ወሊሶ፡- በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የጤና ሽፋን 98 ከመቶ መድረሱ ተገለፀ። 120 ሚሊዮን ብር የተበጀተለት የወሊሶ ሁለተኛ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ 98 ከመቶ ተጠናቋል።
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጉተታ ደገፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ አገሪቱ የጀመረችውን የጤና ልማት ከግብ ለማድረስ ሰፊ ሥራ እየሰራ ነው። በአሁኑ ወቅት በዞኑ አምስት ሆስፒታሎች፣ 54 የጤና ጣቢያዎች እና 253 ጤና ኬላዎች ለማህበረሰቡ በማገልገል ላይ ሲሆኑ ይህም የዞኑን ጤና ሽፋን 98 ከመቶ አድርሶታል።
እንደ ምክትል ኃላፊው ገለፃ፤ የእናቶችና ህፃናትን ሞት በመቀነስ ረገድም ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን የእናቶች ቅድመ እና ድህረ ወሊድ ክትትል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። ለዚህም ከጤና ጣቢያዎች ጀምሮ እስከ ሆስፒታሎች አሰራርና መዋቅር ተዘርግቷል። በዚህም ረገድ 95 ከመቶ ስኬታማ መሆን ተችሏል።
እንደ አቶ ጉታ ገለፃ፤ የህፃናት ሞት ለመቀነስም በሰፊ እየተሰራ ሲሆን፤ ለህፃናት ብቻ የሚውል 10 ክትባቶች እየተሰጡ ይገኛሉ። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ይከሰት የነበረውን የህፃናት ሞት ለማስቀረት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው፡ በተለይም ለህፃናት በሽታ መከሰት ትልቅ ድርሻ ያለው ማይክሮ ኒውትረንት የሚባሉ ንጥነገሮች ማነስን ለመቀነስ ያስችል ዘንድ እነዚህን ኒውተረንቶች ለጨቅላ ሕጻናት እየተሠጡ ይገኛሉ።
በዞኑ ከፍተኛ የሆነ የወባ በሽታ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን በርካታ ወረዳዎችም ነፃ ማድረግ መቻሉን አቶ ጉታ ተናግረዋል። አጎበር በሰፊው እየተሰራጨና የኬሚካል ርጭትም በተገቢው ጊዜ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። «አጎበር ማግኘት ካለባቸው 95 ከመቶም ስርጭት ተከናውኗል» ብለዋል።
የጤና ሽፋኑን ለማሳደግም በዞኑ በ32 ሚሊዮን ብር ማስፋፊያ ስራ እየተከናወነ ሲሆን በወሊሶ ከተማ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ሆስፒታል እየተገነባ መሆኑንም ምክትል ኃላፊ አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው 98 ከመቶ መድረሱን ጠቁመው ግንባታው በ80 ሚሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየት በመፈጠሩ ወደ 120 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱን አስረድተዋል። በዞኑ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ያሉ ሲሆን ለእነዚህም እንደ ሪፈራል ሆኖ እንዲያገለግል ታሳቢ የተደረገ ሆስፒታል መሆኑንም አብራርተዋል።
ምንም እንኳን እነዚህ ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም ችግሮች መኖራቸውንም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል። «ሆስፒታሎቹ በቂ የመድሃኒት እና መሣሪያዎች አቅርቦት የሉም። ለአብነት ዞኑ በ2011 ዓ.ም ማግኘት ከሚገባው መድኃኒት የተረከበው 91 ከመቶ ብቻ ነው» ብለዋል። በተጨማሪም ላብራቶሪ አገልግሎት እና መድኃኒት አቅርቦትም አኳያ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ጠቅሰው፤ የሠለጠነ ባለሙያ በተለይም ደግሞ ስፔሻሊስቶች ከፍተኛ እጥረት መኖሩን አስገንዝበዋል።
የፅህፈት ቤቱ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አምስት ሆስፒታሎች፣ 54 የጤና ጣቢያዎች እና 253 ጤና ኬላዎች የሚገኙ ሲሆን ለ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር