ወቅቱ ጥር ነው። ድሮ ድሮ ከገጠር እስከ ከተማ የሚገኙ ተማሪዎች በሁለት ምርጫዎች የሚወጠሩበት ጊዜ ነበር። አንድም በፈተና ጥናት፤ ሁለትም በሰርግ ጭፈራ። አሁን ላይ ግን መልኩ ተቀይሯል። የፈተና ወቅት ስለመሆኑም አስታዋሽ ያለው አይመስልም። የተማሪዎች የጥናት ወከባም በኩረጃና በሱስ ከተተካ ብዙ ዓመታት መቆጠራቸውን አስተማሪዎች በትካዜ ሲያነሱ ይደመጣል። አልፎ አልፎም ምግባረ ሰናዮች ለመካሪ አለመጥፋታቸው ተመስገን ያሰኛል።
‹‹አስተማሪዎች ሲያስተምሩ አጫጭር ማስታወሻ እጽፋለሁ። እነዚያን በአጋዥ መጽሐፍት እያዳበርኩ አስፋፍቼ አነባለሁ። ከሌሌቱ ስምንት ሰዓት እስከ 11፡30 ድረስ ባለው ጊዜ ማንበብ ያስደስተኛል›› በማለት ተሞክሮዋን ያካፈለችው የጥቁር አንበሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ ሶስና ጌቱ ናት። አምና 2ኛ ደረጃ ይዛ ማለፏንም ገልጻለች።
የሥነልቦና ባለሙያ ለመሆን ተስፋን ሰንቃ በትጋት እየተማረች እንደሆነ የተናገረችው ተማሪዋ፤ በዚህ የተነሳም በትምህርት ቤቱ የ«ማማከር ክበብ» መመስረት ችላለች። ለተለያዩ ሱሶች የተጋለጡ ከ30 በላይ ተማሪዎችን በምስጢር በማማከር የቀጣይ ሕይወታቸውን ማስተካከል እንዲችሉ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይም ትገኛለች።
ለኩረጃ የሚዳርጉ ችግሮች ምን ይሆኑ?
ተማሪ ሶስና ከተግባር ተሞክሮዋ እንደተናገረችው፤ የኩረጃ መንስኤዎች የአንድ አካል ብቻ ተደርገው የሚታዩ ችግሮች አይደሉም። ተማሪዎች ሰፊውን የችግር ድርሻ ይይዛሉ። ነገ ችግሩ ለራሴ ተመልሶ የሚተርፍ ይሆናል ብለው የሚያስቡ ተማሪዎች ብዙም የሉም። ወላጆችም፣ አስተማሪዎችም የጉዳዩ ተጋሪዎች ናቸው።
ምክንያቱም ወላጆች በየቀኑ ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሲማሩ የዋሉትን አይጠይቁም፤ አይከታተሉም። የት እንደዋሉ እንኳን መረጃ የመለዋወጥ ልምድ የላቸውም።
በአስተማሪዎች በኩል ደግሞ የተሻሉና ጎበዝ የሆኑትን ተማሪዎች ብቻ አስተምሮ የመውጣት ሁኔታዎች ይስተዋላሉ። ቀስ ብለው እና ዘግይተው የሚረዱ ተማሪዎችን የሚያካትቱ የማስተማር ሥነዘዴዎች እየተጠቀሙ አይደለም። በዚህ የተነሳ ትምህርቱን በደንብ ማስረጹ ቀርቶ የገባቸውን ተማሪዎች ብቻ ይዘው መሄድ ይስተዋልባቸዋል። በዚህ የተነሳም ተማሪዎች በራስ መተማመናቸውን እያጡ ይመጣሉ። በውስጣቸው የጥገኝነት አስተሳሰብን በማጎልበት ለኩረጃ እንደሚዳረጉም ተማሪ ሶስና አስረድታለች።
የሒሳብ አስተማሪው ብርሃኑ ወርቁ እንደገለጹት፤ ተማሪዎች ብዙ ጊዜ ሰጥተው አያጠኑም። የትምህርቱ ባህሪ ደግሞ በተደጋጋሚ ሳይሰለቹ መስራትን የሚጠይቅ ነው። የሚከብዳቸውንም ለይተው አስተማሪዎቻቸውን አይጠይቁም። በዚህ የተነሳም የተማሪዎች ፍላጎትና ውጤት ከዕለት ዕለት እየቀነሰ ነው። በተለይም በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች። ቤተሰብም ልጆቹን መረን ለቋል። ተገቢውን ክትትል አያደርግም።
ከዚህ የከፋው ችግር ደግሞ ልጆቹ ከታች ጀምረው በትምህርቱ እንዲገሩ አለመደረጉ እንደሆነ የሚናገሩት መምህር ብርሃኑ፤ በመሆኑም መሠረት እንዲይዙ መምህራን ሳይሰለቹ ማገዝና ለትምህርቱ ፍቅር እንዲያድርባቸው ማድረግ ነበረባቸው ይላሉ። ነገር ግን ይህ በአግባቡ እንዳልተሰራ ነው የሚናገሩት። አሁን የሚታየው ተማሪዎች ኩረጃ ነውር መሆኑን ከነጭራሹ እየረሱ እንደመጡ ነው። የሚሰሩት ተማሪዎችም ጭምር መስራት የሚችሉትን ለመስራት የሚያስችላቸው ወኔ አጥተዋል። ከአጠገባቸው የተቀመጠውን አምነው ይኮርጃሉ። በሽታው በሁሉም ዘንድ መዛመቱን መምህር ብርሃኑ ተናግረዋል።
ምን ሊደረግ ይገባል?
ተማሪ ሶስና እንደምትለው በሌሎች አገራት ተማሪዎች የፈለጉትን መርጠው መማር ይችላሉ። በዚህ የተነሳ ውጤታማነታቸው የሚያድጉባቸው ዕድሎች ሰፊ ናቸው። የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት በዚያ ደረጃ ዕድል የሚሰጥ አይደለም። ቢሆንም ተማሪዎች በመጀመሪያ ፍላጎታቸውን ለይተው ማወቅ ይኖርባቸዋል። በትምህርት ሂደታቸው ውስጥ መሆን የሚፈልጉትን እያሰቡ ብቃታቸውን በሙሉ እምነት እያወጡ ማሳየት አለባቸው። የውስጥ ፍላጎቶቻቸውን በተግባር አውለው ማጎልበትና ማሳደግ እንዳለባቸው ትመክራለች።
ሕፃናት ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው አገር እንዲረከቡ ካስፈለገ በተገቢው ማደግ ይኖርባቸዋል። ወላጆች ከሚሰሩት ድርጊት እስከ ቴሌቪዥንና ማስ ሚዲያ መልዕክቶች ድረስ አዎንታዊ ሚና ያላቸው መልዕክቶች እየተቀረጹ ስለመተላለፋቸው አዋቂዎች ማጤን አለባቸው።
ምክንያቱም «ጎረቤቴ የምትኖር አንዲት ሕፃን ሁልጊዜ ከ18 ዓመት በታች የተከለከለ የሚል ማስታወቂያ በቴሌቪዥን ትመለከታለች። ከዚያም እማዬ እማዬ መቼ ነው 18 ዓመት የሚሞላኝ? እኔም ግጥም አድርጌ እንድጠጣ ብላ ጠየቀቻት። ትውልዱ ከ18 ዓመት በላይ ሲሆነው ሁሉም የሚጠጣ ተደርጎ ተሰርቷል» በማለት ገጠመኟን አካፍላለች።
በተጨማሪም የትምህርት ቤቶች በር አካባቢዎች የተለያዩ ሱስ አስያዥ ቁሶች ገበያቸው የደራ ነው። መንግሥት ወጣቱን ትውልድ ለማዳን ሰፊ ሥራ መስራት አለበት። ወላጆችም ተማሪ ልጆቻቸውን ውጤት መቀነስና የባህሪ ሁኔታ መከታተል አለባቸው። ችግር መኖሩን ባወቁ ጊዜ ደግሞ ከማግለልና ከማባረር ይልቅ አስተምሮና መክሮ ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመለሱ ማድረጉ መለመድ ይኖርበታል። ባህል መደረግም አለበት።
ተማሪዎች በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ከዚህ በፊት ከሚተገብሯቸው ነገሮች ለየት ባለመንገድ ጊዜያቸውን በአግባቡ መምራት አለባቸው። ከፊልምና ከጨዋታ ራሳቸውን ማራቅ ይኖርባቸዋል። ይሄን ማድረግ ሲችሉ ከኩረጃ ሥነልቦና መላቀቅ እንደሚችሉ ተማሪ ሶስና ትመክራለች።
የተማሪዎች የመኮራረጅ ልማዶች በሰፊው እያደጉ መጥተዋል። ነገር ግን ለመቅረፍና ለማስቀረትም በዚያው ልክ የሚሰሩ ሰፊ ሥራዎች አሉ። ተማሪዎችን በሥነልቦና ባለሙያ ጭምር እንዲመከሩ እየተደረገ ነው። ኩረጃ በባህሪው በራስ የመተማመንን ሥነልቦና የሚያሳጣ በመሆኑ በተለያዩ መንገዶች ጥገኛ እስከመሆን የሚያደርስ ነው ያሉት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህሩ ደረጀ ጋሻው ናቸው።
ምክትል ርዕሰ መምህሩ በበኩላቸው፤ ችግሩን ለማስቀረት የተለያዩ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ያስረዳሉ። የተማሪ ክፍል ጥምርታው አንድ ለአርባ ሲሆን በፈተና ወቅት ግን አንድ ለሃያ (አንድ ክፍል ውስጥ ሃያ ተማሪዎች እንደማለት ነው) እንደሚሆን ተናግረዋል። ጥር 13 እንደሚጀመርም ጠቁመዋል።
ትምህርት ቤቶች የጤናማ ትውልድ መፍለቂያ እንዲሆኑ በቅንጅት መስራትን ይጠይቃል። በመሆኑም ኩረጃና መጥፎ ባህሪ (ሲጋራና ጋንጃ ማጨስ፣ መቃም፣መጠጣት) እንዲሁም ሌሎች ወጣ ያሉ ድርጊቶች ሲፈጽሙ በሚገኙ ተማሪዎች ላይ ከወላጆች ጋር በመተባበር ከትምህርት ቤቱ እስከማባረር የሚደርሱ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ምክትል ርዕሰ መምህሩ ገልጸዋል።
ከደንብ ልብስ አለባበስ፣ጸጉር ቁርጥ፣ሰዓት አከባበር በመነሳት የተማሪውን ሥነምግባር ማስተካከልና ማረም እንደሚሰራ የሚናገሩት አቶ ደረጀ፤ የሥነምግባር ዝንፈቱ በተማሪዎች ብቻ የሚወሰን ሳይሆን እስከ አስተማሪዎችም የሚታይ ነው ይላሉ። ክፍለ ጊዜያቸውን በተገቢው ሁኔታ የማይጠቀሙ መምህራን ለተማሪዎች የሥነምግባር ችግሮች ሰፊውን ቦታ የሚይዙ በመሆናቸው ለይቶ ማረም እንደተቻለ አብራርተዋል። የሌሎች ተቋማት ሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማጥቅሞችን አሻግሮ በማየት የመቆዘምና ሥራን በሞራል መከወን አለመቻል መስተዋላቸውንም አልደበቁም።
በአጠቃላይ ስብዕናው የተስተካከለ፣ኩረጃን የሚጸየፍ፣በማህበረሰቡ ተወዳጅ ወጣት እንዲፈጠር መንገድ ማሳየት ተገቢ ነው። ወጣት ተማሪዎች ከአላስፈላጊ ሱሶች ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል። አላማቸውን ለማሳካት መንገዳቸውን ማሳመርም ሆነ ማስተካከል የሚችሉበት መቀየሻ መሣሪያ በእጃቸው መሆኑን ተገንዝበው ተግባራቸውን ማሳመር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይሆንም።
ሙሐመድ ሁሴን
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 8/2012