ለአንድ ሀገር ብልፅግና እንደ አንድ አመላካች ተደርገው ከሚቆጠሩ ነገሮች መካከል አንዱ ትምህርት ነው:: የሃገራት የኢኮኖሚ ደረጃም የሚለካው ባላቸው የተማረ የሰው ኃይል ልክ ነው:: ለዚህም ነው ‹‹ለአንድ ሀገር እድገት መሰረቱ ትምህርት ነው›› የሚባለው::
ለትምህርት ትኩረት ሰጥተው የሰሩ ሀገራት አሁን ለደረሱበት የኢኮኖሚ እድገት ትምህርት ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቶላቸዋል:: በሰዎች አእምሮ ላይ በርካታ መዋእለ ነዋይ ማፍሰስ በመቻላቸውም በርካታ ምርምሮችን በማካሄድ ከውጤት ላይ ደርሰዋል:: ይህም ከዛሬ አልፎ ለቀጣዩ ትውልዳቸው ሊተርፍ የሚችል ነገር ማቆየት እንዳለባቸው ግንዛቤ እንዲውስዱ አስችሏቸዋል::
አሜሪካን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይናና ሩሲያን የመሳሰሉ የዓለማችን ሃያላን ሀገራት ከታች ጀምሮ ለትምህርት ትልቅ ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው ኢኮኖሚያቸውን ማዳበር ችለዋል:: በተለይም አሜሪካውያን በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ሊህቃንን አድነው በመሰብሰብ የዓለማችን የኢኮኖሚ ቁንጮ ለመሆን በቅተዋል:: በአሁኑ ወቅት ደግሞ ቻይና በተለይ ህፃናትና ታዳጊዎች በራሳቸው ቋንቋ ትምህርትን በጥራት እንዲቀስሙ በማድረግና ከፍ ሲሉም የከፍተኛ ትምህርታቸውን ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ እንዲማሩ በማድረጓ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአሜሪካ ባልተናነሰ መልኩ ኢኮኖሚዋን ማፈርጠም ችላለች፤ ዓለም አቀፍ ተፅእኖዋም እያየለ መጥቷል::
ቻይና ልክ እንደ አሜሪካን ሁሉ ለትምህርት ሰፊ ትኩረት በመስጠቷ በቴክኖሎጂ፣ ንግድ፣ በግንባታና በሌሎችም ዘርፎች በስፋት ተሳትፎ በማድረግ ከራሷ አልፋ በሌሎች ሀገራትም ጭምር አሻራዋን ለማሳረፍ በቅታለች:: በአሁኑ ወቅትም ሃያሏን አሜሪካ በሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ መስክ ከሚፈተኑ የዓለማችን ሀገራት ውስጥ ግንባር ቀደም ለመሆን ችላለች::
የትምህርት አሰጣጥ ስነ ዘዴ ከሀገር ሀገር ቢለያይም የሚያግባባው እውነት ግን በተለይ ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠት በዋናነትም በህፃናትና ታዳጊዎች ላይ መስራት ለሀገራት ኢኮኖሚ እድገት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል:: ይህን አካሄድ የተከተሉ ሀገራትም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መትረፍ ችለዋል:: እንዲያውም አንዳንዶቹ የሀገራቸው ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ያለቀ ይመስል ጥቅማቸው እንዳለ ሆኖ የሌላውን ሀገር እድገት በምን መልኩ ማሻሻል እንዳለባቸው ማስላት ከጀመሩ ሰነባብተዋል:: በተለይ ቻይና ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ አፍሪካ የራሷ ቤት እስኪመስላት ድረስ በልዩ ልዩ መስኮች በመሰማራት የራሷን ኢኮኖሚ በሚገባ እየገነባች ትገኛለች:: ኢትዮጵያም የቻይናውያን አሻራ ካረፈባቸው የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ከግንባር ቀደም ጎራዎች ውስጥ ተሰልፋለች:: ህንድ፣ቱርክና ሌሎችም ሀገራት ቻይናን በመከተል በኢትዮጵያ ልማት ላይ እጃቸውን አሳርፈዋል::
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ግን ቻይናን ጨምሮ የሌሎችም ሀገራት ኢትዮጵያን የማልማት ተፅእኖ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከፍ እያለ መምጣቱ ነው:: ኢትዮጵያን የማልማቱ ጉዳይ ክፋት ያለው ባይሆንም ለተፅእኖው መበርታት ግን በኛ በኩል አንዳች ክፍተት መኖሩን ያሳያል:: በተለይም ትምህርት ላይ በሚገባ በመስራት በእውቀት የዳበረ የሰው ኃይል በጥራትና በብዛት በማፍራት በልዩ ልዩ መስኮች ላይ በማስማራት ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ ቀሪ የቤት ስራዎች እንዳሉ ይጠቁማል::
ኢትዮጵያ ልክ እንደሌሎቹ ሀገራት ሁሉ ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥቼ እየሰራሁ ነው ብትልም ትምህርትን ከማዳረስ በዘለለ ለጥራት አሁንም በቂ ትኩረት የሰጠች አትመስልም:: ብዙ ግዜ ‹‹ለትምህርት ሽፋንና ጥራት አበክረን እየሰራን ነው›› የሚሉ ስብከቶች በተደጋጋሚ ከመንግስት በኩል ቢደመጡም፣ በተለይ ታች ያሉ ህፃናት ትምህርትን በጥራት ተከታትለውና መሰረት ጥለው ወደከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ሲደርሱ የሚፈለገውን እውቀት በመያዝ ለሃገራቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበርከቱ የሚደረገው ጥረት ደካማ ነው::
በዋናነትም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለህፃናትና ታዳጊዎች ጥራት ያለው ትምህርት በተሟላ መልኩ እየተሰጠ ባለመሆኑ ህፃናትና ታዳጊዎቹ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ሲጀምሩ ትምህርቱ ከብዷቸው የማይወጡት አቀበት ይሆንባቸዋል:: በዚህም ደካማ ውጤት ለማስመዝገብ ይገደዳሉ:: ጥራት ያለው የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት የሃሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚደረገው ጥረትም ጥያቄ ውስጥ ይገባል:: ሁሉም ባይሆኑ ከመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ መምህራንም የሚፈለገውን ያህል እውቀት ይዘው ወደ ስራው ዓለም ስለማይቀላቀሉ ለተማሪዎቻቸው ተገቢውን እውቀት አያስተላልፉም::
እዚህ ጋር ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ጥቂት የማይባሉ መምህራን የሚከፈላቸው ክፍያና በመንግስት በኩል የሚደረግላቸውም ድጋፍ አነስተኛ ቢሆንም ዛሬም በእውቀትና በስነ ምግባር የበቃ ትውልድ ለማፍራት ይጣጣራሉ:: ቀጣዩን ትውልድ ለማዳን ሲሉ ተስፋ ባለመቁረጥ ለሚወዱት ሙያ ሲሉ መስዋትነት እየከፈሉ ይገኛሉ:: ይሁንና መንግስት ለታችኛው እርከን የትምህርት ደረጃ ትኩረት መስጠት በቀጣይ ሀገሪቷን የሚረከበውን በእውቀትና በአስተሳሰብ ብሎም በስነ ምግባር የዳበረ ትውልድ ማፍራት መሆኑን የዘነጋው ይመስላል::
የሆነው ሆኖ ግን የትምህርት ጥራትን በማሻሻል በዋናነት ከታች ጀምሮ በህፃናት ላይ አተኩሮ በመስራትና በእውቀት የዳበረ ዜጋ በማፍራት ሃገሪቷን ወደ ብልፅግና ማማ ማውጣት ያስፈልጋል:: ይህም ጉዳይ ለነገ ሳይባል ከአሁኑ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል:: አለበለዚያ ግን ቻይናውያን በቀደዱት ሌሎችም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በእኛ ሰዎች እውቀት ሳይሆን በራሳቸው ሰዎች እውቀት ኢትዮጵያን እንዲያበለፅጉ በር እንከፍታለን:: ይህም በተዘዋዋሪ ለውጪ ሃይሎች ቅኝ ተገዢ የመሆንና የእነርሱ እጅ ጠባቂ የመሆን እድላችንን ያሰፋዋል:: እነዚህ ሀገራት ዛሬ የጀመሩት ጠጋ ጠጋ ከወዲሁ መላ ካልተበጀለት እና የተማረ የሰው ኃይል በጥራትና በብዛት ማፍራት ካልቻልን ክፍተታችንን በማየት በፖለቲካም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮቻችን ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው አይቀርም:: ስለዚህም ያለትምህርት ብልጽግና አይታሰብምና ቅድሚያ ለትምህርት!!
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
አስናቀ ፀጋዬ