ሕመም በሕይወት ውስጥ ከሠው ልጆች ቁጥጥር ውጪ ከሆኑ ክስተቶች ውስጥ አንዱ ሆኖ ቢመደብም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ውስጥ ግን መታመም ክልክል ነው ሲሉ የዛሬው የፍረዱኝ ባለጉዳዮቻችን አቤት ይላሉ:: የሴቶች የወሊድ ጊዜም ቢሆን እንደ ባከነ ይቆጠራል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በድርጅቱ ሕገመንግሥቱን በሚፃረር መንገድ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽም መብት የተገደበ እንደሆነ ነው የሚናገሩት:: ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የአየር መንገዱን አስተዳደር አካላት በመንቀፍ በተለያዩ የማህበራዊ ሚድያዎች ጽፋችኋል በሚል ከሥራ ዕግድ እስከ መባረር ዕጣ የደረሳቸው የተቋሙ ሠራተኞች በርካቶች ናቸው በማለት ስለሁኔታው ያብራራሉ:: ይህንን በሠራተኞች ላይ የሚደርሰውን ግፍ የመታገል ኃላፊነት ታዲያ በዋናነት የሠራተኛ ማህበሩ ሚና እንደሆነ ይታወቃል::
ሠራተኞች የአየር መንገዱን ገጽታ ላለማጉደፍ ጉዳታቸውን ችለው በመኖራቸው ችግሮቹ ለረጅም ዓመታት በተቋሙ የተዳፈነ እሳት ሆነው እንዲቆዩ እንዳደረገ በመግለጽ፤ በአሁኑ ወቅት ሁኔታውን ይፋ ለማውጣት የተገደዱበትን መነሻ ይናገራሉ:: ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 406/2009 አንድ ተቋም በመደረጉ፤ በሁለቱ ተቋማት የነበሩት ማህበራትም መዋሃዳቸው አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል:: ይህንን ተከትሎ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ተብሎ ቢቋቋምም ተቋሙ ግን ‹‹ዕውቅና የሰጠሁት ለሌላኛው ማህበር ነው›› በሚል ያደረሰባቸው ጫና አቤቱታቸውን እንዲያሰሙ እንዳስገደዳቸው ነው የሚያስረዱት:: ድርጊቱም ተቋሙ ደሴት እንዲሆን የመፈለግና ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ አለመሆንን ማሳያ በመሆኑ ፍረዱን ይላሉ:: እኛም አቤቱታቸውንና በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን አካላት ምላሽ ከሰነዶች ጋር አዋህደን እንዲህ ይዘንላችሁ ቀርበናል::
መሠረታዊው ማህበር
አየር መንገዱ በብዙ ዓመታት ልምዱ ያዳበረው ጠንካራ መዋቅር ያለው ተቋም ቢሆንም ልምዶቹን እየተጠቀማቸው አይደለም የሚሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር ካፒቴን የሺዋስ ፈንታሁን፤ በዚህም በርካታ ቅሬታዎችን ሲፈጥር እንደሚስተዋል ይጠቁማሉ:: ለዚህም ተጠያቂው የአስተዳደር አካሉ ነው ይላሉ:: ብዙ ሠዎች ችግሮቹን ከአሁኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ወደ አመራር መምጣት ጋር አያይዘው ሲያነሱት ቢሰማም ችግሩ ግን ቆየት ያለ መሆኑንም ይገልፃሉ::
የአየር መንገዱ አስተዳደር ፍልስፍና በሂደት እየተሸረሸረ መምጣቱ ለችግሩ ምንጭ ነው የሚሉት ካፒቴን የሺዋስ፤ በአሁኑ ወቅት ሁኔታው ጠንከር ብሎ ቢታይም ይህን መሰል ባህል ግን የቆየ መሆኑን ነው የሚናገሩት:: ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳትም 12 ዓመታትን የኋሊት ተጉዘው ያስታውሳሉ:: ለመጀመሪያ ጊዜ የአብራሪነት (ፓይለት) ሥልጠና ትምህርት ቤት ሲገቡ ያልጠበቁት እንግዳ ሁኔታ እንደተቀበላቸው የሚናገሩት ሊቀመንበሩ፤ እየተቆነጠጡ፣ በቡጢና በመምህሮቻቸው ክርን እየተደቆሱ እና ስድቦችንም እያስተናገዱ የትምህርት ቆይታቸውን ማጠናቀቃቸውን ይገልፃሉ::
ካፒቴን የሺዋስ፤ በአሁኑ ወቅት ያለው የአቶ ተወልደ አስተዳደር ፍልስፍና የተለየ በመሆኑ የተጋነነ ይሁን እንጂ አጠቃላይ በተቋሙ ያለው የአለቃ መፈራት መንፈስም የቆየና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እንጂ አዲስ አይደለም ይላሉ:: በዚህም አስተዳደሩ ቢሮ ድረስ እየጠራ እንደሚያስፈራራም ነው የሚናገሩት:: በቅርቡ በካፒቴን አዲሱ ወልደሚካኤል ላይ የተወሰደ ዕርምጃን እንደ ማሳያ በማንሳት፤ ‹‹የተቋሙን አስተዳደር በቴሌግራም ገጽ ተሳድበሃል›› በሚል ሰበብ ብቻ እግድ እንደተጣለባቸው በቆይታም ከሥራ እንደተሰናበቱ ይናገራሉ::
የይቅርታ ፖሊሲው ላይ ግልጽነት የጎደላቸው ሐሳቦች እንደሚገኙ የሚጠቁሙት ካፒቴን የሺዋስ፤ አየር መንገዱ ደጋግሞ እንደሚጠቀመው ይናገራሉ:: ከዚህም ባለፈ ሰሚ የሚፈርደው በግልጽ ተገቢነት የራቃቸው ውሳኔዎችም ይስተዋላሉ:: ለአብነትም የካፒቴን አዲሱ ጉዳይን ያወሳሉ:: በካፒቴኑ ላይ እስከመባረር የደረሰ ቅጣት ያረፈውና ከእግድ ደብዳቤያቸው ጋር እንደ ማስረጃ በተቋሙ የተሰጣቸው በቴሌግራም ላይ የፃፉትና ከዚያም ደግሞ በሶሻል ሚድያ ላይ አንድ ጽሑፍን አድንቀው ያደረጉት ምልልስ በወረቀት ታትሞ ተሰጥቷቸው ነበር::
ለካፒቴን አዲሱ ሥም ማጥፋት በሚል የደረሳቸው እግድ ከዚያም መባረር ለተመለከቱት አንድ ጽሑፍ የሰጡት ምላሽ ‹‹በሕገመንግሥቱ ዜጎች የተሰጣቸውን ሐሳብን በነፃነት የማራመድ መብት ለመንካት የተዘጋጁ መሆናቸውንና ሠራተኞች ቢያጠፉም በአገሪቱ ሕግ መዳኘት አለባቸው›› የሚል እንደነበር ነው የገለጹት:: ይሁን እንጂ ይህ ሃሳብ አመጽ ቀስቃሽና የኢንዱስትሪ ሠላሙን የሚያናጋ ነው በሚል ማባረር በግልጽ የሚታይ ሥልጣንን አለአግባብ መጠቀም ነው ይላሉ:: መጀመሪያ ለ30 ቀናት ከታገዱ በኋላ እንዲባረሩ መደረጉን ይገልፃሉ:: በቆይታ ግን በይቅርታ ፖሊሲው መሠረት የይቅርታ ደብዳቤ በማስገባት ዳግም ወደ ሥራ ገበታቸው ሊመለሱ ችለዋል:: በዚህ መልኩ ተጠቂ የሆኑ በርካቶች እንደሆኑም ይገልፃሉ::
የሥራ ኃላፊ ሲሰደብ ኃላፊነቱን ተጠቅሞ ከሥራ ሲባረር፤ በሌላ በኩል ሠራተኛ ሲሰደብም ሆነ ሲቆነጠጥ ግን በዝምታ ማለፍ ይኖርበታል የሚለው የአየር መንገዱ እሳቤ ይህንን ተላልፎ ስለምንም የመብት ጉዳይ ጥያቄ ባነሱ ግለሰቦች ላይ አፀፋዊ ምላሽ ይሰጣል:: ስለሆነም በዚህ መሰል እንቅስቃሴ የተባረሩ ሠራተኞች በደላቸውን መናገራቸው ሊያስከትልባቸው የሚችለውን መዘዝ ፍራቻ ብቻ አፋቸውን ይዘው ይቀመጣሉ በማለት በተቋሙ ለመብት መሟገትም ሆነ መጠየቅ የተከለከለ መሆኑን ያብራራሉ::
በሠራተኞች ላይ የሚያርፉ ቅጣቶች በቅድሚያ በጀርባ ግለሰቦች ከተስማሙባቸው በኋላ ቢደረጉም በኋላ ግን የይቅርታ ፖሊሲው መነሻ ተደርጎ እንደሚሠራ ሲገለጽ ይደመጣል:: የፖሊሲው አፈፃፀምም ቋሚነት የጎደለው ለመሆኑ በሰነዱ ላይ በሰፈረው መልኩ ስድስት ወር ሳይሞላቸው በይቅርታ የሚመለሱ ሠራተኞች መኖራቸው ማሳያ ይሆናል:: የአየር መንገዱ አስተዳደሮች አይነኬ ስሜትን በሠራተኞች ላይ መፍጠራቸው ተገቢነት የሌለው ድርጊት ነው ሲሉ የሚኮንኑት ካፒቴን የሺዋስ፤ አመራሮቹ ሊጠበቁ የሚገባቸው እንደ አስተዳደር አካላት እንጂ እነርሱ ስለተነኩ የአየር መንገዱ ገጽታ ይጠለሻል ብሎ ማሰብ ትክክል አይደለም ባይ ናቸው::
የአስተዳደር አካላትን መስደብ የአየር መንገዱን ጥቅም ይነካል የሚለው እሳቤና ትርጓሜ ትክክል አይደለም:: የተቋሙ የአመራር አካላትን መናገር የአየር መንገዱን ሥም አጠልሽተሃል ብሎ ከሥራ እግድ እስከ መባረር የሚያደርስ ቅጣት ማሳረፍ ትክክል አይደለም:: ምክንያቱም ደግሞ ሠራተኞች የሚያቀርቡት ትችት ትክክል ሊሆንም ይችላል ብሎ ከግንዛቤ መክተት ይገባል:: በመሆኑም ትችትን ከመሸሽና ከማራቅ ይልቅ ቀርቦ በችግሮች ላይ መወያየትና መፍትሔውንም ማፈላለግ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ይላሉ::
ማህበሩ የሚጠቀመው አጠቃላይ 8 ሺህ 600 ያክል አባላት ያሉት የቴሌግራም ቡድን አለ:: በዚህ ላይ የሚፃፈውን ሁሉ እያንዳንዱ ሠራተኛ ምን ተናገረ በሚል የሚከታተል አካል ያለ እስኪመስል ሠራተኞች በነፃነት ሃሳባቸውን ማራመድ በከለከለ መልኩ ክትትል ይደረጋል:: በዚህ ሂደት ውስጥ የአስተዳደሩን አካላት ነካችሁ በሚል ዕርምጃ ሲወሰድም ይስተዋላል:: ይህ ድርጊትም ሠራተኞችን ለመቅጣት አሰፍስፎ የሚጠባበቅ አካል ያለ ያስመስለዋል ይላሉ::
ካፒቴን የሺዋስ፤ እህቱ ፌስቡክ ላይ እናቷ በበረራ ላይ ሻንጣቸው ያጋጠመውን ችግር በመጻፏ የሦስት ዓመት የትኬት ጥቅማ ጥቅም የተነሳበት ዋና አብራሪ ዘካሪያስ ከሊል ጉዳይን እንደ ሌላ ማሳያ ያነሳሉ:: ዋና አብራሪው እህቱ በፌስቡክ ገጿ የጻፈችውን እንዲያስነሳ አየር መንገዱ ትዕዛዝ ከሰጠውና እንደተባለው ካደረገ በኋላ የሦስት ዓመቱ የትኬት ጥቅማ ጥቅሙ (እርሱም ሆነ ቤተሰቦቹ ትርፍ መቀመጫ እስካለ ድረስ የነበራቸውን የመብረር ዕድል ምንም ዓይነት ጥቅማ ጥቅም (ነፃ) ትኬት) ከአየር መንገዱ እንዳያገኙ የሚያደርግ ነው:: ለምን? ብሎ ላቀረበው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ‹‹ የተነሳብህ ጥቅማ ጥቅም እንጂ አልቀጣንህም›› የሚል እንደነበር ነው ካፒቴን የሺዋስ የሚናገሩት:: እህቱ ያደረገችው መብቷ ነው ብሎ ሳይከራከር ከተቋሙ የአስተዳደር አካላት የተሰጠውን ትዕዛዝ በመቀበል ጽሑፉ እንዲጠፋ ካደረገ በኋላ ቅጣቱ የተጣለበት ዋና አብራሪ ይህን ባያደርግ ኖሮ ምናልባትም ከዚህ የአስተዳደሩ አፀፋዊ ምላሽ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም ይላሉ::
ሊቀመንበሩ፤ አቪየሽን ትምህርት ቤት ውስጥ የነበሩ አንድ መምህር ላይ የደረሰ በደል ሌላው በማሳያነት ያቀረቡት ጉዳይ ነው:: መምህሩ በቆይታ የአቪየሽን አካዳሚው የሴፍቲ እና ኳሊቲ ኢንሹራንስ ማኔጀር ሆነው እንደነበር በማስታወስ፤ በክፍሉ ለሚያስፈልገው ኤክስፐርት ኦዲተር የሥራ መደብ መስፈርት ወጥቶ የውስጥ ማስታወቂያ ወጥቶ እንደነበር ይናገራሉ:: ይሁን እንጂ ‹‹ሠው ተገኝቷል›› የሚል ዜና ይሰማል::
እንዴት? ሲባል ደግሞ ከውጭ እንደተገኘ ይገለፃል:: የሥራ መደቡ የሚጠይቀው ለረጅም ዓመት በአቪየሽን ውስጥ የሠራ፣ የኦዲት ልምድ ያለው ቢሆንም የተባለው ግለሰብ ግን ይህንን የሚያሟላ ሆኖ ማኔጀሩ አላገኙትም:: በመሆኑም ‹‹ከፈለጋችሁ ሌላ ቦታ ቅጠሩት እንጂ ቦታው ላይ አይገባም›› ብለው በመታገላቸው ቢሯቸው ለምርመራ ስለሚፈለግ እንዲወጡ ይደረጋሉ:: በዚህ ሁኔታ ከሥራ ገበታቸው ተነስተው መቆየታቸው ግርታን ቢፈጠርባቸው እየደወሉ ‹‹መቼ ልምጣ?›› ብለው ጥያቄ ሲያቀርቡም እንደሚደወልላቸው ምላሽ እየተሰጣው ይቆያሉ:: በኋላም ለ30 ቀናት በሥራ ገበታ ላይ ባለመገኘት በሚል መባረራቸውን የሚያረዳ ደብዳቤ ይደርሳቸዋል:: ይህን መሰል ችግሮችም በስፋት እንደሚታዩ ይጠቁማሉ::
በአንድ ተቋም ሁለት የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ውስጥ የተለያዩ አሠራሮች መኖርም ሌላኛው ችግር እንደሆነ ሊቀመንበሩ ያስረዳሉ:: ይህም በተለይ ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ዕቃዎችን የሚሸጡ የበረራ አስተናጋጆች፣ ቲኬት ኤጀንቶችና የተወሰኑ ክፍሎች ላይ የሚስተዋል ሲሆን፤ ክፍሎች ተመሳሳይ ሽያጭ ቢያከናውኑም ጉድለት ሲኖር ግን የአከፋፈል ሕግጋቶቻቸው ይለያያሉ:: አየር መንገዱ ጉድለት መኖሩን በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ካሳወቀ በኢትዮጵያ ብር እንዲከፍሉ ሲደረግ በበረራ አስተናጋጆች ላይ ግን ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም እንኳ ጉድለቱ በታወቀበት ጊዜ ያለምንም ክርክር በዶላር የመክፈል ግዴታ አለባቸው::
ይህን መሰል የተለያየ አሠራርም ተገቢ አይደለም በማለት ይተቻሉ:: በሌላ በኩል የሥራ ልምድ አለመስጠትና አየር መንገዱ የአገሪቱ ሕዝብ ቢሆንም በሩን የሚከፍተው ግን በኢኮኖሚ የተሻለ አቅም ላላቸው አካላት ብቻ መሆኑም ሌሎች መማር እንዳይችሉ በር የሚዘጋና ከፍተኛ ችግር እንደሆነም ነው የሚገልጹት:: በዚህ ደረጃ ገንኖ የሚስተዋለውን ችግር ለማቃለል ታዲያ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ማህበራቸው ቢቋቋምም አየር መንገዱ ግን ለመቀበል እንዳዳገተው ይናገራሉ:: የሠራተኞች ወርሐዊ ተቆራጭ እንዲደረግ ቢጠይቁም ፈቃደኛ አለመሆኑንም አክለው ያነሳሉ::
ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የተደረገውን የማህበር አመራር ምርጫ ተከትሎ በቀጣይ ቀናት ውስጥ አብራሪዎች የሠራተኛ ማህበር አባል የሆኑት ለምንድን ነው? በአስቸኳይ አስወጧቸው የሚል ደብዳቤ መፃፉን ያስታውሳሉ:: በአገሪቱ አሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት የሥራ መሪ የሚል ጽንሰ ሐሳብ አለ:: ስለዚህ ‹‹ካፒቴኖች የሥራ ባህርያቸው መሪ ስለሆነ በማህበር መደራጀት አይችሉም›› የሚል ሃሳብን የያዘ ነው:: በደብዳቤው ዋና አብራሪዎች የማህበር አባል እንደነበሩ ጉዳዮን እንደማያውቁና ጭርሱን አመራር ሆነው መመረጣቸውን ያሳያል:: ነገር ግን ቀደም ብሎ በነባሩ ማህበር ውስጥ የክፍል ተወካይ ሆነው ይሠሩ እንደነበሩ፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴዎች ላይ ይሳተፉ እንደነበርና የማህበሩ ሊቀመንበር ከመሆናቸው ቀድሞም አስተዳደሩ ይህን ያውቅ እንደነበር በመግለጽ፤ በደብዳቤው አብራሪዎች መግባታቸው ስለምን? ብሎ አየር መንገዱ የጠየቀው የተቋቋመው ማህበር እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ችግሮችን በጄ እያለ የማያልፍ ሆኖ ስላገኘው እንደሆነ ይናገራሉ::
የአየር መንገዱ አውሮፕላን አብራሪዎች ለብዙ ዓመታት የሠራተኛ ማህበር አባል እንዳልነበሩ የሚናገሩት ካፒቴን የሺዋስ፤ በአንድ ወቅት ማህበሩ ላይ በነበራቸው ቅሬታ ወጥተው መቅረታቸውን ያስታውሳሉ:: የሙያ ማህበሩም የሠራተኛ ጉዳይ ላይ የመሳተፍ ሥልጣን ባይኖረውም በሁለቱ መካከል በነበረው ስምምነት እስከተወሰነ ወቅት እንደተደራዳሪ ሆኖ የጋራ ስምምነት ላይ ይሳተፍ ነበር:: በዚህ መልኩ ከቆየ በኋላም ዘጠነኛው የጋራ ስምምነት ሲፈራረሙ የሙያ ማህበሩ ተወካዮች የተስማሙባቸውን ነገሮች ወደጎን በመተው ሌሎች ነገሮችን አስገብተው ተፈራረሙባቸው::
የሥራ ሁኔታዎችን በተመለከተ ክፍል ሦስት ውስጥ አንቀጽ 25 ላይ የበረራ ሠራተኞችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ወይንም ስምምነቶች አሉ:: ይህንን በተመለከተ በድርድር የተቀመጡትና ከስምምነት የተደረሰባቸው ስምምነቶች ተትተው ሰነዱ ወጣ:: ይህም በሠራተኛና በሙያ ማህበሩ መካከል የነበረውን ዕምነት በማጥፋቱ በ10ኛው የጋራ ስምምነት ላይ ይህንን አንቀጽ ሙሉ በሙሉ አውጥተው ተፈራረሙ:: ነገር ግን የሙያ ማህበሩ እንቅስሴውን ሲያደርግ የነበረው በሠራተኛ ማህበሩ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት የሠራተኛውን የአብራሪዎችን ጥቅማ ጥቅም ለማስከበር የጋራ ስምምነት ላይ የመካፈል ሚና ነው::
በሠራተኛና በአሠሪ መካከል የሚያጋጥም ግጭትና በሙያ ማህበርና በአሠሪ መካከል የሚኖረው ግንኙነት የተለያዩ መሆን አለባቸው የሚሉት ሊቀመንበሩ፤ የሙያ ማህበሩ እንደ መብት ተከራካሪ ሊታይ እንደማይገባውም ይገልፃሉ:: የሙያ ማህበሩ ትኩረቱ ሊሆን የሚገባው ሙያዊ ስለሚሆን በዚህ በኩል ከተቋሙ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መሥራት ይኖርበታል:: ስለሆነም አብራሪዎች የሠራተኛ ማህበር ውስጥ እንዲገቡ በተደረገ ቅስቀሳ በሦስት ወራት ውስጥ 500 የሚጠጉ አብራሪዎች የማህበር አባል እንዲሆኑ ተደረገ:: ይህም የአስተዳደር አካላትን ማስደንገጥ እንደጀመረ ያስታውሳሉ::
የዚህ መነሻም ማንም ሠው ወደ ሙያ ማህበሩ ሙያዊ እንጂ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን ይዞ እንዳይመጣና ሙያ ማህበሩን ነፃ አድርጎ ለማጠናከር የተሠራ ሥራ ነው:: ሙያ ማህበሩን የሠራተኛው ጉዳይ ጎንጉኖ በመያዙ ሙያው እንዲጎለብት፣ ሙያተኞች በሙያቸው ምስጉን እንዲሆኑ፣ ሕብረተሰቡ ስለሙያው በደንብ እንዲያውቅ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች ስለሙያው ያላቸውን ዕውቀት በማሳደግ ግንኙነቱን ማሳደግ እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ተሳትፎዎችን በማድረግ ረገድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዳይወጣ ወደኋላ ይዞት ነበር:: ነገር ግን በአሠሪና
ሠራተኛ መካከል የሚፈጠሩ ጉዳዮች በዋናነት የሠራተኛ ማህበሩ እንጂ የሙያ ማህበሩ ሚና ባይሆንም ሁለቱንም ሲያከናውን በመቆየቱ ግን ማህበሩ የሚጠበቅበትን ሚና እንዳይጫወት አድርጎት ቆይቷል::
በዚህ መልኩ የተጀመረው ማህበሩን የማጠናከር ተግባር በቆይታ ሁለቱ ማህበራት እየተዋሃዱ ስለነበር ኮሚቴዎች ያዘጋጁትን ሠነድ በማዳበር ሥልጣኑን ታች ድረስ በማውረድ ሥራ አስፈፃሚው ሁሉንም ፈላጭ ቆራጭ እንዳይሆን፤ ይልቁንም እያንዳንዱ ሠራተኛ ላይ ዕምነት ለመፍጠር ሲሠራ ቆይቷል:: ይህ ከተደረገ በኋላም ግንቦት ላይ ምርጫ ተደረገ::
ከዚያ ማግሥትም እንቅስቃሴውን ያውቅ የነበረው የአየር መንገዱ አስተዳደር አብራሪዎችን የተመለከተውን ደብዳቤ እንደፃፈላቸው ነው የሚናገሩት:: በዚህም አየር መንገዱ እዚህ ግባ የማይባል ሰበቦችን በመፈለግ በአባላቶቻቸውና በአጠቃላይ ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ ሲሆን፤ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን ለመፍታት ጥያቄዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑና ደብዳቤዎቹንም አልቀበልም በማለቱ በአደራ መልዕክት በፖስታ ቤት በኩል ለመላክ እንደተገደዱ ያስረዳሉ:: በአሁኑ ወቅትም ቅሬታው ዓለም አቀፍ የትራንስፖርት ፌደሬሽን እንዲሁም የሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አፍሪካ ቅርንጫፍ መድረሱን ነው የሚገልጹት::
ሌላው ከማህበራቱ ጉዳይ በላይ የማህበሩ የቀጣይ ዋናው የትኩረት አቅጫ በተቋሙ ሠራተኞች ላይ የሚደርሰውን ተገቢነት የጎደለው ጫና ለመከላከልና ተቋሙ በሕጉ መሠረት እንዲጓዝ ለማድረግ ነው የሚሉት ካፒቴን የሺዋስ፤ በተቋሙ KPI (Key Performance Indicator) የተሰኘ የምዘና ሥርዓት እንዳለ ይገልፃሉ:: አፈፃፀም ሲመዘን በሁለት መንገድ መሆኑን በማብራራት፤ ሠራተኛው ለራሱ ከተሰጠው ግብ አንፃር እንዴት እንደፈፀመ ሲያይ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ንጽጽራዊ ነው:: በዚህም ከሌላው ሠራተኛ አንፃር ምን ተሠራ በሚል መመዘን ይቻላል:: በተቋሙ አሠራር ግን ችግር የሆነው የሁለቱ ድብልቅ መሆኑ ነው በማለት ያስረዳሉ::
በተቋሙ በዓመቱ መጀመሪያ እያንዳንዱ ሠራተኛ ግብ አስቀምጦ ይፈርማል:: በዚህም ሊለካ የሚገባው ከዚህ አንፃር ነው:: አይደለም ከተባለ ደግሞ በእያንዳንዱ የሥራ ክፍል ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች የተሻለ አፈፃፀም ያለውን በንጽጽር ውጤቱ ሊሠራ ቢችልም ሁለቱን በአንድ ላይ ተግባራዊ ሲደረግ ግን ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ይሆናል:: በተቋሙ የምዘና ሥርዓት መሠረት 20 በመቶ ከፍተኛ አፈፃፀም ያለው፣ 70 በመቶ አማካይና 10 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያለው ነው::
ስሌቱ ቋሚ ሲሆን፤ ሠራተኛው ምንም ያክል አፈፃፀም ቢኖረውና በተሻለ መልኩ የተሰጠውን ሥራ ቢፈጽምም ከፍተኛ ደረጃ ውስጥ መግባት የሚችለው ግን 20 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው:: አሠራሩ ግልጽ ባለመሆኑም በየክፍሉ የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ጭንቀት በመሆኑ በአንዱ መንፈቅ ዝቅተኛ ያደረጉትን በሌላው ደግሞ መካከለኛ እያደረጉ በዕደላ መልክ ሁሉንም ሠራተኛ ላለማስከፋት ይጥራሉ:: አልያም ደግሞ አንዳንዶች ይህ የምዘና ሥርዓት በከፈተላቸው በር ተጠቅመው አይነ ውሃው ያላማራቸውን ሠራተኛ ሲጎዱ ይስተዋላል:: ይህም ምዘና ሒደቱ ምን ያክል ትክክለኛ እንዳልሆነ ያሳያል:: በዚህ ውስጥ ያለአግባብ ተጠቃሚ የሚሆን ወይ ደግሞ ያለአግባብ ተጎጂ የሚሆን አይጠፋም:: አፈፃፀሙ ላይ መነሻ ተደርጎ በዓመቱ መጨረሻ አየር መንገዱ ለሠራተኞቹ ጉርሻ (የማበረታቻ ጭማሪ ክፍያ) ሲሰጥ ቅሬታዎች እንደሚስተዋሉም ነው ካፒቴን የሺዋስ የሚናገሩት::
በምዘና ሥርዓቱ ስሌት ውስጥ የባከነ ጊዜ በሚል የተቀመጠው ሃሳብ ሌላው የቅሬታ ምንጭ እንደሆነ ካፒቴን የሺዋስ ይናገራሉ:: በዚህ ላይ ነጥብ ተቀንሶ የተመለከተ ሠራተኛ ‹‹ስለምን ተቀነሰብኝ?›› ብሎ ቢጠይቅ በወቅቱ ታምሞ እንደነበር ይገለጽለታል:: ምንም እንኳ ሕመም ተፈጥሯዊና ከሠው ልጆች ቁጥጥር ውጪ ቢሆንም በተቋሙ ግን መታመም የተከለከለና “አውቆ ነው የታመመው” የሚል እሳቤ ይስተዋላል:: የሴቶች የወሊድ ጊዜም እንደ ባከነ ጊዜ ይቆጠራል::
ከዚሁ ጋር አያይዘው በአንድ ወቅት አንድ ዋና አብራሪ የሥራ ባልደረባቸው በዚሁ በተቋሙ አስተሳሰብ አውቆ ትርፍ አንጀት የያዘው ዋና አብራሪ እንደነበር በፈገግታ ያስታውሳሉ:: ዋና አብራሪው ወደ አሜሪካ በረራ ባቀኑበት ወቅት ትርፍ አንጀት ይይዛቸውና ለስምንት ቀናት ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸው ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ:: ወደ መደበኛ የሥራ ገበታቸው ሲገቡም የቆዩበትን ቀናት አበል ተሰልቶ እንዲከፈላቸው ቢጠይቁም ተቋሙ ግን ቀናቱን አስልቶ አፈፃፀም ላይ ይቀንስባቸዋል:: አበል እንዲከፈላቸው ለመብታቸው ሲሟገቱ የነበሩት ዋና አብራሪም ከአፈፃፀማቸው ላይ የተቀነሰባቸው ነጥብ ግራ ቢያጋባቸው ለምን? ብለው ይጠይቃሉ::
ተቋሙም በባሕር ማዶ ጉዞ ወቅት ታምመው የነበሩበት እንደነበር ይገልጽላቸዋል:: ይህም እንዴት የሠው ልጅ ይታመማል የሚለው ከተፈጥሮ ሚዛን ውጪ የሆነ እሳቤ የሴቶች ወሊድ ላይ መተግበሩ ኀዘን እንደሚፈጥር ካፒቴን የሺዋስ ይናገራሉ:: ሴቶች ለምን ይወልዳሉ? ልጅ እንኳ ካስፈለጋቸው ለአየር መንገዱ ሲሉ ቢያዘገዩት፤ ከቻሉ ደግሞ በማደጎ ቢወስዱ? የሚል አመለካከትን ያዘለ ነው ሲሉ ይኮንኑታል:: ይህም በተቋሙ ፖሊሲ ጭምር ተደግፎ ተግባራዊ ቢደረግም በየትኛውም ሠራተኛ ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘቱንና መንግሥት ‹‹አሳምኖ ማሠራት – ለትክክለኛ ዕድገት›› በሚል በፖሊሲዎቹ ያስቀመጣቸውን እሳቤዎችም የሚሸረሽር ነው ይላሉ:: የምዘና ስርዓቱ ለረጅም ዓመታት ተግባራዊ ተደርጎ ውጤት ማምጣት ካልቻለ በግድ ሠራተኛውን ለመጋት ከመጣር ይልቅ ችግሩን መፈተሽ ይገባ ነበር:: በዚህም ምዘናው ሠራተኞች ምንም ቢሠሩ ‹‹ሺህ ቢታለብ በገሌ›› እንደሚባለው ከዚህ እንደማያልፉ እንዲያስቡና ተነሳሽነታቸውም እንዲቀንስ ያደርጋል ይላሉ::
ታዲያ ይህ ሁሉ ችግር ካለ ተቋሙ እንዴት ለሚነገርለት ስኬት በቃ? ሠራተኛውስ ስለምን በተቋሙ መቆየትን ምርጫው አደረገ? ለካፒቴን የሺዋስ ያቀረብነው ጥያቄ ነበር:: እርሳቸውም በምላሻቸው፤ ‹‹በአንድ በኩል ምንም እንኳ ይህ ሁሉ ችግር ቢኖርም ሠራተኛው ጥሩና ውጤታማ ነው ማለት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ግን ምናልባትም የሚባለው ውጤት የለ ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄንም ሊያጭር ይችላል:: ምክንያቱም ደግሞ ገጽታ ግንባታና መሬት ላይ ያለው ዕውነተኛ ማንነት የተለያዩ መሆናቸውንም መገንዘብ ያስፈልጋል›› ይላሉ::
ካፒቴን የሺዋስ፤ ሠራተኛው ወደሌላ አማራጭ ተቋማት እንዳያማትር ምርጫ የለውም በማለት ይናገራሉ:: በአገሪቱ ብቻ ገበያው የተገደበባቸው ሠራተኞች ችግሩን ችለው ሥራቸውን ይቀጥላሉ:: ከዚህ አገር ለቅቀው መውጣት የሚችሉት ደግሞ እንዳይለቅቁ ፓስፖርታቸው እየተቀማ እንዲቀሩ ይደረጋል:: የተማሩበትን የሙያ ሠርተፊኬትም አየር መንገዱ አይሰጥም:: ፈቃዱንም ቢሆን ሲቪል አቪየሽን እንዳይሰጥ አየር መንገዱ ጫና ይፈጥራል::
ስለዚህ ሠራተኞች ቢፈልጉም ስለማይችሉ አይሄዱም:: በዚህ መሰል ሒደት ውስጥ ደግሞ በዕውቀት ብሎም በሥራ ልምድ የተሻሉ ተወዳዳሪዎች ባሉበት እንዴት እንደሆነ ባልታወቀ መልኩ ሹመት ሲደረግ ይስተዋላል:: ምንም እንኳ መታየት ያለበት ሥራ ቢሆንም በተቋሙ ውስጥ አጎብዳጅነት ወይንም ሥራን ማዕከል ያላደረጉ ግንኙነቶች ስለሚበረታቱ ከዚህ ተግባር ውጪ ያሉ ሠዎች ዓይን ውስጥ አይገቡም ሲሉም ጫናውን ያብራራሉ:: በመሆኑም የተቋሙን ጤነኞቹን ፖሊሲዎች ማጠናከር፣ ችግር የሚስተዋል ባቸውን ደግሞ ቆም ብሎ መፈተሽና ችግሮቹን ለማቃለል የሚመለከታቸው አካላት ተቋሙን ሊፈትሹ ይገባል ሲሉ ይጠይቃሉ::
ሰነዶች
የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሠረታዊ ሠራተኞች ማኅበር ለአባላቱ በ22/08/2011 ዓ.ም በቁጥር አ.አመሠማ/132/11 ወጪ ባደረገው ደብዳቤ ጠቅላላ ጉባዔውን አስመልክቶ ጽፏል:: በዚህም ማህበሩ የአመራር አባላት ምርጫ ለማካሄድ፣ ከኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የሠራተኞች ማህበር ጋር ውህደት እንደሚያደርግና የማህበሩ ስያሜ ስለሚቀየርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሠራተኛ ማህበር ተብሎ ስለሚጠራ በተጨማሪም የሠራተኞች ማህበር ደንብ ለማፅደቅ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ በሰባት ሰዓት በአቪየሽን አካዳሚ በሚገኘው ኦዲቶሪየም በሚደረገው ጠቅላላ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ማሳለፉን ያሳያል::
በ09/09/2011 ዓ.ም ማህበሩ ለአየር መንገዱ ኮርፖሬት የሠው ሀብት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት የመሠረታዊ ማህበሩን ሽግግር አስመልክቶ የላከው ደብዳቤ ሌላው የተመለከትነው ሰነድ ነው:: በደብዳቤው ከሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጵያ ኤርፖርች ድርጅት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 406/2009 መሠረት በመዋሃድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በመባል በአዲስ መልክ መቋቋማቸውን ያብራራል:: ይህንን ተከትሎም የሁለቱ ማህበራት መዋሃድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ይገልፃል::
የሁለቱም ማህበራት አመራሮች በመገናኘት ተከታታይ ውይይቶችን እንዳደረጉ፣ ከሁለቱ ማህበራት የተውጣጣ በድምሩ ስድስት አባላት ያሉት አዋሃጅ ኮሚቴ መቋቋሙንና ኮሚቴው ሠፊ ተከታታይ ውይይቶች ማካሄዱን፣ የሁለቱን ድርጅቶች አቻ የሠራተኞች ማህበራት ባማከለ ሁኔታ የጋራ ሕገ ደንብ ረቂቅ መዘጋጀቱንም ደብዳቤው ያሳያል:: ከዚህ በተጨማሪም መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበሩ ተቋሙን ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ የስብሰባ ፈቃድ የጠየቀበት፣ አየር መንገዱ አስተዳደር የተጠራው ስብሰባ ከፈቃዱ ውጪ በመሆኑ ሠራተኞች በስብሰባ እንዳይገኙ በኢሜል መልዕክት ያሳሰበባቸው ሠነዶች፣ ይህንን ተላልፈው በስብሰባ በተገኙ ሠራተኞች ላይ ደግሞ ለሌሎች አስተማሪና የማያዳግም እርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ ያዘዘበት ሠነድ፣ ወርሃዊ መዋጮ እንዲቆረጥለት የጠየቀበት፣ በርካታ የተቋሙ ሠራተኞች አባል በሆኑበት ቴሌግራም ላይ የአየር መንገዱን አስተዳደር “ባልተገባ መንገድ ዘልፈህ መልዕክት እንዳስተላለፍክ በተደረገ ምርመራ ስለተደረሰበት” በሚል ለካፒቴን አዲሱ የተሰጠ የዕግድ ደብዳቤና ጽፈዋል የተባለው መልዕክት ከመሠረታዊ ማህበሩ አግኝተን ከተመለከትናቸው ሰነዶች መካከል ይገኛሉ::
ሠራተኞች ይደርስብናል ስለሚሉት ጫናና ችግር ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ ያሳወቁባቸው ደብዳቤዎችንም ለመመልከት ችለናል:: በተያያዘ አየር መንገዱ ለቀዳማዊ ሠራተኞች ማህበር አባላት ጥቅምት 14 ቀን 2012 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ማህበሩ ሕጋዊ ህልውናውን ጠብቆ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ ሠራተኞች ማህበር ተብሎ መሰየሙን ማብሰሩን ያሳያል:: በሌላ በኩል ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የተደረገው ስብሰባ በርካታ ችግሮች ያሉበት መሆኑን በማብራራት፤ ማህበሩ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፀድቆ ሥራውን በይፋ የጀመረ መሆኑን እንደገለፀና ለበርካታ ዓመታት የቆየ አንጋፋ ማህበር እንደሆነም ያትታል:: በመሆኑም ማህበሩ የኢንዱስትሪ ሠላምን ለማስፈንና የሠራተኞች ጉዳይ ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እንደሚሠራ በመግለጹ፤ ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ማሳወቁን በደብዳቤው አስፍሯል::
ሕገ መንግሥቱ ምን ይላል?
በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 29 የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብትን ይደነግጋል:: በዚህም ማንኛውም ሠው ያለማንም ጣልቃገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝ፣ የመግለጽ ነፃነት እንዳለው በግልጽ አስቀምጧል:: ነፃነቱም በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሃሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል:: ነገር ግን እነዚህ መብቶች ነፃነቱ በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትሉ ከሚችሉት አስተሳሰባዊ ውጤት ገደብ ሊጣልባቸው ይገባል ይላል::
በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 31 ደግሞ የመደራጀት መብት አስመልክቶ ተደንግጓል:: በዚህም ማንኛውም ሠው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት እንዳለውና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሠረቱ ድርጅቶች የተከለከሉ መሆናቸውን አስቀምጧል::
ሌላኛው ማህበር
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር ኢንጂኒየር ተሊላ ዴሬሳ፤ ቅሬታ እያቀረበ ያለው አዲስ የተፈጠረው ማህበር በመሆኑ ‹‹የእኛን ማህበር አይወክልም›› በማለት ይናገራሉ:: ማህበራቸው ከ58 ዓመት በፊት እንደተቋቋመ በመግለጽ፤ ቀዳማዊ ማህበሩ በተለያዩ ጊዜያት ከፍታና ዝቅታን ሲያስተናግድ መቆየቱንም የኋሊት ተጉዘው ያስታውሳሉ:: በፋይናንስ አቅሙም በጣሙን ጠንካራ የሆነና ብዙ ልምዶችን ያካበተ ሲሆን፤ አዲስ አመራር ተመርጦ ወደ ሥራ ከገቡ ሁለት ወራት ማስቆጠራቸውን ነው የሚናገሩት::
ተቋሙ እ.አ.አ. 2017 ስሙን ቀይሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንብ ቁጥር 406/2017 ላይ ውህደት ፈጠረ:: በዚህ መሠረት ተቋማት ሲዋሃዱ ማህበራቱም ለመዋሃድ ብዙ ጥረቶች ያደርጉ ነበር:: ይህንንም ፌዴሬሽንና ኮንፌዴሬሽን ሲያደራድራቸው ነበር ይላሉ:: ድርድሩ ከአንድ ዓመት በላይ መፍጀቱን በማስታወስ፤ ሁለቱ ማህበራት በደንብ ተዋህደው ሳይጨርሱ ሌላ ደንብ ደግሞ ይወጣል:: ይህም የደንብ ቁጥር 452/2019 ይባላል:: ደንቡም አየር መንገድ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶችን ድርጅት ያጠቃልላል ይላል:: በዚህም መሠረት ምርጫ ተካሂዶ ለሦስተኛ ጊዜ ምርጫ ተደረገ::
በድርድሩ መሃል አዲሱ ማህበር ኢሠማኮ ያቋቋመው ሲሆን፤ ቀዳማዊ ባለበት ሥራ አስፈፃሚ እንደ አዲስ መምረጥ ብቻ ሲጠበቅበት አዲስ ማህበር እንዲቋቋም መደረጉ አካሄዱ ክፍተት እንዳለበት ያሳያል ባይ ናቸው:: የነበረውን ክፍተት ሞልተው ጠንካራ ጎኑን አሳድገው መራመድ እንጂ ሌላ አዲስ ማህበር እንደማይፈልጉም ይገልፃሉ:: በሌላ በኩል አዲሱን ማህበር ለመቀላቀል አቋም የያዙ በመኖራቸው ሁለት ወገን ሊፈጠር እንደቻለም ነው የሚናገሩት::
ቀዳማዊ ማህበሩ ሰባት ሺህ የሚደርሱ አባላት የነበሩት ሲሆን፤ ለአምስት አሰርት ዓመታት ቅጥር እንደተካሄደ የሠራተኛ ማህበር ቅጽ በመሙላት አባል ይሆኑ ነበር:: በሌላ በኩል አዲሱ ማህበር ግን አባላትን ከዜሮ ተነስቶ ምዝገባ ያካሂዳል:: ከተቋሙም ጋር ምንም ድርድር የለውም:: በሕግ መሠረት ደግሞ ተቋሙ ከፍተኛ ቁጥር ካለው ማህበር ጋር ነው የሚሠራው:: በዚህም በአሁኑ ወቅት ቀዳማዊው ማህበር ከድርጅቱ ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ያስረዳሉ::
ሁለቱን ማህበራት አንድ ለማድረግ በቅርበት እንደሚነጋገሩ በመጥቀስ፤ ዓለም ወደ አንድ በሚያመራበት በዚህ ዘመን በአየር መንገዱ ግን ሁለት የተለያዩ ማህበራት መፈጠራቸው ተቋሙ ካለው ሥምና ዝና አንፃርም አብሮ የማይሄድ እንደሆነ ኢንጂኒየር ተሊላ ይገልፃሉ:: በአንድ ተቋም በሁለት ማህበር መካከል በሚፈጠው ፉክክርም ሠራተኛው ከመጥቀም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል:: ስለሆነም አንድ ለመሆን የሚደረገው ጥረት እንደሚቀጥል ይጠቁማሉ::
የተቋሙን ውጤታማነት በሚጎዳ መልኩ ስለ ማህበር ሲያነቡ የሚቆዩ ግለሰቦችም እየተፈጠሩ ናቸው የሚሉት ኢንጂነር ተሊላ፤ ተቋሙን የእያንዳንዱ ሠራተኛ ጥረት ለስኬቱ ያበቃው ቢሆንም ሐሳቡ ተወጠረ ማለት አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖረው ወደ አንድነት መምጣቱ የተሻለ ነው ይላሉ:: ተቋሙ ከዚህ ቀደም ያለው ገጽታ መልካም በመሆኑም ጉዳዩን ለብዙሃን መገናኛ አድርሶ ከማጠልሸት ይልቅ በቅድሚያ መምከር የተሻለ ይሆናል ባይ ናቸው::
ተቋሙ የሠው ልጆች እንጂ የቅዱሳን ስብስብ ባለመሆኑ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉም ኢንጂነር ተሊላ ያምናሉ:: ማህበሩ በሠራተኛው መብት ስለማይደራደር አለአግባብ የተባረረ ሠራተኛ ካለ መብቱ እንዲከበርለት በየደረጃው አስፈላጊውን ትግል ያደርጋል:: በተቋሙ በርካታ የአስተዳደር አካላት ስላሉ ከእነዚህ ውስጥ ጫና የሚፈጥሩ ሊኖሩ ቢችሉም ሁሉም ያደርጋል ማለት ግን አይደለም:: ስለሆነም ጠቅልሎ መኮነን ሳይሆን መፍትሔው ላይ መሥራቱን ይመረጣል በማለት በተቋሙ ሠራተኞች ላይ ይደርሳሉ ስለሚባሉ ችግሮች ያላቸውን አስተያየት ይሰጣሉ::
ከምዘና ሥርዓቱ ጋር ተያይዞም ምዘና ግዴታ መኖር አለበት የሚሉት ኢንጂነር ተሊላ፤ ግለሰብ ላይ መሠረት ያደረገ ሳይሆን ዓላማና ግብ ያለው ምዘና ሊኖር እንደሚገባ ግን ማህበሩ ዕምነት እንዳለው ነው የሚናገሩት:: በዚህም የሚፈጠሩ ችግሮችና በአንዳንድ የአስተዳደር አካላት ላይ የሚስተዋለው ያልተገባ ድርጊቶች ላይ ከአስተዳደሩ ጋር ውይይት እንዳደረጉና እየሠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ:: ችግሮቹም በአንድ ጀምበር የሚቃለሉ ሳይሆኑ ጥናትንና ሌላ አማራጭ ሥርዓት መዘርጋትን የሚጠይቅ ነው ይላሉ:: በዚህም ማህበሩ ያጠፋ ሠው ይቅርታ ጠይቆ እንዲመለስ ያለአግባብ የተባረረ ከሆነ ደግሞ አስተዳደሩ እንዲመልሰው አልመልስም ካለ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት ይወስደዋል::
በዚህ መልኩ ፍርድ ቤት የደረሱ ጉዳዮች እንዳሉም ይናገራሉ:: ይሁን እንጂ የአየር መንገዱን ገጽታ በሚያበላሽና የአገርን ጥቅም የሚጎዳ አካሄድ መኖር የለበትም:: በመሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር ችግሮችን አግዝፎ የማቅረብ ሁኔታዎች እንደሚያስተዋሉ በመግለጽ፤ ከማውራት ባሻገር ምን መፍትሔ መደረግ አለበት? በሚል መመልከት የተሻለ ይሆናል ይላሉ::
በአሠሪና ሠራተኛው መካከል መቃቃር የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ለመፍትሔው እንደሚሠራ የሚገልጹት ኢንጂነር ተሊላ፤ አየር መንገዱ ወደብ ተደርጎ የሚወሰድ የአገሪቱ ሀብት በመሆኑ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን እንደሚገባቸው ይመክራሉ:: ኢኮኖሚው ካለበት ችግር ለማዳን የሚችል ዘርፍ በመሆኑም በዚህ ላይ መሥራት ሲገባ ጣት በመቀሳሰርና በመበቃቀል ችግሮችን ለማጉላት ጥረት ማድረግ ከግለሰቦች አልፎ በአገሪቱ ላይ የሚኖረው ችግር ከፍተኛ ነው:: በመሆኑም የአገሪቱ ሕዝብ ሐብት የሆነውን ይህን ተቋም በክስ ሳይሆን የሚመለከተው አካል በቅርበት እየተነጋገረና እየተማመነ፤ አስተዳደሩም ሆነ ማህበራቱም ወደ መፍትሔ ለማምራት የበኩላቸውን ማድረግ እንደሚገባቸው መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ::
ኢሠማኮ
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ፤ ኮንፌዴሬሽኑ የኢትየጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር እንዲቋቋም ቢያደርግም አየር መንገዱ ለምን ይህንን ማህበር መቀበል እንዳልፈለገ ግን እንደማያውቁ ነው የሚናገሩት:: ‹‹ዕውቅና የሰጠሁት ለዚህኛው ነው፣ ለዚያኛው ነው›› የማለት መብት እንዳሌለውም ይገልፃሉ:: ተቋሙ ለአገር ካለው ጠቀሜታ አንፃር እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል:: ነገር ግን ሠራተኞች ሠብዓዊ መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባም መገንዘብ ተገቢ ነው:: ችግር ያለባቸው አካሄዶችም መስተካከል ይገባቸዋል ይላሉ::
አቶ አያሌው፤ በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ የዓለም የትራንስፖርት ፌዴሬሽን እንደደረሰ ይናገራሉ:: ፌዴሬሽኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ጽፏል:: ይህም አየር መንገዱን ሊጎዳ ይችላል:: ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ኮንቬንሽኖች በመኖራቸው ክሱ አደገኛ ሊሆን እንደሚችልም ስጋታቸውን ይገልፃሉ:: በማህበራቱና በአየር መንገዱ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብም የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽንና ኢሠማኮ ከተቋሙ ጋር ተነጋግሮ እንዲሁም መንግሥት ባለበት ለማደራደር ጥረት እየተደረገ ነው:: በመሆኑም ገመናውን መፍታት የሚቻል ከሆነ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሠራ ይጠቁማሉ::
አቶ አያሌው፤ ሠራተኞች ላይ እስከ የሥራ ስንብት እንዲሁም ኢሠማኮ የሚያውቃቸው ችግሮች እንዳሉ በመጠቆም እነዚህም በአለመግባባት የተከሰቱ ሊሆኑ ስለሚችል መፈተሽ እንደሚያፈልግ ይገልፃሉ:: በዚህም ሠራተኞች እንዲሁም አስተዳደሩ በጋራ ለድርጅቱ የሚያስቡበት መንገድ መፈለግ፣ ማስተካከያ የሚሹ ጉዳዮች እንዲስተካከሉ ማድረግ ላይ፣ ሁለቱ ማህበራት ወደ አንድ ሊመጡ የሚችሉበትን መንገድና በድርጅቱና በሠራተኞች መካከል ያሉ አለመግባባቶች ሊፈቱ የሚችሉበት መፍትሔዎች ላይ አቅጣጫ ቀይሷል:: በዚህም ሠላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት እንዲኖር በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል::
ፌዴሬሽኑ
የትራንስፖርትና መገናኛ ኢንዱስትሪ ማህበራት ፌዴሬሽን በጉዳዩ ላይ መረጃ ለመስጠት ቢስማሙና ቃል ቢገቡም በተደጋጋሚ ግን መሸሽን መርጠዋል:: በዚህ የተነሳ ልናካትታቸው አልቻልንም::
አየር መንገዱ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከሰሞኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው አስተያየትና ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ አየር መንገዱ ለስኬታማነቱ ትልቁ ምስጢሩ ሥነምግባር እንደሆነ ገልፀው ነበር:: ተቋሙ ከሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት ጀምሮ ጥብቅ ሥነምግባር ነው የሚመራው:: ነገር ግን በአገሪቱ ካለው የሥራ ባህል አንፃር ይህ የማይዋጥላቸውና ምቾት የሚነሳቸው ሠራተኞች አሉ:: እርሳቸው ከ35 ዓመት በፊት በአየር መንገዱ ሥራ ሲጀምሩ የበላይ ኃላፊዎቻቸው በዚሁ ጥብቅ ሥነምግባር ውስጥ እንዳሳለፏቸውና ትክክልም እንደሆነ ያምናሉ::
አራት መቶ መንገደኞችን ይዞ ከባህር ወለል 40 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ የሚበር አውሮፕላን የሚጠግን ቴክኒሺያን ትንሿ ስህተት ሕይወት ልታስከፍል ስለምትችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠበቅበታል:: በመሆኑም እያንዳንዱ አቋሙ የሥራ ቦታው ላይ ተፅዕኖ ስላለው በዚህ ልክ በትኩረት ነው የሚሠራው:: በዚህ ደረጃ ሕጉን ለማስፈፀም ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ቅሬታዎች ይበዛሉ:: ነገር ግን አየር መንገዱ ከቅጥር ጀምሮ እስከ ስንብት፣ ዕድገት ዝውውር ሁሉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሠው ሀብት አስተዳደር አለው:: ሒደቱም በገለልተኛ ወገን እየተገመገመ ይሄዳል:: በአገሪቱ የይቅርታ ፖሊሲ ያለው አየር መንገዱ ብቻ እንደሆነም አቶ ተወልደ ይገልፃሉ:: በዚህም ሠራተኛው ከሥራ እስከመሰናበት የሚያደርስ ስህተት ሠርቶ ስድስት ወር ቆይቶ ‹‹አጥፍቻለሁ ይቅርታ ይደረግልኝ›› በሚልበት ወቅት ጉዳዩ ፍርድ ቤት ሳያመራ ድርጅቱ ይቅርታ አድርጎለት እንዲመለስ ይደረጋል::
ከሥራ እንዲሰናበት አሠሪው ጥፋቱ ከሥራ የሚያሰናብት ነው ብሎ ሲወስንበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩ ይታያል:: በዚህም መሰናበቱን ከወሰነ ለዋና ሥራ አስፈፃሚ የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል:: ጠንካራ የቅሬታ አፈታት ሥርዓት እንዳለም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ይናገራሉ:: ነገር ግን የማህበራዊ ድረገጽ ለሁሉም ዕድል ስለሚሰጥ በዚህ ቅር የተሰኙ ሠዎች ሐሳባቸውን ሲያወጡ ይስተዋላል:: በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹የሠራተኛ ደመወዝ በድርድር ሳይሆን በፈቃደኝነት የሚጨምር፣ ከሥራ ወደ መሥሪያ ቤትና ከመሥሪያ ቦታ ወደ መኖሪያ ቤት ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎት ያለው፣ ሽሮ በስድስት ብር የሚበላበት ድርጅት፣ የመኖሪያ ቤት ገንብቶ ለሠራተኞቹ የሠጠና መሰል ጥቅማ ጥቅሞችን የሚሰጥ በመሆኑ ሠራተኛ በአጠቃላይ ደስተኛ መሆኑን ያረጋግጣሉ::
ፍትሐዊ ዕድገት እንዲኖርም ለእያንዳንዱ የሥራ ኃላፊነት ቦታ ላይ ከታች ጀምሮ ዕጩዎች እየተቀመጡ የማብቃት ሥራ ይሠራል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ ብዝሃነት የጠበቀ ከመሆን ጋር ተይያዞ የሚነሱ ሃሳቦች ላይ አቶ ተወልደ እንደሚናገሩት፤ አየር መንገዱ ከአገሪቱ አልፎ ብዝሃነትን ዓለም አቀፍ በሆነ መልኩ ይመለከተዋል:: በዚህም የተለያየ አገር ዜግነት ያላቸው ዜጎች በተቋሙ ተቀጥረው ይሠራሉ:: ነገር ግን ኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዝሃነቱን ሊላበስ እንደሚገባ ስለሚታመን ሙያን ከብዝሃነቱ ጋር አያይዞ ይሠራል:: እንዴት ይጣጣሙ? የሚለው ግን ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይም እንደሆነ መዘንጋት የለበትም::
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ‹‹አየር መንገዱ የእኔ ነው›› እንዲል ውክልና ያስፈልጋል:: ነገር ግን ደግሞ ሙያ በኮታ ስለማይሆን በትኩረት መሥራት ይገባል:: በሂደቱም ብቃትን በቅድሚያ ያያል:: ባለሙያው ማሟላት ያለበትን መስፈርት ማሟላት ይጠበቅበታል:: በዚህ ውስጥ ለሥራው እኩል ዕድል እንዲያገኝም ሁኔታዎች የተመቻቹ ሲሆን፤ አየር መንገዱ በአካሄዱ ላይ ጽኑ ዕምነት አለው:: የብዝሃነት ማሳያ በሆኑት በከፍተኛ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እየመለመለ ነው:: ታዳጊ ክልሎች ላይም ቀርበው እንዲሠሩ ይጋብዛል::
አየር መንገዱ ላይ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች የሚጽፉ አካላት ተቋሙን ፖለቲካ ውስጥ ለመክተት ፍላጎት ቢኖራውም ድርጅቱ ግን በምንም መልኩ ፖለቲካ ውስጥ አይገባም:: ሠራተኞች በተቋሙ ለረጅም ዓመት የሚቆዩትም አየር መንገዱ ለአገሪቱ ወሳኝ በመሆኑና በቁጭት ለማሳደግ ካላቸው ተነሳሽት እንደሆነ አቶ ተወልደ ይናገራሉ::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሠው ሀብት ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ መሳይ ሽፈራው በአየር መንገዱ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ ሁለት ማህበራት መመስረታቸውን ይናገራሉ:: በምርጫ ሂደቱ ላይ በነበረ አለመግባባት አዲስ ማህበር ተቋቁሟል:: አዲሱ ማህበር ቅሬታዎች ነበሩት:: በዚህም በግንዛቤ ክፍተት ‹‹አስተዳደሩ ለነባሩ ማህበር ይደግፋል›› የሚል አስተያየት ነበረው:: አስተዳደሩ ደግሞ ከሁለቱም ጋር አብሮ ለመሥራት ፈቃደኛ እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቷል:: ነገር ግን ቅሬታው ሊፈታ ባለመቻሉ በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጉዳዩ እንደገና እንዲታይና ማህበራቱ ተነጋግረው ችግሩ ተፈትቶ አንድ ማህበር ሆነው የሚቀጥሉበት፣ ሁለትም ከሆኑ ህልውናቸውን ጠብቀው የሚሄዱበትን አግባብ እያነጋገሯቸው ነው:: ጉዳዩ መፍትሔ አግኝቶ ሠራተኛው ለድርጅቱ ድርጅቱም ለሠራተኛው እጅና ጓንት ሆነው ድርጅቱን የሚያሳድጉበት መንገድ እንዲቀጥል የአስተዳደሩም ፍላጎት ነው:: ካለፈው ችግር ተምሮ ከዚህ በኋላ በምን ዓይነት መንገድ ጠንካራ ማህበርና ተቋም ተፈጥሮ ሠራተኛውን ተጠቃሚ አድርጎ የሚሄድበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ያላቸውን ዕምነት ይናገራሉ:: በቅርቡም ውይይት እየተደረገ በመሆኑ በቅርቡ ችግሩ መፍትሔ እንደሚያገኝ ይጠበቃል ይላሉ::
ነባሩ ማህበር 58 ዓመት ስላስቆጠረ እስከ 10ኛ ሕብረት ሥምምነት ተደርጓል:: አዲሱ ማህበር ደግሞ ‹‹ለዛኛው ማህበር የሚደረገው ድጋፍ አይደረግልንም›› የሚል ነው:: ነገር ግን ድርጅቱ ያንን የመከልከል ሥልጣንም የለውም:: ተቋሙ ከየትኛው ማህበር ጋር ይሠራል የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ግን በሕግ ማዕቀፍ ነው:: ማህበሩን የሚወክሉትም ሠራተኞች በመሆናቸው አስተዳደሩ የሚከለክለው አልያም የሚፈቅደው፤ አንዱ የሚጠጋበት ሌላኛው የሚርቅበት ሁኔታም የለም::
ለግርታዎቹ መፈጠር ምክንያት አካሄድ አለመረዳትና ተቋሙም ሁለት ማህበር ይዞ የመጓዝ ልምድ አለመኖር እንደሆነ አቶ መሳይ ያብራራሉ:: አስተዳደሩ ጋር ችግር እንኳ ቢስተዋል እንኳ ወደ ብዙሃን መገናኛ መሄድ ሳይሆን ወደሚመለከታቸው አካላት በማቅናት በቅርበት መፍትሔ ሊደረግ የሚችልበትን ሁኔታ መፈለግ ነበር በማለት ይናገራሉ:: አየር መንገዱ የመናገር ነፃነትን ባፈነ መልኩ ሠራተኞች ላይ ጫና ስለሚያሳድር በርካቶች ዝምታን ይመርጣሉ ለሚለው ቅሬታ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ምላሽ ሲሰጡ፤ ከሕግ በላይ ማንም ባለመኖሩ ይህን መሰል ችግር እንኳ ካለ በአግባቡ ተነጋግሮ መፍታት እንዲሁም ሕጋዊ ሥርዓትን በተከተለ ሁኔታ እንጂ ብዙሃን መገናኛ ጋር በመሄድ ሊሆን አይገባም ይላሉ:: ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ቅሬታ አቅራቢዎቹ አሉ በሚሏቸው ችግሮች ዙሪያ ከተቋሙ ጋር በቅርበት ለመፍታት አማራጮች በሙሉ አሟጥጠው መጠቀም መሆን ነበረበት ባይ ናቸው::
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ‹‹ይገፉናል ይጨቁኑናል ከማለታቸው በፊት አካሄዱን ያውቁታል ወይ? ማህበር ማለትስ ምን ማለት ነው? የሚለውንስ ያውቃሉ ወይ? በሚል መታየት አለበት:: የሠራተኖች የሥራ ስንብትም በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ አይደለም:: ይልቁንም ማንም ሠው ዕውነትነት በሌለው ጉዳይ ድርጅቱንም ሆነ አስተዳደሩን መወነጃጀል እንዲቆም ማሳሰቢያ አውጥተናል:: ይህንን ማሳሰቢ ተከትሎ ተግባራዊ ካልተደረገ ግን የኢንዱስትሪ ሠላሙን የሚያናጋ በመሆኑ ይህንን ተላልፎ በተገኘ ሠራተኛ ላይ ዕርምጃ ይሰወዳል›› ይላሉ:: በዚህ ሒደት ያለው መመሪያና አካሄድ የማያሠራ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ውስጥ ሆኖ አሠራር የመቀየር የእያንዳንዱ ሠራተኛ ኃላፊነት ነው:: ከዚህ ውጪ ግን የድርጅቱን አሠራር በጣሰ መንገድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሕጋዊ አያደርጉም::
ማሳሰቢያውን ተላልፈው በተገኙ የተወሰኑ ሠራተኞች ተግሳጽና እስከ መባረር የደረሱ እንዳሉ የሚያስታውሱት አቶ መሳይ፤ ዕርምጃው አስተዳደር አካላትን ዘልፈዋል በሚል እንዳልሆነም ያረጋግጣሉ:: ጥፋት አጥፍቷል የተባለ ሠራተኛንም አንድ የአስተዳደር አካል ብቻውን አያባርርም:: ከተለያየ አካላት የተውጣጣ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አለ:: በዚህ ለይ የዕምነት ክህደት ቃሉን ይሰጣል::
በአንድ ተቋም ውስጥ አስተዳደራዊ ዕርምጃ በማንኛውም ወቅት ሊወሰድ የሚችል መሆኑን መገንዘብም ይገባል:: ይህ ደግሞ ሥርዓትን ለማስጠበቅ እንጂ ሠራተኞችን ለማሸማቀቅ አይደለም:: ተባረሩ የሚባሉ ሠራተኞች ደግሞ በጥፋታቸው ተፀጽተው ይቅርታ አቅርበው ወደ ሥራ ገበታቸው እየተመለሱ ነው:: በመሆኑም ቅጣት እንደ ማስተማሪያ እንጂ አጠቃላይ የሠራተኖችን የመናገር ነፃነት የሚያፍን አይደለም:: ነገር ግን ማንንም ሠው የመዝለፍ ወይንም ደግሞ የሐሰት ወሬዎችን የመንዛት አካሄዶችን ድርጅቱ አይፈቅድም:: በድርጅቱ የተወሰዱ ዕርምጃዎችም የአገሪቱን አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፎችን በተፃረረ መልኩ የተወሰዱ አይደሉም:: ለዚህም ደግሞ ተጠያቂ የሚደረግ ካለ በሕግ ሊጠየቅ ይችላል::
አየር መንገዱ የተቋሙ ሠራተኞች ከአገር ውጪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው እንዳይሠሩ የሚይዘው ፓስፖርት እንደሌለ የሚናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ድርጅቱ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ለቅሞ እያስተማረ እንደሆነ ይገልፃሉ:: በዚህም ባለው አቅም ትልቅ መዋዕለ ነዋዩን በሠው ሀብት ላይ እያፈሰሰ ነው:: መሠረተ ልማቶችንና አየር መንገዱን ለማሳደግ የሚሠራቸው ሥራዎች ትልልቅ ብድሮችን ተበድሮ ነው:: በአሁኑ ወቅት ያሉት ሠዎች የድርጅቱ አባላት እንጂ ብቸኛ ባለቤት አይደሉም:: ብቸኛ ባለቤት የሚሆነው ሕዝቡ ነው::
የሕዝብ ገንዘብ ወጥቶባቸው ራሳቸውን ብቻ አውጥተው ለመቀጠር የመፈለግ ዝንባሌዎች ደግሞ ውይይትን ይፈልጋሉ:: የትምህርት ማስረጃና መልቀቂያ ለመስጠትም ለወጣበት ወጪ ሊመልስ ይገባዋል:: ግዴታውን ካጠናቀቀ በኋላ ግን ይሰጠዋል:: ቴክኒሺያንና አብራሪዎች ጋር ተያይዞ ተከታታይ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ አቶ መሳይ ለአብነት ያነሳሉ:: እነዚህ ባለሙያዎች የሚማሩት በሕዝብ ገንዘብ ነው:: የተሰጠው ትምህርትና ሥልጠና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ ስለሆነ አየር መንገዱ ይልቀቀን ከተባለ ከመጀመሪያው ወይ ከፍሎ መማር እንጂ በሕዝብ ገንዘብ ተምሮ ማገልገል የሚገባውን ሳያገለግል የሚደረጉ ሩጫዎች የሚያደርሱት ኪሳራ መታየት ያለባቸው በአገር ደረጃ ነው::
አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም አስተምሮ ይቀጥራል:: ለተማሩበትም በሥራ ይከፍላሉ:: በበረራ አስተናጋጅና መሰል ሙያዎች ግን በቂ የተማረ ኃይል ስላለ አዲስ ማስተማር አይጠበቅበትም:: ጉድለት ባለበት ያስተምራል:: በዚህ ሂደት ውስጥ ትምህርት ቤቱ ባዶ ስለሆነ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ከፍለው እየተማሩ ነው:: ከዚህ በኋላ ሲያስተምርም ከግዴታ ጋር ይሆናል:: ይህ ሲሆን ግን እንደ ሌላው ዓለም ለትምህርት የሚያበድሩ የፋይናንስ ተቋማት ስላሌሉ እንዴት ይደረግ በሚለው ሐሳብ ላይ እየመከረ ነው:: በዚህም መክፈል ለማይችሉት ሥራ ሲይዙ ከደመወዛቸው ተቆራጭ የሚደረግበት አግባብ እየተፈተሸ ነው:: አቶ መሳይ፤ አትራፊ ድርጅት ሆኖ ሲወጣም እንደማንኛውም ኮሌጆች አስከፍሎ ያስተምራል:: ይህም በአየር መንገዱ ብቻ የተጀመረ ሳይሆን በሌሎች ተቋማት የሚደረግም ነው ይላሉ:: በዚህ ደረጃ አየር መንገዱ ያስተማረው ሠራተኛ ራሱን ሲችል ለቅቆ ለመሄድ ፍላጎት ሲያሳይ በማን ገንዘብ ማን ይወስናል የሚል ጥያቄን ያጭራል:: ስለዚህ ሁኔታውን በሚዛኑ መመልከት ይገባል::
ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የምዘና ሥርዓቱ ላይ ከሕመምና ከወሊድ ጋር ተያይዞ በተነሱት ቅሬታዎች ላይ ምላሽ ሲሰጡ፤ አየር መንገዱን የሚያክል ግዙፍ ድርጅት ያለምዘና ሥርዓት መምራት አይቻልም ይላሉ:: ተቋሙ በውድድር ውስጥ እንዳለ ሁሉ በውስጡ የሚገኙ ሠራተኞችም መወዳደር መቻል አለባቸው:: ፍትሐዊ እንዲሆን ደግሞ የሠራተኞች ተሳትፎ ታክሎበት ነው የሚሠራው:: ስለሆነም አልመዘንም ከማለት ይልቅ የሚጠበቅበትን ማዋጣት የሠራተኛው ድርሻ ነው:: ምዘና በሚደረግበት ወቅት ደግሞ ግለሰባዊ እንዳይሆን ወይም በዚህ ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ይሠራል:: በምዘና አፈፃፀሙ ዝቅ ያሉ ሠራተኞች ደግሞ ያሉበት ደረጃ ታውቆ ክፍተታቸውን የሚሞሉ ሥራዎች ይሠራሉ:: በዚህም ተከታታይነት ባለው መልኩ ሠራተኛውን ለማብቃት ድክመት አለበት ተብሎ የተለየው ሠራተኛ ከድርጅቱ ጋር ተፈራርሞ የተሻለ ሠራተኛ ለመሆን ይሠራል:: በዚህም ተቋሙ ግቡን ለመምታትና ውጤታማ ለመሆን ይረዳዋል::
ከሕመም ፍቃድና ከወሊድ ጋር ተያይዞ የተነሳው ቅሬታ ደግሞ ደመወዝም ሆነ የሕክምና ጥቅም ሳይነካባቸው በሕጉ መሠረት ፈቃድ ይወስዳሉ:: በዓመቱ መጨረሻ የሚከፈለው ጉርሻ ግን ሕግ አለው:: በድርጅት ውስጥ በስድስት ወር ከሠራ ግማሽ፣ ዘጠኝ ወር በላይ ከሠራ ደግሞ ሙሉ ጉርሻ ያገኛል:: የሚበረታታው ደግሞ የሠራና በየደረጃው ውጤታማ ሆኖ ድርጅቱን ለተሻለ ትርፋማነት ማብቃት የቻለ ሠራተኛ ነው:: 20 በመቶ ውስጥ የገቡትም ሆነ 70 ውስጥ የገቡት ጉርሻ መጠኑ ቢለያይም ማበረታቻ ግን ያገኛሉ:: በሥራው ውስጥ ችግሮች አይፈጠሩም፣ የተዋጣለት ነው ለማለት የማያስችሉ ሁኔታዎች ሊስተዋሉ ይችላሉ:: ነገር ግን አማራጩ ዳር ሆኖ መመልከት ሳይሆን ክፍተት ካለ ለመሙላት ጥረት ማድረግ መሆኑን በመግለጽ ሁሉም ሠራተኛ በባለቤትነት መንፈስ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው ያሳስባሉ::
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012
ፍዮሪ ተወልደ