ይህንን ቃል-ግጥም በመግቢያነት መጠቀም ካስፈለገበት ምክንያት አንዱ በጉዳዩ መደመም፤ ስነቃላችንን ማድነቅ ሲሆን፤ በተለይ ቃል ግጥሙ ምን ያህል ጥልቀት እንዳለው፣ የእውቀትን ፋይዳ እና “ፋይዳቢስ”ነት በጊዜ ኡደት ውስጥ በማሳየቱና ማወቅም ሆነ አለማወቅ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ምንም ልዩነት እንደሌላቸው የታዘበበት መንገድ ወዘተ ፈገግ በማሳኘቱ ነው። በእግረ መንገድም አንድን ነጠላ ጉዳይ መዝዞ መፃፍ የሚፈልግ እሳት የላሰ ፀሀፊ ካለም ለማቀበል ታስቦ ነው።
የዛሬን አያድርገውና ይህ እየተነጋገርንበት ያለው ርዕሰ ጉዳይ እስከ 1980ዎቹ ድረስ በኢትዮጵያ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ለሁሉም የካምፓስ ተማሪ የሚሰጥ አንድ የትምህርት አይነት (ኮመን ኮርስ) እንደነበረ እድሉን ያገኙ ሰው ነግረውኛል። የኮርሱ ማስተማሪያ መፅሀፍ /ቴክስት/ም “THEORY OF KNOWLEGE” እንደነበረ፤ ደራሲውም (ስሙን የጓደኛቸው ያህል ነው እየደጋገሙ የሚጠሩት) Maurice Cornforth መሆኑን ነግረውኛል። (ለተማሪዎች የተሟላ ሰብእና ጠቃሚ የሆኑ ኮርሶች ከየተቋማቱ ተጠራርገው ወጥተው ይሄው ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።) የኮርሱ (TOK)ን አላማ ከተቋማቱ ማውጫ (ኮርስ አውትላየን) ላይ ማግኘት ባይቻልም በቴክስትነት የሚያገለግለውን የሞውሪሴ ኮርንፎርዝ መፅሀፍ ፈልጎ ለማግኘት ተችሏል። በዚሁ መፅሀፍ፣ ከማውጫው አስቀድሞ በ”FOREWARD” ስር በሰፈረው ፅሁፍ የመጀመሪያው አንቀፅ “THE theory of knowledge is concerned with questions about ideas–their source, the way they reflect reality, the way they are tested and developed, their role in social life. These questions have always formed an important part of philosophy.” ሲል የሚገልፅ ሲሆን ይህም አጠቃላይ የኮርሱን አላማ፣ አስፈላጊነት፣ ግብና ፍልስፍናዊ መሰረቱን በሚገባ ያሳያል ተብሎ ይገመታል።
እንደሚታወቀው ፍልስፍና ስለ ቁስ አካል፣ ነገረ ሕልውና፣ ኅሊና፣ ነፍስ፣ ምንነት፣ ግብረገብ፣ የእውቀት ምንነት፣ አላማና ፋይዳ፣ ጥበብ፣ ንቃተ ህሊና እና ሌሎች በርካታ ፍሬ ጉዳዮችን እንደሚያካትት የፍልስፍና ሀሁ ያስረዳል። ይሁን እንጂ የኛ የእለቱ ትኩረት ከብዙዎቹ አንዱ የሆነውን ስነ-እውቀትን የተመለከተ ይሆናል። አመክንዮ፣ ስነምግባር፣ ሥነ-እውቀት (epistemology) እና ሌሎች በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ሀይማኖታዊ፣ ሥነ-ወሲብ ወዘተ ጉዳዮች ፍልስፍና ተገቢውን ቦታ ሰጥቶ የሚወያይባቸው አበይት ፅንሰ ሀሳቦች ናቸው።
ኤፒስቶሞሎጂ (የሥነ እውቀት ንድፈ ሀሳብ ጥናት – “[…] is the study of the nature and scope of knowledge and justified belief. It analyzes the nature of knowledge and how it relates to similar notions such as truth, belief and justification. It also deals with the means of production of knowledge, as well as skepticism about different knowledge claims.» ይለዋል መዝገበ ቃላቱ። ለሰፊ ትርጉሙ ሌሎችን፤ ለምሳሌ “philosophybasics.com”ን መጎኘት ይቻላል።) በተለይ የእውቀትን ተፈጥሯዊ አመጣጥ፣ ሂደት፣ እንዲሁም የእውቀትን አጠቃቀም ለይተን በማወቅ በኩል ያለው እገዛ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑን፤ ለማወቅ የማንፈልገውን ወይም የምንፈልገውን እውቀት እንዴት ማወቅ አለብን/የለብንም በሚለው ላይ በማተኮር ሰፊ ግንዛቤን የሚያስጨብጥ ዘርፍ ነው።
በፍልስፍና ጥናት መሰረት እውቀት ለሰው ልጅ ያለው ፋይዳ አንድ ሰው ስለ አጠቃላይ የህይወት ልምድ (life experience) ደጋግሞ እንዲያስብ በማድረግ ወደ ተሻለ ህይወት እንዲያመራ ማድረግ ሲሆን ይህም በሂደት የተመሰከረለት የእውቀት ማግኛ መንገድ ወደሆነው ወደ ምክንያታዊነት የመሄጃውን መንገድ ይጠርጋል። እውቀት በበኩሉ ሀቆችን (facts) እንድናገኝ ያደርገናል፤ እነዚህ ሀቆች ደግሞ መቸም ውሸት ሊሆኑ የማይችሉና ፍፁም እውነቶች ናቸው፤ ቢያንስ በሌላ በተረጋገጠ እውነት እስኪሻሩ ድረስ። ይህ ሲሆን ነው እውቀት፤ የሰው ልጅ አወቀ ማለት ይሄን ጊዜ ነው የሚል የብዙዎች ስምምነት ያረፈበት ሀሳብ አለ።
እውቀት ምንጩ ወይም መገኛው ልምድ (ኤክስፒሪያንስ) ነው የሚሉት ወደ ስነልቦናው የቀረበ አስተያየት የሚሰጡ ሲሆን መረጃቸውንም “ልምድ አንድን ነገር በማየት፣ ስለ አንድ ነገር በመስማት እና ስለአንድ ነገር ከሚሰማን ስሜት የሚመጣ” መሆኑን በማስረገጥ ያቀርባሉ።
እውቀት ማለት መለማመድ፣ አንድን ጉዳይ/ነገር ማለትም መረጃ (Data)ን፣ ለይቶ መገንዘብ፣ ክሂሎትና የመሳሰሉትን አመላካች ሲሆን የእነዚህ ሁሉ መገኛ ደግሞ ልምድ እና መደበኛ ትምህርት ነው የሚሉ አሉ፤ ሁለቱንም አጣምረው። ይህ እውቀትም የሚረጋገረጠው የአንድን ጉዳይ (“ቁስ”ም ሊሆን ይችላል) ምንነት በንድፈ ሀሳብ ወይም በተግባር (“ቲዮሪ” ወይም “ፕራክቲስ”) በመረዳት ነው። “Hume’s theory of knowledge” የሚባለው ንድፈ ሀሳብ በበኩሉ ለልምድ ተመሳሳይ እይታ ያለው ሲሆን አስተሳሰብም ሆነ እውቀት ከዚሁ ከልምድ እንደሚመጡ ያምናል።
የምዕራቡ አለም ፍልስፍና የሚባለው ደግሞ ከዚህ የተለየ ሲሆን ሁለቱ የሥነ-እውቀት ክፍሎች በሆኑት ላይ ብያኔን በመስጠት የራሱን ፍልስፍናዊ አቋም ይይዛል። የ”Modern theory of knowledge” አባት መሆኑ የሚነገርለት ካንት እውቀትን በእነዚህ ሁለቱ ከፍሎ ያየ ሲሆን የመጀመሪያው (Priori knowledge) እራሱን የቻለ፣ በምክንያት ብቻ የሚመራና የማንም ጥገኛ ያልሆነ ሲሆን ከልምድ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም ባይ ነው። በተቃራኒው ከልምድ የሚመጣ/የሚገኝ እውቅት አለ ይላል፤ እሱም በሁለተኛነት (Posteriori knowledge) የምናገኘው ነው ሲልም ይገልፃል።
እንግሊዛዊው ፈላስፋ በርትራንድ ራስል በ”Theory of Knowledge” (1926) ጥናቱ ላይ የእውቀት ንድፈ ሀሳብ መነሻው መጠራጠር/ተጠራጣሪነት ነው ባይ ነው። በመሆኑም የእውቀት መገኛው መጠራጠር ሲሆን ንድፈ ሀሳቡም ይህንኑ መሰረት ያደረገ ነው። እንደ ራስል አባባል አንድ ነገር ስንፈልግ ወይም ግር ሲለን ራሳችንን አጥብቀን እንጠይቃለን፤ በዚህ እራስን በመጠየቅ ሂደት ውስጥ እውቀትን ወደ መፈለግና መፈተሽ ደረጃ እንሸጋገራለን። ይህ ደግሞ በተፈጥሮው ወደ እውቀትን አምርረን ወደ መፈተሽና መሻት እንድናመራ ያደርገናል። ይህ ነው ለእውቀት፣ ለእውቀት ንድፍ ሀሳብም ሆነ ሌሎች ከእውቀት ጋር ተያያዥ ለሆኑ ጉዳዮች መሰረታዊ ነገር።
ከሁሉም ወጣ የሚለው የማርክሲስቶች እይታ ነው። በቁስ አካላዊያን አስተሳሰብ የእውቀት ምንጩ ተግባር (Labour) ነው። እንደ ማርክያዝም ፍልስፍና አተያይ ደግሞ እውቀት በማምረት እና በመደብ ትግል ሂደት ሚና መጫወት አለበት። ለዚህ አባባልም በዋቢነት የሚያቀርቡት “የሰው ልጅ እውቀት የእውኑ አለም ነፀብራቅ ነው።” የሚለውን አስተሳሰብ ነው። ይህም እውቀት የሚገኘው ከቁሳዊ እውነታ አስቀድሞ በግለሰብ አእምሮ ውስጥ ሲሆን፤ ሀሳብ ደግሞ ከእውኑ አለም ቀዳሚ ነው” ከሚሉት ሀሳባዊያን (Maurice Cornforth የቡርዥዋ ፍልስፍና/Bourgeois Philosophy ይለዋል) ጋር በተቃራኒ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል።
እውቀት የህይወት ልምድ (experience) ውጤት ነው የሚለውን በሚደግፍ መልኩ የሀያኛው ክፍለ ዘመን እውቅ አሜሪካዊ ባለቅኔ ሎሬትና በኮንግረስ ላይብራሪ የስነግጥም አማካሪ ሮበርት ፍሮስት ስለ እውቀት ተጠይቆ በሶስት ቃላት እንዲመልስ ጠይቆ በተፈቀደለት መሰረት “[I]t goes on.” ሲል መልሷል። ህይወት ይቀጥላል መማርም፤ ማወቁም እንደዛው እንደማለት።
ወደ እኛ አገር ስንመጣ በዚህ ዘርፍ “የተዋጣለት” የተባለለትን ስራ የምናገኘው ከእጓለ ገብረ ዮሀንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ።” ስራ ነው። ይህ መጽሀፍ በአይነቱም ሆነ በይዘቱ ከእስከ ዛሬዎቹ የአገራችን፤ በተለይም በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ለንባብ ከበቁት መፃህፍት በእጅጉ የተለየና ሙሉ ለሙሉ ምሁራዊ/ፍልስፍናዊ ስራና በተራ አንባቢ ብዙ የማይደፈር ነው።
የመፅሀፉ ትኩረት ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ስለ ትምህርት ምንነት፣ አላማ፣ ግብና አጠቃላይ አወቃቀሩ ምን መምሰል እንዳለበት ከግሪክ፣ አቴናዊያን፣ ሮማና ሌሎችን አዳርሶ፤ ስመጥር ፈላስፋዎችን አወያይቶና ወጣ ገባውን አደላድሎ ለአገራችን ልክ በሚሆን መልኩ መፍትሄን ይዞ ለንባብ የበቃ የፍልስፍና መጽሀፍ ነው።
ይህ የመጀመሪያ ሀቲቱን “የትምህርት ፍልስፍና” በሚል ርዕስ የሚጀምረው መጽሀፍ ካነሳቸውና ምላሽ ከሰጠባቸው ፅንሰ ሀሳቦች መካከል አንዱ “እውቀት”፣ “ጥበብ” እና ተዛማጆቹ ሲሆኑ ለእያንዳንዳቸው በበቂ ማስረጃ የተደገፉ ማብራሪያዎችን በመስጠት ሀሳቡን የሚያጠቃልል አስተማሪ ስራ ነው።
መፅሀፉ በገፅ 18 ላይ ሶስቱን፤ እርስ በእርስ የሚቃረኑ፤ ግን ደግሞ አንዱ ያለ አንዱ የተሟላ ስለማይሆኑት የህሊና ተግባራት – አንብሮ፤ ተቃርኖ፤ አስተፃምሮ (thesis; anthithesis; synthesis)ን ዘርዝሮ የሚያብራራ ሲሆን “ይህ የሀሳብ ዘዴ በብዙ የእውቀት ክፍሎች ዘንድ ፍቱን ሆኖ የተገኘ ነው። ሄገል በተለይ የተጠቀመበት መጀመሪያ የመንፈስ ህይወት በህገ ተቃርኖ በዲያሌክቲክ የሚመራ መሆኑን ከተረዳ በኋላ የእስካሁኑ የሰው ቅርስ ማለት ታሪክ ወይም ስልጣኔ እንዴት አደገ? ምን ገፍቷቸው እዚህ ደረሱ? ከአንዱ የእድገት ደረጃ ወደ ሚቀጥለው የደረሱበት የሚደርሱበት ውስጣዊ ህግ አላቸውን? ወይስ አጋጣሚና ድንገተኛ መነሻውና መድረሻው የማይታወቅ የሀሳብ ማእከል ካሉበት አደረሳቸው? ለወደፊቱስ ጉዞው ወዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ በሚመልስበት ጊዜ ነው። ጥያቄው በጣም አስፈላጊ ነው[።] ማንም የመንፈስ ሰው ወደጎን ትቶት ሊያልፍ አይገባውም።” (ገፅ19)
ማንኛውም የህሊና ተግባር በህገ ምክንያት (Causalitas) የተመሰረተ መሆን አለበት። የሚሉት እጓለ “የኢትዮያም ህዝብ ከታሪካዊ ድሉ ለመድረስ ከዛሬው የሚበልጠውን የነገውን ትልቅነት በእጁ ለማድረግ በተምኔት እየተመራ ወደፊት ይጓዛል። ከዚህ አላማው ከሚያደርሱት መሳሪያዎች አንደኛው ትምህርት ነው። ሁለተኛው ትምህርት ነው። ሶስተኛውም ትምህርት ነው።” ሲሉም የሁሉም ነገር ማጠንጠኛው ትምህርት መሆኑንና “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”ያችን ምን መሆን፤ በምን ላይ መመስረትና አላማው ምን መሆን እንዳለበት ያጠይቃሉ።
“ሰናይና እውቀት” የመላው አለም “የትምህርት አላማ ወሳኝ አሀዞች ናቸው። አንደኛው የህሊና ሁለተኛው የልቡና ጠባዮች ናቸው። ሰው ከሌሎች ህላዌያት ተለይቶ የሚታወቅበት በነዚህ ሁለቱ ነው። “[. . .] ሰውን ከሌላው ፍጥረት ከፍ ያደረገውና ከመለኮት ባህርይ ተካፋይነት ያደረሰው እውቀቱ አእምሮው ህሊናው ነው።”
እጓለ ኢማኑኤል ካንትን ጠቅሰው እንደሚሉት በጎ ምግባር ማለት ሰናይነት ከእውቀት፣ ከአእምሮ ይበልጣል። ይሁንና እዚህ ላይ ለማየት የተፈለገው መበላለጣቸው ሳይሆን ሁለቱ በአንድ ሲሆኑና ሲተባበሩ ተፈላጊ የመሆናቸው ጉዳይ ነው። “እነዚህ ሁለቱ በተባበሩ ጊዜ ሰውን ወደ ከፍተኛ ወደ ከፍተኛ ማዕረግ ያደርሱታል።” እጓለ እነዚህ ሁለቱ የሰውን ልጅ ወደ ላይ ወደ አርያም የሚያወጣውን ትምህርት በመሰላል ተምሳሌትነት የገለፁ ሲሆን የመሰላሉን ቀኙን ክፍል ሰናይት (virtue) ግራውን ደግሞ አእምሮ (knowledge) በማለትና “የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ዋና መግቢያ በር ግራና ቀኝ ያሉትን ሁለት አምዶች አንዱን ሰናይት ሁለተኛውን እውቀት ብለን እንጠራቸዋለን።” (ገፅ 27) በማለት ብዙዎቻችን የምናየውን፤ ግን ደግሞ ያልታየንን ረቂቅ ይገልፁልናል።
አልበርት አንስታየን (በ1949) በወቅቱ በ”Theory of knowledge” ላይ በፈላስፎቹ መካከል የነበረውን ውዝግብ መነሻ በማድረግ እሱም የራሱን አስተያየት እንዲሰጥ ተጠይቆ ሰፋ አድርጎ መመለሱ የሚታወቅ ሲሆን “ከሁሉም ግን ሁለት ነገሮች ህልቆ መሳፍርት ናቸው፤ ፍጥረተ ዓለም የሰው ልጅ ድድብና፤ ስለ ፍጥረተ ዓለም ግን እርግጠኛ አይደለሁም። (Two things are infinite: the universe and human stupidity; and I’m not sure about the universe.)” ያላት ሽሙጥ እውቀት ባጠጠባቸው አካባቢዎች ሁሉ ቋሚ ተጠቃሽ ናት።
ወደ ማጠቃለያችን እንምጣ። ከላይ በቁንጣሪ ደረጃ ያየናቸው በሥነ-እውቀት ላይ የተሰነዘሩ የተለያዩ አስተያየቶች ሲጠቃለሉ በሁለት ጎራ ላይ የሚያርፉ ናቸው። እውቀት መነሻው፣ አላማውም ሆነ ግቡ ማህበረሰብ እንጂ ግለሰብ አይደለም፤ መነሻ መገኛውም ማህበራዊ እንቅስቃሴ፣ ተጨባጩ አለም፣ የግለሰብ ሳይሆን የማህበረሰብ ንቃተ ህሊና መዳበር እድገት ውጤት ነው፤ የምርት እያደገ መሄድ ለእውቀት ማደግ ከፍተኛ ድርሻ አለው፣ እውቀት ተጨባጭ እንጂ ረቂቅና ከእውኑ አለም ያፈነገጠ አይደለም ወዘተ በሚሉት ቁስ አካላዊያን (materialist) ጎራ፤ እና ከዚህ በተቃራኒ በቆሙት ሃሳባዊያን (idealist) መካከል ነው ፔንዱለሙ የሚላጋው። ይህን ስንል የየራሳቸው አተያይ፣ መሟገቻ ሀሳብ፣ ንድፈ ሀሳባዊ ቀመር ያላቸው ግለሰብ ፈላስፎች የሉም ማለታችን አይደለም። ያ ዝርዝሩ ብዙ በመሆኑ ለአንባቢ የተተወ ድርሻ ነው።
በአገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚያሳየውና አገሪቱን የሚመሩት በተደጋጋሚ እንደሚሉትም፤ በየተቋማት ያሉ ደንብና መመሪያዎች በእቅፋቸው የያዙት “ወርቃማ ሀሳብ” ቢኖር በሁሉም ዘርፍ በሚባል ደረጃ “የእውቀት፣ ክሂሎት፣ አመለካከት … ክፍተት” በስፋት መኖሩን ነው። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረው “ወርቃማ ሀሳብ” ልቆ፤ ከትምህርት ጥራት መውረድ፣ ከምሩቃን/መምህራን አቅም ማነስ/ከስርዓተ ትምህርቱ አቅጣጫ መሳት … ጋር ተያይዞ የሁሉም ዜጋ ቋንቋ በመሆን ላይ ይገኛል። በመሆኑም እዚህ እኛ አገር ስለእውቀት፣ የእውቀት ንድፈ ሀሳብና ፍልስፍናዊ መሰረቱ ማውራት ቅንጦት ሊመስል ቢችል አይገርምም። ይሁን እንጂ እጓለ ገብረ ዮሀንስ ከላይ በጠቀስንላቸው የተዋጣለት መፅሀፋቸው አጥብቀው እንደሚመክሩት አለም፤ በተለይም ምዕራባዊያን እዚህ የደረሱት በትምህርት፣ ጥበብ፣ እውቀትና መንፈሳዊ ሀብት ነውና የጉዳዩ መነሳት ተገቢነት ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል።
በተለይ የእኛ አገር የትምህርት ዘይቤ ዋና ትኩረቱ ንድፈ ሀሳብ /ቲዮሪ/ ላይ እንጂ ተግባራዊ ልምምድ ላይ አይደለም። በከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር “በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ሶስተኛ ዲግሪ ያላቸው ሰዎች ባሉበት የኮረንቲ ገመድ የሚቀጥል ባለሙያ ከውጪ በውድ ዋጋ እያስመጣን ነው” ሲባል የሚሰማበት ዘመን ላይ ከመሆናችን አኳያ እጓለ እንዳሉት አሁኑኑ ሊታሰብበት የሚገባ ይመስለናል። ካልሆነ ወደ እዚህ ፅሁፍ የገባንበት ቃል ግጥም ላይ እንደተመለከተው የ”ማወቅ” እና “አለማወቅ” ድንበር እንደተደበላለቁ መኖራቸው አይቀሬ ይሆናል። ቸር እንሰንብት።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 8/2012
ግርማ መንግሥቴ