ከሸኖ ከተማ ጥቂት እልፍ ብሎ ከሚገኝ ቀበሌ የተወለደው አማረ የልጅነት ህይወቱ በገጠር ኑሮ የተቃኘ ነው። ወላጆቹ እንደሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ትምህርት ቤት ገብቶ ቀለም እንዲቆጥር አልፈቀዱም። ዕጣ ፈንታውም ከብቶች ጭራ ስር ሆኖ እነሱን ሲከተል እንዲውል ፈረደበት።
እረኝነትን ህይወቱ አድርጎ የዘለቀው ህጻን ከፍ ሲል የግብርና ስራ ጠበቀው። በሬዎቹን ጠምዶ መሬቱን ሲገምስ መዋሉም መልካም ገበሬ አሰኝቶት ወጣትነት ላይ ደረሰ። ይህ ዕድሜው ግን በነበረበት ሁኔታ እንዲቆይ ዕድል አልሰጠውም። ሁሌም ርቆ የሚያስበው ልቡ ሸፈተ። በየቀኑ ስለከተማ መስማቱ ከነበረበት ህይወት አውጥቶ የማያውቀውን ዓለም እንዲያልም አስገደደው።
ሸኖ ለወጣቱ ምቹ መኖሪያው ብቻ አልሆነችም። አልፎ አልፎ ከሰዎች እየተጣላ አጉል ጠባዩን የሚያስቆጥርባት፣ ከአንዳንዶች ጋር ባለው አተካሮም በእስር የሚቆይባት ጭምር ሆነች። ይሄኔ አማረ በሁኔታዎች ብዛት ነገር ገብቶት መሬት መቆርቆር ያዘ። ይህ ስሜት ደግሞ ሁሌም አርቆ ለሚያስበው ሰው ሰበብ እየፈጠረ ዕንቅልፍ አሳጣው።
ብዙዎች ማንነታቸውን ለመለወጥ መነሻ ስለሚያደርጓት አዲስ አበባ ይበልጥ ማወቁ በየቀኑ በሀሳብ ደርሶ እንዲመለስ ምክንያት መሆኑ አልቀረም። አንድ ቀን ደግሞ የልቡ ተሳካና ኑሮውን አደላድሎ ህይወቱን ለመቀጠል ቆርጦ ተነሳ። ጓዙን ጠቅልሎ ካሰበው ሲደርስም ‹‹አይዞህ›› የሚል ተቀባይ አላጣም።
የአማረ ታላቅ አህት ኑሮዋን በአዲስ አበባ ካደረገች ዓመታት ተቆጥረዋል። ትዳር ይዛና ልጆች ወልዳ በምትኖርበት አካባቢም ማለፊያ የሚባል ቤት ሰርታ ቤተሰቦችዋን ትመራለች። ወንድሟ በእንግድነት በመጣ ጊዜ አልተከፋችም። በፈገግታ ተቀብላ እንደአቅሟ እያስተናገደች ለወራት አኖረችው።
ውሎ አድሮ አማረ ራሱን የመቻል ፍላጎት አደረበት። በዘመድ ቤት ተቀምጦ ጊዜ መቁጠሩን እንደነውር ቆጥሮም በላቡ ሰርቶ የሚኖርበትን አማራጭ ፈላለገ። እምብዛም ሳይቆይ በዛው አካባቢ የጥበቃ ሙያ ተገኘለት። በእማኞች ውል ተይዞለትም ስራውን ፈጥኖ ጀመረ። በጥበቃው አዳሪ ባልሆነ ጊዜ የሚውልበት የጉልበት ስራ አላጣም። በዚህ በኩል የሚገኘው ገንዘብም ተጨማሪ ገቢ ሆኖት ኑሮውን መደጎም ያዘ።
አማረ ተቀጥሮ በሚሰራበት አካባቢ የሚያውቀውን አንድ ሰው ከሌሎች ይበልጥ ይቀርበዋል። የጋራ የሚሆን የጉልበት ስራ በተገኘ ጊዜ ተጠራርተው በስምምነት ይሰራሉ። ስራው ካበቃ በኋላም የሚደርሳቸውን ገንዘብ ተሳስበው የድርሻቸውን ይካፈላሉ። ይህ የስራ ግንኙነት ጊዚያትን ማስቆጠሩ ደግሞ ሁለቱን ይበልጥ አቀራርቧል። የቅርበታቸው ወሰንም አብሮ ከመስራት አልፎ በአንድ ቤት እስከመኖር አዝልቋቸዋል።
ተስፋሁን የሚባል ጓደኛውን ማንነት የተረዱት የአማረ ዘመዶች በሁለቱ ባልንጀሮች መካከል ባለው ወዳጅነት ደስተኞች ናቸው። በየቀኑ የሚያስተውሉትን መተሳሰብም የወንድማማችነት ያህል ይቆጥሩታል። ሁሉቱም የጥበቃ ሰራተኞች ክፉና ደጉን አሳልፈዋል። በአንድ ማዕድ ቆርሰውም በአንድ ጣራ ስር ውለው አድረዋል።
አማረ ጓደኛውን እንደራሱ ስለሚያስብ ከእህቱ ቤት አይለየውም። ቤት በደረሱ ጊዜም እህት ሁለቱንም በፈገግታ ተቀብላ በእኩል አስተናግዳ ትሸኛለች። መኖሪያቸው እምብዛም ስለማይራራቅ ማምሻቸውን ከቤተሰቡ ዘንድ ማድረግን ለምደዋል። አብዛኛውን ጊዜም ራታቸውን በዛው ስለሚበሉ በጨዋታና ሳቅ የቤቱን ሳሎን አድምቀውት ይቆያሉ።
ሁለቱ ባልንጀሮች በትርፍ ሰዓት የሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን በመደጎም የሚያግዛቸው ነው። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ መንገድ የሚመጣው ገንዘብ ከባድ ዋጋ ይከፈልበታል። እንዲህ አይነቱ ስራ በተገኘ ጊዜ ለነገ ይሁን ብለው ጊዜ አይሰጡም። ድንጋይ መፍለጥም ይሁን መሸከም፣ ሳያወላውሉ በእኩል ይገቡበታል።
ጉልበት ከፍለው፣ ላባቸውን ጠብ አድርገው የሚቆጥሩትን ብር ሁለቱም ‹‹አንተ ትብስ እኔ›› ተባብለው ሲካፈሉ ኖረዋል። ስለነገው ማንነታቸው የሚያቅዱት ባልንጀሮች ዛሬን ከሚኖሩበት በተሻለ ለመገኘት ቀን ከሌት እየሰሩ የሚሹትን ጥሪት ይቋጥራሉ። የአሁኑን ድካም በኋለኛው እፎይታ እያሰቡም ያለእረፍት ይተጋሉ፣ ይፈጋሉ።
አካባቢው የአዲስ ቤቶች ግንባታ የሚካሄድበት በመሆኑ ለእነሱ የሚሆን የጉልበት ስራ አይታጣበትም። ሁሌም ቢሆን ስራ መኖሩን አንዳቸው ቀድመው ከሰሙም ጉዳዩን የጋራ እንጀራቸው ያደርጉታል።
ከስራ መልስ ስራ
ሰሞኑን በቋሚ ጥበቃቸው ላይ ብቻ የከረሙት ሁለቱ ባልንጀሮች ተጨማሪ ስራ ባለመገኘቱ ሌላ ገንዘብ አልቆጠሩም። እንዲህ አይነቱን አጋጣሚ ባይወዱትም ጥበቃቸውን አጥብቅው ይዘዋል። ድንገት ግን ተስፋሁን ለሁለቱም የሚሆን የጉልበት ስራ ማግኘቱንና ዋጋ ተነጋግሮ መምጣቱን ለጓደኛው አበሰረው።
አማረ የጉልበት ስራው መገኘቱን በሰማ ጊዜ የጥበቃ ስራውን አመቻችቶ ለአዲሱ ስራ ጊዜ ሰጠ። ተስፋሁንም እንደሁሌው ቋሚ ስራውን በሌሎች ተክቶ የተገኘውን መዋያ ሊገባበት ጓደኛውን አስከተለ።
ቀናት ያስቆጠረው የጉልበት ስራ ከጥበቃው ጋር ተዳምሮ ወር ላይ የሚያመጣለትን ገቢ ያሰበው አማረ በላቡ ጠብታ መሀል ብዙ ጉዳዮችን ሲያቅድ ከረመ።
ተስፋሁን በበኩሉ በጉልበቱ ድካም የሚያገኘውን ገንዘብ በሀሳቡ እያሳለፈ መቁጠሩ አልቀረም። ገጠር ያሉትን ዘመዶቹን ሲያስታውስም በዓመቱ መጨረሻ ማድረግ ስለሚገባው ሁሉ ማቀድ ይዟል። ሀሳቡ ከዳር የሚደርሰው ደግሞ እንዲህ በላቡ ወዝ በሚቋጥረው ጥሪት እንደሆነ ከገባው ቆይቷል።
አሁን ጓደኛሞቹ ከጥበቃ ሙያቸው መሀል ጣልቃ አስገብተው ሲደክሙበት የቆዩትን የጉልበት ስራ በአግባቡ አጠናቀዋል። የሚቀራቸው ቢኖር የልፋታቸውን ዋጋ ከአሰሪያቸው ተቀብለው የልምዳቸውን መካፈል ብቻ ነው።
አስቀድሞ ስለስራው የተዋዋለው ተስፋሁን ማምሻውን ከአሰሪያቸው የተነጋገረውን ገንዘቡን ቆጥሮ ተቀበለ። አማረም ከባልንጀራው እጅ የገባውን ገንዘብ አጅቦ ከኋላው ተከተለው። ይህን ሲያደርግ በገጽታው ላይ ደማቅ ፈገግታ እየተነበበ ነበር።
ግቢውን አልፈው ጥቂት እንደራቁ የጓደኛውን ፍላጎት በቅጡ ያስተዋለው ተስፋሁን የድርሻውን ለመስጠት ከአንድ ቦታ አረፍ ብሎ ገንዘቡን ከኪሱ አወጣ። መቁጠር የጀመረውን ብር አጠናቆ በአንደኛው እጁ ያስቀረውን ለጓደኛው ሲያቀብል ፈገግታ የተመላው የአማረ ገጽታ በተለየ ስሜት ሲለዋወጥ ተስተዋለ ።
ተስፋሁን የአማረን ሁኔታ ቢረዳም በፊቱ ላይ አንዳች ነገር አልተነበበም። ገንዘብ የያዘውን እጁን እንደዘረጋ ጓደኛው አስኪቀበለው ጠበቀ። ባልተለመደ ሁኔታ ቁጣና ንዴቱን መቆጣጠር የተሳነው አማረ የጓደኛውን እጅ በሀይል መልሶ ለምን በሚል ብሽቀት አፈጠጠበት።
ተስፋሁን ያሰበውን ለመናገር ከመጀመሩ በፊት አማረ የሰሩበት ገንዘብ ይህ ብቻ እንዳልሆነና ብሩን ፈጽሞ እንደማይቀበል ነገረው። በንግግራቸው መሀል ጭቅጭቁ አየለ። ተስፋሁን ሁኔታውን እያስረዳ ለእሱ የሚገባውን አስቦ እንደሰጠው ሊያሳምነው ሞከረ።
ጥቂት ቆይቶ አማረ ቅር እያለው ገንዘቡን ቆጥሮ ኪሱ ከተተ። ያሰበውና ከእጁ የገባው ብር አለመደራረሱን ባሰበ ጊዜም ንዴቱን ውጦ አብሮት ለመሄድ ጉዞ ጀመረ። የዛን ቀን በሁለቱ መሀል የተፈጠረው ያልተለመደ ሁኔታ ቅሬታን አስከትሎ ምሽቱን በዝምታ እንዲያሳልፉ ምክንያት ሆነ።
ከዛን ቀኑ አጋጣሚ በኋላ የሁለቱ ባልንጀሮች ቅርበት እንደቀድሞው አልቀጠለም። ኑሯቸው በአንድ ቢሆንም የማይነጋገሩበት ቀናት መበርከት ያዘ። በተለይ አማረ በገንዘብ ጉዳይ ተስፋሁን እንዳታለለው በማመኑ ቅያሜውን መሻር አልቻለም።
የባልንጀሮቹ ቅርበት እንደቀድሞው ያለመሆኑን ሁለቱም ልቦናቸው ያውቃል። ያም ሆኖ ግን አብረው መኖርና በአንድ ገበታ መቁርስን አልተውም። አልፎ አልፎም ከአማረ ታላቅ እህት ቤት ጎራ ብለው ምሽቱን አጋምሰው ይመለሳሉ።
የካቲት 17 ቀን 2001 ዓ.ም
ዕለቱን በስራ ሲደክሙ የዋሉት ባልንጀሮች በተለመደው ሰዓት ከቤታቸው ደርሰዋል። ጥቂት አረፍ እንዳሉም ወደ አማረ ታላቅ እህት ቤት የመሄድ ዕቅድ አላቸው። አማረ አሁንም ስለገንዘቡ እያሰበ ነው። ይህን ሲያስብ ደግሞ ውስጡ በትኩሳት ይግላል። መላ ሰውነቱም በእልህ ሲቀጣጠል ይሰማዋል።
ይህ ስሜት አብሮት የዘለቀው አማረ ጓደኛው ቅያሜውን እንዳያውቅበት መጠንቀቅ ጀምሯል። መሬት እየቆረቆረ ቢውልም ተስፋሁንን ሲያገኝ የሚያሳየው ፈገግታ ከወትሮው የተለየ አይደለም። የዛን ቀን ስራ ውለው ማምሻቸውን ሲገናኙም ወደ አማረ እህት ቤት የመሄዱ ሀሳቡ የጋራቸው ነበር።
አሁን ሁለቱም በየራሳቸው ጉዳይ እንደተዋጡ ከታሰበው ቤት ደርሰዋል። እንደተለመደው ሆኖ በፍቅር የተቀበላቸው ቤተሰብን ሲቀላቀሉም የወትሮው አይነት ጨዋታ ቆይቷቸዋል። ከቀድሞው የተለየ ስሜት ያላስተዋለቸው እህት ራታቸውን አብልታ ቡና ለማፍላት ከሳሎን ጓዳ እያለች ነው።
ምሽቱን ከቤተሰቡ መሀል አሳልፈው ለመሄድ በተነሱ ጊዜም እንግዳ ተቀባይዋ እህት ለሁለቱም መልካም አዳር ተመኝታ አስከበሩ ሸኝታቸው ተመልሳለች ።
የዝምታው ጉዞ
ካመሹበት ወጥተው ወደ ቤታቸው ጉዞ እንደጀመሩ በመሀላቸው ዝምታ ነገሰ። ሁለቱም ከደቂቃዎች በፊት አብረው እንዳሳለፉት አልሆኑም። እንደማይተዋወቁ መንገደኞች በዝምታ ተውጠው እርምጃቸውን ቀጠሉ።
ተስፋሁን ይህን ስሜት ያስተዋለው አይመስልም። አማረ ግን ተወት ያደረገው ብሽቀት አገርሽቶበት ይብሰለሰል ይዟል። ሁሌም የሚይዘውን የእንጨት ዱላም በተለየ አጥብቆ አረማመዱን ጭምር ቀይሯል።
ጨረቃ ብርሀኗን ብትነፍግ ጨለማው ‹‹አይን ቢወጉ አይታይም›› ይሉት አይነት ሆኗል። አካባቢው አዳዲስ ቤቶች የሚገነቡበት በመሆኑ ከእንቅስቃሴ የራቀ ነው። ያሉት ጥቂት ነዋሪዎችም በራቸውን የዘጉት በጊዜ በመሆኑ ስፍራው በጭርታ ተውጧል ።
አማረ አንዳች ነገር የተናነቀው ይመስላል። ያሰበውን ከመናገሩ በፊት የቀደመውን አጉል ስሜት ለመቋቋም እየሞከረ ነው። እንደምንም ከራሱ ታገለና ንግግሩን ጀመረ። ጥያቄው ሰሞኑን ሲብሰለሰልበት የቆየው የገንዘብ ጉዳይ ነበር።
ተስፋሁን የጓደኛውን የገንዘብ ‹‹መልስልኝ›› ሀሳብ እንደሰማ የተለመደውን አጭርና ግልጽ ምላሽ ሰጠው። ገንዘቡ ቀድሞ ከተሰጠው በላይ እንደማይገባውና ከዚህ በኋላም ዳግም እንዳይጠይቀው በጥብቅ አስጠነቀቀው።
አማረ የተስፋሁንን ምላሽ እንደሰማ ንዴቱን መቆጣጠር ተስኖት ዱላውን አነሳ። ባልንጀራው ሁኔታው ቢያስደነግጠውም ሀሳቡን መቀየር አልፈለገም። አቋሙን ሲያረጋግጥ የሰነዘረውን ዱላ አልመለሰውም። ጆሮ ግንዱ ላይ አሳረፈበት። ተስፋሁን ባረፈበት ከባድ ምት ተንገዳግዶ ሲወድቅ በዱላው ደጋግሞ ቀጠቀጠው። እየጮኽ እንዲምረው ለመነው። መስሚያ ጆሮ አልነበረውም። በወደቀበት እግርና ጭንቅላቱን ያለማቋረጥ ደብድቦ ትንፋሹ ቀጥ ሲል ወደመጣበት እየሮጠ ተመለሰ።
እያለከለከ ከእህቱ ቤት ሲደርስ እህቱና ባለቤቷ በሁኔታው ደንግጠው ስለጓደኛው ጠየቁት። የሆነውን ሁሉ ሳይደብቅ ነገራቸው። የባልንጀራው ህይወት ስለማለፉ እርግጠኛ ነበር።
አማረ በስፍራው የነበሩ ሁሉ አውነታውን ሰምተው መደናገጣቸውን ሲያውቅ ወዲያው እልህና ስጋት ያዘው። አፍታ ሳይቆይም እያንዳንዳቸውን አስጠነቀቃቸው። የሰሙትን ለሌሎች ቢናገሩ እነሱንም እንደሚገላቸው በዱላው አያስፈራራ ዛተ። ሁሉም በድንጋጤ ተንቀጠቀጡ።
ምሽቱን ከነበረበት ወጥቶ ወደ ዘመድ ቤት ያመራው አማረ አዳሩን በእዛው አድርጎ ሲነጋ ወደ ስራው አመራ። ትናንት ጓደኛውን የገደለበት አካባቢ ሲደርስ ግን ስፍራው በፖሊሶችና በበርካታ ሰዎች መከበቡን አስተዋለ። ወዲያው መንገዱን አሳብሮ ‹‹እግሬ አውጭኝ›› ሲል ተፈተለከ።
የፖሊስ ምርመራ
በማግስቱ በስፍራው የደረሰው ፖሊስ የሟችን አስከሬን በባለሙያዎች አስፈትሾና በርካታ የቴክኒክ ምርመራዎች አካሂዶ ማስረጃን ከመረጃ አጠናቀረ። የጥርጣሬ አቅጣጫው ወደ አማረ እንደሚያመላክት በማወቁም ተጠርጣሪውን ለመያዝ እንቅስቃሴውን ቀጠለ።
በረዳት ሳጂን አማረ ቢተው የሚመራው ቡድን ተጠርጣሪው ከአካባቢው ከራቀ በኋላ በሌላ አካባቢ ድንጋይ እየፈለጠ እንደሚኖር አረጋግጧል። ይህንንና ሌሎች መረጃዎችንም የፖሊስ መዝገብ ቁጥር 509/01 በየዕለቱ መመዝገብ ጀምሯል። አንድ ቀን ደግሞ ፖሊስ በጥብቅ ሲፈልገው የቆየውን ተጠርጣሪ ካለበት ደርሶ በቁጥጥር ስር አዋለው። ተገቢውን ምርመራም አጠናቆ ለክስ ወደ ፍርድ ቤት አሳለፈው።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2012 ዓ.ም
መልካምስራ አፈወርቅ