የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ – ለገጠሩ ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር መጎልበት

ከሀገሪቱ የገጠር ሕዝብ በርካታ የሚባሉት በተራራማ አካባቢዎች እና በወንዞች መብዛት ምክንያት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው የተገደበ ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡ እነዚህ ማህበረሰቦች ለማህበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽ ካለመሆናቸውም በተጨማሪ ምርቶቻቸውን ገበያ አውጥተው ለመሸጥና የግብርናና የመሳሰሉትን ግብአቶችን ለማግኘት በእጅጉ ይቸገራሉ፡፡

ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የግድ በሆነ ጊዜ ዙሪያ ጥምጥም መጓዝ ይገደዳሉ፤ በዚህም የጊዜ ብክነትና እንግልት ይደርስባቸዋል፡፡ በአንዳንድ አስቸጋሪ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጦች ሲያልፉም እስከ ህይወት ማጣት ለሚደርሱ አደጋዎች የሚጋለጡበት ሁኔታ እንዳለም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይህን አይነቱን ችግር ለመፍታት በሚል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት የተንጠልጣይ ድልድዮች ግንባታዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ የድልድዮቹ መገንባትም ድልድይ ባለነበረባቸው ጊዜያት በአካባቢዎቹ በሰዎች ላይ ይደርሱ የነበሩ አደጋዎችን ማስቀረት ችሏል።

የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ የማህበረሰብ ትስስሮችን ከማጠናከሩም በላይ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ወይም ለማግኘት በሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ወቅት ጊዜን፣ ወጪን ከመቆጠብ አኳያም የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይታመናል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የመሰረተ ልማት ዘርፍ አማካሪ መሀመድአሚን አደም በገጠር ትስስር እና ተደራሽነት ፕሮግራም ደግሞ አስተባባሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚገልጹት፤ የገጠር ትሰስር እና ተደራሽነት ፕሮግራም የመንግሥት የ10 ዓመት የልማት እቅድ አንድ አካል ነው።

ህብረተሰቡ ከዋና መንገድ ጋር ባለመተሳሰሩ ሳቢያ ከፍተኛ የተደራሽነት ጥያቄ ሲያነሳ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ምርት ወደ ገበያ ባለመድረሱ በተለይ የገጠሩ ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እየቀነሰ መጥቷል ይላሉ። ይሄንንም ችግር ለመፍታት ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን የገጠር ትሰስር እና ተደራሽነት ፕሮግራም መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። ፕሮግራሙ በዓለም ባንክ ፈንድ የሚደረግለትና ለአምስት ዓመት የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመው፣ በተለይ በገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት ማህበረሰብ ከማህበረሰብ ጋር የማይገናኝበት፤ የገጠሩ ማህበረሰብ ከገበያ ማዕከላት ጋር የማይገናኝበት ሁኔታ ይታያል። የጤናና የትምህርት ተቋማትም እንዲሁ በቀላሉ ማግኘት አይቻልም፡፡ ይህን ችግር በመቅረፍ እና የማህበረሰብ ግንኙነት ለመፍጠር የተንጠልጣይ ድልድይ ማስፈለጉን አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በዚህም ረጅም እና አጭር የተንጠልጣይ ድልድይ አሰራር ማኑዋል የተዘጋጀ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ እስካሁን የረጅም ድልድይ (ሎንግ ስፓን) ስራው ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ ይህንንም በቀጣይ ተግባራዊ ለማድረግ ይሄንን ባካተተ መልኩ ማኑዋል እየተዘጋጀለት ነው።

አሁን የሚሰሩት አጭር የሚባሉት አይነት ሲሆኑ፤ የራሳቸው ዲዛይን፣ ቅርፅ አላቸው። የአገልግሎት ጊዜያቸው፣ የሚጠቀሙባቸው ማህበረሰብ እና የእንቅስቃሴው ብዛት ጥናትም ይደረግበታል።

በዚህ ጥናት መሰረትም እንስሳትን እስከማሻገር፣ ሞተር ሳይክል፣ ብስክሌት እና አልፎ አልፎም ባጃጆችን ጨምሮ ማሳለፍ የሚችሉ ተንጠልጣይ ድልድዮች የሚገነቡ ይሆናል፡፡ በቀጣይም መለስ ያሉ ተሽከርካሪዎችን ታሳቢ በማድረግ ድልድዮቹን ለመስራት ጥናት እየተደረገ ነው።

እሳቸው እንዳሉት፤ እስካሁን ባለው ሂደትም እንስሳትን እና ሰውን ማሻገር የሚችሉ ተንጠልጣይ ድልድዮች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ የገጠር ትስስር ፕሮግራም በዲዛይንም ሆነ በአገልግሎት ከዚህ ቀደም ሲሰሩ ከነበሩት ተንጠልጣይ ድልድዮች በተሻለ መልኩ ለመስራት ፕሮግራም ተይዟል።

በተለይም ተራራማ በሆኑ የገጠር አካባቢዎች ህብረተሰቡ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚቸገርበት ሁኔታ እንዳለ አማካሪው ገልጸው፤ በግንባታው ረጅም ርቀት ተጉዘው ትምህርት፣ ጤና የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎቶችን የማግኘት ተግዳሮትን ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

ቆላማ በሚባሉ አካባቢዎችም ተንጠልጣይ ድልድይ ባለመኖሩ የተነሳ ጎርፍ በመጣ ቁጥር ሰዎች ለአደጋ ሰለባ እየሆኑ መሆናቸውን አስታውቀው፤ በተደረገው ጥናትም በሁሉም ክልሎች ድልድዮቹ እንዲገነቡ ከፍተኛ ፍላጎት እንደሚታይ ጠቅሰው፤ በጥቅሉ ከ10 ሺህ በላይ የተንጠልጣይ ድልድዮች ፍላጎት እንዳለ ተረጋግጧል ብለዋል።

በዚህ ፕሮግራምም 373 ተንጠልጣይ ድልድዮችን በሁሉም ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመስራት በዓለም ባንክ ፕሮግራም ተካቶ ይሰራል ያሉት አማካሪው፣ ክልሎቹም አምስት መስፈርቶች ተልኮላቸው በመረጡት አካባቢ ግንባታው የሚከናወን ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።

አማካሪው ‹‹ሄልቬታስ ኢትዮጵያ› በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የተንጠልጣይ ድልድይ ስራዎችን እየሰራ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ግንባታው አሁንም ከክልል መንግሥታት ጋር በመሆን 20 በመቶውን ወጪ እሱ እየሸፈነ፣ ቀሪውን 80 በመቶ ክልሎች እየሸፈኑ በአምስት ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

አማካሪው እንዳብራሩት፤ በዚህ የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም ተግባራዊ የሚደረገው የአዲስ መንገድ ጥርጊያ፣ የነበሩትን መንገዶች ጠግኖ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ድልድይ በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ውሃ ማሳለፍ እንዲችሉ ተደርገው ድልድዮች ይሰራሉ፤ የመዳረሻ መንገድ ይሰራል፤ የተንጠልጣይ ድልድዮች ይገነባሉ።

ግንባታው ከዚህ ቀደም የገጠር መንገድ ፕሮጀክት /ዩራፕ/ ሲሰራበት በነበረው ሳይሆን፣ ወይም በቀጥታ ለግለሰቦች ተሰጥቶ ግንባታዎች የሚካሄዱበት ሳይሆን ውድድርንና ውድድርን መሰረተ ያደረገ ነው። ለዚህም በየክልሉ በፌዴራል ደረጃ የተመዘገቡ በርካታ ኮንትራክተሮች፣ የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ፕሮግራሙ በቀጥታና በተዘዋዋሪ 560 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጠርበት እንደሆነም አስታውሰዋል።

የሄልቬታስ ኢትዮጵያ አስተባባሪ ወይዘሮ ፀሐይ ፀጋዬ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ‹‹ሄልቬታስ›› በኢትዮጵያ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ አንዱ ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን የተንጠልጣይ ድልድዮችን በመስራት ህብረተሰቡ እርስበርስ እንዲገናኝ እና የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ማድረግ ነው። በዚህም ለሀገራዊ የድህነት ቅነሳ ስራ የራሱን በጎ ሚና እየተወጣ ነው።

በኢትዮጵያ መንግሥት የተንጠልጣይ ድልድዮች ግንባታ በገጠር መንገዶች ትስስር እና ተደራሽነት ፕሮግራም ውስጥ መካተቱ ትክክለኛ እርምጃ ነው፡፡ ከተንጠልጣይ ድልድይ አስተዋፅኦ መካከል ድልድዩ ተገልለው ለቆዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይሰጣል፤ በሕይወት ላይ አደጋ በሚያስከትሉ አስቸጋሪ ቦታዎች ላይ ድልድዩ ይገነባል፡፡ ለኢኮኖሚ፣ ለጤና እና ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦቶችን ያመቻቻል።

ሄልቬታስ በኢትዮጵያ በፓይለት ደረጃ መንቀሳቀስ ከጀመረ 20 አመታት ማስቆጠሩን አስታውሰው፣ አሁን ደረጃውን በማሻሻል በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ እያስተዋወቀ ያለው ሶስት ዓይነት ተንጠልጣይ ድልድይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ እስከ 120 ሜትር ርዝመትና አጭር ቋሚ /ሾርት ስታንድ/ ያለው ተንጠልጣይ ድልድይ አንዱ ሲሆን፤ ከ120 ሜትር በላይም የሚርዝሙ ድልድዮች አሉ። እነዚህ ሎንግ ስፓን የሚባሉ ተንጠልጣይ ደልድዮች በሌላው ዓለምም ይሰራባቸዋል።

በኢትዮጵያ ማኑዋል ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው እስከ 120 ሜትር የሚረዝመው ወይም አጭር የሚባለው አይነት ተንጠልጣይ ድልድይ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ መሰረት ከ32 ሜትር በታች የሆኑትን እንዲሁም እንደ መሬቱ አቀማመጥ እየታየ እስከ 120 ሜትር ያለው ተግባራዊ ተደርጓል ሲሉ አብራርተው፣ በኢትዮጵያ ረጅም የተንጠልጣይ ድልድይ አይነት ፍላጎት እንዳለም አመላክተዋል።

ወይዘሮ ጸሀይ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል ሄልቬታስ ከክልል መንገዶች አስተዳደር ጋር በመተባበር እና ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር በመሆን ለ15 ዓመታት የተንጠልጣይ ድልድይ ፕሮጀክቶችን የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት በሚል በስድስት ክልሎች ላይ ተግባራዊ አድርጓል።

ሄልቬታስ በፓይለቱ ወቅት በደረሰበት ውጤት ላይ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን እና ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር ተወያይቷል። በውይይቱም ዘላቂ እና ደረጃው የተሻሻለ የተንጠልጣይ ድልድይ ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው እና የተሰሩትም አገልግሎታቸውን በመጠበቅ በቂ ጥገናዎችን ማከናወን ላይ ተግዳሮት መኖሩ ተመላክቷል።

ሄልቬታስ የማስተባበር ሚናውን እንዲጫወት ጠቅሰው፣ የእውቀት ሽግግሩን በማስፋት ላይ የአቅጣጫ ለውጥ ተደርጓል ሲሉ አስተባባሪዋ ተናግረዋል። መንግሥትም ይሄንን አቅጣጫ በመከተል ከዚያ በኋላ ዲዛይን የተደረጉ “ፈርስት ማይል” የሚባለው ፕሮጀክት በአማራ ክልል ላይ ሙከራ (ፓይለት) መደረጉን ጠቅሰው፣ በዚህም የአማራ ክልል 80 በመቶውን፣ ሄልቬታስ 20 በመቶውን (በይበልጥ በአቅም ግንባታ ስራ፣ በስልጠና እና በማስተባበር፣ ከውጭ በሚገቡ ቴክኖሎጂ አቅርቦት) ላይ ተሳትፎ አድርጓል ብለዋል።

በአማራ ክልል ይህ ስኬታማ መሆኑ በመታየቱ ወደ ሌሎች ክልሎች የማስፋት እንቅስቃሴ ተጀምራል ሲሉ ጠቅሰው፤ ይህም ስድስት ክልሎች ላይ ለመፈፀም ታቅዶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አምስት ክልሎች ላይ ፕሮጀክቱ በስኬታማነት መተግበሩን ጠቅሰው፣ በዚህ አሰራር ሄልሜታስ የመንገድ ቢሮ ባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት ስራ ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ለአማካሪዎች፣ ተቋራጮች፣ አምራቾች እና ክልሉ በሚመርጣቸው መሰረት ስልጠና መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በዚህም የኮንትራት አስተዳደሩን ክልሎች እንደሰሩትና የሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች እና አምራቾች የሀገር ውስጥ መሀንዲሶችም ክህሎቱን ማግኘት መቻላቸውን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የሶስት ዓመቱ ፕሮጀክትም ወደ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ቀደም ሲል የተገነቡት ተንጠልጣይ ድልድዮች ከዚያ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተጠቀሙባቸው ነው። ፕሮጀክቱ በተሰራባቸው አካባቢዎች በአማካይ አንዱ ድልድይ 20 ሺህ ሰዎችን እያገለገለ ስለመሆኑ ሪፖርት መደረጉን አስተባባሪዋ ጠቁመዋል።

ሄልቬታስ ከአሜሪካው ብሪጅስ ፎር ፕሮስፒሪቲ ጋር በመሆን በሶስት ዓመት ውስጥ የሚያስገነባው 10 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት የተመደበለት ሲሆን፣ በአምስቱ ክልሎች (አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ) በዲዛይን፣ በግንባታ እና በፋብሪኬሽኑ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ከፕሮጀክቱ ሶስት ዋና ዋና ዓላማዎች አንዱ የሆነው የአቅም ግንባታ ተፈጥሮበታል።

ከወጪ አኳያም በትንሽ ወጪ ብዙ ውጤቶች ያሉት ስራ ነው ያሉት አስተባባሪዋ፣ በአማራ ክልል በአንደኛው ዓመት ከተሰሩ ተንጠልጣይ ድልድዮች ሥራ በኋላ በተሰራ ጥናት መሰረት በአማካይ በ53 ደቂቃ የማህበረሰቡን የጉዞ ሰዓት ማሳጠር መቻሉንም ጠቁመዋል። ይህም ጊዜን መቆጠብ ብቻ ሳይሆን ብዙ አደጋዎችን እንደሚያስቀርም ተናግረዋል፡፡

ሄልቬታስ በሶስት ዓመት ውስጥ ወደ 150 ተንጠልጣይ ድልድዮችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል የ48ቱ ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን የ35ቱ ግንባታ በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ እንደ ሀገር በሺዎች የሚቆጠሩ ድልድዮች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በሀገር ደረጃ የገጠር ትስስር እና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም በተለይ ከምርትና ምርታማነት ከግብርና ልማት ጋር ተያይዞ የሚሰራ ነው። በተለይ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እና በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ልማትን በመደገፍ የጎላ ፋይዳ አለው ።

ከአማራ ክልል አኳያ ሲታይ ቀደም ሲል በገጠር መንገድ ፕሮጀክት/ዩራፕ/ የተሰሩ መንገዶች የማቅረብ እንጂ የተሟላ የድልድይ እና መሰል ስራዎችን ያሟሉ አልነበሩም። መንገዶቹ የነበራቸውን የጥራት፣ የተሟላ አገልግሎት አለመስጠት ችግር አሁን ያለው የገጠር ተደራሽነት እና ትስስር ፕሮግራም ይፈታዋል ተብሎ ይገመታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

እንደ ኃላፊው፤ የክልሉ ማህበረሰብ በጥሬ ገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በሀሳብ እና በጉልበት ባለቤትም ተሳታፊም ሆኖ በመስራት የተሻለ ልምድ አካብቷል። ፕሮግራሙ በክልሉ ተግባራዊ የሚደረገው የወረዳዎችን የቆዳ ሽፋንና የሕዝብ ብዛት ታሳቢ በማድረግ ነው።

የመንገድ ሽፋን ዝቅተኛ የሆነባቸውን ወይም ያልተቀራረበባቸውን ወረዳዎች ታሳቢ ያደረገ ነው። በየወረዳው የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት በመንግሥት እና በግል ደረጃ የተወሰነ ተቋማት ተሟልተው ከግብኣት፣ ከፋይናንስ እና ከቴክኖሎጂ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ተቋማት ያሉበትን ታሳቢ ባደረገ መስፈርት መሰረት ወረዳዎቹ ተመርጠዋል።

በዚህ መሰረት በክልሉ በሁሉም ዞኖች ሁለት ወረዳዎች በድምሩ 28 ወረዳዎች ላይ ፕሮግራሙ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። በቀጣይም ፕሮግራሙ በእነዚህ ወረዳዎች ውጤቱ ታይቶ ወደ ሌሎች ወረዳዎች ሊሰፋ እንደሚችል አመልክተው፣ ይህም እንደ ሀገር እንደሚወሰን ገልጸዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You