• ስምንት የጥበቃ ሰራተኞቼ በተደራጁ ሌቦች ተገደሉብኝ ብሏል
አዲስ አበባ፡-ባለፉት ስድስት ወራት 100 ሚሊዮን ብር በሚያወጡ በ547 የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆትና ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ኢትዮ-ቴሌኮም ገለጸ።ስምንት የጥበቃ ሰራተኞቹ በሌቦች እንደተገደሉም አስታውቋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ “የኢትዮ-ቴሌኮም የመሰረተ ልማት ጉዳትን አስቀድሞ ለመከላከል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የጋራ ኃላፊነት ነው” በሚል በተዘጋጀው ውይይት ላይ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ 20 እና 30 ዓመታት ያገለግላሉ ተብለው የተዘረጉ የቴሌኮም ኬብሎችና ፋይበሮች በመሰረቃቸውና ጉዳት እየደረሰባቸው በመሆኑ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር እየፈጠረ ይገኛል።
ተቋሙ በአዲስ አበባ ከ750 በላይ ለሚሆኑ የጸጥታ ሀይሎችና በመላ አገሪቱ 170 ሺህ ለሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ቢሰራም የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ስርቆትና ጉዳት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም ብለዋል።
በፋይበርና በኮፐር ኬብሎች ላይ እየደረሰ ያለው ስርቆትና ጉዳትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸው 100ሚሊዮን ብር የሚገመት የቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ባይደርስ ኖሮ 25 የሞባይል ጣቢያዎችን በመገንባት ከ58ሺ በላይ ደንበኞችን የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻል ነበር ብለዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም ከ18ሺህ በላይ የጥበቃ ሰራተኞች ቢኖሩትም ስርቆቱንና ጉዳቱን መከላከልና መቆጣጠር አልተቻለም ያሉት ወይዘሪት ፍሬህይወት እንዲያውም “ለጥበቃ የተመደቡት የድርጅቱ ሰራተኞች በተደራጁ ሌቦች ተገድለውብናል “ሲሉ ገልጸዋል።
በአገሪቱ የተዘረጋውን 22ሺህ ኪሎ ሜትር የኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማትን በመጠበቅ ረገድ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ዋና ስራ አስፈጸሚዋ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በፋይበርና በኮፐር ኬብሎች ከደረሱት 547 ጉዳቶች መካካል 296ቱ ስርቆት የተፈጸመባቸው መሆኑን የገለጹት በኢትዮ ቴሌኮም ስልታዊ ዕቅድና አፈጻጸም ሀላፊ አቶ ሰለሞን መኮንን በዚህ ምክንያት በሰባት ሺህ 441 የኔት ወርክ ጣቢያዎች ላይ መቆራረጥ በመፈጠሩ ሳቢያ በኩባንያው ገቢ ፣በአገልግሎት ጥራትና በባንኮችና መሰል ተቋማት አገልግሎት ላይ ችግር መፍጠሩን አብራርተዋል።
ማህበረሰቡ ስለ ቴሌኮም መሰረተ ልማት ጥበቃ አነስተኛ ግንዛቤ ያለው መሆኑ አጥፊዎች አስተማሪ ቅጣት ሳይሰጣቸው መለቀቅ፣ ለመሰረተ ልማቶች ጥበቃ ትኩረት አለመስጠት ለስርቆቱና ለጉዳቱ መጠን እየጨመረ መምጣት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
ባለፉት ስድስት ወራትም ስምንት የድርጅቱ የጥበቃ ሰራተኞች የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን እየጠበቁ ሳለ በተደራጁ ሌቦች መገደላቸውን ገልጸዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የጸጥታና የሚመለከታቸው አካላት አስተያየታቸው እንደሰጡት በሌቦች የሚሰረቁ ኬብሎች መኖራቸውን አውስተው ሆን ተብሎ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የሚቆረጡ ኬብሎች መኖራቸውንም አመልክተዋል። ለአብነትም ፒያሳ ማዘጋጃ ቤት ፊት ለፊት ሌሊት ላይ ዋናው የኢትዮ ቴሌኮም ኬብል ተቆርጦ መገኘቱን አውስተዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም ከ45ሺ በላይ ደንበኞች ያሉት ሲሆን የኢተርኔትና ዳታ ተጠቃሚዎች 22ነጥብ 15 ሚሊዮን፣ የሞባይል 43 ነጥብ 68 ሚሊዮን፣ አንድ ነጥብ 02 ደግሞ የመደበኛ ስልክ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል።
አዲስዘመን ጥር 1/2012