የአበረታች ቅመም ተጠቃሚነት በአሁኑ ወቅት የስፖርቱ ዓለም በተለይም የአትሌቲክስ ስፖርት ስጋት መሆኑ ይታወቃል። ሩሲያዊያን አትሌቶች ደግሞ በዚህ ችግር ቅድሚያ ተጠቃሽ እንደመሆናቸው በተለያዩ ጊዜያት እርምጃዎች ሲወሰዱባቸው ቆይቷል። ሃገሪቷም እኤአ ከ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ ከየትኛውም የአትሌቲክስ ውድድር ተሳታፊነት ውጪ እንድትሆን መደረጓም የሚታወስ ነው። ዓለም አቀፉ የጸረ አበረታች መድሃኒቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲም በሃገሪቷ ላይ የሚያደርገውን ምርመራ አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል። ይሁን እንጂ ሩሲያ ካለፈ ጥፋቷ የምትማር አልሆነችም፤ በዚሁ ምክንያትም በቅርቡ ተጨማሪ እገዳ ሊጣልባት እንደሚችል እየተጠበቀ ነው።
ዓለም አቀፉ ተቋም ለሚያደርገው ምርመራ በሞስኮ የሚገኘውን ቤተ-ሙከራ መረጃ እንዲሰጡት ቢጠይቅም የሃገሪቷ ባለስልጣናት ግን ዝምታን መርጠዋል። እስከተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት 2018 የመጨረሻዋ እለት ድረስ የጊዜ ገደብ ቢሰጥም የተለወጠ ነገር የለም። ይህ ጉዳይም በአትሌቶች ዘንድም ጭምር ቅሬታን የፈጠረና ሃገሪቷ መቀጣት አለባት የሚል ሃሳብ ያስነሳ ሆኗል። የኤጀንሲው አመራሮች በአንጻሩ ጥቂት ጊዜ መስጠት የፈለጉ የሚመስል እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ።
አምስት አባላት ያሉት የዋዳ አጣሪ ቡድኖች ባለፈው የፈረንጆቹ ወር አጋማሽ ወደ ሩሲያ ያቀኑ ሲሆን፤ ቤተ-ሙከራው በምን መልኩ ይተዳደራል፤ መረጃዎች በምን መልኩ ይቀመጣሉ የሚለውን መመርመር ነበረባቸው። ይሁን እንጂ በባለስልጣናቱ እምቢተኝነት እስከ ወሩ መጨረሻ ሲቆዩ መስራት ያለባቸውን መስራት አልቻሉም። ከዚያ ቀደም ብሎም ይህንን ስራ ለማከናወን የተቋሙ ባለሙያዎች እንደሚላኩና መረጃዎችን መስጠት እንዳለባቸው ተነግሯቸው እንደነበረም አጣሪዎቹ በሪፖርታቸው ላይ አመላክተዋል።
የዓለም አቀፉ ጸረ-አበረታች መድሃኒቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ፕሬዚዳንት ሰር ክሬግ ሬዲ፤ ነገሩ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ጠቁመው በተያዘው ወር አጋማሽ አጣሪ ኮሚቴው ከተሰበሰበ በኃላ የስራ አስፈጻሚው ምን ዓይነት ቅጣት ሊወሰድ ይገባል የሚለው ላይ እንደሚወያይ ማሳወቃቸውን ዘ ጋርዲያን በድረገጹ አስነብቧል። ይሁን እንጂ በኤጀንሲው የአትሌቶች ኮሚቴ ሩሲያ በድጋሚ መታገድ እንደሚገባት በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። በጻፉት ደብዳቤ ላይም፤ «ሩሲያ ቀነ ገደቡን በመተላለፏ በእጅጉ ቅር ተሰኝተናል። ከዚህ በኃላም ህጉን በተከተለ መንገድ ሩሲያ ትቀጣለች ብለን እንጠብቃለን። ነገር ግን በሃገሪቷ ላይ እርምጃ የማይወሰድባት ከሆነ ለተቋሙ ውድቀት ሲሆን፤ ንጹህ አትሌቶችን ከመፍጠር ረገድ እየሰራ አለመሆኑንም እንገነዘባለን» ሲሉም ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ተቋም ከአትሌቶች ብቻም ሳይሆን ከሃገራት የጸረ አበረታች መድሃኒት መቆጣጠሪያ ተቋማትም ጭምር ግፊት እንደበዛበትም በዘገባው ተመልክቷል። በተለይ አሜሪካን እና ጀርመንን የመሳሰሉ ሃገራት ደግሞ በአፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ ይገባልም ብለዋል። የአሜሪካው የጸረ አበረታች መድሃኒት መቆጣጠሪያ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ትራቪስ ታይገርት «ሙሉ ለሙሉ ቀልድ ነው፤ አሳፋሪም ነው» ሲሉ ነው የገለጹት። ዓለም አቀፉን ተቋምም «ከሩሲያዊያን ጋር መጫወቱን አቁማችሁ ወደ እገዳ ግቡ» ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አሜሪካዊው ጨምረውም «አትሌቶቿ አበረታች መድሃኒት እንዲጠቀሙ የምታበረታታ ሃገር፤ መረጃዎቹን አለመስጠቷ የሚያስደንቅ አይደለም። አትሌቶች ከአበረታች መድሃኒት የጸዳ ውድድር እንዲያካሂዱ መስራት ይገባል፤ አትሌቶች ታማኝ መሆን አለባቸው፣ በኦሊምፒክ መድረክ ህግ እንዲጣስም መፍቀድ የለብንም» ሲሉም ሃገሪቷ ቅጣት እንደሚገባት አስረግጠዋል። እንግሊዝም በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት እንደሚገባ ነው የጠቆመችው።
የሩሲያ ስፖርት ሚኒስትር ፓቬል ኮሎብኮቭ በበኩላቸው ቴክኒካዊ ችግሮች እንዳጋጠማቸው ገልጸው የዋዳ ባለሙያዎች በሌላ ጉብኝት በቤተሙከራው ተገኝተው ማጣራት እንደሚችሉ ነው የገለጹት። የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባች የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት መግባት ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ፤ ሩሲያዊያን እኤአ በ2020ኦሊምፒክ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ከፈለጉ መረጃውን መስጠት እንደሚገባቸው ጠቅሰው እንደነበረ የዘገበው ደግሞ ዘ ቴሌግራፍ ነው።
ሩሲያ እንደ ሃገር የአበረታች መድሃኒት ተጠቃሚ አትሌቶችን የምትደግፍ ሃገር መሆኗን ተከትሎ ከዚህ ቀደም ቅጣት እንደተጣለባት ይታወሳል። እኤአ በ2014 99 ከመቶ የሚሆኑት ሩሲያዊያን አትሌቶች አበረታች መድሃኒት ተገኝቶባቸዋል። ይህንን ተከትሎም እኤአ በ2015 ጉዳዩን ሪቻርድ ማክላረን የተባሉ የህግ ምሁር ለዓለም ይፋ አደረጉት። በ30የስፖርት ዓይነቶች የሚሳተፉ 1ሺ አትሌቶቿም የአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጧል። እንዲያም ሆኖ ሩሲያ ለማጣራት ስራው ተባባሪ አለመሆኗ ነው የታየው። በመሆኑም ዓለም አቀፉ የጸረአበረታች መድሃኒቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ወደ እርምጃ ከገባ ሃገሪቷን በየትኛውም ውድድር እንዳትሳተፍ ሊያግዳት እንዲሁም የትኛውንም ውድድር እንድታዘጋጅ ሊከለክላት ይችላል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011
ብርሃን ፈይሳ