የበዓል ግርግሩ በርትቷል። የገና በዓል መምጣትን የሚያመለክቱ የመብራት ጌጦች እዚህም እዚያም ሲብለጨለጩ ላስተዋለ የፈረንጆቹ አከባበር ምን ያህል ተጽእኖ እያሳደረብን እንደሚገኝ ይረዳል። ከትንሿ የህጻን ልጅ የገና ቀይ ኮፍያ ጀምሮ እስከ ትልቁ የገና ዛፍ ድረስ ቤት ለማድመቂያነት ለበዓሉ ይውላል። የገና በዓል ያለውም አዳዲስ እቃዎችን ሸምቶ፤ የሌለው የነበረውን አጸዳድቶ የሚውልበት በዓል ነው።
በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በተጋነነው ማስታወቂያው የ ኑ ጎብኙኝ ጥሪውን አጧጡፎታል። በማስታወቂያቸው ተስበውም ሆነ ለመዝናናት አስበው በየቀኑ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ገበያተኞች ማዕከሉን ይጎበኛሉ። በኤግዚቢሽኑ ላይ የሚተላለፉ የዋጋ ቅናሽ ማስታወቂያዎች ደግሞ ይበልጡን ቀልብ ይስባሉ። የቅናሽ ማስታወቂያው ከ30 በመቶ እስከ 50 በመቶ ይደርሳል መባሉ ደግሞ እኔንም ገበያውን እንድመለከት ስለገፋፋኝ ወደቦታው አቅንቼ ነበር።
በኤግዚቢሽኑ ከምግብ እና አልባሳት ጀምሮ እስከ ትላልቅ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ድረስ በጊዜያዊ መደብሮች ውስጥ ተደርድረዋል። አንዳንድ ሻጮች «ሁለት ሸሚዝ ለገዛ አንድ ፓክአውት እንመርቃለን» ብለው ሲለጥፉ ሌሎቹ ደግሞ በደፈናው «ታላቅ የዋጋ ቅናሽ» የሚል ማስታወቂያቸውን በራፋቸው ላይ ሰድረዋል። ሸማቾችም ሆኑ ሻጮች ፋታ የሌለው ግብይት ውስጥ በመሆናቸው ትርምሱ በርትቷል።
ከሱቆቹ መካከል ወደ አንዱ ጎራ አልኩና የሽያጭ ሠራተኛውን ለጥቂት ደቂቃዎች አናገርኩት። አቶ ፍላጎት አሰፋ ይባላል፤ የሚዊ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች አምራች ድርጅት ሠራተኛ ነው። በኤግዚቢሽኑ የዋጋ ቅናሽ ያደረጉና የተወሰነ ጭማሪ ያላቸውም መደብሮች መኖራቸውን ይናገራል። የእርሱ ድርጅት የገና ግብይት ጊዜያዊ መደብር ግን በርካታ ሰዎች የሚጎበኙት በመሆኑ ከብዛት በሚገኝ ትርፍ ላይ አተኩሮ እየሠራ እንደሚገኝ ይገልጻል።
ከ19 ኢንች ጀምሮ እስከ 65 ኢንች ቴሌቪዥኖች እንደሚሸጥ የሚናገረው አቶ ፍላጎት፤ ለአብነት 65 ኢንቹን ቴሌቪዥን በ42 ሺ ብር ለሽያጭ ማቅረቡን ያስረዳል። ይህ ዋጋ ከመደበኛ የመርካቶ እና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መደብሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም እርካሽ ነው። ምክንያቱም በሌሎች አምራች ድርጅቶች ስም የሚሸጠውን ተመሳሳዩን የኤሌክትሮኒክስ ምርት እስከ 60 ሺ ብር የሚሸጡ ነጋዴዎች መኖራቸውን አስተውሏል።
በርካታ የኤግዚቢሽኑ ተሳታፊ ነጋዴዎችም በአንድ ቦታ በብዛት የሚያገኙትን ሸማች ለመሳብ ቅናሽ አድርገው ለመሸጥ የወሰኑ አሉ። ድርጅታቸው በእያንዳንዱ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ ለኤግዚቢሽኑ ተብሎ ከሁለት መቶ ብር ጀምሮ እስከአምስት መቶ ብር ቅናሽ አድርጓል። ይህም ከብዛት የሚገኝ የአነስተኛ መጠን ትርፍ ለማግኘት በማሰብ መሆኑን ያስረዳል። ቅናሽ ያላደረጉ የተወሰኑ ነጋዴዎች ግን የራሳቸው የነጻ ዋጋ ገበያ አካሄድ በመሆኑ ሸማቹ ያዋጣኛል ካለ ሊገዛቸው ካልሆነም ሊተዋቸው እንደሚችል አስበው የተሻለ ዋጋ ቢያቀርቡ መልካም መሆኑን ይናገራል።
ወጣት ውብአለም በላይ ከሸመታው ይልቅ በግቢው ውስጥ የሚታዩት ትዕይንቶች እንደሚስቧት ትናገራልች። በመሆኑም አመሻሽ ላይ የሚቀርቡትን የሙዚቃ ትዕይንቶች ለማየት ስትገባ የሚቀርቡት ትኩስ ምግቦች ከምትጠብቀው በላይ አስደንግጧታል። «የሚገርመው ውጭ ላይ በአምስት ብር የሚሸጡ ሳንቡሳዎች እዚህ እስከ ሃያ አምስት ብር ይሸጣሉ። ችብስ እንኳን በአቅሙ እስከ ሰላሳ ብር እየተሸጠ ነው፤ በአጠቃላይ ሲታይ ፈጣን ምግብ የሚያቀርቡት ከፍተኛ ዘረፋ እያካሄዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም» በማለት አዘጋጆቹ ሊያስቡበት እንደሚገባ አሳስባለች።
«ነጋዴዎቹ የቦታ ኪራይ ስለሚጨምርባቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ምንም ቦታ ሳይዙ እየተዘዋወሩ የሚሸጡት ግን እስከ አምስት እጥፍ ዋጋ ጨምረው መሸጣቸው ተገቢ አይደለም» የምትለው ወጣት ውብአለም በአጠቃላይ የጨረታውን ዋጋ በመቀነስ ተከራዮችም ሆኑ ሌሎች በግቢው ውስጥ የሚነግዱት ሁሉ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ መደረግ አለበት የሚለውን ምክረሃሳብ ሰንዝራለች።
ወይዘሮ ትዕግስት ቢራራ ደግሞ በኤግዚቢሽኑ የገና በዓል የቤት መስዋቢያ ዕቃዎችን እና የህጻናት ልብሶችን ሲሸምቱ ነው ያገኘኋቸው። ለስሙ የዋጋ ቅናሽ ይባላል እንጂ አብዛኛው ምርቶች ላይ ጭማሪ መኖሩን ታዝበዋል። ለአብነት አንድ መካከለኛ የገና ዛፍ ሁለት ሺ ብር እያሉ የሚጠሩ ነጋዴዎች ከመደበኛው ዋጋ ላይ በግማሽ መጨመራቸውን መታዘብ ይቻላል። ከበዓል ውጪ በሆኑ ቀናት አምስት መቶ ብር የሚገኘውን የህጻናት ልብስ ስድስት መቶ ብር የሚሉ ነጋዴዎች አጋጥመዋቸዋል። በመሆኑም ታላቅ የዋጋ ቅናሽ አለ ተብሎ የሚገለጸው የኤግዚቢሽን ግብይት እንደሚጠበቀው ለሸማቹ አዋጭ አለመሆኑን ይናገራሉ።
በሌሎች ተመሳሳይ ኤግዚቢሽኖች ላይ የዋጋ ቅናሽ አለመኖሩን አውቀው እንደሚሄዱ የሚናገሩት ወይዘሮ ትዕግስት፤ ምርቶችን በአንድ ቦታ የሚያገኙበትን እድል ስለሚፈጠርላቸው ብቻ እንደሚመርጧቸው ያስረዳሉ። ለሻጩም አዋጭ የሚሆነው አካሄድ ከብዛት የሚገኝ አነስተኛ ትርፍ ላይ ማተኮር ነው። ምክንያቱም እያንዳንዱ ሸማች የዋጋ ቅናሽ ካገኘ ለሌላም ጊዜ የሚሆነውን ዕቃ በመሸመት ካሰበው የበለጠ መጠን ያለውን ምርት ሊገዛ እንደሚችል ያስረዳሉ።
«እኔ ለምሳሌ የህጻናት ልብስ ቅናሽ ቢኖረው ለልጆቼ ተጨማሪ ልብሶችን ገዝቼ እንድሄድ ዋጋው ሊገፋፋኝ ይገባል። ነገርግን አሁን ዋጋው ስላላስደሰተኝ መግዛት ከምፈልገው በታች አሳንሼ ነው የሸመትኩት። ስለዚህ የበዓል ገበያ አቅራቢዎች ይበልጥ ትርፋማ የሚያደርጋቸውን ምርታቸውን ለማስተዋወቅ የዋጋ ቅናሽ ቢያቀርቡ ሸማቹም ለመግዛት ይበረታታል እነርሱም ትርፋማ ይሆናሉ» ይላሉ።
አቶ በላይ መኩሪያ ከመግቢያ ዋጋው ጀምሮ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ። የአውድ ዓመት ገበያ በመሆኑ ቢያንስ ከመርካቶ በተሻለ ዋጋ መሸመት ነበረብን። መርካቶ የምናውቀው እቃ ዋጋውን ጨምሮ ባዛር ላይ መቅረቡ ተገቢ አይደለም ይላሉ። «ነጋዴዎቹ የቦታ ኪራዩ ስለተወደደባቸው በምርቶቻቸው ላይ ዋጋ መጨመራቸውን ይገልፃሉ፤ ኤግዚቢሽኑን የሚያዘጋጁትም በከፍተኛ የጨረታ ዋጋ ስለሚይዙት የቦታ ኪራይ ዋጋው ላይ ይጨምራሉ። ይህ በመሆኑ የሁሉም ጭማሪ ተጠራቅሞ ሸማቹ ላይ እያረፈ ነውና መንግሥት ቢያንስ በዓውድዓመት ባዛሮች ላይ የጨረታ ዋጋውን በመቀነስ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል» በማለት ትዝብታቸውን ሰንዝረዋል።
አቶ አዲኒክ ወርቁ በኤግዚቢሽን ማዕከል የገና ኤክስፖን ያዘጋጀው የሃበሻ ዊክሊ ኃላፊ ናቸው። በአጠቃላይ 500 ነጋዴዎች በኤግዚቢሽኑ ቦታ ተከራይተው እንደሚገኙ ይገልጻሉ። በአጠቃላይ እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ 500 ሺ ሰዎች ባዛሩን እንደሚጎበኙት ይጠበቃል። በመሆኑም በርካታ ሸማቾች ዕቃዎችን እንደሚሸምቱ አያጠራጥርም። የዋጋ ቅናሽ ያደረጉም ሆነ በመደበኛ ዋጋቸው የሚሸጡ መኖራቸውን ይናገራሉ።
ባዛሩ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ እና ብዙ የማስተዋወቅ ስራ የሚሰራበት ነው። በመሆኑም ተሳታፊ ድርጅቶች በዋነኛነት ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ ይፈልጋሉ። ከዚህ አንጻር በርካታ ሰዎች ስለሚመጡ የዋጋ ቅናሽ አድርገው መሸጣቸው እንደሚያዋጣቸው ያሳስባሉ። በሌላ በኩል አምራች ድርጅቶችም ስለተሳተፉበት በፋብሪካ ዋጋ እቃዎች ቀርበዋል። ይሁንና ሁሉም ቅናሽ አለው ማለት አይቻልም። የነጻ ገበያ ውድድር በመሆኑ ሸማቹ የሚመቸውን መርጦ መግዛት እንደሚችል ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011
በጌትነት ተስፋማርያም