በኢትዮጵያ የመጣውን ሁለንተናዊ ለውጥ ተከትሎ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የዜጎች መብት ነው። በተለይ በውጭ አገራት የሚኖሩ ዜጎች በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚደርስባቸውን በደልና እግልት ለማስቀረትና ችግራቸውንም በቅርበት ተከታትሎ ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ።
በዚህ እሳቤም የኢትዮጵያ ኤንባሲዎችና ቆንፂላ ፅሕፈት ቤቶች ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ በጎረቤት አገሮችና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ዜጎች መብታቸው ተከብሮ ህጋዊ በሆነ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ የሚያግዝ ነው። የተለያየ ችግርም አጋጥሟቸው ከሆነ ክብራቸው በተጠበቀ መልኩ ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታን ለማመቻቸትም ትልቅ ሚና ያለው ነው።
ይህንን ተከትሎም ወደ አገር ቤት የሚመለሱ ዜጎች ቁጥር ከእለት እለት እየጨመረ መሄዱን መረጃዎች ያሳያሉ። ስለሆነም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ውስጥ ይህ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አንድ ራሱን ችሎ የተቀመጠ አቅጣጫ ነው። ፖሊሲው ከዜጎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት መንገድ ይከፍታል።
ሌላው አፅንዖት የተሰጠው ጉዳይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ነው። ከጎረቤት አገሮች ጋር እየተፈጠረ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ እየተገነባ ይገኛል። ለዚህም አገራቱን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የሚደረጉ ጥረቶች ማሳያ ናቸው።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ያላት አገር እንደመሆኗ ከጎረቤት አገሮች ጋር ብቻ ሳይሆን ሰፊ የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴን የምታደርገው በተለያዩ አጋጣሚዎች ባልተቀናጀ መልኩም ቢሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች አሉ። ያንን ግን በታቀደ እና በተደራጀ መልኩ እንዲሁም በውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ውስጥ ተገቢው ስፍራ ተሰጥቶት እንዲቀመጥ ማድረግ ያስፈልጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ለተለያዩ ጉዳዮች በሄዱባቸው አገራትም ለዜጎቻቸው ልዩ ትኩረት በመስጠት ለከፊሉ ባሉበት ቦታ የተሻለ እድል እንዲያገኙ ከመንግስታቱ ጋር በመደራደር ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ ለችግር የተጋለጡትን ደግሞ እሳቸው በተመለሱበት አውሮፕላን ጭምር ይዘው በመመለስ ለዜጎች ያላቸውን ክብር አሳይተዋል።
ሰሞኑንም ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በደቡብ አፍሪካ ለቀናት ቆይታ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጆሐንስበርግ ከተማ” ኢምፔሪያል ዎንደረርስ ክሪኬት” ስታዲየም ለተገኙት ኢትዮጵያውያን ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም ልዩ ትኩረት ከሰጧቸው ነገሮች መካከል አንዱ የዜጎች ጉዳይ ነው። በዚህም ከሀገሪቱ መሪ ጋር በመነጋገር ኢትዮጵያውያን መብታቸው እንዲጠበቅና በሰላም እንዲኖሩ የሚያስችል ፍሬያማ ድርድር መደረጉን ገልጸዋል።
ሌላው የዜጋ ዲፕሎማሲ ማሳያ የሆነውና ጠቅላይ ሚኒስትሩም በንግግራቸው ያካተቱት ከአገሪቱ ጋር የነበረው ረዘም ያለና የጭንቅ ቀን ደራሽ የመሆን ታሪካዊ ግንኙነት ነው። ‹‹ኢትዮጵያ ለማዲባ በጭንቁ ዘመን ፓስፖርት ሰጥታ የትግል አጋር እንደሆነችው ሁሉ ዛሬ ደቡብ አፍሪካን ቤታችን ብለው የሚሠሩ፣ የሚተጉ ኢትዮጵያውያን ተከብረው እንዲኖሩ ሕጋዊ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ያቀረብነው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል›› ሲሉ ይፋ ማድረጋቸውን ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረትና የተገኘውን ተቀባይነት አመላካች ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ተጠናክሮ ሊቀጥልና ይገባዋል።
ዜጎች እራሳቸውን አሸንፈው ለወገን ለመትረፍ በዓለም ላይ ሁሉ ተበትነው ይታትራሉ፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከምንኮራበት እኛነታችን ግንባር ቀደሙ ነው። ይህ አኩሪና የእኛነታችን መገለጫ የሆነውን የስራ ባህላችንን እኛም እየጠበቅን መንግስታችንም ለዜጎቹ ክብርና ነጻነት ቀናኢ ሆኖ መታየቱ በእውነትም የሚያስመሰግን በመሆኑ እውቅና ሊቸረው ብሎም ይበል፣ ይጠንክር ሊባል የሚገባው ነው።
ይህን የመሪውን ለዜጎቹ ተቆርቋሪነት ወይም ዜጋ ተኮር ሁኔታ የተመለከቱት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪየል ራማፎሳ በውጭ ጉዳያቸው የሚመራ ኮሚቴ አቋቁመው የኢትዮጵያን ዳያስፖራዎች ጉዳይ በተለየ መንገድ በማየት ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስዱ ቃልም ገብተዋ። ይህ ለዜጋ ዲፕሎማሲያችን ስኬታማነት ማሳያውም በመሆኑ በቀጣይ በሌሎች አገራት ያሉ ዜጎቻችንንም መብትና ደህንነት በማስጠበቅ ሊደገም ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 6/2012