ከአዲስ አበባ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የደምቢ ደሎ አጠቃላይ ሆስፒታል የተመሰረተው በ1911 ዓ.ም ነው። በዞኑም ብቸኛው ሆስፒታል እንደመሆኑ እንደ ሪፈራል ሆስፒታልም እያገለገለ ይገኛል። ሆስፒታሉ በየቀኑ 400 ያህል ሰዎች የሚያስተናግድ ሲሆን፣ ከጋምቤላም አካባቢ ጭምር አገልግሎት ፍለጋ ወደ ሆስፒታሉ የሚሄዱም ጥቂት አይደሉም። በዚህ የተነሳም ከፍተኛ ጫና አለበት። ሆስፒታሉ በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም ዋና ችግር ሆኖ የፈተነው ግን የውሃ እጥረት ነው።
በሆስፒታሉ ተገኝተን አገልግሎት ፈላጊዎችን ባነጋገርንበት ወቅት የሶስት ልጆች አባት የሆኑት አርሶ አደር ገመቹ ፈቀደ እንደነገሩን፤ ውሃ በግቢው ውስጥ ባለመኖሩ ከውጭ እየገዙ መገልገል የግድ ነው። እርሳቸውም የመጠጥ ውሃ ፈልገው ከግቢ ውጪ ገዝተው ለመምጣት ተገደዋል። በሆስፒታሉ የውሃ እጥረት ብቻ ሳይሆን መድኃኒት የማይገኝበት ሁኔታም አለ። መዳህኒቱንም ከውጪ ለመግዛት ተገደዋል። የሚገዛው መድኃኒት ደግሞ በዋጋው ከሆስፒታል ከሚገዙት ይልቅ በጣም ውድ ነው።
‹‹የሆስፒታሉ አገልግሎትና መስተንግዶ ግን መልካም ነው። ማንም ይሁን ማን በያዘው ወረፋ መሰረት እንዲስተናገድ ይደረጋል። ይህ አይነቱ አሰራር ከሁለት ዓመት በፊት አልነበረም፤ መስተንግዶው በትውውቅ ላይ የተመሰረተ ነበር።
የደምቢ ደሎ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አባይነሽ ፈቃዱ በቀጠሯቸው መሰረት በሆስፒታሉ ተገኝተው ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት እንዳገኙ ይገልጻሉ። ‹‹አሁንም በድጋሚ ተቀጥሬያለሁ። ቀደም ሲል ልክ ሌላውም ቦታ እንደሚደረገው አገልግሎት የሚሰጠው በትውውቅ ነበር፤ ዛሬ ግን ይህ የለም።›› ይላሉ።
‹‹የውሃ እጥረት አገልግሎቱን እያጓደለ ይገኛል። አንዳንዴ ውሃ ቢኖርም ጥራቱ የተጠበቀ ባለመሆኑ ከውጭ ገዝቼ ነው ለመጠጥ የምገለገለው።›› የሚሉት ወይዘሮ አባይነሽ፣ ‹‹በግቢው ውስጥ የመድኃኒት እጥረት በመኖሩም ብዙ ጊዜ መድኃኒት የገዛሁት ከውጭ ነው። እሱ ደግሞ ለተጨማሪ ወጭ እየዳረገኘኝ ነው።›› ሲሉ ያብራራሉ።
የሆስፒታሉ አዋላጅ ነርስ ሲስተር አስቴር ገላዬ እንደሚሉት፤ እናቶችን ለማዋለድ ዝግጅት ሲደረግ ውሃ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም፣ ላይገኝ ይችላል፤ አንዳንዴም አዋልደው ለቀጣይ የማዋለድ ስራ በሚዘጋጁበት ጊዜ ውሃ ባለመኖሩ ምክንያት እጃቸውን በአልኮል ብቻ አፅድተው ወደ ስራ ይገባሉ።
ሲስተር አስቴር በዚህ አካሄድ ወላዷ ጤነኛ ሆና መጥታ ሌላ በሽታ ውስጥ እንዳትገባ ስጋት አላቸው። አንዳንዴም ወላዷ ሳትታጠብም ወደቤቷ የምትሄድበት ጊዜ አለ። ስለዚህም ውሃ ወሳኝ በመሆኑ 24 ሰዓት መቋረጥ የለበትም፤ አልፎ አልፎ ችግሩ ባስ ሲል ቅርብ ከሆነው ከሜጢ ወንዝ ውሃ በመቅዳት ለላወንደሪ አገልግሎት እንደሚጠቀሙ ሲስተር አስቴር ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚገልፁት፤ መብራትም የማይኖርበት ጊዜ አለ/ የለም። ከዚህ የተነሳ እናቶች ይጎዳሉ።
እናቶች ከርቀት ቦታ መጥተው የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት በአግባቡ ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ያሳዝናል። የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም ሆስፒታሉ ግን በተቻለው አቅም ሁሉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እያረጉ ነው። በሆስፒታሉ ያሉ ባለሙያዎች የቡድን መንፈሳቸው የተነቃቃና መልካም በመሆኑ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በትጋት እየሰሩ ናቸው።
የአጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ከማል እርኮ እንደሚሉት፤ የሆስፒታሉ ዋና ችግር በመጀመሪያ የበጀት እጥረት ሲሆን፣ የመድሃኒት በበቂ ሁኔታ አለመገኘትና የውሃ ችግር ተጠቃሾች ናቸው። ከዚህ አካባቢ መድኃኒት የሚያገኙት ከኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ድርጅት ነው። ይሁንና ከዚያም የሚጠይቁትን ያህል መድኃኒት አያገኙም። ከሚጠይቁት የሚያገኙት 20 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው። የሚፈለገው መድኃኒት እንደልብ ባለመገኘቱም ህዝቡ ቅሬታ ያነሳል፤ እጥረቱ ብቻ ሳይሆን የሚፈለገው አይነት መድኃኒትም ጭምር አይገኝም።
‹‹የመሰረተ ልማት ችግርም አለ።›› የሚሉት ስራ አስኪያጁ፣ ‹‹ሆስፒታሉ እንደ አጠቃላይ ሆስፒታልነቱ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም። የውስጥ ለውስጥ መንገዱም የጠጠር በመሆኑ ለህሙማንም ሆነ ለወላዶች ምቹ አይደለም። የክፍሎች ጥበትም አለብን። ወላዶችን ያለውሃ ማስተናገድም ፈተና ሆኖብናል፤ በእርግጥ የከተማው የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት እየረዱን ቢሆንም አጥጋቢ አይደለም።›› ሲሉ ይናገራሉ።
የመብራት ችግር እንዳለም ተናግረው፣ በአካባቢው ያለው ትራንስፎርመር አነስተኛ በመሆኑ እንዲቀየር ነቀምት ላለው ዲስትሪክት ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም ምላሽ አለማግኘቱን ይገልጻሉ። በዚህም የተነሳ ሆስፒታሉ ብዙውን ጊዜ የሚጠቀመው ጄነሬተር መሆኑን ጠቅሰው፣ የነዳጅ ፍጆታቸው በራሱ በጀት የሚያቃውስ መሆኑን ነው የገለፁት።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ መንግስት ለሆስፒታሉ የመደበው በጀት ደግሞ አራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ነው፤ እሱም በአሁኑ ወቅት እየተጠናቀቀ ነውና የክልሉን ጤና ቢሮ ለመጠየቅ ሆስፒታሉ ተዘጋጅቷል። ጊዜ የማይሰጡ መድኃኒቶችን ከጎረቤት ሆስፒታል በመዋስ አገልግሎቱን ለመስጠት እየተሰራም ነው።
‹‹ሆስፒታሉ የህክምና መሳሪያም የሰው ኃይል እጥረትም አለበት›› የሚሉት ስራ አስኪያጁ፣ በተለይ የህፃናት ሐኪም እንዲሁም የውስጥ ደዌ ሐኪም አለመኖር በእነሱ አቅም ሊፈቱ ለሚችሉ ጥቃቅን ችግሮች እንኳ አገልግሎት ፈላጊዎች በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ወደ አዲስ አባባ ጳውሎስና ጥቁር አንበሳ ለመሄድ እንደሚገደዱ ያመለክታሉ። ችግሩን አስመልክቶ ለክልሉ ጤና ቢሮ ጥያቄ ቀርቦ ምላሹ እየተጠበቀ መሆኑን አስታውቀዋል። እንዲህም ሆኖ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የዓይን ባንክ፣ መድኃኒትና የህክምና እቃዎች አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ደረሰ አበራ እንደሚናገሩት፤ በሆስፒታሉ የመድኃኒት እጥረት መኖሩ እሙን ነው፤ ለዚህም ምክንያቱ እንደ አገርም አብላጫው መድኃኒት የሚገባው ከውጭ አገር ተገዝቶ እንደመሆኑ የምንዛሬ እጥረት ያመጣው ጉዳይ ነው። እንደ ቢሮ እየተሰራ ያለው ችግሩን ለመቅረፍ ሲሆን፣ መንግስትም በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። ከዚህ ባሻገር ጨረታም በማውጣት መግዛት የሚቻል ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ደግሞ የደምቢ ዶሎ አጠቃላይ ሆስፒታል ልምድ አለው ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በህክምና መሳሪያ ላይ በተቻለ መጠን ለአዳዲሶቹም ሆነ ቀደም ሲል ለተገነቡ ሆስፒታሎች የሚገዛውን በማካፈል ድጋፍ እየቀረበ ነው። እንደዚህም ሲባል በሆስፒታሎች አቅም መግዛት የማይቻሉትንና በሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግባቸውን ነው እኛ የምናቀርበው። በእነሱ አቅም የሚገዛውን ራሳቸው እንዲገዙ ይደረጋል።
‹‹ደምቢ ዶሎ በውሃ የታደለች ናት። ነገር ግን ውሃው ወደ ሆስፒታሉ መድረስ ያልቻለበትን ጉዳይ በሚመለከተው በማስገምገም በጀት ተይዞለት እንዲሰራ ማድረግ ይቻላል።›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የውሃ ጉዳይን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ መውሰድና መስራት ግድ እንደሚል ይገልጻሉ። የውሃው ችግር መሰረቱ ምን እንደሆነ እንደሚጣራና ከሚመለከታቸውም ጋር እንደሚመከርበት ያብራራሉ።
የባለሙያን ችግር በተመለከተም እንደገለፁት፤ ሆስፒታሉ አጠቃላይ እንደመሆኑ ባለሙያ ያስፈልገዋል። በመሆኑም በጀት በመያዝ የባለሙያ ችግር እንዳይፈጠር የበኩላቸውን እያደረጉ ነው። በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ ጎደለ የሚለውን ባለሙያ አይነቱን ለይቶ ካቀረበ ችግሩን ለመፍታት የሚሰራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 / 2012 ዓ.ም
አስቴር ኤልያስ