አንዲት ትንሽ ልጅ በእጇ ይዛው የቆየችው አንድ ብር ጠፋባት አሉ። አንድ ብር የወረቀት በነበረበት ጊዜ እንኳን አያስቸግርም ነበር፤ የሳንቲሙ ግን መጥፊያው ብዙ ነው። ታድያ እንባ አውጥታ ስለአንድ ብሯ መጥፋት ስታለቅስ የተመለከተ ሰው ተጠግቶ ምን እንደሆነች ይጠይቃታል። እርሷም አንድ ብሯ መጥፋቱን እንባዋን ሳትገታ ትነግረዋለች።
እናም ይኼ ሰው እጅጉን ያዝንና፤ «በቃ አታልቅሺ…እኔ አንድ ብሩን እሰጥሻለሁ» ብሎ ከኪሱ አውጥቶ አንድ ብር ይሰጣታል። በዚህ ደግ ሰው ልግስና አንድ ብር ስላገኘች የተሰማት ደስታ ከጥቂት ሰከንዶች የዘለለ አልነበረም። ጭራሽ ኀዘንዋ በዝቶ አምርራ ማልቀስ ቀጠለች። ይሄኔ ሰውዬው ግራ ገብቶት፤ «አሁን ምን ሆነሽ ነው? የጠፋብሽን ብር ተካሁልሽ አይደለም እንዴ?» ቢላት፤ «ያኛው ባይጠፋብኝኮ ይሄኔ ሁለት ብር ይሆንልኝ ነበር» አለች አሉ።
ይህን ታሪክ በተለያየ መንገድና ሁኔታ፤ ከተለያየ ሰው ሰምተነው ይሆናል። ምን አዲስ ነገር አለ? ምንም። ታሪክ ሁሌም ይደጋገማል። በዚህ በተለያየ መንገድ በሚነገር የትንሿ ልጅ ታሪክ ውስጥ የምናየው አንድ ትልቅ እውነት ግን አለ፤ ባገኘነው ጥሩ ከመሥራት ይልቅ ስላጣነው ማነሳሳት እንደሚቀናን። ይህን ደግሞ አንዴ ያደረግነው ወይም የምናደርገው ነገር አይደለም፤ ሁሌም የምንደጋግመው ሆኗል።
ሰዎች ሁሌም ጥፋት ያጠፋሉ። አንዱ ከአንዱ የተለየ ሆኖ አይደለም፤ ግን አኳኋኑ ይለያያልና ነግቶ አዲስ ይሆንብናል። አዲስ በመሰለንና በምንደጋግመው የራሳችን ታሪክ ውስጥ ወደኋላ ተመልሰን እናለቅሳለን፤ ወደኋላ ተመልሰን እንጸጸታለን፤ ወደኋላ ተመልሰን እንወቅሳለን፣ ወደኋላ ተመልሰን እንካሰሳለን። አሁን ላይ በአገራችን እየሆነ ያለው ይኸ ነው፤ አካሄዳችን በዚህ ከቀጠለም ታሪክን ደጋሚ መሆናችን አይቀሬ ነው።
ታሪክ የደገምንበትን፤ ዛሬን ይዘን ስላጣነው ትናንት ያለቀስንበትን ዘመን እንመልከት። ለዚህም መስታወት የሚሆኑን ሦስት ክፍላተ ጊዜ አሉ። ይህ ጊዜ ወደኋላ ጥንት ወይም ወደፊት ሩቅ ዘመን የሚያሳይ አይደለም። ይልቁንም ልክ የዛሬ ዓመትን፤ ከዛም የዛሬ ስድስት ወርን እና ዛሬን የሚያስተያይ ነው።
የዛሬ ዓመት ኢትዮጵያና እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ነገራችን ስጋት ላይ ወድቆ በደመነፍስ እንደምንንቀሳቀስ ሆነን ነበር። ከተሞች በስጋት ተከብበው፣ ተኩስ በዝቶ፣ ካሉበት መውጣትም ሆነ መግባት አስጊ ሆኖ «ኧረ አባቶች እግዚኦ በሉ! ኧረ ዱአ ይደረግ! ኧረ የአገር ሽማግሌ ያለህ!» ይባል ነበር። የጠየቀ የለም እንጂ ያኔ «ስምንተኛው ሺህ መቼ ነው?» ተብሎ ቢጠየቅ፤ ዛሬ ማታ የሚለው ሳይበዛ አይቀርም።
አለፈ፤ ከስድስት ወር በፊት፤ አዲስ ተስፋን የያዘ ብሩኅ ሰው ለአገሩ ብቅ አለ። በምናውቀውም በማናውቀውም ሽኩቻ መካከል አልፎ ፋናውን ከፍ አድርጎ አሳየ። በፍቅር አንተ፤ በክብር አንቱ እየተባለ የሚጠራ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሾም፤ አዲስ እይታና ተስፋ የአንድነትም ወሬ በአገሩ ተሰማ። የሸሹ መለስ ብለው አዩ፣ የራቁ ተመለሱ፣ ተስፋ የቆረጡ አንገታቸው ቀና አለ፣ መጠራጠር ለመንገሥ ደጅ ቢጠናም ከፍ ሊል ግን አልቻለም።
ውጭ ሆነው «አገሬን አገሬን» ይሉ የነበሩ፤ «እንካችሁ» ተብሎ ተሰጣቸው። ጥሪው ለሁሉም ነበር፤ «እንካችሁ አገራችሁን ሥሯት» ከያኒው፣ ጥበበኛው፣ ተፎካካሪና ተቃዋሚው፣ ሴቷ፣ አርሶ አደሩ፣ መምህሩ፣ ተመራማሪው፣ ጋዜጠኛው…ሁሉም፤ ሁላችንም «እነሆ ሜዳውም ፈረሱም» ተሰጠን። «ሆ…!» ብለን ተመምን፤ ቃል ገባን፤ ማልን ተገዘትን።
ዛሬ። ባለፈው ሳምንት ውስጥ አንድ ዜና በስፋት ሲደመጥ ነበር። የዜናው ርዕስ እንዲህ ይላል፤ «ከ3 ሚሊዮን ዲያስፖራ በቀን አንድ ዶላር እንዲያዋጣ በዶክተር አብይ ከተጠየቀው ውስጥ እስካሁን ያዋጣው የተጠበቀውን ያህል አይደለም» ከዚህ ዜና እልፍ እንበል፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብጥብጦች የየእለት ወሬ ሆኑ። ጠፍቶብን የኖረው ፍትህ ደጃችን ሲደርስ ላገኘነው ደስታ ረጅም ዕድሜ አልተሰጠውም፤ ድጋሚ ወደኋላ።
በክርስትና እምነት በቅዱሱ መጽሐፍ ላይ አንድ ደጋግሜ የማስበው ታሪክ አለ። ክርስቶስ በምድር በተመላለሰበትና ያስተምር በነበረበት ዘመን፤ የሚከተሉት ሰዎች እልፍ ነበሩ። መጻሕፍትም የአምስት ገበያ ሕዝብ ይከተለው እንደነበር ይነግረናል። ታድያ በመጨረሻ የእውነት ተከታዮቹ ሆነው የቀሩት አንድ መቶ ሃያ ሰዎች ብቻ ነበሩ።
የራቁበትና የተበተኑበት፤ እስከመጨረሻውም አብረውት ያልተገኙት፤ ምርጥ ከተባሉት መካከል ያልተካተቱት ብዙዎቹ፤ እርሱን ይከተሉበት የነበረው ምክንያት ለየቅል በመሆኑ ነው። ማን ያውቃል! ግርግሩ ተመችቶት የተከተለ ይኖራል፤ የክርስቶስን መልኩን ሊያይ የወጣም አይጠፋም። አሁንም ታድያ እኛም አገር እየሆነ ያለው ይኸ ነው፤ ኢትዮጵያን ብሎ የወጣ አለ፤ ግርግሩን አይቶ የሚከተልም ደግሞ አለ።
እንደዛ ባይሆን ኖሮ፤ ከሦስት ሚሊዮን ሕዝብ መካከል እንዴት አንድ ሚሊዮኑ እንኳ ቃሉን አያከብርም። በእርግጥ ሃሳብና ቃል መወርወር፤ ቤት መሥሪያ የሚሆን ጠጠር ከማቀበል ጋር ሲነጻጸር በጣም ቀላል ነው። በየቀኑ አንዲት ጠጠር ከመወርወር፤ ሃሳብና ቁጣን እያካፈሉ መኖር አይከብድም። ቢሆንም ግን እንዴት ከዛ ሁሉ ሰው መካከል ይህን ያህል ትንሽ ሰው ብቻ ለአገሩ ይተርፋል?
በየከተማውና ክፍላተ አገሩ «ሆ!» ብሎ የወጣውስ ያ ሁሉ ሰው የት አለ? «ሜዳውን ተቀማሁ፤ ፈረሴም ታስሯል!» ይል የነበረው፤ አሁን ሜዳውም ፈረሱም ሲሰጠው እግሩን ያሰረው ምንድን ነው? ኧረ ሜዳውና ፈረሱን ተቀብሎ ጦር የመዘዘውስ ምን ማለቱ ነው? ያጎረሰን እጅ መንከስ? በደጋጎች አገር ተንኮለኛና ሸረኛ ሆኖ መገኘት ምን ይሉት ነገር ነው?
ከዛም አለፍ በሉ፤ ሜዳውን አጥሮ፤ ፈረሱን አስሮ የቆየው «አካል» ተቀማሁ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል። የፈረሱ መፈታት፤ የሜዳው ነጻ መሆን ሕመም ሆኖበታል። ሰው እንዴት በገዛ አገሩ ላይ ሆኖ አገሩን ይረሳል? የጠላት ገንዘብ ይመስል እንዴት አገሩን ያደማል? በእርግጥ በትዕቢት የታወረና እንደ ፈርዖን የደነደነ ልብ መጥፊያውን እስኪያገኝ ድረስ አያርፍም። እስከዛ ግን ነገሩ ያሳዝናል፤ ልብንም ይሰብራል።
የእኛ የሜዳውና የፈረሱ እውነት ይህ ነው። ስናገኘው እንዴት መጋለብ እንዳለብን አናውቅም፤ ፈረሱ ሳይሆን እኛው ራሳችን መገራት እንደሚቀረን እናሳብቃለን። ለዚህም ይመስላል በአገራችን ከሚነገሩ ታሪኮቿና ከልጆቿ ገድላት ጋር ብዙ ጊዜ ተያይዞ ቀጣዩ መንታ ስንኝ ይጠቀሳል፤
«ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ»
በአገራችን ብዙውን ጊዜ አትራፊው ገዳይ ነው። ኢትዮጵያም ከሠራላት ይልቅ ለሠራባት የቆመች ትመስላለች። ይኸ ደግሞ የሕዝብ ጉዳይ ነው። ሜዳውንና ፈረሱን እንዴት መጠቀም እንዳለበት ካለማወቁ የተነሳ፤ ራሱ መጋለቡን ትቶ ነጻ ፈቃዱን አሳልፎ ይሰጣል። «እነርሱ…እኛ» ብለው ረቂቅ ከሆነ የሰው ልጅነት ወደ አንድ ብሔር ተወላጅነት የጠበቡ ሰዎች ልጓሙን ይዘው እንዲመሩት ይፈቅዳል። በዛ ውስጥ እነርሱ እንዲያዩ የፈለጉትን ያሳዩታል፤ እንዲሄድ ወደፈለጉት ይመሩታል።
በጠፋበት ነገር ማዘኑን አስተውለውና ቀርበው አጽናንተው የጠፋበትን ሲሰጡት፤ ከአሁን ጀምሮ ማድረግ ስለሚችለው ሳይሆን ያለፈው ባያልፍ ኖሮ የሚሆነውን በማሰብ ጊዜውን ይጨርሳል። ሜዳውን ነጻ አድርጎለት ፈረሱንም ካስረከበው ይልቅ አጥሮበት የቆየውን ያነሳሳል። እርሱ ማድረግ ስላልቻለው ሁሉ ተጠያቂ ያዘጋጃል። «ሜዳውን ሲሰጠኝ ሜዳውን ሳር አንጥፎበት ቢሆን ምን ነበረ? ፈረሱን ሲሰጠኝ አልምዶና ገርቶ ቢሆን አይሻልም?» ያለቅሳል፤ እናለቅሳለን።
አሁንም ጊዜው አልረፈደም። በየዘመናቱ ለኢትዮጵያ እጅግ በጎውን በማሰብና ኃያል ሊያደርጓት በመፈለግ ብዙ ነገሥታት ዛሬም ድረስ ስማቸው ይነሳል። ግን ስንቶቹ ተሳክቶላቸዋል? እቅዳቸውን ያከሸፉት እንግሊዝና ጣልያን ወይም ፈረንሳይ ናቸው? አልነበሩም። ነገሥታቱ የእኔ ያሏቸውና አገልጋይ ሊሆኑለት የወደዱት የራሳቸው ሕዝብ ነበር እንቅፋት የሚሆናቸው። ሜዳውንና ፈረሱን እንዴት መጠቀም እንዳለበት ያልተረዳ ሁሉ ከሃሳባቸው አስቀርቷቸዋል።
አሁን፤ ሜዳውም ፈረሱም ሲሰጠን የታየው ማንነታችን፤ ለራሳችንም የተገለጠልን እውነት ያሳዝናል፤ ያሳፍራል። በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የምንገኝ እኛ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን አሁን ከእጃችን ያለውን ዕድል ብናጣ፤ በቀደመው ዘመን ከነበሩት ይልቅ በእኛ አስቀያሚ ይሆናል። ክፉ አሳቢና አድራጊ ይጠፋል ማለት አይደለም፤ግን ቢያንስ አሁንም በነጻ ሜዳችን ላይ ስንሆን ልበ ደንዳኖችን ከመተባበር ብንቆጠብ ለእኛ መልካም ይሆናል።
ኢትዮጵያ እንደሆነ በዘመናት መካከል ተሻግራለች፤ ትሻገራለችም። ከውስጥ ጥቃቅን ነፍሳት ፈትነው አልጣሏትም። ከውጭም የሚነፍስ አውሎ ነፋስና የሚያጓራ መብረቅ አላፈረሳትም። አምስት ገበያ ሕዝብ ቢከተላትና እስከመጨረሻው አብረዋት መቶ ሰዎች ቢቀሩ እንኳ እርሷ ትኖራለች። የኢትዮጵያ መኖር ክብሩ ለእኛ እንጂ ሌላ ለማንም አይደለም። ይህ ሰላም!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2011
ሊድያ ተስፋዬ