ እንደታዘባት ሁሉ እኔም ልትደምቅ ዳር ዳር እያለች ያለችውን በጧፍ ብርሃን የምትመሰለውን የሀገሬን ዴሞክራሲ ሊያዳፍኑ ቀን ከሌት የሚተጉ “ስመ ጋዜጠኞችን” በማሰብ ውስጤ “ውሸታሞች” እያለ ሲንቃቸው ታውቆኛል። የማይታየውን እንደሚታይ፣ የሚታየውን እንደማይታይ የሚቆጥሩ በርካታ ጨለምተኛ ሚዲያዎች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።
ቤቢሾን የመሳሰሉ ሕጻናትና የሕዝባችንን ሦስት አራተኛ ቁጥር ይሸፍናሉ የሚባሉት ወጣቶቻችን የዕድሜያቸው ውሎ “በፀሐይ አልባ ጨፍጋጋ ደመና” እንዳይጠቁር በመስጋት ልቤን የፍርሃት ወጀብ ሲያናውጠው በሚገባ ታውቆኛል። እርግጥ ነው ለብዙኃኑ ሕዝብ “ፀሐይዋ በጨፍጋጋ ደመና ብትሸፈንም” ዕድልና ጊዜ ለተመቻቸላቸው ጥቂት ገደኞች ግን የስኬት ወጋጋን በዚያኛው ወገን ቦግ ብሎ እንደበራላቸው አይካድም። በእነ ቤቢሾ ሠፈርና በብዙኃኑ ቀዬ ግን ዛሬም “ፀሐይዋ ገና ደምቃ አልወጣችም።” የልጆቻችን ንፁህ አእምሮ በብዙ ጉዳቶች ተበክሏል። የዘመናቸው ፀሐይ በርግጥም በጨፍጋጋ ደመና የተከበበ ይመስላል። የነገይቱ የሀገራችን የተስፋ ፀሐይ ደመናውን ሰንጥቃ ደምቃ እንድትወጣ ዜጎች ሁሉ ድርሻ ያላቸው ይመስለኛል። በተለይ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች የሕጻናቶቻችንን የነገ ፀሐይ እንዳያጨልሙ ደጋግሞው ሊያስቡበት ይገባል። የእነ ቤቢሾ ሠፈር ፀሐይ ከዛሬዋ ከእኛ መንደር ፀሐይ ይበልጥ ደምቃ እንደምትወጣ ሳንሰለች ልናስተምራቸው ይገባል። በእናንት ሠፈርስ ፀሐይ ወጥታለች? ሰላም ይሁን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 9/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)