ለአለማችን (ዩኒቨርስ) የመጀመሪያዋን ሳተላይት ያበረከተችልን እንቁዋ ተፈጥሮ ነች። በመሆኑም ነው የመጀመሪያና ብቸኛዋ የተፈጥሮ ሳተላይት ጨረቃ ለመሆን የበቃችው። ለጨረቃ አይን ገላጭነት ምስጋና ሰጥተን ወደ ሰው ሰራሹ ሳተላይት እንመለስ።
ከተፈጥሮ ሳተላይቷ ጨረቃ ቀጥላ በሰው ሰራሽ ሳተላይትነት ቀዳሚውን የምትይዘው ኦክቶበር 4 ቀን 1957 ህዋ (Space)ን የተቀላቀለችው የሩሲያዋ ስፑትኒክ 1 ስትሆን፤ በጃንዋሪ 2019 የወጣው የUNOOSA መረጃ እንደሚያመለክተው እስከዛሬ 8ሺህ 378 ሳቴላይቶች ወደ ጠፈር ተልከዋል። በአሁኑ ሰዓትም 4ሺህ 994 ሳቴላይቶች በምህዋር (orbit) ላይ ይርመሰመሳሉ፤ ከእነዚህም ሰባቱ ከመሬት ውጪ ያሉት ፕላኔቶችን የሚያጠኑ ናቸው።
እ.አ.አ በ2014 በአጠቃላይ ንብረትነታቸው የንግድ ተቋማትና የመንግስታት የሆኑ ሁለት ሺህ ሳተላይቶች ምህዋር ላይ ሆነው መሬትን ይቃኙ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የመሬት ምልከታ ስራቸውን በመስራት ላይ ያሉ 2ሺህ 062 ሰው ሰራሽ ሳተላይቶች ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል 901 የሚሆኑት የአሜሪካ ሲሆኑ 299 ደግሞ የቻይና መሆናቸውን ይሄው የUNOOSA (ማርች 31, 2019) መረጃ ያመለክታል። ለመነሻ ያህል ይህን ካልን ወደ “ስፔስ ልማት” እንመለስ።
ልማትና ከልማት ጋር የተያያዙ ተግባራት ሁለ-ገብ ናቸው። በመሆኑም ነው የግብርና ልማት፣ የሰው ሀይል ልማት ወዘተ እየተባለ በየዘርፎች ሁሉ በመግባት የበላይና የተለየ ማጠናከሪያ ሆኖ ሲውል የሚታየው። እርግጥ ነው አንዳንድ ጊዜ ቃሉ ሲሰለች ሁሉ ይስተዋላል። ያለ ምክንያት አይደለም። በተለይ ቃሉ የማስቲካ ያህል ሲላመጥና ያለ ቦታው፤ ወይም እጅግ ተጋኖ ሲገለፅ፣ ከቃሉ ትርጉም ጋር መሬት ላይ ያለው እውነታ አልገጥም ሲል፤ በተለይም ደግሞ “ፀረ-ልማት” እና “ልማታዊ” ይሉ ፍረጃ አየሩን ሲያጥለቀልቀውና ዜጎችን ለሁለት ከፍሎ የጎሪጥ ካስተያየ ቃሉን መስማት ቢጎፈንን አይገርምም። ብቻ ምንም ሆነ ምን ከቃሉም ሆነ ትርጉሙ ችግር የለበትም። ችግሩ ያለው ከቃሉ ተጠቃሚ ጋር ነው። በዚሁ ተማምነን ስፔስ ሳይንስ በአገራችን በሁለት እግሩ ይቆም ዘንድ መደረግ ስለሚገባቸው አንዳንድ ነገሮች መረጃ ጠቅሰን እንነጋገር።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ካሰበችበት ቆይታለች። በኢትዮጵያ በሕዋ ሳይንስ ዘርፍ እንቅስቃሴ ማድረግ የተጀመረው በ1950 (እ.ኤ.አ) መሆኑን የኢንስቲቲዩቱ መረጃዎች ያመላክታሉ። የሥነ ፈለክ ቅኝት፣ ሳተላይት መከታተል እና ፎቶ ግራፍ ማንሳት እንዲሁም የሕዋ መረጃ ልውውጥ ተግባራት ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር ቀደም ባሉት ጊዜያት በጅምር ደረጃ ይከናወኑ እንደነበር የ”ስፔስ ፖሊሲ” ሰነድ ያስረዳል። ዘርፉ በ1960ዎቹ እና 1970ዎች (እ.ኤ.አ) ካሳየው መሻሻል አንፃር ሲታይ ደግሞ እስከ 2004 (እ.ኤ.አ) የጎላ እድገት ሳያሳይ መቆየቱንም ይሄው ሰነድ ይገልፃል።
በአሁኑ ሰዓትም ይህንኑ የስፔስ ሳይንስን አስፈላጊነት በማመን እየሰራች ሲሆን ውጤታማነቷንም በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነችውንና መረጃን ከምድር ወደ ህዋ ከህዋም ወደ ምድር የምትልከውን 70 ኪሎ ግራም ክብደት ያላትን ETRSS-1 “የመሬት ምልከታ ሳተላይት” (Earth Observation Satellite) ታህሳስ 10/2012 አ/ም ከንጋቱ 12፡21 ላይ ከምድረ ቻይና (ከቤጂንግ 400 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ታዩዋን ከተማ ባለው የማምጠቂያ ጣቢያ) በማምጠቅ ከአምጣቂዎች ተርታ ለመሳለፍ በቅታለች። ያመጠቀቻት ሳተላይትም በተዘጋጀላት ምህዋር ላይ በመዞር ስራዋን (የምስል መረጃ የመላክ ተግባሯን) በተሳካ ሁኔታ እያከናወነች መሆኗን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት በየጊዜው እየተናገረ ነው።
በአገሪቱ መሪዎች “ለሃገራችን የብልፅግና ጉዞ ታሪካዊ መሰረት የምትጥል” የተባለላት ይህች ለአገራችን የመጀመሪያ የሆነችው ETRSS-1 ሳቴላይት የአሁኑን ኢትዮጵያዊ (እኛን ማለት ነው) ትውልድም “The Space Generation” የሚል ስያሜን አጎናፅፋዋለች። በሁሉም መስክ እንዲሁ ያዝልቅልን እንጂ ይህን ማዕረግ ማግኘት በእውነት መታደል ሲሆን ስያሜው ለመጪው ትውልድም የሞራል ተነሳሽነትን ከመፍጠሩም ባሻገር እሴት ሆኖ እንደሚያገለግል አያጠራጥርም። በ”ስፔስ ልማት” ዘርፉ ከገፋንበት ደግሞ የሚሆነውን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
በመንግስት ከተያዙት የልማት ፕሮግራሞች አንዱ የስፔስ ሳይንስ ዘርፍ መሆኑን ከ”የኢፌዲሪ ስፔስ ፖሊሲ” በጥቅል፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተገኙ መረጃዎች በዝርዝር ያስረዳሉ። እንደነዚሁ መረጃዎች ማብራሪያ ከሆነ የስፔስ ሳይንስ ዘርፍን በአገራችን ማልማትና መጠቀም ያስፈለገበት አቢይ ምክንያት የህዋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እርሻን፤ የደን ሽፋን፤ ውሃ የሚገኝባቸውን አካባቢ መለየትና መከታተል የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕዋ ሳይንስ እና የሕዋ ቴክኖሎጂን ለማኅበራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት፣ ለአካባቢ ሀብት ጥበቃ እና አስተዳደር፣ ለአደጋ መከላከል ሥርዓት፣ ለሠላም እና ደኅንነት መከበር፣ ለሕዋ ምርምር፣ በሕዋ ዘርፍ ከሚሠሩ ሀገራት ጋር ዓለም አቀፍ ትብብር ለማጎልበት ማሰብ ነው።
በዚሁ መሰረትም በሚቀጥሉት 15 አመታት ኢትዮጵያ 10 ሳተላይት እንዲኖራት ታስቦ እየተሰራ ነው:: በሶስት ዓመት ውስጥ ከተያዙት ፕሮጀክቶች በዋንኛነት የኮሚዩኒኬሽንና ብሮድካስት ሳተላይ ፕሮጀክት፣ የከፍተኛ መሬት ምልከታ ሳተላይት ፕሮጀክት፤ እንዲሁም የሳተላይት መገጣጠሚያ ፋብሪካና ፍተሻ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክቶችን እንደሚያካትት በ”እንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል” የምረቃ ስነ-ስርአት ላይ ተነግሯል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ኢትዮጵያን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ባለብዙ ተልዕኮ የሳተላይት መረጃ መቀበያ ተከላ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ መግለፁም የዚሁ የአገራችን የወደፊት ጉዞ አካል ነውና ይበል ማለቱ ጥሩ ነው።
በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ስራ እንደገባው የ”ሳይንስ ካፌ” እና በደሴ፣ ደብረ ብርሀንና ጎንደር ዝግጅታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉት ተመሳሳይ ካፌዎች የቴክኖሎጂና የዚሁ የ”ስፔስ ልማት” አካል ናቸውና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም ተመመሳሳይ ስራዎች ቢሰሩ የዘርፉን እድገት ያፋጥነዋልና በሁሉም ዘንድ ቢታሰብበት ጥሩ ነው።
ባደረኩት የዳሰሳ ጥናት ዝቅተኛ የሳይንሰ መሠረት፣ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት፣ ደካማ የሕዋ ቴክኖሎጂ አቅም መኖር፣ እጅግ አነስተኛ የሕዋ መሠረተ ልማት፣ የሕዋ ጉዳዮች ቁጥጥር አለመኖር፣ ከሀገራዊ የልማት ፕሮግራሞች ጋር አለመናበብ፣ ዘርፉ የሥራ ዕድል ላይ አለመዋልና የመሳሰሉት ጉዳዮች የ”ስፔስ ልማት”ን እጅጉን አስፈላጊ ያደርገዋልና ባለድርሻ አካላት ሁሉ በዚሁ እይታ እንዲተባበሩ ነው የኢንስቲቲዩቱ ተደጋጋሚ መልእክት የሚያስረዳው።
አገሪቱ (ለደህንነት የሚወጣውንና ዩኒቨርስቲዎች የሚከፍሉትን ሳይጨምር) በዓመት 250 ሚሊየን ብር ከሳቴላይት ለሚገኙ መረጃዎች ግዥ ታወጣለች። (ሰሞኑን የማህበሩ መስራች አቶ ተፈራ ዋልዋ በኢቴቪ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብቻ በአመት 30 ሚሊዮን ብር ለሳቴላይት ግዥ ያወጣል።) ዘርፉን በማልማት እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ወጪዎችን መቀነስ ብቻ ሳይሆን መረጃዎችን በመሸጥ ያገር ገቢን ከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይቻላል፤ ይገባልም ነው የሚሉት ባለሙያዎች። የዚህ ጥሩ ማሳያ ደግሞ ገና ከወዲሁ ስምንት የአፍሪካ ሀገራት የሳተላይት ምስል ግዢ ጥያቄን አቅርበዋል መባሉ ነው። የምግብ ዋስትና እጥረትን፣ የማዕድን ሀብትን በበቂ ሁኔታ ለመጠቀም፣ የመሬት መረጃ ሥርዓት በማዘመን፣ የምድርን፣ የሕዋንና በራሪ አካላትን መሠረት አደርጎ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ማስቻሉም ሌላው ፋይዳው ነውና ልማቱን ማፋጠን አማራጭ የለውም።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 8/2012
ግርማ መንግሥቴ