አለማወቅ የአእምሮ እውርነት ሲባል እሰማለሁ። የአእምሮ እውርነት ደግሞ ከምንም በላይ ይከፋል። ሰው በአእምሮ እውርነት በሽታ ከተጠቃ ሰው ሳይሆን ለማዳ እንስሳ ይሆናል። ህጻናት ሳለን እንደ ህጻናት እናስባለን፤ እያደግን ስንመጣም ጤነኞች ከሆንን ከእድገታችን ጋር ተመጣጣኝ እውቀት በአእምሮአችን ይሞላል። የቅድሚያውን እውቀት ከቅርብ ወላጅ ከእናታችን እናገኛለን። ከወላጅ አባትና ከአጠቃላይ ቤተሰቦቻችን መረዳቶቻችን ይዳብራሉ። ግንኙነቶቻችን ከቤተሰብ አልፈው ወደ ጎረቤት ሲሻገሩ እንደዚያው እውቀቶቻችንም እየሰፉና እያደጉ ይመጣሉ።
ይህንን ቅደም ተከተላዊ የእውቀት ማግኛና የሚዛናዊ አስተሳሰብ ቀመር ባለመከተላችን ያለማወቃችን ጥጉ ከራስ አልፎ ሌላውንም ወገን ለመጉዳት ምክንያት ሲሆን የምናስተውልበት አጋጣሚ ብዙ ነው።
አሁን ላይ በአገራችን እንኳን ጉድለት ለመሙላት ይቅርና ራሳቸው እውቀት የጎደላቸውና የወጣት ጡረተኞች ሆነው ሳይሰሩ የሚበሉ አያሌ ሰዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል። በእርግጥ ሳይሰሩ መብላት ከተራው ግለሰብ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ድረስ የተዘረጋ ሰንሰለት ነው። ግን ዝምታውና እርምጃው መዘግየቱ ለምን ይሆን?
በሸገር ውስጥ በየዕለቱ የምናየውና የምንሰማው ነገር የአስገራሚነቱ ጥግ ከመብዛቱ የተነሳ ወደ ፊት ‹‹ግርምት›› የሚለው ቃል ራሱ እንዳይቀር እሰጋለሁ።
እስኪ ለዛሬ የመሰረታዊ ፍላጎት ያህል ከምንም በላይ ወደሚያስፈልጉን የትራንስፖርትና ተያያዥ ጉዳዮች ጎራ እንበል። ትራንስፖርት እጅጉን አስፈላጊ ጉዳይ ቢሆንም በእድሜአችንና ከእኛ ቀደም ባሉ የእድሜ ባለጸጎች ይነገረን በነበረው መረጃ በአገራችን ያለው የመኪና ትራንስፖርት የክፍያ ዋጋ በአንጻራዊነት እጅግ የተሻለ የሚባል ነበር። ዛሬ ላይ ግን ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ ሆኗል። በቂ ምግብ ከማግኘት ይልቅ በሰዓት መኪና አግኝቶ መጓዝ ከብዷል።
እውነት ግን እንደ አዲስ አበባ ሕዝብ አንጀት የሚበላ አለ? ከተማ ለመኖር በመፈለጉ ብቻ ፀሐይና ብርድ የሚፈራረቅበት ሳያንሰው በትራንስፖርት እጥረትና በህገ ወጦች እየተታለለ የሚኖር አዲስ አበቤን የመሰለ ምስኪን ሕዝብ ካለ ንገሩኝ። ለታክሲ እንጂ ለተቃውሞ ሰልፍ የማይወጣው ይህ ምስኪን ህዝብ ሲንገለታ እንደማየት ምን የሚያስተክዝ ነገር ይኖራል። የታክሲ ረዳቱ ስድቡ አቶሚክ ቦንብ የሆነበት ህዝብ፤ በስድ ቃላት እየተሰደበ ዝም በማለት በትዕግስት የሚያሳልፍ ህዝብ፤ ተጋፍቶ የታክሲ ወንበር ማግኘት ስልጣንን የመቆናጠጥ ያህል ፈተና የሆነበት ህዝብ…ጥሮ ግሮ ለመኖር እግሩ እስከሚዝል ለመኪና ሰልፍ ሰዓታትን የሚያባክነው ምስኪን ህዝብ እንዳለ ሁሉ የሱን ሰልፍ እንደ ‹‹ሰለሜ ሰለሜ›› ጨዋታ የሚመለከት ስንት እፍረተ ቢስ አለ?
እንደሚታወቀው የአዲስ አበባ ታክሲ አገልግሎት የከተማዋ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የደም ስር ነው። የአዲስ አበባ ታክሲዎች የማይገቡበት የከተማዋ ጓዳ ጎድጓዳ የለም። የታክሲዎቹ ሾፌሮችና ረዳቶች ከተሳፋሪዎቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት የገንዘብ መልስ አይሰጡም፤ የስነ-ምግባር ችግር አለባቸው፤ መንገድ እነሱ በሚመቻቸው መንገድ ያቆራርጣሉ የሚሉ ወቀሳዎች ሲቀርብባቸው ይስተዋላል። በእርግጥ ይህ በግልጽ የሚታይ ችግር ቢሆንም ሌላ ያልተሰማ በርካታ ጉድም አለ። ለዛሬ ከተራ አስከባሪዎች ጋር ተያይዞ ያልተሰማ አንድ ምስጢር ለመተንፈስ ወደድኩ።
ሰሞኑን በስድስት ኪሎ በኩል ሳልፍ፤ ስድስት ኪሎ የመገናኛ ታክሲ መያዣን ይዞ ጋዝ ማደያውን ታኮ አንበሳ ጊቢ ጋር የሚደርስ የወንዝ ጅረት የመሰለ ሰልፍ ተመለከትኩ። የፊልም ሰልፍ አለመሆኑን በአካባቢው ምንም ሲኒማ ቤት አለመኖሩን ከእማኞች ካረጋገጥኩ በኋላ ነው። ታክሲዎች አልፈው አልፈው ይመጣሉ ከተፈቀደው ጭነት በላይም ትርፍ ሰው ይዘው ይሄዳሉ። አካባቢው ላይ ከሚርመሰመሰው ሰው ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተራ አስከባሪዎች አሉ። እንዳሻቸው ብር ይቀበላሉ፤ ከረዳቶች ጋርም ይጨቃጨቃሉ። ይህ ትኩረትን የሳበው ጉዳይ ነበር ቀጥሎ ያለውን ዳሰሳ እንድጽፈው የገፋፋኝ።
እውነት አላችኋለሁ በዛሬዋ ሸገር መኪና ከቅንጦትነት ወጥቶ መሠረታዊ ቁስ ሆኗል። ኬክ ሳይሆን ዳቦ ሆኗል። በከተሜነት የመዝለቅ ሕልውና የሚወሰነው ተሽከርካሪን ይዞ በመገኘት ሆኗል። መኪና የገዛ ትዳሩ ይሰምርለታል። በታክሲ ምክንያት ትዳር እየተናጋ ነው። ባል ያመሻል፤ ሚስት ታመሻለች። ንፋስ ይገባል፤ ትዳር ይፈርሳል።
መቼም የአዲስ አበባ ታክሲ ነገር ሲነሳ ከሁሉ አስቀድሞ ስሙ አብሮ የሚነሳ ዋና ተዋናይ ቢኖር የታክሲ ተራ አስከባሪው ነው። ታክሲይቱን አይሾፍራትም እንጂ በዚያች ጠባብ የብረት ሳጥን ውስጥ በሚከናወኑ አብዛኞቹ ነገሮች ላይ ተዘዋዋሪ ተሳታፊ በመሆን ያስተዳድራታል ቢባል ፈጽሞ ማጋነን አይሆንም።
ዛሬ ላይ ከአንድ እንጀራ የማያልፍ ሆድ ብዙ እያሳየን ነው። የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ምስጢራዊ ዘረፋ፡- የሥራው ጥንስስ ሥራ አጥ ወጣቶች በሚል ሰብበ የተጀመረ ሲሆን፤ የትራንስፖርት ስምሪት ችግርን ለመፍታት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽሕፈት ቤት የሥራ ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ውስጥ እንዲደራጁ ተደረገ። በየወረዳው በመደራጀት የታክሲ ተራ አስከባሪ በሚል ስያሜም በተደራጁባቸው አካባቢዎች ወደ ሥራ ገብተዋል። ህጋዊ እውቅናም ተሰጥቷቸዋል። ሥራውንም በፈረቃ እንዲሰሩ አቅጣጫ ተቀምጦላቸዋል። በአንድ ቀጣና ላይ የተደራጁት ቁጥራቸው ከአስር በላይ ስለሚሆን በወር አንድ ሰው እስከ ሶስትና አራት ተራ ሊደርሰው ይችላል።
የስራውን አዋጭነት የተረዱት ‹‹አውራዎቹ›› ተራ አስከባሪዎች በሥራቸው ሌሎችን ቀጥረው ማሰራት ጀመሩ። (ያለ መንግስት እውቅና) እነዚህ ተቀጣሪ ተራ አስከባሪዎች እንደየቦታው በቀን ከ2ሺ 500 ብር ጀምሮ እስከ 5ሺ ብር ድረስ ለቀጣሪ ተራ አስከባሪዎች ያስገባሉ። ለራሳቸው ደግሞ ከ500 ብር ጀምሮ ወደ ኪሳቸው ያስገባሉ። ቀጣሪዎቹ ያለምንም እንግልትና ድካም እንደ ጡረታ ብር ቁጭ ብለው መቀበል ነው ሥራቸው። ሥራ በሚበዛበት ቦታ በወር እስከ 30ሺ ብር ድረስም ገቢ ይደረግላቸዋል። ሥራው እንዴት ይከናወን ምን ችግር ተፈጠረ፣ እንዴት ገንዘብ ተሰበሰበ ወዘተ. የሚሉ ጉዳዮች እነርሱን አይመለከትም። ብቻ ትኩረታቸው የቀን ገቢያቸውን ቀጥረው ከሚያሰሯቸው ተራ አስከባሪዎች በመረከብ ኪሳቸውን ማጥገብ ነው።
እንግዲህ ልብ ሊባል የሚገባው እዚህ ላይ ነው። እነዚህ ሳይሰሩ የሚበሉ አካላት ሌላ ሥራ እያላቸውና ያለ አግባብ ብር ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ሥራ አጥ ለሆኑ ወጣቶች ቦታውን መልቀቅ አለመቻላቸውም ነው።
ማንነቱ እንዳይገለጽ ስለ ጉዳዩ ያብራራልኝ አንድ የታክሲ ረዳት ስድስት ኪሎ አካባቢ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ 22 የሚሆኑ ወጣቶች አሉ። እያንዳንዳቸው በሥራቸው እስከ 5 ሰው ድረስ ቀጥረው ያሰራሉ። ‹‹ተግባሩን ህገ ወጥ ያሰኛውም ሰርተህ ብላ የተባለው ቁጭ ብሎ መብላቱ ነው። ››
እንግዲህ ይህ ተግባር ፍጹም ከሥርዓት የራቀና ከሌብነት የማይተናነስ ነው። የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ማረፊያው ተሳፋሪ ላይ ነው ማለት ይቻላል። አውራውና ሳይሰራ የሚበላው ተራ አስከባሪ የቀጠረውን ሰው ጉሮሮ አንቆ ብር ይቀበለዋል። ተቀጣሪው ተራ አስከባሪ ባለ ታክሲዎችን አስጨንቀው ዋጋ በመጨመር ከፍተኛ ብር ይቀበሏቸዋል። ባለ ታክሲው ደግሞ የፈረደበት ህዝብ ላይ እጥፍ በመጨመር ያለ ኃጢአቱ ህዝቡን ያማርራል።
የታክሲ ስምሪትን የሚቆጣጠሩ ህጋዊ የመንግስት ሠራተኞችም ቢሆኑ ይህ ተግባር መኖሩን በሚገባ ያውቃሉ ነገር ግን እነርሱም የተግባሩ ተሳታፊ በመሆን የድርሻቸውን ይወስዳሉ። የተደረሰባቸው ቅጣት ሲጣልባቸው በርካቶች ግን ህገ ወጡን ሰንሰለት በመጋራት በዚህ ተግባር ውስጥ ስለመሳተፋቸው አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም። እነርሱም በነጻ ከሚሰበሰበው ገንዘብ የድርሻ አላቸው። ጉዳዩን በምስጢር ይዞ በማቆየት፣ ታክሲዎች ያለ ስምሪት ቦታቸው እንዲሄዱ በመፍቀድ ወዘተ. ህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ በርካቶች ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች በቀን ከእያንዳንዱ ታክሲ 50 ብር ድረስ ይሰበሰብላቸዋል። ታዲያ በአንድ ቀን ብቻ የአንድ የመንግስት ልማት ድርጅት የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀጣሪን ወርሀዊ ደመወዝ መዝጋት ይችላሉ። በዓመቱ መጨረሻ ላይም ባለሀብት ሆነው የራሳቸውን መኪና ማሽከርከር ይችላሉ ማለት ነው።
እንዲያው ነገሬን ለማዋዛት ያህል አንድ ቁምነገር ላንሳ፤ ‹‹ከለማኝና ከቀማኛ የቱ ይሻላል?›› ተብላችሁ ብትጠየቁ መልሳችሁ ምን ይሆናል? ነገሩ ከሁለት መጥፎ ነገሮች የተሻለ መጥፎ መምረጥ ነው። (የተሻለ መጥፎ ስንል ጉዳቱ ያልከፋ እንደማለት ነው።) ስገምት፥ ብዙዎቻችሁ ለማኝ የምትመርጡ ይመስለኛል፤ ግን ለማኝ ከቀማኛ በምን ይሻላል? ሁለቱም የሰው ገንዘብ ፈላጊዎች አይደሉም? ተራ አስከባሪው በቅፅበት እየመጡ ከሚመለሱት ታክሲዎች የራሱን ቀረጥ ይሰበስባል፣ ለማኙ ከሚዘረጉ በርካታ እጆች ሳንቲም ይለቃቅማል። ምስኪኑ ማስቲካና ቺብስ አዟሪ ግን ከስንት አንዴ ማስቲካ ገዢ ያገኛል።
ሦስቱንም አሰብኳቸው። ተራ አስከባሪው ለኔ ቀማኛ ነው። ግልፅ ያልሆነ ሥራ ሰርቶ ገንዘብ የሚያጋብስ (ንገረኝ ካላችሁ ሥራቸው ገንዘብ መቀበል ነው፤ ልብ ካላችሁ እኮ ተራ አስከባሪዎች ብዙ ጊዜ የሚያስከብሩት ተራ የለም) ለዚህ ነው ተራ አስከባሪዎች ጉልበተኛ መሆን የሚኖርባቸው – አፈንጋጭ ባለታክሲ ሲመጣ ለመደቆስ።
ይህንን በምሳሌ አነሳሁኝ እንጂ ሃገራችን በየመስኩ በቀማኞችና በለማኞች መወረሯን ዓይናችን ይመሰክራል። በየሄድንበት ትርጉሙ የማይታወቅ ‹‹የኮቴ›› የሚባል ነገር እንከፍላለን። በተለይ ቤት ለመቀየር ወይም አዳዲስ የቤት እቃዎችን ስንገዛ ከእቃው በላይ የአውራጆቹ የማውረጃ ጥያቄ ከወዲሁ የሚታሰበን ፈተና ነው። ከፊት ለፊታችን የሚዘረጉ እጆችን ለማለፍም ቢሆን ጀባ እንላለን። በሥራ የሻከሩ እጆችን ግን እንጠየፋለን። በየት በኩል….?
አዲስ አበባ ያለምንም ሥራ በወር እስከ 30ሺ ብር የሚበዘብዟት የታክሲ ተራ አስከባሪዎች እንዳሉ መናገር ለአንባቢው ሰበር ዜና ቀርቦ ለሚያውቃቸው ግን ቋንጣ ወሬ ነው። በስራው ተቀጥረው የሚሰሩት ተራ አስከባሪዎች በአንድ መስመር ለሚጓዝ እንደ ርቀቱና የባለታክሲው የጥቅሙ መጠን እስከ 60 ብር ይቀበላሉ። ፍትሐዊ ከፍያው ግን ርቀቱ ቢለያይም ከ10 ብር በላይ ሊከፍሉ እንደማይገባ ነው የሚነገረው።
እንዲህ ባለው እጅግ ኋላቀር አስተሳሰብ ውስጥ እየኖርን የኢኮኖሚ እድገት ከማምጣት ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል። ተግባራቸው በውስብስቡ ድህረ-ዘመናዊ ዘመን እየኖርን በቅድመ-የድንጋይ ዘመን ነጠላ የኑሮ ዘይቤ የመኖር ያህል ነው። በአንዲት ከተማ ህይወት ውስጥ ከሚያስፈልጉ በሳል ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ህግ ነው። ህግና ቅጣት የህዝብን የአኗኗር ዘይቤ ከብልሃት ጋር አጣጥሞ ለማስኬድ ይጠቅማልና እነዚህ ህገ ወጦች እርምት ሊወሰድባቸው ይገባል።
ታክሲ የሚባለው ‹‹የቀን ጅብ›› ባይኖርና ግዙፍ መኪኖች አገልግሎታቸው ቢበዛ መች ይህ ሁሉ ይሆን ነበር፤ የመከላከያ ቢሾፍቱ አውቶቡሶች የከተማ አውቶቡሶችን ቀለም ተለቅልቀው በገፍ ወደ ሥራ ቢገቡም ወር ሠርተው ወገቤን ይላሉ። ተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋዎችን በማድረስም ተወዳዳሪ አልተገኘላቸውም። ተረግመዋል መሰለኝ ቶሎ ያረጃሉ። ከሆላንድ የሚመጣው ዳፍ አውቶቡስ ደርግን አገልግሎ ኢህአዴግን አስቀጥሏል። የሥርዓቶቹ መመሳሰል እንዳለ ሆኖ ዘመን ተሻጋሪነቱ ግን የሚደነቅ ነው። ትናንትና የተመረቱት ቢሾፍቱ ባሶች ግን ሥርዓት ቀርቶ የአድዋ ድልድይን መሻገር ተስኗቸዋል። ለዚህ ነው ራሳችንን ለታክሲ አጋልጠን በመስጠት ይህን ሁሉ ጉድ የምናስተናግደው።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2012
አዲሱ ገረመው