አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ካፈራቻቸውና ለአሁኗ አለም እንዲህ ሆኖ መገኘት አስተዋፅኦ ካደረጉት ሰዎች መካከል አንዱና ጎላ ብሎ የሚታየው ካርል ሔንሪክ ማርክስ (1818 – 1883) ነው። ማርክስ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ታሪክ፣ ፍልስፍናና ሶሽዮሎጂ የጥናት መስኮቹ ሲሆኑ በእነዚሁ ልክም ኃላፊነቱን የተወጣ ድንቅ ፈላስፋ ነው።
በ64 አመት እድሜው ይህችን አለም የተሰናበተው የፖለቲካ ንድፈ ሀሳብ ቀማሪና ሶሻሊስት አብዮተኛው ካርል ማርክስ በዚህች አጭር እድሜው የማያልፉ ስራዎችን በመስራት ስሙን ከመቃብሩ በላይ ያኖረ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ፈላስፋ ነው።
ማርክስ በጥልቀት ከፈተሻቸው ዘርፎች መካከል ምጣኔ ሀብት፣ ሀይል /ፓወር/፣ የሀይል ፖለቲካ /ፓወር ፖለቲክስ/፣ ትግል፤ እንዲሁም የካፒታሊዝምን ስርአት አስከፊነት ነው። ማርክስ ተለይቶ ከሚታወቅባቸው መሪ ሀሳቦቹ መካከል “ደመወዝ ተከፋይ ጉልበት ባለበት ሁሉ የመደብ ትግል ይኖራል”፣ «ስግብግብ ያበደ ካፒታሊስት ሲሆን ካፒታሊስት ደግሞ ጤነኛ ስግብግብ ነው። ትግሉም በሰራተኞች አሸናፊነትና የበላይነት የሚደመደም ነው።»፣”ሃይማኖት፣ ሥነ ምግባር እና ማህበረሰባዊ መዋቅሮች በሙሉ መሰረታቸው ኢኮኖሚክስ ነው።” (ከተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ አንፃር ማለት ነው) የሚሉት የሚገኙ ሲሆን መሬት የመንግስት ነው እና የመሳሰሉት የእርሱ ፍልስፍና ውጤቶች ስለመሆናቸው የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ። በልዩ ቃናዋ የምትታወቀው “The last capitalist we hang shall be the one who sold us the rope.”ም ብዙዎች ይወዷታል።
ካርል ማርክስ በርካታ መጻሕፍት ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከልም ከፍሬድሪክ ኤንግልስ ጋር በመሆን በ1840 ዓ.ም ያዘጋጀው “ኮሚዩኒስት ማኒፌስቶ” ከሁሉም በላቀ ደረጃ የተወደደለትና እሱንም ታዋቂ ያደረገው ስራ ነበር። ይህ መጽሐፍም የኮሚዩኒዝምን ሃሳቦችና አላማዎች ለማብራራት አስፈላጊውን ሁሉ ያደረገበት ሲሆን ቆይቶም “ማርክሲዝም”ን አስገኝቶለታል። ባለ ሦስት ክፍሉ “ዳስ ካፒታል” ካፒታሊዝምን አበጥሮ ያሳየበት መፅሀፉም ሌላውና ዝናውን ያጎረፈለት ስራው መሆኑን ዘመነኞቹም ሆኑ የአሁን ዘመን ጥናቶች ያመለክታሉ። እስካሁንም ድረስ የማርክስን ሃሳብ የሚከተሉ በርካቶች ሲሆኑ በተለያዩ ጥናትና ምርምሮችም እያሳደጉት ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል አንዱና ስራዎችን በማብራራት፣ በመተንተን፣ በማስረፅ በኩል በከፍተኛ ደረጃ ሲሰራ የቆየው አሜሪካዊው የላንሳስተር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ቴሪ ኤግልተን ይገኝበታል፤ “Why Marks Was Right?” የሚለውም ከቅርብ ስራዎቹ ይጠቀሳል።
በቅርቡ በአለም ዙሪያ ያሉ አድናቂዎቹ 200ኛ የልደት በአሉን ያከበሩለት ካርል ሔንሪክ ማርክስ ስራዎቹ የሶሻሊዝም ርእዮተ-አለምን በማራመድ ለሩሲያ አብዮት መነሳት ዋና ምክንያት መሆናቸው፤ ይህም አብዮት ወደ ሌሎች አገራት እንዲስፋፋና የበላይነትንም እንዲይዝም ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው ይነገራል።
ካርል ማርክስ በስራዎቹ ምክንያት በርካታ ተቃዋሚዎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ደጋፊዎችም አሉት። ተቃዋሚዎቹ ሀይማኖት ጠል ነው፣ በትግልና ጦርነት ያምናል፣ ሌላም ሌላም ሲሉት። ይህ ሁሉ ግን በደጋፊዎቹ በኩል ከንቱና ማርክስን በቅጡ ካለመረዳት የመጣ እንደሆነ ነው የሚገለፀው። በተለይ ከካፒታሊስቱ ጎራ ለተሰለፉት ማርክስ አይረቤ ብቻ ሳይሆን የከንቱ ከንቱ ነው።
ይህን አይነት ተቃውሞ ይኑር እንጂ ምድር ላይ ያለው እውነታ ግን የሚያሳየው የዚህ ተቃራኒን ነው። አስቀድመን “ሰርክ አዲስ” እንዳልነው በተለያዩ ጊዜያት ማርክስና ፍልስፍናው /ማርክሲዝም/ ለተበደሉ፣ ካፒታሊዝም በጨካኝ እጁ ለጨፈለቃቸውና ብልሹ የኢኮኖሚና ሀብት ክፍፍል ለገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የትግል መሳሪያ ሲሆን ነው የሚታየው።
አለምን በበላይነት ሲያሽከረክር የቆየው ይህ የማርክስ ማርክሲዝም ኢትዮጵያን ሳይቀር ዳብሶ ማለፉ አይዘነጋም። ከመዳበስም አልፎ በወቅቱ ለነበረው ትውልድ ስቃይ እንደነበር እስካሁን ድረስ እየተፃፈ እያነበብን፤ እየተነገረ እያዳመጥን አለን። በተለይ በነጭና ቀይ ቀለም ተቃራኒ ጎራ የነበረው የተቃርኖ አሰላለፍ ያስከፈለው ዋጋ ዛሬም ድረስ ትኩስ ዜና ነው።
ከላይ በማርክስ ፍልስፍና ላይ የሚሰነዘረውን ትችት ደጋፊዎቹ “ፍልስፍናውን ካለመረዳት የመነጨ …” በማለት እንደሚያጣጥሉት ጠቅሰን ነበር። ይህ እኛም ሀገር ለተፈጠረው ነጭ/ቀይ መተላለቅ አስተዋፅኦ ሳያደርግ የቀረ አይመስልም።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከሸገሯ መአዛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጉዳዩን አንስታላቸው “አያውቁትም፤ ቢያውቁት ኖሮ ሁሉም ኮሚኒስት/ሶሺያሊስት ነን እያሉ ለምን እርስ በእርስ ይጋደላሉ? ትግሉ የርእዮተ አለም ሳይሆን ለስልጣን ነበር።” ማለታቸውን ስናስብና ከአንዳንድ የኢህአፓ አባላት “ኢህአፓ ስህተት ፈፅሟል” የሚለውን ስንሰማ እውነትም ያለመረዳት ሁኔታ ነበር ብለን ሀሳብ መስጠት እንችላለን።
ይህ የስልጣንና ጥቅማጥቅም ጉዳይ አሁንም የተሟጠጠ ጉዳይ አይደለም። በቅርቡ የፍትህ መፅሄት አምደኛ በአሁኑ ሰአት ያለውን የፖለቲካ ውጥንቅጥ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት “አንድም ጥርት ያለ የመርህ ልዩነት ይዞ የመጣ ፓርቲም ሆነ ሌላ አካል የለም። ይሄ ሁሉ ሁከትና ህዝብን ከህዝብ የማጋጨቱ ጉዳይ መነሻው የስልጣንና ጥቅም ጉዳይ ነው።” ነበር ያሉት።
ፕሮፌሰር መስፍን እና ከፍትህ አምደኛ ማብራሪያ ተነስተን አስተያየት ስጡ ብንባል መልሳችን ሊሆን የሚችለው “ፖለቲካችን አላደገም፤ ገና እዛው አዙሪት ውስጥ ነው ያለው” የሚል ከመሆን ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ባዬ “የማይቸነፍ ፀጋቸው” በሚል ርእስ በፃፉት መፅሀፍ ታዋቂ ሰዎችን፣ ላገርና ለወገን ብዙ የለፉ፣ ህይወታቸውን የገበሩ ሰዎችን ደብዛቸውን ለማጥፋት መሞከር ከንቱ ልፋት መሆኑን፤ እንደውም ጭራሽ ስማቸውን ጥላሸት ለመቀባት በተሞከረ ቁጥር እየገነኑ እንደሚሄዱ (ከራሳችን አውድ አኳያ) ጥሩ መፅሀፍ ፅፈዋል። የማርክስም የዚሁ አይነት ነውና ፍልስፍናው እያደር እየገነነ፣ እየተወደደና ወደ ተግባርም እንዲለወጥ እየተፈለገ ያለበትን ምክንያት እንመልከት።
“ከጥንት ጀምሮ ስናየው የኖርነው …” እንደሚባለው አስቀድመን እንደምናውቀው የማርክስ ፍልስፍና /ኮሚኒዝም/ ቀንደኛ ጠላት ካፒታሊዝም ነው። የአለማችን ዋንኛዋ ካፒታሊስት አገር ደግሞ አሜሪካ ነች። እሳትና ጭድ እንደምንለው ማለት ነው። የሚገርመው ይሄ አይደለም፤ የሚገርመው የማርክስ ፀረ-ኢምፔሪያሊስት አቋም በየጊዜው ሲነሳና ሲወደስ የሚሰማው በእዚሁ ምድረ አሜሪካ መሆኑ እንጂ።
በ2011 በአሜሪካ የደረሰውን የከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የአገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች የተለያዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን አስተናግደው ነበር። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተይዘውና ሲስተጋቡ የነበሩት መፈክሮች ጠንከር ያለ ፖለቲካዊ መልእክቶችን የያዙ ሲሆን ከሁሉም ጎልቶ ይሰማ የነበረው ግን “እኛ 99 በመቶ ነን” የሚለውና የአገሪቱን አጠቃላይ ሀብት አንድ በመቶ የሚሆኑት መቆጣጠራቸውን የሚያመለክተው ነው።
ካርል ማርክስ ከ190 አመት በፊት ማርክስ «ስግብግብ ያበደ ካፒታሊስት ሲሆን ካፒታሊስት ደግሞ ጤነኛ ስግብግብ ነው።” በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ቃል በቃል መደገሙ ነው የብዙዎች ግርምት። አንድን ስራ ፍልስፍና ነው ከሚያስብሉት መስፈርቶች አንዱ ዘመን ተሻጋሪነቱ ነውና ይሄው የማርክስ ሀሳብ እዚህ ደርሶ መፍትሄ የማፈላለጊያ ብልሀት ሆኖ ቀርቧል። ይህ “እኛ 99 በመቶ ነን” የሚለው መፈክር በህዝቡ ውስጥ ከመስረፁ የተነሳ እስካሁን ድረስ በተለያዩ አውዶችና ህዝባዊ ተቃውሞዎች ላይ ጎልቶ በመሰማት ላይ ይገኛል፤ “እኛ 99 በመቶ ነን!”
ይህ “እኛ 99 በመቶ ነን።” የሚለው በአደባባይ መናኘት እንደጀመረ በተንታኞች በኩል ሲገለፁ የነበሩት ሀሳቦች ካርል ማርክስ በዛን ጊዜ ካፒታሊዝምን፣ ታክስን፣ ሰራተኛውንና አሰሪውን ወዘተ አስመልክቶ ያስቀመጣቸው ነጥቦች ምን ያህል ትንቢት እንደሆኑና እሱም ሆነ ስራዎቹ ምን ያህል ከጊዜው የቀደሙ እንደነበሩ ነው። በተለይም ለሰራተኛው ዝቅተኛ ክፍያን መፈፀምና ከፍተኛ ትርፍ ማግበስበስን፣ የካፒታሊዝም ተፈጥሯዊ የጨካኝነትና በጥባጭነት ባህርይን፣ የካፒታሊዝም አለምን ለመቆጣጠር ያለውን የተስገበገበ ፍላጎት (ግሎባላይዜሽን) እና የመሳሰሉት የእለት ተእለት የመገናኛ ብዙሀን ቀዳሚ ርእሶች ነበሩ።
በዚህ ከካፒታሊዝም እኩይ ባህርይ ጋር በተያያዘ ማርክሲዝም ነገሮችን የሚመለከተው “ፍልስፍናው የአንድ የማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አተናተን ዘዴ ሲሆን የጉዳዩን ታሪካዊ አመጣጥ በቁሳዊያን ትርጓሜ በመጠቀም፤ እንዲሁም ዲያሌክቲካዊ ምልከታንና ማህበራዊ ለውጥን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።” ይህ ነው የኮሚኒዝም የጨቋኝ/ተጨቋኝ፣ገዥ/ተገዥ፣ የላብ አደሩና ቡርዥዋውን ለይቶ ማያ መስፈርት፤ መመልከቻ መነፅር።
ሶሻሊዝም/ኮሚኒዝም እነቻይና ጋር ባደባባይ ስራ ላይ ሲውል ይታይ እንጂ ህገ መንግስታቸውን በዚሁ ርእዮት የቃኙ አገራት በርካቶች ናቸው። ፌዴራል ሪፐብሊክ ኦፍ ኔፓል፣ ሪፐብሊክ ኦፍ ኒካራጓ፣ ፖርቹጊስ፣ ዲሞክራቲክ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ ኦፍ ስሪ ላንካ እና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል። በአሁኑ ሰአት ራሳቸውን ኮሚኒስት መንግስታት (Communist states) ብለው የሚጠሩ አገራት ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ቻይና፣ ኩባ፣ ላኦስ እና ቬትናም ተጠቃሽ ናቸው። ጀርመን ነፃ ገበያን የምትከተል ካፒታሊስት ትሁን እንጂ ባብዛኛው ህጎቿ ከሶሻሊዝሙ ርእዮት የተቀዱና የሶሻሊዝም ህግጋትን ያካተቱ ናቸው። ኮሙኒዝም ወድቋል፤ ግብአተ መሬቱ ተፈፅሟል የሚለው የካፒታሊስቱ ጎራ እንግዲህ ይሄንን ነው።
ሶሎ የተባሉ ተመራማሪ “ማርክስ አስፈላጊና ተፅእኖ ፈጣሪ ሰው ነው፣ ማርክሲዝምም እንዲሁ በልሂቃን ዘንድ ከቀኖናም አልፎ ተግባራዊ ተፅእኖን የፈጠረ” መሆኑን ሲመሰክሩ መነሻቸው እነዚህን አይነቶቹ ማስረጃዎች ነበሩ ማለት ነው። እውነትም የበርካታ ፈላስፎች ስራዎች አእምሮን በማንቃት፣ ተጠየቅንና ምክንያታዊነትን ከማጎልበት፤ ከአካዳሚያዊ ተግባራት ባለፈ መሬት ረግጠው በአለም አቀፍ ደረጃ ተፅእኖ ፈጣሪ፣ ከሁሉም በላይ ከዘመን ዘመን በመሸጋገር የየትውልዱ የህይወት አካል ሲሆኑ በማይታዩበት አለም የማርክስ ሀሳብና ስራዎቹ በተፅእኖ ፈጣሪነታቸው ቢወደሱ ሊገርም አይገባም።
ነፍሱን ይማረውና የማርክስና ስራዎቹ አድናቂው ጋሽ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር “እግዚአብሄር/መፅሀፍ ቅዱስ፣ ማርክስ፣ ሼክስፒር እና ጥላሁን ገሰሰ ያላሉት ነገር የለም።” ይል ነበር። እውነቱን ነው። ማርክስ ከሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊ መብትና ስርአተ-ፆታ እኩልነት፤ ከፖለቲካ እስከ ኢኮኖሚያዊ መዋቅርና ፍትሀዊነት፤ ስለ በዝባዥና ተበዝባዥ፤ ጨቋኝና ተጨቋኝ ወዘተ ያላለው የለም። መሆን ያለበትን ከሌለበት፤ ፅድቁን ከኩነኔ፤ ስራን ከስንፍና፤ ተፈጥሮን ስለመጠቀም ሁሉ የሚቻለውን ብሏል።
ከላይ “እኛ 99 በመቶ ነን።” መባሉን ተንተርሰን ነበር ሀሳብ የተለዋወጥነው፤ በርእሳችን “ሰርክ አዲስ” ያልንለት ማርክስና ስራዎቹ ሰሞኑንም በዛው በምድረ አሜሪካ በተደረገ ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነትን የተመለከተ ተቃውሞ ላይ “ማርክስ ልክ ነበረ።/Marks Was Right!!” የሚል መፈክር ተይዞ አደባባይ ተወጥቷል። ከመልእክቱ ግልፅነቱ አኳያ ዝርዝሩን እዚሁ ላይ እንተወውና ወደ ማርክስ ስራዎች እንሂድ።
ከላይ ካየናቸውና የኮሚኒዝም ቀጥተኛ ተቃራኒ በሆነው ካፒታሊስቱ አለም የማርክስ ድጋፍና ሰብአዊ ፋይዳ ያላቸው ስራዎቹ ተደጋግመው መነሳታቸው ያለ ምክንያት አይደለም። ህዝቡ የጎደለው ነገር በመኖሩና ያ ጎደሎ ይሞላ ዘንድ የመፍትሄ ሀሳብን ለመሪዎቹ ማቀበል ላይ የተመሰረተ የመፍትሄ አካል ስለሆነ ነው። ይህ “እኛ 99 በመቶ ነን”ም ሆነ “ማርክስ ልክ ነበረ” መታገያ ሀሳብ ዝም ብሎ ድንገት መጥ ነገር አይደለም። በህዝቡ ውስጥ ያለና ሲውጠነጠን የነበረ ሀሳብ እንጂ። የሚያመላክተውም የአገሪቷ አጠቃላይ ሀብት አንድ በመቶ እጅ በሆኑ ዜጎች መዳፍ ውስጥ መውደቁን ሲሆን ይህም ከነቢይ ባልተናነሰ አይኑ ማርክስ ቀደም ብሎ ያየው፤ መፍትሄውንም የጠቆመና ችግሩ እየከፋ ከሄደ መጨረሻው ውድቀት መሆኑን አሻግሮ የተመለከተ መሆኑን ነው።
ወደ አፍሪካም ስንመጣ “ማርክሲዝም አልቆለታል” የሚለው እንደማይሰራ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ምሁራን ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እንደ የኩዋዙሉ ዩኒቨርሲቲ (ደቡብ አፍሪካ) ምክትል ቻንስለርና የዚምባቡዌ ተወላጁ ኢማኑኤል ንጋራ ጥናትና ግኝት አፍሪካ በሰቆቃ የተሞላች፣ አፈና ያልተለያት፤ ረሀብ፣ ድርቅ፣ ኢፍትሀዊነት፣ ቅኝ ግዛት ጥሏቸው የሄደው ኮተታ ኮተቶች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የዲሞክራሲ እጦት፣ ግድያ፣ ያለምርጫ ወደ ስልጣን መውጣት . . . ወዘተ ተዘርዝረው የማያልቁ ችግሮች ያሉባት አህጉር ነች። እነዚህን ሁሉ ችግሮች ነቅሶ ለማውጣትና የመፍትሄ ሀሳብ ለማፍለቅ ደግሞ በራሳቸው ልክ የሰሩትን የምእራባውያንን ፍልስፍና አምጥቶ ስራ ላይ ላውል ማለት ቀልድ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ይላሉ አጥኚው “የአፍሪካን ችግር ለመፍታት ዋነኛው ፍልስፍና የማርክስ ሲሆን የሱን የተመረጡና ለአፍሪካ የሚበጁትን ንድፈ ሀሳቦች በተግባር ማዋሉ ጠቃሚ ነው።”
ማጠቃለያ፤ ዓለምን እየናጧት ያሉት ሁለት ጎራዎች ናቸው፤ ካፒሊዝምና ኮሚኒዝም። ለጊዜው ጉልበቱ ያለው የመጀመሪያው ጋር ሲሆን ሁለቱም የጎሪጥ የሚተያዩ ወገኖች ናቸው። የሁለቱን መኖር የማይፈልጉ እንዳሉ ሁሉ የሁለቱንም መኖርና ሚዛኑ የተጠበቀ አለም ማየት የሚፈልጉም አሉ። ያም ሆነ ይህ የዚህ ፅሁፍ አላማ አገራት ይሄን ርእዮት ይከተሉ ያን የሚል አስተያየት መስጠት አይደለም። የዚህ ፅሁፍ አላማ የጠንካራ ፍልስፍናን የእድሜ ጥግ ማሳየት ሲሆን የካርል ማርክስን ፍልስፍና ዘመን ተሻጋሪነትና ሰርክ አዲስነት ማስቃኘት ነበርና ተሳክቷል ብለን እናስባለን። እግረ መንገዳችንንም ካፒታሊዝም የእጁን ጥልቀትና ርዝመት ቢያስብበት ጥሩ ነው ለማለትም እንወዳለን።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2012
ግርማ መንግሥቴ