በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሥነስርዓት የሚከበረው የገና በዓል ተቃርቧል። የበዓሉ ግብይትም ገና ከአሁኑ መጧጧፍ ጀምሯል፤ መደበኛ የገበያ ሥፍራዎችና የእሁድ ገበያዎች ግብይት እየተሟሟቀ ይገኛል። ኤግዚቢሽኖች በየአካባቢው ተከፍተው ጎብኚዎችንና ሸማቾችን ወደ ማስተናገድ ገብተዋል። በዚህ ወቅት ትናንሽ የሚባሉ ገበያዎች ወይም ጉልቶች ጭምር ትልቅ ይሆናሉ።
በዚህ ግብይት የግብርና ምርቶች፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የሆኑ ሸቀጣ ሸቀጦችና ሌሎች አገልግሎቶች በስፋት ይቀርባሉ። ከግብርና ምርቶች መካከል እንደ እህል፣ ቅመማ ቅመም፣ ቅቤ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ አትክልት፣ ከብቶች፤ ከኢንዱስትሪ ምርቶች መካከል ደግሞ ዘይት፣ ስኳር፣ ዱቄት፣ በዚህ ወቅት ከፍተኛ ግብይት ይካሄድባቸዋል። የአልባሳት፣ የቤት እቃ፣ የስጦታ እቃ ወዘተ ግብይቱም ሌሎች በዚህ ወቅት በስፋት ግብይት የሚካሄድባቸው ምርቶች ናቸው።
በዓሉ እየቀረበ ሲመጣ ሊደርስ የሚችለውን ግፊያ የፈራ፣ የቤት ሥራዎቹን በኋላ እንደልብ ማካሄድ የፈለገ፣ ወዘተ. የሚችለውን ያህል ገበያውን አጥንቶ ግብይቱን በጊዜ ይፈጽማል። ሌሎች ደግሞ ምርቱ በበቂ ሁኔታ ይግባ፣ ምርቶች ይግቡ በማለት ገበያውን ለማጥናት ብቻ ብቅ ይላል፤ ከቀናው ይገዛል፤ አለያም መረጃ እየሰበሰበ ይቆያል።
አዲስ አበቤዎችም በዚህ የገና በዓል ግብይት ውስጥ ገብተዋል። የከተማ አስተዳደሩም በዓሉን ታሳቢ ያደረጉ ዝግጅቶችን ማድረጉን አስቀድሞ ገልጿል። ለበአሉ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችን ሁሉም በአቅሙ መሸመት እንዲችል የተለያዩ የገበያ አማራጮች አዘጋጅቷል።
ከእነዚህም መካከል በመዲናዋ መግቢያዎች አካባቢ የተዘጋጁ የገበያ ማዕከላት እና የቅዳሜ፣ የእሁድ ገበያዎች ይጠቀሳሉ። በተለያዩ የእንስሳት መሸጫ በረቶችም እንዲሁ የቁም እንስሳት በስፋት እንዲቀርቡ ይደረጋል፤ ህብረተሰቡ በበዓሉ የአቅርቦት ችግር እንዳያጋጥመው የሚያስችሉ ምርቶች ከአምራቹ በቀጥታ ለሸማቹ የሚቀርቡባቸው አማራጮችም ተዘጋጅተዋል።
በበዓላት እየተለመደ የመጡትና ኤግዚቢሽኖች እና ባዛሮች በብዛት ተከፍተው ግብይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ባዛሮቹም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የኢንዱስትሪ እንዲሁም የግብርና ምርቶችን ይዘው ቀርበዋል። ለእዚህ በዓል ሲባል የእሁድ ገበያዎች በየቀኑ እንዲሰሩ ተደርጓል። በከተማዋ ተዘዋውረን ካየናቸው የእሁድ ገበያዎች አንዱ ስድስት ኪሎ አካባቢ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ቀጥሎ ያለው ነው። በገበያው አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎች፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶች የሆኑ የፍጆታ ምርቶች በስፋት ቀርበዋል።
አቶ ሀብታሙ ባዩ በገበያው ሽንኩርት ይሸጣል፤ ሽንኩርቱን ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አምራቾች እየተረከቡ በጅምላ ያከፋፍላሉ። በገበያው በቂ የሽንኩርት አቅርቦት መኖሩን ገልፀው፣ በገበያው ሽንኩርትን ጨምሮ የአቮካዶና የፓፓያ አቅቦት በበቂ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
በዘመን መለወጫ በዓል አካባቢ የሽንኩርት እጥረት እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህ የገና በአል ወቅት ግን ምርቱ ከተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እየመጣ መሆኑንና የአቅርቦት አጥረት እንደሌለም አመላክተዋል። እጥረት ሲኖር ዋጋው ይወደዳል፤ አሁን ግን በቂ አቅርቦት አለ፤ ዋጋውም የተረጋጋ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዘመን መለወጫ ወቅት ሽንኩርት 100 ብር አካባቢ ተሸጧል ሲሉም አስታውሰው፤ አሁን ግን 75 ብር በኪሎ እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመዋል። ሁለተኛ ደረጃ የሚባለው ደግሞ ዋጋው ከዚህ እንደሚቀንስ አመልክተዋል። አሁን ከሁሉም ቦታዎች የደረሱ ምርቶችን ይመጣሉ። ከሸዋ ሮቢት፣ ከአፋር ክልል አዋሽ እና ገዋኔ አካባቢ፣ ከራያ ቆቦ፣ ከቦረና አካባቢ ምርቱ በስፋት እየመጣ ነው ሲሉ አመለክተዋል።
የሽንኩርት ምርቱን በማጓጓዝ ወቅት በመንገድ ላይ በተደጋጋሚ ችግሮች እየገጠሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ሽንኩርት በባህሪው አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ከቆየ የመበላሸት እድሉ ሰፊ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ፣ ይህን ለማስቀረት ለሊት ጭምር ይጓጓዛል ሲሉም ተናግረዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ከምሽት 12 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ መከልከሉም ምርቱ ቶሎ ገበያ እንዳይደርስ በማድረግ ለብልሽት ሊዳርገውና ነጋዴውን ለኪሳራ ሊዳርገው ይችላል ይላሉ፤፤ ‹‹እነዚህን ችግሮች በመቋቋም እየተሰራ ነው ሲሉም ጠቅሰው፣ በመንግሥት በኩል ችግሮቹ እንዲፈቱ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ሌላዋ ያነጋገርናቸው ወይዘሮ አበበች ይልማ ይባላሉ። ሸማች ናቸው፤ ቅቤ 900 ብር ከመርካቶ ገበያ መግዛታቸውን ጠቅሰው፣ ሽንኩርት በ80 እና 90 ብር በኪሎ እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቲማቲም በኪሎ 40 ብር መሸመታቸውን ነግረውናል። የሸንኩርት ዋጋ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ውድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በመዲናዋ መስቀል አደባባይና ኢግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተውን ኤግዚቪሽንና ባዘርም ለመቃኘት ሞክረናል። በባዛሩ የቀረቡ ምርቶች ሲታሰቡ፣ ያልቀረቡ የምርት አይነቶች የሉም ማለት ያሰኛል። ዘይት፣ ስኳር፣ ዱቄት እና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋና በስፋት ቀርበዋል። ግብይቱ በቴሌብር የሚካሄድበት ሁኔታ እንዳለም አስተውለናል፤ በቴሌብር ግብይት ያካሄዱ 10 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግላቸው ለመታዘብ ችለናል።
አምራቾችም በባዛሩ ገብተው ምርቶቻቸውን እየሸጡና እያስተዋወቁ ናቸው፤፤ የዘይትና ሌሎች ምርቶችን የሚያመርተው ሮቡስት ቢዝነስ ግሩፕ ከእነዚህ አምራቾች አንዱ ነው። የግሩፑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ ሙሊሳ በኤግዚቪሽን ባዛሩ ላይ ድርጅታቸው የሀማሬሳ ዘይትና ስኳር ምርቶቹን ለሕብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ይዞ መቅረቡን ይናገራሉ።
ድርጅቱ ለአዲስ ገና የ2017 በዓል የሮቡስት ቢዝነስ ግሩፕ እህት ኩባንያ የሆነው የሐማሬሳ የምግብ ዘይት ፋብሪካ የዘይት ምርቶችን ይዞ መቅረቡን ጠቅሰው፣ ሮቦስት የፎሬክስ ቢሮ፣ ሮቦስት ትሬዲንግ በመሳሰሉት እህት ኩባንያዎቹ በኩል ከውጭ የሚያስመጣቸው የፍጆታ ምርቶችንም እንዲሁ በተመጣጣኝ ዋጋ ይዞ መቅረቡን ጠቁመዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ድርጅቱ ሀገር ውስጥ የሚመረተውን ዘይት ከገበያው በቀነሰ ዋጋ አቅርቧል። በባዛሩ ሁለት አይነት ዘይቶችን ይዞ ቀርቧል፤ አንዱ ሐማሬሳ ፈሳሽ የምግብ ዘይት ሲሆን፣ ይህም ከጎመን ዘር የሚዘጋጅ ሬድ ሲድ ፈሳሽ ዘይት የሚባል ነው፤ በተጨማሪም የፓልም ዘይት እና ስኳር ምርት አቅርቧል። የፓልም ዘይቱ ድፍድፉ ከውጭ እንደሚጣ ተደርጎ ዘይቱ በሀገር ውስጥ እንደሚመረት ተናግረዋል። የስኳር ምርቱም የድርጅቱ እህት ኩባንያ የሆነው ሮቡስት ትሬዲንግ ከውጭ የሚያመጣው ነው። ሁሉም ለሕብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ተደርጓል።
ከውጭ የገቡ ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ የምግብ ዘይትንም ይዞ መቅረቡን ጠቅሰው፣ እነዚህም ምርቶች ቢሆኑ ከባዛሩ ውጭ ከሚሸጡበት ዋጋ ባነሰ እየተሸጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ባዛሩ እስኪያልቅ ድረስ ድርጅቱ ከበቂ በላይ ምርቶች ይዞ ማቅረቡን አስታውቀዋል። ድርጅቱ በባዛሩ ምርቱን ያቀረበው በቀጥታ ለተጠቃሚው እንጂ ለጅምላ ነጋዴው እንዳልሆነም አስታውቀዋል። ተጠቃሚው በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቹን እንዲገዛም ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ የገና በዓል ገበያው ዋጋና ግብይት የተረጋጋ እንዲሆን የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር በተለያዩ አማራጮች ላይ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ጥበቡ እንዳስታወቁት፤ ለገና በዓል ምርቶች በስፋት ወደ መዲናዋ እንዲገቡ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተደርገው ወደ ትግበራ ተገብቷል። ገበያው እና ዋጋው የተረጋጋ እንዲሆን፣ ሕብረተሰቡም ካለምንም መሳቀቅ እንዲገበያይ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ማኅበረሰቡ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የግብርናም ሆኑ የኢንዱስትሪ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጠነ ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል ምርቶቹ ወደ ከተማዋ በስፋት እንዲገቡ ተሰርቷል። ምርቶቹን ወደ ሕብረተሰቡ ለማድረስ የሚያግዙ ሶስት አማራጮች ተዘጋጅተዋል። አንደኛው አማራጭ በመደበኛነት ገበያ ማዕከላት ውስጥ የሚደረገው ግብይት ነው። በዚህም የከተማ አስተዳደሩ አራት የገበያ ማዕከላትን በከተማዋ መውጫ በሮች ላይ አደራጅቶ ሥራ ማስጀመሩን አስታውሰዋል።
ማዕከላቱም በኮልፌ፣ በአቃቂና፣ በለሚኩራ እና በላፍቶ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ናቸው ያሉት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፣ በመጀመሪያዎቹ ሶስት የገበያ ማዕከላት የአትክልትና የሰብል ምርት ይቀርባሉ ብዋል። በላፍቶ የገበያ ማዕከል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ብቻ እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል። በእነዚህ ማዕከላት የከተማዋ ነዋሪ የሚፈልጋቸው በርካታ የአትክልት፣ የፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል ምርቶች እንደሚቀርቡ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።
አቶ ፍሰሃ እንደተናገሩት፤ ሁለተኛዎቹ የግብይት አማራጮች የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎች ናቸው። እነዚህ ገበያዎች አሁን 197 መድረሳቸውን ጠቅሰው፣ በገበያ ማዕከላቱ የሚሳተፉ አምራቾች፣ ኢንዱስትሪዎች እና አርሶአደሮች በተመሳሳይ ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። በመዲናዋ ደረጃቸውን የጠበቁ 172 የቅዳሜና እሁድ ገበያ ይገኛሉ ያሉት ምክትል ኃላፊው፣ በእነዚህ የገበያ ማዕከላትም ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት እየቀረቡባቸው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በሶስተኛው አማራጭም በየከፍለ ከተሞቹ ባዛሮች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል። ይህም በ11 ክፍለ ከተሞች በተመረጡ 11 ቦታዎች እንዲሁም በሶስት የገበያ ማዕከላት ተግባራዊ ይደረጋል። በድምሩ በ14 ቦታዎች ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የሚሳተፉባቸው፣ አርሶ አደሮች እና አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ አምጥተው ከሸማቹ ጋር የሚገናኙባቸው ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በርካታ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ራቅ ብለው በየክልሉ የሚገኙ አርሶአደሮች በባዛሩ ባቀሩበት ጥያቄ መሰረት እንዲሳተፉ መደረጋቸውንም ገልጸዋል። በዚህም ሕብረተሰቡ ትኩስ የሰብል እና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን የሚያገኝበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል። የቁም እንስሳትም እንዲሁ ወደ ቁም እንስሳት የገበያ ማዕከላት በስፋት እንዲገቡ ለማድረግም ከኢትዮጵያ የቁም እንስሳት አቅራቢዎች ማሕበራት እና ከክልሎች ጋር በመነጋር የማቅረቡ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። ክልሎች በበዓሉ ዋዜማ ሳምንት ወደ የገበያ ማዕከላቱ የቁም እንስሳቱን ይዘው በመምጣት ሽያጭ እንዲፈፅሙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
የገበያውን ሁኔታ በማየት መንግሥት በሚያስፈልግባቸው ቦታዎች ሁሉ ሕግና አሰራሩን በመከተል ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ ማሕበረሰቡ በተረረጋጋ የገበያ ሁኔታ ግብይት እንዲፈፀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ የሕብረት ሥራ ኮሚሽንም እንዲሁ ለበዓሉ የበኩሉን ዝግጅት አድርጓል። የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ጌታቸው እንደገለፁት፤ ኮሚሽኑ በከተማ ደረጃ 164 የሚሆኑ መሰረታዊ የሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት አሉት። ለእነዚህ ማሕበራት ምርቶችን ለማቅረብም ከከልል የገበሬዎች የሕብረት ሥራ ማሕበራትና ከፋብሪካዎች ጋር ቀጥታ የገበያ ትስስር በመፍጠር እየሰራ ነው። በዚህ መሰረት 11 ክፍለ ከተሞች መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማሕበራት በኩል ለሕብረተሰቡ ምርቶቹን የማሰራጨት ሥራዎች ተመቻችተዋል።
በከተማ ደረጃ ያሉት የሸማች ሕብረት ሥራ ማሕበራት በባህሪያቸው አምራች አለመሆናቸውን ጠቅሰው፣ በአዋጅ 985/2009 መሰረት አንደተቋም ተደራጅተው ለአባሎቻቸው እና ለአካባቢው ማሕበረሰብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚ ያቀርቡ ተናግረዋል። በዚህም በምርት ዋጋ ላይ ንረት የሚያመጡ የተንዛዛ የንግድ ሰንሰለቶችን መቅረፍ እያስቻሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም