ቅድመ- ታሪክ
ገጠር ተወልዶ ማደጉ እንደ እኩያ ባልንጀሮቹ የከብት ጭራን እንዲከተል አድርጎታል። በቤተሰቦቹ ፈቃድና በእሱ ዕድለኛነት በዕድሜው ትምህርት ቤት ገብቶ ቀለም እንዲቆጥር አጋጣሚው መልካም ሆነለት።
በላይ ዕጣ ፈንታው ከትምህርት አውሎ ከቤት ሲመልሰው ወላጆቹን በአቅሙ ማገዝን አልተወም። እንደልጅነቱ እየታዘዘ፣ ታናሽነቱን በስራ ትጋት ለማሳየት ደፋ ቀና ማለትን ያዘ። ከትምህርት መልስ ከአረም ከጉልጓሎው እየገባ የድርሻውን ይከውናል።አለፍ ሲል ደግሞ ከእርሻ ማሳ ወርዶ በሬን ከጥማድ እያገናኘ ታላላቆቹን ከድካም ያሳርፋል።
ያለምንም ችግር ከትምህርት ውሎ መመለሱን ያስተዋሉ አንዳንዶች የታዳጊውን በጎ ጅምር በቀና ተርጉመው ስለነገ መልካሙን ተመኙለት።ይህኔ በላይ ከብዙዎች ግምት ተነስቶ ራሱን አጀገነ። ለትምህርቱም ትኩረት ሰጠ። አሁንም ለወላጆቹ መታዘዝን አልተወም። በብርታቱ ቀጥሎ አምስተኛ ክፍል ደረሰ።
በላይ አምስተኛ ክፍል ሲገባ መጪውን የትምህርት አመታት እያሰበ የራሱን ዕቅዶች ነደፈ።በእሱ ቀዬ ተወልደው በትምህርት የላቁ ያገሩ ልጆችን እያስታወሰም የእነሱን ፈለግ መከተል እንዳለበት ወሰነ። መጪዎቹን ጊዜያት በወጉ ከተጠቀመ ሌሎች ከደረሱበት ጫፍ እንደሚገኝ እርግጠኛ ሆኗል።
አሁን ካለበት ጥቂት ፈቅ ሲል በተሻለ ደረጃ እንደሚቆም ያሰበው ታዳጊ ጅምሩን አጠንክሮ ለነገ ሩጫውን ቀጠለ። የእርሻ ውሎውንና የትምርህት ቆይታውን እያቻቻለም በጥንካሬው ገፋ ።አሁንም መልካ ምነቱን ያስተዋሉ ሁሉ ምርቃትን ከምስጋና እየቸሩ ‹‹እሰዬው›› ሲሉ አበረቱት።
አዲስ አመል
በላይ አምስተኛ ክፍል ገብቶ ትምህርቱን እንዳጋመሰ ከቤተሰቦቹ ጋር የነበረው የቀድሞ ሰላማዊነት በጠብና ጭቅጭቅ ተተካ። የትናንቱ ፍቅርና አክብሮት እንደቀድሞ ያለመሆኑን የተረዱ ወላጆችም ልጃቸውን እንደ ትንሽነቱ ገስጸው ሊመልሱት ሞከሩ። አንዳንዴ እንደልጅነቱ ሊቀጡት አስበው ብትር ያነሱበታል።ይህ ድርጊት ግን ጉርምስና ለጀመረው ወጣት በጎ ትርጉም አላመጣም።በ‹‹አትናገሩኝ›› ሰበብ ኩርፊያና ግልምጫን አስከትሎ በእልህና ንዴት ያናግር ያበሳጨው ያዘ።
በበላይና በወላጆቹ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት የተለመደ አይነት የቤተሰብ ግጭት አልሆነም።ጠዋት ማታ መሬት ሲቆረቁር የሚውለው ወጣት በታላላቆቹ ላይ ቂምና ጥላቻን ቋጠረ። ለወዳጅ ዘመድና ለጎረቤት ምክርም ጆሮ ዳባ ሲል ትኩረትን ነፈገ።
አንድ ቀን ደግሞ በላይ መክረሚያውን ሲያስብበት በቆየው ጉዳይ ላይ መቁረጥ እንዳለበት ወሰነ።ይህን ዕቅዱን ካሰበበት የቆየ ቢሆንም ለውሳኔው ተቸግሮ እንደነበር ያስታውሳል።አሁን ግን ፈጥኖ ከመወሰን ሌላ መፍትሄ አላገኘም። የሚጣሉትንና የሚጣላቸውን ቤተሰቦቹን ከነአካቴው ለመራቅ ያለው አማራጭ ከአካባቢው መጥፋትና ከአይን መሰወር ብቻ ነው።
በላይ ስለአዲስ አበባ ህይወት ብዙ ሲባል ሰምቷል።አንዳንድ የአገሩ ልጆች ከስፍራው ቆይተው ሲመለሱ በእጅጉ ተለውጠውና አምሮባቸው ጭምር ነው።እስከዛሬ እንደተረዳው በከተማዋ የደረሰ ሁሉ የልፋቱን ፍሬ አያጣም። አሁን ደግሞ እሱም በቦታው ተገኝቶ የሚባለውን ሁሉ ማየትና ማግኘት ፈልጓል።
ከቀዬ መውጣት
በላይ እንደዋዛ ሲያስብበት በቆየው ጉዳይ ላይ ወስኖ ጓዙን ሽክፏል። የሚሄድበት አገረ – አዲስ አበባ ምንም አይነት ወደጅ ዘመድ እንደሌለው ያውቃል። አንዳንድ ዘመዶች እንኳን ቢኖሩ ወላጆቹን ብቻ የሚያውቁ ናቸውና ለእሱ የሚበጁት አይሆኑም።ያም ሆኖ ግን የአዲስ አበባ ሰው ባይተዋር እንደማያደርገው ገምቷል።
ማልዶ ከቀዬው ሲወጣ ብዙ ሀሳብ በአይምሮው ይመላለስ ነበር። አንድ ቀን ወደ ሀገሩ ሲመለስ ራሱን ለውጦና እንደሌሎች በኑሮው ተሻሽሎ እንደሚሆን እርግጠኛ ሆኗል።ይህ ስሜትም የነበረበትን ስፍራ እስኪለቅ አብሮት ተራምዷል።
በላይ ተወልዶ ያደገበትን መርጦለማርያምን ትቶ ወደአሰበው ከተማ ለመግባት በአውቶቡስ ጉዞውን ጀመረ።አድካሚውን የአባይ በረሀን አቋርጦም ብዙ ሲያልማት ወደነበረችው አዲስ አበባ አመሻሹ ላይ ደረሰ።
አዲስ አበባና የገጠሩ ወጣት ከዚህ ቀድሞ ተያይተው አያውቁም።ከተማዋ አዲስ እንግዶችን መቀበል ብርቋ አይደለም።በላይ ግን በእንዲህ አይነቱ ስፍራ ለመገኘት ገና የመጀመሪያው ነው።የምሽቱ መብራት ከመንገዱ ስፋት ጋር ተዳምሮ ግራ ሲያገባው ለአፍታ ምን ማድረግ እንዳለበት ተቸገረ። ምሽቱ ሲገፋና ግርግሩ ሲቀንስም ከአንድ ጥግ አረፍ ብሎ ወጪ ወራጁን መቃኘት ያዘ።
አዲስ ህይወት
በላይ ከተቀመጠበት ሆኖ ድካሙን ሊያሳርፍ ጎኑን ከመሬት አስነካ።ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ መሆኑን አላጣውም።ከአጠገቡ እንደሱው ስፍራውን የተጋሩት ግን በዚህ ስሜት እንዳይዘልቅ ምክንያት ሆነው ምሽቱን በጎ አደረጉለት። ከያዙት ምግብ አቅም ሰው ረሀቡን አስረሱት። ከብርድና ቅዝቃዜው ሊታደጉትም ከለበሱት ገፈው ሙቀትን አጋሩት።
ሲነጋ በላይ ራሱን ከጎዳና ላይ እንዳሳረፈ አገኘው።አዲስ አበባን በዚህ መልኩ ያወቃት ወጣት አብረው ካደሩት ልጆች ተላምዶ ባልንጀርነትን አጠነከረ። እነሱም ከለበሱት እያጋሩ፣ ከለመኑት እያቀመሱ እንግድነቱን አስረሱት።አካባቢውን እያዞሩም መግቢያ መውጫውን አሳዩት።
ከቀናት በኋላ በላይ የጎዳና ህይወትን ተቀብሎ ከጓደኞቹ ተመሳሳለ።ውሎ አዳሩን በዛው አድርጎም ብርድና ዝናቡን፣ ሙቀትና ንፋሱን በፈረቃ ለመደው።ከነበረበት ርቆ በሌላ ሰፈር ኑሮን ሲጀምር ደግሞ የጎዳና ህይወት ስራ አልባ እንደሆነ ይገባው ያዘ። ይህኔ ቀላል የተባለ አማራጭን ለመጠቀም ከራሱ ጋር ምክር ያዘ።
ሀያት ሆስፒታል ፊት ካለ ጫካማ ስፍራ አዲሱን ህይወት እንደጀመረ በአካባቢው ካሉ ሌሎች ልጆች ጋር በቀላሉ ተላመደ። እነሱን ለመምሰል ሲል የጀመረው የሲጋራና የመጠጥ ልምድም የከፋ ሱስ ጣለበት።እንደዋዛ የጀመረውን አመል ባሻው ጊዜ ካላገኘ ሰላም እንደሌለው የሚያውቁት ጓደኞቹ ከሚቅሙትና ከሚያጨሱት እያጋሩ አብረውት ይቆያሉ።
ይህ ባልተሳካ ጊዜም በላይ አሳቻ ሰዓት እየመረጠ ከአስፓልቱ ዳርቻ ይቆማል።ሁሌም ተስፈንጣሪ ጩቤ ከጎኑ የማይጠፋው አድፋጭ አላፊ አግዳሚውን እያስፈራራ ያገኘውን ይዘርፋል።ሞባይል የያዙ፣በአጉል ሰዓት የደረሱና ያላቸውን ያልሰጡ መንገደኞች በዋዛ አይለቀቁም።ንብረታቸውን አስረክበውና በዘራፊው ጡጫ ተደቁሰው በማስጠንቀቂያ ይባረራሉ።
በላይ በየቀኑ ተደጋጋሚ ወንጀሎችን በስፍራው ይፈጽማል።አንድም ቀን ግን ከፖሊሶች ዓይን ገብቶ ተይዞ አያውቅም። ክስ ቀርቦበትና ተጠርጥሮ ያለማወቁ ደግሞ የልብ ልብ እየሰጠው ቀኑን ሙሉ በጫካው እየተኛ ምሽቱን የሚያካሂደው ዝርፊያ የመተዳደሪያ ያህል ሆኖት ለሱስ አመሉ ተርፎታል።
ሰኔ 22 ቀን 2009 ዓም
ክረምቱ እየገፋ ነው። ምሽቱም ከሌሎች ቀናት የከበደ ይመስላል። ውሎውን ሲዘንብ የቆየው ዝናብ ደግሞ ማምሻውን በካፊያ ተመልሶ አካባቢውን እያጨቀየው ነው። ገና በጊዜ ወደቤታቸው መሰብሰብ የጀመሩ ነዋሪዎች አካባቢውን ከእንቅስቃሴ ገድበውታል።ጥቂቶች ብቻ ከወዲያ ወዲህ በሚሉበት ቦታ የአንድ ሰው ዓይኖች ያለ ዕረፍት ከወዲያ ወዲህ ይቃብዛሉ።
ገርጂ ልዪ ስሙ ‹‹አለምነህ ጋራዥ›› ከተባለ ስፍራ ብርድና ዝናቡን የፈሩ ነፍሶች ሙቀትና እረፍትን ሽተው በጊዜ መሰብሰባቸው ለበላይ የዘወትር ድርጊት አመቺ ሆኖለታል።እንደሁልግዜው ዓይኖቹን ከመንገዱ ተክሎ ወጪና ወራጁን እየጠበቀ ነው። እንዲህ አይነቱ ዝናብና ጨለማ ለእሱና ለባልንጀሮቹ ብርቅ ሆኖ አያውቅም። አሁን ለሚፈጽመው ድርጊት ግን ድንቅ ነውና ውስጡ በፈገግታ መሞላት ይዟል።
ከአንድ ጓደኛው ጋር ምሽቱን በአረቄ ቤት ሲያሳልፉ ከያዙት ፉት እያሉ ብዙ አቅደዋል፤ከሚኖሩበት ጫካ ወጣ ብለው ወደገርጂ ለመሄድ ሲወስኑም በጋራ ተስማምተው ነው።
በላይ አሁን ከምሽቱ ሶስት ሰዓት መሆኑን አረጋግጧል።ከአሁን በኋላ በአካባቢው የሚያልፍ መንገደኛ ደግሞ ከእነሱ ወጥመድ ሊወድቅ ግድ ይለዋል።ይህን እያሰበ በጎኑ የሻጠውን ተስፈንጣሪ ጩቤ በእጁ ዳሰሰ። እንዳኖረው ሆኖ በተገቢው ቦታ ተቀምጧል።የጊዜውን ምቹነት እያሰበ ፈጣን ዓይኖቹን ባሻገር ላካቸው። ባዷቸውን አልተመለሱም።ከአንዲት ወጣት ላይ አርፈው በተለየ መልኩ ትኩረቱን ሳቡት። ልማደኞቹ ዓይኖች ከወዲያ ወዲህ ቃበዙ። ፈጥኖ ለጓደኛው በእጁ ምልክት ሰጠውና ተጠቃቅሰው ወደ እሷ ቀረቡ ።
ወጣቷ ማንገቻው አጠር ያለ ቦርሳ በደረቷ ይዛ ወደፊት እየተራመደች ነው። አካባቢውን ስለምታውቀው ፍርሀት አይታይባትም።አካሄዷ የፈጠነ አልያም ያዘገመ አይደለም፤ተረጋግታ ወደአሰበችው መንገድ ማቅናቷን ይዛለች።በድንገት ግን ሁለቱ ጎረምሶች መሀል መሆኗን ስታውቅ በድንጋጤ ክው ብላ ወደ ኋላ አፈገፈገች።
ሁኔታዋን ያስተዋለው በላይ አይኑን በንዴት አፍጥጦ ሞባይሏን እንድትሰጣቸው አስገደዳት፤ ቁጣና ማመናጨቁን ያየቸው ወጣት ግን በድርጊቱ ተናዳ እምቢተኝነቷን አሳየቸው። እልህና ንዴት ይዟትም ፊትለፊቷ የቆመውን ሰው እንዳይቀርባት ታገለችው። ይህኔ በላይ ከእሷ በላይ ግሎ እጇን የኋሊት ጠመዘዛት።
በጎረምሳ ክንድ የተያዘችው ወጣት ስቃዩ ቢበዛባት ለመጮህ ሞከረች። አሁንም ግን የእጇን ሞባይል መስጠት አልፈቀደችም። በዚህ መልኩ ትፈትነኛለች ብሎ ያልገመተው በላይ እልህ ይዞት በቀኝ ጎኑ የሻጠውን ስለት መዥርጦ አወጣ። አፍታ ሳይቆይም ከጡቷ በታች ሆዷ ላይ ሻጠው። ስለቱን ነቅሎም ሞባይሏን ከጣቶቿ አላቆ ወደኪሱ ከተተ ።
የወጣቷ የጣር ድምጽ ከወደቀችበት ስፍራ ወደነሱ አቅጣጫ በጉልህ ይሰማል። ባልንጀሮቹ ግን በእጃቸው የገባውን ሲሳይ እያገላበጡ አስፓልቱን ከተሻገሩ ቆይተዋል።
የፖሊስ ምርመራ
ሲነጋ በስፍራው የተገኘው ፖሊስ ትናንት ምሽት በአካባቢው የተፈጸመውን ድርጊት ለማወቅ የስፍራው መረጃዎችን ሰበሰበ። በዕለቱ ተጎጂዋን አግኝተው ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ያደረሱ ሰዎችን አግኝቶም ስለሁኔታው ሙሉ ማስረጃዎችን ያዘ።በቦርሳዋ የተገኘ 575 ብር መኖሩን ያወቀው ፖሊስ ምናልባት ጉዳዩ ዘረፋ ላይሆን ይችላል በሚል ሁኔታዎችን በየአቅጣጫው አጣራ።
የ28 አመቷ ወጣት ለሊቱን በህክምና ስትረዳ ብትቆይም ንጋት ላይ ህይወቷ ማለፉን ያረጋገጠው ፖሊስ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለመያዝ አሰሳውን ቀጠለ። በመርማሪ ዋና ሳጂን ሲሳይ ተሾመ የሚመራው ቡድንም በመዝገብ ቁጥር 1246 /09 በተከፈተው ዶሴ የዕለት ሁኔታዎችን እየመዘገበ ምርመራውን አጣደፈ።
ከድርጊቱ በኋላ ሞባይሉን በእጃቸው ያስገቡት እነበላይ አዳራቸውን ማርያም ቤተክርስቲያን ጀርባ ካለው ጫካ ውስጥ አደረጉ። በማግስቱም ስልኩን በ750 ብር ሸጠውና የድርሻቸውን ተካፍለው ተለያዩ።
ሲሳይ የወጣቷን ሕይወት ማለፍ ከሰማ ቀን ጀምሮ ጸጸትና የተለየ ሀዘን ገብቶታል። እስከዛሬ በርከት ያሉ ወንጀሎችን ፈጽሟል፤ እንደአሁኑ የተቆጨበት ግን የለም።በተለይ ወጣቷን ሲወጋት በልብሱ ላይ የቀረው ደም ቀን ከሌት ዕንቅልፍ ነስቶ ቕዠት ውስጥ ከከተተው ቆይቷል።
ሁሌም ሲጋራ ሲያጤስ የሚንቀጠቀጠው እጁ የድርጊቱን ክፋት ያስታውሰዋል። ከራሱ ጋር የማይሸነፍ ትግል የያዘው በላይ በለቅሶና በሀዘን እየተጨነቀ ነው።በሌላ ድርጊት ተጠርጥሮ በገባበት እስርቤት ዘወትር በአካል እየመጣች የምታሳድደውን የሙት መ ንፈስ መቋቋም ተ ስኖታል።
ከቀናት በአንዱ ቀን ከአንድ ፖሊስ ጣቢያ ካለ ተጠርጣሪ የፈቃደኝነት ቃል የተቀበለው መርማሪ ጸጸት የገባውን ሰው ሀሳብ መዝግቦ ጨረሰ። በራሱ አንደበት ያለማንም አስገዳጅነት ድርጊቱን ስለማመኑ በማስረጃዎች አስደግፎ አረጋገጠ።ሲሳይ የፈጸመውን የግድያ ወንጀል አንድ በአንድ መናገሩ በማስረጃነት ተመዝግቦም ክስ ተመሰረተበት።ክሱን የመረመረው ዓቃቤ ህግም ያሉትን ሰነዶች ሁሉ ለፍርድቤት አቅርቦ ለውሳኔ አሳለፈ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 9/2012
መልካምስራ አፈወርቅ