ስልጣን ምንድነው? ስልጣን ነዋ! እንዴት አይነት ጥያቄ ነው? ስልጣን ምንድነው ማለቴ ድሮ አንድ ሰው ስልጣን አገኘ ከተባለ በቃ የሚኮራው እሱ ብቻ አይደለም፤ ቤተሰቡ፣ ዘመድ አዝማድ ጓደኛም አካባቢው ሁሉ ነው። እከሌን እከሊትን አውቃታለሁ/አውቀዋለሁ/ ባዩ ይበዛል። ከዛማ የቅርብ የተባለው ሰው ሁሉ አማላጅ ነው፤ መፍትሄ ፈላጊና አፈላላጊም ነው። የባለስልጣን ልጆች፣ ቤተሰቦቹ ሁሉ ሳይቀሩ የባለስልጣን ልጆች ተብለው ይከበራሉ፤ ይሄ ብቻም አይደለም፤ ይፈራሉም። አፋሽ አጎንባሽ ሁሉ ይበዛል። ለከፋ ምናምን አይታሰብም፤ ጓደኝነቱም ትንሽ ከበድ ይላል፤ አላፊ አግዳሚ ሁሉ ኮቴውን ሰብሰብ ነው።
ባለስልጣን ከሆንክ የሚኖርህን ቤት አስበው ማለቴ የግል ቤት ቢኖርህም የተንጣለለ የመኖሪያ ቤት መርጠህ አማርጠህ ይሰጥሀል። ጸጥ ረጭ ያለ ግቢ፤ ይሄ ለባለስልጣን የሚሰጠው ቤት፣ መኪና፣ ጥበቃ ጭምር ከስልጣናቸው ጋር ተያይዞ የሚኖር ጥቅማ ጥቅም ነው። ለደህንነታቸው ጭምር ጥበቃ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸውም ነው።… ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመደብ መኪና ደግሞ ለሚስት፣ ለልጆች፣ ወጣ ብሎ ለመዝናኛ ብቻ ምቾቱ ይበዛል። የተባረከ የሆነ ወይም ምናምንቴ የሚተርፈው ሹፌር ከሆነ ደግሞ የገበያ ስፍራው፣ በየዘመዳ ዘመዱ፣ በየሆስፒታሉ … ሁሉ ፈጥነህ ይባላል፡፡ እሱም የመንግሥት ሰራተኛ መሆኑን እስኪረሳው ወይም ይሄም ቀን ያልፋል እያለ ብቻ ሁሉን በሆዱ አድርጎ ታዛዥነቱን ይቀጥላል።
ይሄ ሁሉ የሚደረገው ምቾት ተስምቶት ሀገሩንና ህዝቡን በታማኝነት፣ በብቃት፣ በትጋት እና በቅንነት እንዲያገለግል ይመስለኛል። ግን ግን በዚህ ልክ ሲያገለግሉን ነበር እንዴ? አሁንስ እያገለገሉን ነው? ማለቴ እያገለገልን ነው? ምላሹ ይቆየኝ። እኔ የምለው ባለስልጣን መሆን የሌለ አመል ያስወጣል? አንዳንዶች እኮ ከወንበሩ ነው የሚያሰኝ ቀድሞ ያልነበራቸውን መጥፎ ድርጊት ይፈፅማሉ፤ እንዲፈጸም ያደርጋሉ። ቀድሞ በስነምግባራቸው እናውቃቸዋለን የምንላቸው ሁሉ አሁን በሙስና ተጠርጥረው ለህግ ተጠያቂነት ስማቸው ሲጠራ ድንግጥ ያስብላል፤ ኧረ እንዳውም ይሄ ነገር ሳይነኩት ይነካል እንዴ! ያስብላል፤ ማለቴ በሌለንበት ስማችን የሚጠራ ያክል ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል።
መቼም የእኛ ጉድ ልበል የእኛ ጉድ ማለቂያ የለውም። የሜቴክን ዝርፊያ እና የኃላፊዎቹን ድፍረት ስንሰማ አቤት …አቤት አልን። አንዳንዶች ለምን ተነገረ? ለምን ይጠየቁ ተባለ፣ ይሄ የብሄር ጥቃት ነው ብቻ የመሰላቸውን ሁሉ አሉ፣ ተንጫጩ ልበል በጓዳ፣ በአዳራሽ ብቻም ሳይሆን በአደባባይ፣ በሰልፍ አይነኩ ሲሉ ተደመጡ። ይሄን ያሉ ወገን ነን ባዮች ግን የሌላው ብሄር አብሮ ተጠያቂ እንደሚሆን ቢገለጽላቸውም ማለቴ ሌባ እናዋጣ ሳይሆን የሰረቀ ሌባ በየትኛውም ብሄር ካለ እንደማይቀርለት ተወተወተ። አንዳንዶችም በሰሩት የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ በሌብነት ጭምር ተጠርጥረው ተያዙ። አሁንም ግን ጉምጉምታው ቀጥሏል። የብሄር ጥቃት ነው የሚለው። ሌላም ሌላም ካለ ይጨመርበት። እኔ ይሄን ያክል አነሳሁ ።
ህግ ግን ብሄር፣ ጎሳ፣ ባለስልጣን፣ ታጋይ… ምናምን አልልም ብሎ ስራውን ቀጥሏል። ሰሞኑን ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አደመጥን። ቁጥራቸው 79 መድረሱ ዜና ላይ መስማቴን አስታውሳለሁ፤ የቁጥር ስህተት ከፈጸምኩ ግን አፉ በሉኝ። ይሄም የብሄር ጥቃት ይሆን? ብቻ ምን ሊባል እንደሚችል ባላውቅም አሁንም ግን መንግስት ተጠያቂዎችን ከጥጡ መሀል ጥጥ ፍሬ የማውጣት ያህል በጥንቃቄና ጥበብ በተሞላበት መልኩ የማድረጉን ሂደት እንደሚቀጥል ቁርጠኝነቱን እያሳየ ነው። እና የእገሌ ብሄር ሳይሆን ይሄንን የፈጸመ፣ ያስፈጸመ በሚል መሆኑ ቢያዝ፤ ቁርጠኝነት ማሳየት ሳይሆን ቆርጦ ገብቶበታል ልበል ? እውነት ቆርጦ ተነስቷል። አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ነገም ሌላ ቀን ነውና የሚንጫጫልን ብሄር፣ ዘመድ አዝማድ፣ ባለስልጣን… ይኖራል (ማለቴ ከምንም ባያድን) ይኖር ይሆናል! ያድነኛል ከሚል ደፋር አስተሳሰብ ሳንገባ በጨዋነት፣ በሀቅ ሥራችንን ብንስራ፤ ኃላፊነታችን ብንወጣ «ሰርቆ ከማሰብ እጅን መሰብሰብ»ይል የለ የሀገሬ ሰው። እውነት ነው ዛሬ ስንቱ እንቅልፉን አጥቷል። በር ኳ…ኳ… ባለ ቁጥር ልቡ ታምቡር ይመታል።
ይሄን ስል ምን ታወሰኝ የሰማዩ ቤት፤ የምድሩን እንሙላ ብለን እኮ የሰማይ ቤቱንም እየዘጋን አልመሰላችሁም? ስርቆት፣ ማጭበርበር፣ ያልሰሩበትን ለማግኘት መጣር እኮ በሀይማኖትም ጸያፍ ነው። ማለቴ ሀጢያት ተብለው ከሚታወቁት መካከል አንዱ ነው። በእስልምና እንኳን የሌላን ሀብት መስረቅ ቀርቶ የራስንም ሀብት በባንክ አስቀምጦ ወለድ መብላት ሀጢያት ነው። በፍጹም ውግዝ ነው። እናም እኮ ለዚህ ነው ባንኮቻችን ከወለድ ነፃ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት። ይሄ የራስን ሀብት አስቀምጦ ባንኩ ለተጠቀመበት፣ ላገኘው ትርፍ ለአስቀማጩም ትንሽ የሚያስብበት መንገድ ነው ብለን እንውሰደው ወለድን፤ ያም ሆኖ ሙስሊሙ ይሄንን እንኳን ሀይማኖቴ አይፈቅም ብሎ አይወስድም። የሚወስድ ሊኖር እንደሚችል ግን ገምቱ ፤ ሃይማኖቱን አስተምህሮ በደንብ አውቃለሁ፣ አከብራለሁ የሚለው ግን አያደርገውም።
ወደ ክርስትና እምነት ስንመጣም የራስ ያልሆነን ሀብት መውሰድ ከሀጢያትም በላይ ሀጢያት ነው። ሰው እንኳን የራሱ ያልሆነውን ገንዘብ ሰርቆ፣ አታሎና አጭበርብሮ ቀርቶ የራሱ የሆነውን ንፁህ ሀብት እንኳን አስራት እንዲከፍል ሀይማኖቱ ያዛል። በራሱ ንጹህ ላብ ያላገኘውን ገንዘብ አስራት እንኳን ልክፈል ቢል ከሀይማኖቱ አንፃር አስራቱን በማውጣት ንፁህ አይሆንም ምክንያቱ ያ የመጀመሪያው ገንዘብ የእሱ አይደለማ። ህዝብን አስለቅሶ፣ አሳዝኖ፣ ሀገርን ዘርፎ የሰበሰበው ነው። ሌብነት ደግሞ ሀጢያት ነው በማንም እምነት፤ በማንም አእምሮ ጸያፍ ነው። እናም እላለሁ በየትኛውም መንገድ በምድርም ተደስቶ፤ በንፁህ አእምሮና ልቡና ለመኖር፤ በሰማይ ጽድቅን ለማግኘት ሌብነት ጠያፍ ነው። በምድርም በህግ ተጠያቂነት አለው።
ይሄን ስል ግን ሌብነት የብዙ ነገር ጥርቅም መሆኑ አይዘንጋ። ሌብነት አንዱ ሀሰተኛነት ነው። የመንግሥት ሪፖርት የሀሰት፣ ከጓደኛ ጋር የሚደረገው ጭውውት የሀሰት፣ በቤት ውስጥ ሳይቀር ወንድም እህት ሁሉ ጋር ይወርዳል። ከታች የጀመረው ጠቅለል ብሎ ሀገር ላይ ሲደርስ ታዲያ ጉዳቱ ገዝፎ ይሄዳል። አሁን አሁን «ከማንኛውም ሀብት ጀርባ ወንጀል አለ» የሚለው ነው ገዝፎ የሚሰማው፤ እኔ አውቅ የነበረው «ከማንኛውም ጥንካሬ፣ ውጤታማነት ጀርባ ሴት አለች» የሚለውን ነበር። አሁን አሁን ሴቶችም የወንጀሉ ተባባሪ ሆኑ እንዴ? ማለቴ ሴቶች ስል ሁሉንም ሴት እንዳልሆነ ይያዝልኝ «ጠንቃቃ ናቸው፣ ደፋር አይደሉም(ለስርቆት)፣ የቤተሰብ ኃላፊነት ይሰማቸዋል፣ ብዙም ውጪ ውጪ ማለት መዝናኛ ስፍራዎች አይውሉም» በሚል ብዙ ቦታ ረጅም ዘመን ሴቶች ለገንዘብ ያዥነት፣ ለንብረት ጠባቂነት ሲታጩ ነበር።
ንብረትና ገንዘብ ያዥነት ለሴቶች የተሰጠ ስራ እስኪመስል አሁን ድረስ የገንዘብ ያዥነት ስራው ቀጥሏል። እነሱም ኃላፊነታቸውን ከሞላ ጎደለ ሲወጡ ቆይተዋል። ጥቂቶች ባይጠፉም። አሁን የራሳቸው ያልሆነ ሀብት ወደ ቤታቸው ሲጎርፍ እንዴት ነው ያዩት ማለቴ በእኔነው ስሜት፣ ሰርተን አገኘነው ብለው እያሰቡ ነው አንዳንዶች እጃቸውን ዘው የሚያደርጉት? ቤት መኪና የገና ስጦታ ሲባሉ እውነት የተለፋበት ሀብት ውጤት እየመሰላቸው ይሆን? ወይስ ማንም አይጠየቅም!ማንም አይነካንም! ከሚል መነሻ ብቻ አንዳንድ ቦታ ላይ የሚታዩት ምነው ሴቶቻችን የነበረ ስማችንን አታስጎድፉ! በአዲሱ ፋሽን በዘመናዊ መኪና መኪናሽ ይቀየር ሲባል ምንጩ ምንድነው የሚለውን የማሰቢያ ክፍል ማስራቱን ይጀምር። ይሄ ደግሞ ነገም አንገትን ከመድፋት ዛሬም ካልተገባ ትዕቢትና ጥጋብ ያድናል። እናም እላለሁ የምንጠቀምበት፣ የምንዘንጥበት፣ የምንደሰትበት ገንዘብ በላብ በወዛችን ሰርተን ያገኘነው ይሁን፤ ይሄ ግን በአንድ ጀምበር የሚገኘው ሀብት የእኛ አይደለም። ይመለሳል፤ ሲመለስ ደግሞ ውርደትን ጨምሮ ይሆናል። ህግ ደግሞ ቢዘገይም ጊዜና ሁኔታው ሲፈቅድ ከጥጡ ፍሬውን መለየቱ የማይቀር ነው። አሁን የምናየው የህግ ተጠያቂነት የዛ ጅምር ይመስላል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011
አልማዝ አያሌው
Your blog post had me hooked from the first sentence.