ኮንትሮባንድ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተከለከሉ ነገሮችን ይዞ መገኘት ወይም መግዛት ህገወጥ ተግባር መሆኑን ለማመከት እኤአ ከ1529 ጀምሮ ጥቅም ላይ መዋሉ ይነገራል። ዓለምአቀፉ የጉምሩክ ድርጅት፡-ኮንትሮባንድ ማንኛውም በህግ የተከለከለ አሰራር መሆኑን ጠቅሶ፣ ከማምረት፣ ከማጓጓዝ፣ ከመቀበል፣ ባለቤት ከመሆን፣ ከማከ ፋፈል፣ ከመግዛትና መሸጥ እንዲሁም ማንኛውም ለዚህ አሰራር ሁኔታዎችን ማመቻቸትን ያካትታል ሲል ተርጉሞታል።
በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድ ንግድ መቼና እንዴት እንደተጀመረ የሚገልጽ የተሟላ ማስረጃ ባይኖርም እንቅስቃሴው ከተጀመረ ግን በርካታ ዓመታትን ማስቆጠሩ ይታመናል።ሀገሪቱም በየጊዜው እየጎለበተ የመጣውን ኮንትሮባንድ ለመግታት የተለያዩ ህጎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ አድርጋለች።
በኢትዮጵያ የጉምሩክ አዋጅ 859/2006 ላይ እንደተመለከው ፤ኮንትሮባንድ ማለት ህጎችንና በህግ መሰረት የወጡ መመሪያዎችን በመተላለፍ ወደ ጉምሩክ ክልል ዕቃዎችን ማስገባት፣ በህጋዊ መንገድ የወጡትን በህገ ወጥ መንገድ መልሶ ማስገባት፣ መያዝ፣ ማከማቸት፣ማዘዋወር፣ ማስተላለፍ፣ እንዲገቡ ወይም እንዲወጡ ለማድረግ መሞከር፣ እንዲሁም እነዚህ ዕቃዎችን መግዛትን፣ መሸጥንና ለዚህ ድርጊት ተባባሪ መሆንን ያጠቃልላል።
በ1996 ዓ.ም በወጣውና አሁን በሥራ ላይ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 352 ላይ እንደተቀመጠውም ፣ማንም ሰው አስቦ በሕግ የተወሰነው ቀረጥ ወይም ግብር ያልተከፈለበትን ማናቸውንም ዓይነት የንግድ ዕቃ፣ ንብረት፣ ልዩ ልዩ ዕቃ ወይም የፋብሪካ ወይም የእጅ ጥበብ ሥራ የሚያፈራውን ማናቸውንም ዓይነት ነገር ከኢትዮጵያ ወደ ውጪ ያስወጣ ወይም ከውጪ ወደ ኢትዮጵያ ያስገባ እንደሆነ፤ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን እያወቀ… ዕቃውን ያከማቸ፣ ለሽያጭ ያቀረበ፣ የገዛ፣በቅን ልቦና ለወንጀሉ ባዕድ የሆኑ ሰዎችን መብት ሳይነካ ከተፈጸመ ዕቃው ይወረሳል፤ወንጀሉ የተፈጸመው በኀይል፣ በዛቻ፣ በማጭበርበር ከሆነ ዕቃው ከመወረሱ በላይ ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ያስቀጣል።
ምንም እንኳን አገሪቱ ተግባሩን ለመቆጣጠር እነዚህንና መሰል ህጎችን ተግባራዊ ብታደርግም በኮንትሮባንድ እቃዎችን በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የማስወጣትና ማስገባት እንቅስቃሴን መግታት ግን አልተቻላትም።ይህም ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገቷ ሳንካ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዳንኤል ደንድር፣ በኢትዮጵያ ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ እየተባባሰ ጉዳቱም በዚው ልክ እየጨመረ ስለመምጣቱ ከሚስማሙት መካከል አንዱ ናቸው።እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ በአሁኑ ወቅትም የጦር መሳሪያ፣መድኃኒቶች፣ተሽከርካሪዎች፣መለዋወጫዎች፣ልብሶች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ምግብና መጠጥ፣ አደንዛዥ ዕጽ ፣ሲጋራ፣ በኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ።የውጪ ሀገር ገንዘቦች፣ አደንዛዥ ዕጽ፣ ጫት፣ ምግብ፣ ከብቶችና ማዕድናት ደግሞ በኮንትሮባንድ ወደ ውጪ ከሚወጡት የሐገሪቱ ሀብቶች መካከል ግንባር ቀደም ሆነው ይጠቀሳሉ።
ተግባሩ ሰለመባባሱ ለማስረዳት ፣የገቢ ኮንትሮባንድ በየዓመቱ በአማካይ በ12 ነጥብ 6 እንዲሁም፣የወጪ ኮንትሮባንድ በየዓመቱ በአማካይ በ28 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ስለማሳየቱ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ የሚጠቁሙት አቶ ዳንኤል፣በአጠቃላይ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የወጪ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሬ እጥረት እየፈጠረ፣በህጋዊ የወጪ ንግዱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ ስለመሆኑም አፅእኖት ይሰጡታል።
ኮንትሮባንድ በአይነትም ሆነ በመጠን በመጨመሩም በተለይ ፍትሃዊ የንግድ ስርዓቱን እያመሰቃቀለ፣ የታክስ አስተዳደሩን እየተፈተነ፣ህጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ ውጪ በማድረግ መንግስት ማግኘት የነበረበትን ቀረጥና ታክስ እያሳጣ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡት ባለሙያው፣በተለይ‹‹ጥቁር ገበያን በማስፋፋት የውጪ ምንዛሬ እጥረት በመፍጠር፣የሃገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በማዳከምና ባለሃብቶች በሃገር ውስጥ ያመረቱትን ምርት ገበያ እየተሻማ ይገኛል››ይላሉ።
ለህገወጥ ተግባሩ መጎልበት ምክንያት ከሚሏቸው መካከል፣ደካማ የቁጥጥር ስርዓት፣ የኮንትሮባንዲስቶች አቅም መጎልበት፣የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ጉድለት፣ የዶላር እጥረት፣የፖለቲካ አለመረጋጋት፣የታክስ ስርዓቱ በተለይ በአንዳንድ ምርቶች ላይ ከፍተኛ መሆን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
ምን ይደረግ ለሚለው በተለይ የአገር አለመረጋጋት ለተግባሩ መጎልበት ጉልህ ድርሻ ስላለው ለዚህ ቀውስ ተገቢውን አፋጣኝ መልስ መስጠትን ቀዳሚ የሚያደርጉት አቶ ዳንኤል፣ ከዚህ ባሻገር አደጋውን የሚመጥን ቅንጅት፣ የቁጥጥር ስርዓቱን ጥብቅ ማድረግና አመለካከት ላይ በቋሚነትና በስፋት መስራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
የህግ ባለሙያና ጠበቃው አቶ ሚካኤል ተሾመም፣ በኮንትሮባንድ እቃዎችን በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የማስወጣትና ማስገባት እንቅስቃሴን በአንድ አገር ላይ ከባድ ኪሳራ እንደሚደርስና ጉዳቱም የእያንዳንዱን ጓዳ እንደሚያንኳኳ ያሰምሩበታል። ‹‹ለአብነት ኮንትሮባንድ ለማሳለፍ የሚሰጥ ሙስና ብቻውን የፍትህ ስርዓቱን ያዛባል፣ሁሌም ቢሆን ገንዘብ ያለው ሰው አሸናፊ እንዲሆን እድል ይፈጥራል። ይላሉ።
‹‹ሀገሪቱ ኮንትሮባንድን ለመግታት የተለያዩ ህጎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ ብታደርግ ያስቀመጠችው ቅጣት ግን ዝቅተኛ ነው፣ምንም እንኳን ጉዳቱ በሁሉም ቢሆንም ጦር መሳሪያን የሚያዘዋውረው ሰው የሚያደርሰው ጉዳት ከሌላው ይበልጥ ይከፋል›› የሚሉት አቶ ሚካኤል፣ የኮንትሮባንድ ንግዱ እየተስፋፋ ላለበት ሁኔታ የቅጣቱ ማነስ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ይጠቁማሉ።
ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለተግባሩ መጎልበት ምቹ መድላድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፣ የጦር መሳሪያ ዝውውሩም ለዚህ ማሳያ መሆኑን የሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ። አሰራሮችና ህጎች የማስተካከል ስትራቴጂው ተጋላጭነትን ለመቀነስ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ እንደመሆኑ ጊዜ የማይሰጠው አብይ ተግባር ስለመሆኑም አፅእኖት ይሰጡታል።
የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩል አዲስ የሕግ ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑን የሚጠቆሙት አቶ ሚካኤል፣ይህ መልካም እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፣ሕግ ማርቀቅ ብቻውን ለውጥ ሊፈጥር እንደማይችልም ያመለክታሉ። በተለይ በጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠርና የተጠናከረ የመከላከል ስራ መስራት ብሎም ለፖለቲካዊ መረጋጋት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። የመገናኛ ብዙሃንም የህገ ወጥ ተግባሩ የደቀነውን አደጋ በመከላከል ብሎም በማስተማር ረገድ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ይጠቁማሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ዶክተር ተሻገር ሽፈራው፣ኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ይገልጻሉ።‹‹መገናኛ ብዙኃን የድርጊቱን ፈፃሚዎች ማዕከል ያደረገ አራሚና አስተማሪ ስራ በመስራት፣የምርመራ ዘገባ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ አለባቸው››የሚሉት ዶክተር ተሻገር፣የኮንትሮባንድ ተዋንያኖች ተያዙ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ የት ደረሰ የሚለውን ተከታትለው ህጋዊ እርምጃዎችን ለማስተማሪያነት መጠቀም፣ለህዝብ ማድረስ እንደሚገባቸው ነው አፅእኖት ሰጥተው የተናገሩት።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 / 2012ዓ.ም
ታምራት ተስፋዬ