ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ወደ ጀርመን ኤምባሲ በምታወርደው ጠባብ አስፋልት መንገድ ላይ በተለይ በሆስፒታሉ አጥር አካባቢ አንድ ለዓይን የሚማርክ፤ ቀልብንም የሚገዛ ነገር ያያሉ፡፡ ስፍራው አረንጓዴ ከመሆኑም በላይ በቦታው ላይ ወጣቱም አዛውንቱም አረፍ ብሎ መጽሐፍ ሲያነብ ይመለከታሉ፡፡ አብዛኞቹ ችግኞች አገር በቀል ናቸው፡፡ ሙዝ፣ ኮሶ፣ ጽድ፣ ኮባ፣ ጤናአዳም፣ ዳማከሴና ሌሎችም የአበባ ዛፎች አሉ፡፡ ወድቀው ቆሻሻ የሚሆኑ ሃይላንዶችም በየግድግዳው ተሰቅለው የአበባ መትከያ ሆነዋል፡፡ የአጥር ግድግዳውም፣ በኢትዮጵያ መሪዎች፣ በፊደልና የዓለም ካርታ ጭምር ታግዞ በራሱ የውበት ብቻ ሳይሆን ልብ ብሎ ላያቸውና ጠይቆ መረዳት ለሚሻ የታሪክ መዝገብ ሆኖ ቀርቧል፡፡
ለተማሪዎችም፤ ለወጣቶችም፤ ለሌላውም ጠቃሚ የሚሆኑ የትምህርት፣ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የጠቅላላ እውቀትና ልቦለዶች ስብስብ መጽሐፍትም የዚሁ አንድ አካል ናቸው፡፡ ሆኖም ቦታው ቀደም ሲል አሁን ከሚታየው በተቃራኒው የሚገለጽ የሰው ሳይሆን የቆሻሻ ማረፊያ እንደነበር የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ ታዲያ ይህ እንዴት ሆነ፣ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ስለሚችል በአንድ ወጣት መልካም ፈቃድና ተነሳሽነት፤ በጓደኞቹ አጋዥነት ለዚህ የበቃ ስለመሆኑ ወጣቱም ሆነ ጓደኞቹና የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
ወጣት ኤልያስ አብደላ፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ነዋሪ ሲሆን፤ በሶፋ ስራ ላይ የተሰማራ ሲሆን ይህ ቦታ አሁን ያለውን ገጽታ እንዲይዝ መነሻ ነው። ስለሁኔታው ሲያስረዳ እንደሚገልጸውም፤ የቦታውን ገጽታ ለመቀየር የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ነው የታቀደው፡፡ የዛኔ ቦታው ሽንት የሚሸናበትና የአብዛኛው ህብረተሰብ ቆሻሻ መድፊያም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከቦታው በሚነሳው ሽታ አማካኝነት ለበሽታ የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ፤ በአካባቢው ከሶስት ያላነሱ ትምህርት ቤት እንደመኖራቸው ወደትምህርት ቤት የሚሄዱ ህጻናት የሚያዩት ስለሚያስጠላቸው እና ለበሽታ ስለሚጋለጡ ይሄን እያዩ ዝም ማለት ተገቢ ስላልሆነ ነበር፡፡ ለራስም ቢሆን በሚሸትና በቆሻሻ አካባቢ ቁጭ ብሎ ከመስራት ይልቅ ስፍራውን አጽድቶ በንጹህ አካባቢ ሆኖ መስራት ያለውን እርካታ ከግንዛቤ በማስገባት ስራውን ጀመረ፡፡
የዛኔ ግን አብዛኛው ህብረተሰብ ቦታው ይለወጣል ብሎ ስላላሰበ ስራውን ሲጀምር ነገ ለምትተውት ምን አለፋችሁ ይሏቸው ነበር፡፡ አሁን ላይ ስፍራው ንጹህ በመሆኑና ጥላም ስላለው ሰዎች አረፍ ብለው ድካማቸውን ሊያሳልፉ፤ ንጹህ አየርም ሊቀበሉ ይችላሉ፡፡ ሁለተኛም አረፍ ብለው ቁም ነገር የሚያገኙበትን መጽሐፍ መርጠው ማንበብ የሚችሉበት እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ከከተማው ነዋሪ ባለፈ ስፍራው ሆስፒታል አካባቢ እንደመሆኑ የግቢውን አየር ለመቀየር ያሰቡ ህሙማን መጥተው አረፍ ሊሉበት የሚያስችል ነው፡፡ አሁን ያ ሁሉ አልፎ ስፍራው ለዚህ በመብቃቱም ከህብረተሰቡ ከፍ ያለ ክብርን ማግኘት ችሏል፤ እርሱም ቢሆን ይህን ማድረግ በመቻሉ እንደ አንድ ወጣት ብቻ ሳይሆን እንደዜጋ ለአካባቢው ገጽታ መቀየር የድርሻውን እንደተወጣ እየተሰማው ነው፡፡
ወጣት ኤልያስ፣ በአካባቢ ጽዳትና መጽሐፍትን በነጻ በማስነበብ ስራ ብቻ አልተወሰንም፡፡ ይልቁንም በዛው ስፍራ ሆኖ የተቀደደ የተማሪዎችን ዩኒፎርም በነጻ ይሰፋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ሲናገርም፤ በዚህ ዓመት መንግስት የመማሪያ ቁሳቁስና ዩኒፎርም ለተማሪዎች በነጻ ሰጥቷል። መንግስት ይሄን ማድረግ ከቻለ እኛ ደግሞ እነዚህ ተማሪዎች ዩኒፎርሙ ሲቀደድባቸው በነጻ ብንሰፋላቸው ችግር የለውም በማለት የተቀደደ የተማሪዎች ዩኒፎርምን በነጻ እየሰፋን እንገኛለን፡፡
ይህ ደግሞ ምንም እንኳን ወጪ ቢጠይቅም ለሶፋ ጨርቅ ስፌት ብዬ ከምገዛው የመስፊያ ቁሳቁስ ቀንሼ የማደርገው እንደመሆኑ በተግባሬ ደስተኛ ነኝ፡፡ መጽሐፎቹንም ቢሆን አንዳንድ ጓደኞቼ የተወሰነውን የሰጡኝ ሲሆን፤ አብዛኛውን ራሴ እየገዛሁ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በትውልዱ አዕምሮ ላይ አንድ ጠብታ የምታክል የእውቀትና አስተሳሰብ መለወጥን ለመፍጠር ያግዛል በሚል መነሻ ሲሆን፤ ሰው ደግሞ ካነበበ ያውቃል፤ ይለወጣልም፡፡ የሰው አእምሮና አስተሳሰብ በመልካም ነገር ሲሞላ ደግሞ ከራስ አልፎ አካባቢንና አገርን የመለወጥ አቅም አለው፡፡
የኤልያስ ጓደኞች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና ተማሪዎችም ይሄን ሀሳቡን ይጋራሉ፡፡ ማትያስ ከበደ፣ የአካባቢው ነዋሪና የኤልያስ ጓደኛ ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው፤ ኤልያስ ስራውን ሲጀምር የዛሬ ስድስት ዓመት አንድ ዛፍ በመትከል ነው፡፡ እኔም በወቅቱ ቦታው በዚህ ልክ ይለወጣል የሚል ሀሳብ ስላልነበረኝ እንደማንኛውም ሰው ስራው ከልፋት የዘለለ ውጤት ያመጣል የሚል እሳቤ አልነበረኝም፡፡ ሆኖም ሳይሰለች ሰርቶ አካባቢውን መለወጥ ሲጀምር ላግዘው እንደሚገባ ተሰማኝ፡፡ እናም አትክልቶቹን ውሃ በማጠጣት፣ በመኮትኮትና በማረም እናግዘው ጀምር፡፡
አሁን ስፍራውም ከቆሻሻ መጣያነት ወደ ማረፊያነትና ማንበቢያነት ተለወጠ፡፡ እኛም ለንባብ የሚሆኑ መጽሐፍቶችን ጭምር ባገኘነው አጋጣሚ በማምጣት እየሰጠነው የመጽሐፍቱን ቁጥር እያሳደግን ነው፡፡ መሰል ማረፊያ ስፍራዎች ባለመኖራቸው ብዙ ወጣቶች ባልባሌ ቦታ እየዋሉ አዕምሯቸው ስራ ስላቆመ፤ ይህ ቦታ ከማረፊያነት ባለፈ የንባብ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉ ማንበብ አዕምሮ ስራ እንዲጀምር ስለሚያደርግ ሰውም በተለይ ተማሪዎች በስፍራው አረፍ ሲሉም እንዲያነቡ እያበረታታን መሄድ ጀመርን፡፡
ሂደቱም በትንሽ ቦታ ይሄን ያክል ለውጥ ማምጣት ከተቻለ፤ የተሻለ ድጋፍና ስፍራ ቢኖር የበለጠ መስራትና አካባቢን ማጽዳት እንደሚቻል ያሳየ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ወጣቱ ጊዜውን በአልባሌ ቦታ ከሚያሳልፍ ይህንን በመሳሰሉ አረንጓዴ ስፍራዎች አረፍ እያለ የንባብ ባህሉን እንዲያጎለብት ማድረግ እንደሚቻል ያሳየ ነው፡፡ እናም በትንሽ ምንጭ ውሃ ታግዞ ይሄን መሰል አረንጓዴ አካባቢ መፍጠር ከተቻለ፤ ቀበናን የመሰለ ወንዝ ይዞ ቆሻሻ ከማሽተት ይልቅ ለልማት ማዋል ቢቻል ምን ያክል መለወጥ እንደሚቻል ያሳያል፡፡ ምክንያቱም ወጣቱ በቀናነትና በትጋት መሰል ተግባር ቢከውን፤ ህብረተሰቡና መንግስትም ቢደግፍ አዲስ አበባን ቀርቶ ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ መለወጥ ይቻላል፡፡
‹‹ኤልያስ ስራውን ሲጀምር ከላይ እየተሸናበት እርሱ ሲያጸዳ ሳሾፍበት ነበር፤›› የሚለው ደግሞ የኤልያስ የልጅነት ጓደኛ ሱዑድ ዑስማን ነው፡፡ ሱዑድ እንደሚለው፤ በዚህ ተግባሩ እልህ የተጋባው ኤልያስም ‹‹ሰርቼ መጀመሪያ አንተን መለወጥ ካልቻልኩ ሌላውን መለወጥ አልችልም›› በማለት ተግቶ በመስራት ለውጤት አብቅቶ ከማሳመንም በላይ የስራው አጋዥ እንድሆን ስላደረገኝ ለዚህ ተግባሩ ደግሞ ላመሰግነው እወዳለሁ ይላል፡፡ እኔ የልጅነቴን ጊዜ ሳስታውስ እንዲህ አይነት ቦታ ስለማላውቅና በቆሻሻ ስፍራ ስጫወት በማደጌ ተጎድቻለሁ፤ እናም ለልጆቼና ለዚህ ዘመን ትውልድ ምን ልንሰጣቸውና ትተንላቸው ልናልፍ ነው ብሎ ማሰብ የግድ ሊሆን እንደሚገባ ይናገራል፡፡
እንደ ሱዑድ ገለጻ፤ ኤልያስ ይሄን ሰርቶ ሲያይ ለካ ማድረግ እንችላለን፤ ከቆሻሻ የጸዳ አካባቢን ፈጥሮ ለልጆች ማስተላለፍ እንችላለን የሚል ስሜት አድሮበታል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ልጆች ነገ አገር የሚገነቡ እንደመሆናቸው አዕምሯቸውም፣ ጤናቸውም በመልካም ነገር ሊታነጽ፤ በጽዱ አካባቢ ተጫውተው ማደግ ይኖርባቸዋል፡፡ እናም ኤልያስ ካከናወነው ተግባር አንጻር እነርሱ እድለኞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በኤልያስ ፈር ቀዳጅነት በተፈጠረው አረንጓዴ ስፍራ እነሱም ታዳጊ ልጆችም አብረው እየተጫወቱ፤ ከለምለሙ ስፍራ አረፍ ብለውም እያነበቡ ነው፡፡
‹‹እኔ ያላየሁትን የእኔ ልጆች ሲያዩ፤ አፍንጫዬን ይዤ አልፍበት ከነበረው ስፍራ አበባ እየበጠሱና እየተሳሳቁ ሲያልፉ ማየት ያስደስታል፤›› የሚለው ሱዑድ፤ “መንግስት ብቻውን ምንም ሊለውጥልን አይችልም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም ቢሆኑ ብቻቸውን ሳይሆን ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው ነው አገርን መለወጥ የሚችሉት፤ እናም በኤልያስ ፈር ቀዳጅነት ይህ ቦታ ሲጸዳ እንደ ከተማ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ለሚሰራው አካባቢንና ከተማን የማጽዳት ተግባር ኃላፊነትን የመወጣት፤ በአረንጓዴ ልማቱም አሻራን ማኖር ይገባል” ሲልም ይገልጻል፡፡ በስፍራው መጽሐፍ ማንበብ እንዲጀመር መደረጉም ወጣቱን ከአልባሌ ቦታ በመታደግና አዕምሮውን ከመለወጥ አንጻር እንደ ዜጋ የድርሻችንን ለመወጣት በማሰብ እንደመሆኑ፤ ይህም ንጹህ፣ የበለጸገችና ገናና ኢትዮጵያን መልሶ መገንባት፤ የሚተሳሰቡ፣ በአንድ ተሰባስበው መምከርና መነጋገር የሚችሉ፣ አንባቢና ምክንያታዊ ትውልድን የመፍጠር አንድ አካል ስለመሆኑም ይናገራል፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ተማሪ የሆነችው ጽናት ግርማ እንደምትለው ደግሞ፤ በመንገዱ ቢያንስ በቀን ሁለቴ የመመላለስ አጋጣሚ አላት፡፡ ቦታው ያለው ለውጥ ቀድሞ ከነበረው ጋር የሚነጻጸር አይደለም፡፡ ቀድሞ በጣሙን የሚያስጠላ ሽታ ስለነበረው ለአካባቢው መቆሸሽ ብቻ ሳይሆን ለጤና ጭምር ጎጂ ነበር፡፡ አሁን ግን በመጽዳቱና በእጽዋት በመሸፈኑ ለእይታ የሚያምር፤ ለጤናም ተስማሚ በመሆኑ የደከመው ሰው አረፍ የሚልበትን እድል ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ባለፈ በስፍራው የማንበቢያ ቦታና የንባብ መጽሐፍት መዘጋጀታቸው አካልን ከማሳረፍ ባለፈ ለአዕምሮም ምግብ ማግኛ አድርጎታል፡፡ በትንሽ ቦታና ባልተመቻቸ ሁኔታ ይሄን ሰርተው ያሳዩ ወንድሞችም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ይሄንን ተግባራቸውም አጠናክረው ሊቀጥሉ፤ የሚመለከተውም እነዚህንና ሌሎች መሰል ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶችን ትኩረት ሰጥቶ ሊደግፍ ይገባል፡፡
ተማሪ ሔዋን እንዳለ እና ተማሪ ናትናኤል ተወልደ፣ የኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች እንደሚሉት፤ የተለያዩ ሰዎች የሚጸዳዱበትና ቆሻሻ መጣያ የነበረ ስፍራ በዚህ መልኩ ተለውጦና አእምሮ ማየት እጅጉን ደስ ይላል፡፡ ይሄን ያደረጉ ወጣቶች ደግሞ ስፍራውን ከማስዋብ ባለፈ የንባብ መጽሐፍ በቦታው አስቀምጠው ንባብን እያለማመዱ ሲሆን፤ በተለያየ ምክንያት በጭንቀት ከቤት ወይም ከሌላ ቦታ በዚህ ስፍራ የሚያልፉ ሰዎች አካባቢው ማርኳቸው አረፍ ከማለትና ንጹህ አየር እየሳቡ መንፈስን ከማደስ ባለፈ መጽሐፍትን በቀላሉ አግኝተው ማንበብ መቻላቸው እንዲረጋጉ ያደርጋቸዋል፡፡ የተቀደደ የተማሪ ዩኒፎርምንም በነጻ በመስፋትም ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ በመሆኑም ተግባሩ የተበላሸ አካባቢን መቀየርና ተበላሽቷል የተባለ ሀብትን መልሶ መጠቀም እንደሚቻል ያስተማረ ነው፡፡ በቀጣይ የተሻለ ለመስራት ደግሞ መጀመሪያ የህብረተሰቡን አመለካከት መለወጥ ላይ መስራት፤ ወጣቱን በመሰል የአርአያነት ተግባር ማሰለፍም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን አዲስ አበባ ቆሻሻ መስላ የምትታይበትን ገጽታ መቀየር፤ አገርንም ማሳደግ ይቻላል፡፡
በአካባቢው ለ45 ዓመታት የኖሩት ሻለቃ ጌታቸው ደረሰ እንደሚሉት ደግሞ፤ አካባቢው ቀደም ሲል ሰንሰል የሞላው የልጆች ኳስ መጫወቻና የአካባቢው ቆሻሻ መጣያ ነበር፡፡ ኤልያስ ደግሞ በአካባቢው ካሉ ሱቆች በአንዷ የሚሰራ ሲሆን፤ ቆሻሻ መጣያ የነበረውን ስፍራ ራሱ አጽድቶ፣ ቆፍሮና አትክልት ተክሎ ነው ከቆሻሻነት ወደ ተዋበ ማረፊያነት የቀየረው፡፡ ኤልያስ ይሄን ለማድረግ በጣሙን ጥሯል፡፡ ምክንያቱም ስፍራው ከቆሻሻ ባለፈ የሞተ ውሻ ሁሉ የሚጣልበት እጅጉን ለጤናም ለዐይንም ምቾት ነስቶ የኖረ ነው፡፡ ኤልያስ ይሄን ለማጽዳት በሚያደርገው ውጣ ውረድ ጥቂት ጓደኞቹ ከማገዛቸው ባለፈ የእርሳቸው ባለቤት ወይዘሮ ዓይናለም አማረ ጊቢያቸውን በአግባቡ ያስውቡና ያጸዱ ስለነበር ውጪውን ሲያጸዳ ሲያዩት አበባ በመስጠት ጭምር ይደግፉትና ያበረታቱት ነበር፡፡
አሁን ላይ ስፍራው ንጹህና አረንጓዴ በመሆኑ ሰዎች ደስ እያላቸው ያርፉበታል፡፡ ለማረፊያነት ሲበቃ ደግሞ ሰው ቁጭ ብሎ ያልተገባ ወሬና ሌላም ነገር ከሚያደርግ በሚል መጽሐፍን በራሱም በጓደኞቹም ድጋፍ በማዘጋጀት ሰው ቁጭ ሲል መጽሐፎቹን በነጻ ወስዶ እንዲያነብ እያደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሰው በተለይም ወጣቱ ንባብን እንዲለማመድ የሚያደርገው፤ ከተለያዩ ሱሶች የሚያርቀውና ከሚያነበውም መጽሐፍ አንዳች ቁምነገር እንዲያገኝ የሚያደርገው ነው፡፡ ተግባሩም የኤልያስን ጥሩ ጸባይ ያለውና ታዛዥ ልጅነት የሚያሳይ፤ ከዚህ ስራው በተጓዳኝ የሚያከናውነው የተቀደደ የተማሪዎች ዩኒፎርም በነጻ የመስፋት ስራም በገንዘብ ቢሰፋ የሚያገኘውን ጥቅም ትቶ የአእምሮ እረፍት ለማግኘት ሲል መከወኑ ለሰው ቀና አሳቢና ሰውን ለመደገፍ ያለውን ደግነት አመላካች ነው፡፡
ለወጣቶች ከፍተኛ አርዓያነት ያለውና ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አጠገቡ ሆነው የሚያግዙት ወጣቶች የመኖራቸውን ያክል፤ ዛሬም በቅርብ ሆነው ከእርሱ መማር ያልቻሉ ጥቂቶች በየመኪና ውስጥ ቁጭ ብለው ሲቅሙና ለሌሎች ሱሶች ሲጋለጡ የሚውሉ አሉ። በመሆኑም በህብረተሰቡም ሆነ በመንግስት አካላት፤ እንደ ኤልያስ እና ጓደኞቹ አይነቶች በትንሽ ቦታና በመልካም መነሳሳት ስሜት አርዓያ ሆነው የሚሰሩትን የሚያበረታታበት፤ በየመኪናውና ሌላም ስፍራ በሱስ ተጠምደው ቁጭ ብለው የሚውሉትን ደግሞ አርሞ ወደ ስራ ገብተው ለራሳቸውም ለአገራቸውም የሚጠቅሙበትን እድል ለመፍጠር መስራት ይገባል፡፡
‹‹አገር የምትለወጠው አንድ ሰው ወይም መሪ ስለለፋ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ በዛው ልክ አውቆ ማገዝ ሲችል ነው፤›› የሚለው ወጣት ኤልያስ በበኩሉ፤ ‹‹እኔም ጓደኞቼን አስተባብሬ ይሄንን ተግባር ሳከናውን የአገር ግንባታና እድገት አንድ አጋዥ አካል ለመሆን ያክል የማከናውነው እንጂ የተለየ ተዓምር የፈጠረ ተግባር አይደለም›› ሲል ሁነቱን ይገልጻል፡፡ ኤልያስ እንደሚለው፤ ሰው ይህ አካባቢ በዚህ መልኩ ተለውጦ ሲያይ ደስተኛ ይሆናል፡፡ ማድረግ ቢችል ከዚህ በላይ እንዲሆንም ይመኛል፡፡ ተማሪዎችም እዚህ ቦታ መጥተው ዩኒፎርማቸውን ሲያሰፉ የእኔነት ስሜት ተሰምቷቸው ነው፡፡ አረፍ በሚሉበት ሰዓትም የሚፈልጉት መጽሐፍ ካለ ከማንበብ ባለፈ ተውሰው ወስደው በመሄድ አንብበው ይመልሳሉ፡፡
እንደ ኤልያስ አባባል፤ ወጣቱ ተምሯል፤ ግን አብዛኛው ስራ ሳይኖረው ቁጭ ብሏል፡፡ ሆኖም ስራ እስኪያገኝ የሁሉም በሆነች ኢትዮጵያ ውስጥ በየአካባቢው ሳይከፈለው ይሄን መሰል መልካም ስራ ማከናወን መልመድ ይኖርበታል፡፡ ሳይከፈለው መስራት የቻለ ወጣት ደግሞ ተከፍሎት መስራት ሲጀምር ሁሉን መስራት የሚችል፤ ለስራ ተነሳሽነቱ ስላለውም በሚሰራውም ውጤት የሚያመጣ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ወጣቱ ይሄን በሚያደርግበት ሂደት ህብረተሰቡም የመንግስት አካልም ሊያግዙትና ሊያበረታቱት ይገባል፡፡
ባለው ሁኔታ ደግሞ በተለይ ከህብረተሰቡና ወጣቱ ጋር በቀጥታ የሚገናኙት ቀበሌና ወረዳ ላይ ያሉ የመንግስት አካላት አብዛኛውን ወጣቱን ከማበረታታ አንጻር ምንም የሉበትም፡፡ እንደውም እንዲህ አይነት መልካም የሆኑ ስራዎች ሲከናወኑ ገና ከጅምሩ ከማበረታታት ይልቅ ‹‹ይሄን የምትሰራው የሆነ ነገር አስበህ ነው፤ ቦታውንም ወደሌላ ነገር ልትቀይር ነው›› በሚል የማስበርገግ አካሄድ ነው ያላቸው፡፡ ነገራቸው ሁሉ አሰልቺና የማይጥም ነው። በመሆኑም የወጣቱን አስተሳሰብ መቀየር፤ ዝቅ ብሎም የወጣቱን ችግር ማየት፤ ከታች ያለውን ችግር ለይቶ የችግሩ ፈጣሪዎችን ማጥራት፤ በወረዳና ቀበሌዎች ያሉ ቆሻሻ አስተሳሰቦችንም ማጽዳት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 1/2012
ወንድወሰን ሽመልስ