ኢትዮጵያ ከግማሽ ቢሊዮን ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ክምችት እንዳላት መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህን የመሰለ ሀብት እያላት ግን ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጋትን የድንጋይ ከሰል ከውጭ ስታስገባ ኖራለች።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በሀገሪቱ እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ለሚፈልጉ ፋብሪካዎች የድንጋይ ከሰል ከውጭ ሃገር በውድ ዋጋ ስታስገባ ቆይታለች። ለዚህም በዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ታደርግ ነበር።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግሥት ከውጭ የሚያስመጣውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት አቅዶ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። በተፈጠረው ምቹ ሁኔታም የግል ባለሀብቱ የድንጋይ ከሰል በማምረት ለኢንዱስትሪዎች እያቀረበ ነው። ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ሙሉ በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩም ናቸው።
በድንጋይ ከሰል ማምረት ሥራ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በርካታ አምራቾች በዘርፉ መሰማራት ችለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ‹‹ጅሚቲ›› የድንጋይ ከሰል አምራች ድርጅት ነው። ድርጅቱ በ2013 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ጦላይ ወረዳ ነው የተቋቋመው።
የጅሚቲ የንጋይ ከሰል አምራች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ እስማኤል አባነጋ እንደሚሉት፤ ድርጅቱ የተቋቋመው በሁለት ባለሀብቶች ሲሆን፣ በጅማ ዞን የመጀመሪያው የድንጋይ ከሰል አምራች ነው። በዘርፉ ለመሰማራት ፍቃድ ወስዶ ወደ ሥራ የገባው ከዘጠኝ ዓመት በፊት ቢሆንም፣ የማምረት ሥራ ከጀመረ ግን ገና ሦስት ዓመቱ ነው።
ድርጅቱ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በአካባቢው ያለውን የድንጋይ ከሰል ክምችት አስጠንቷል፤ በጦላይ ወረዳ ያለው የዚህ ድንጋይ ከሰል ክምችት የካሎሪ መጠንም እንዲሁ ተጠንቶ በዚህም መሰረት ከሰል ማምረት እንደሚቻል ታምኖበት ነው ሥራው የተጀመረው። ወደ ሥራ ከገባ አንስቶም የድንጋይ ከሰል እያመረተ ይገኛል።
ዋና ሥራ አስኪያጁ ድርጅቱ ጦላይ ወረዳ ላይ በሁለት ቦታዎች ላይ ማምረቻ እንዳለው ጠቅሰው፣ አሁን ደግሞ ቅርንጫፉን በማስፋት በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ቦረዳ በሚባል አካባቢ ሌላ ቅርንጫፍ ለማቋቋም በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። ጦላይ ወረዳ ኦፕቲማም ትሬዲንግ ፒኤልሲ የተሰኘ እህት ድርጅት እንዳለው ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅት በቀን ከሁለት ሺቶን በላይ የድንጋይ ከሰል እያመረተ ለሀገር ውስጥ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያቀርባል ብለዋል።
ድርጅቱ የድንጋይ ከሰል ምርት ጥራቱን ለማወቅ ወደ ኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዮት እና ፋብሪካዎች በየጊዜው እየወሰደ እያስፈተሸ መሆኑን አቶ እስማኤል ያመላክታሉ። አሁን ያለው የድንጋይ ከሰል ኃይል የማመንጨት አቅሙ ከ600ሺ ካሎሪ በላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከ450ሺ በላይ ካሎሪ ኃይል ማመንጨት የሚችል የድንጋይ ከሰል በአካባቢው እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ምርቱን ለፋብሪካዎች የሚያቀርቡ አካላት የድርጅቱን የድንጋይ ከሰል ምርት ተረክበው ለፋብሪካዎች እንደሚያቀርቡ ጠቅሰው፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አምራቹ ቀጥታ ለፋብሪካዎች የሚቀርብበት ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል። ከምርቶቹ ተጠቃሚዎች መካከል ሙገርና ሀበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ምርቱን በመግዛት በቁጥር የተወሰነ ቢሆንም ለፋብሪካዎች የሚያቀርቡ አምራቾች መኖራቸው ገልጸው፤ ለድሬዳዋ ናሽናል፣ ለለሚ፣ ለመሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንዲሁም ሆለታ አካባቢና አዲስ አበባ ዙሪያ ላይ ላሉ ፋብሪካዎች ያቀርቡ መሆኑን ይገልጻሉ። ለብረታ ብረት ፋብሪካዎችም የሚቀርብበት ሁኔታ እንዳለ ይጠቁማሉ።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት በመንግሥት በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀው፣ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ መመረት በራስ አቅም መስራትን እያበረታታ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ ደግሞ ትልቅ ለውጥ እንዲመጣ እያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ እንደ ጅሚቲ አይነት የድንጋይ ከሰል አምራች ፋብሪካዎች እንዲስፋፉ ያስችላል ሲሉ ያስረዳሉ።
የሀገር ውስጡ የድንጋይ ከሰል በአብዛኛው ያልታጠበ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከውጭ የሚመጣው ግን የታጠበና የተጣራ መሆኑን ገልጸዋል። አንዳንድ ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ የተመረተውን ከመጠቀም ይልቅ የውጪውን የመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻሉ። በሀገር ውስጥ የተመረተው የድንጋይ ከሰል ባይታጠብም በካሎሪ አቅሙ ከውጭ እንደሚበልጥ ጠቅሰው፣ በተለይ ወላይታና ጅማ አካባቢ ያለው የሰልፈር መጠን ወረድ ያለ ከመሆኑ ጋር ተይይዞ የፋብሪካዎች ምርጫ መሆኑን ተናግረዋል። የሰልፈሩ መጠን ከፍ ሲል ፋብሪካዎች ማሽናችንን ይጎዳብናል በሚል አይፈልጉትም ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የድርጅቱ የድንጋይ ከሰል ግን ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን የሚያሟላና የሚፈልጉት አይነት መጠንና ጥራት ያለው ሆኖ ሳለ በፋብሪካዎች ውስጥ ባሉት ያልተገቡ ብልሹ አሰራሮች የተነሳ ከገበያ እንዲወጣ ሲደረግ ቆይቷል። በዚህ የተነሳ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ገበያ ፍላጎት በጣም የቀዘቀዘና የወረደበት ሁኔታ አጋጥሟል። ይህ ችግር የድርጅት ተግዳሮት ሆኖ እንደነበር አመላክተዋል።
በተለይ 2016 ዓ.ም ላይ ድርጅቱ የሚያመርተው የድንጋይ ከሰል ገበያ እጦት ገጥሞት እንደነበር ያስታወሳሉ። የድንጋይ ከሰል ለማምረት የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ምርቱ ገበያ የሚያጣና ወጥቶ መሬት ላይ የሚቀመጥ ከሆነ ደግሞ ይነዳል። ምክንያቱም የድንጋይ ከሰል በባሕሪው ወጥቶ መሬት ላይ ሲቀመጥ የሚነድበት ሁኔታ አለ ሲሉ ያስረዳሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የድርጅቱ ዋንኛ ተግዳሮት ፋብሪካዎች ላይ ያለው የፍላጎት ማነስ ነው። የድርጅቱ ምርት ብዙ ሆኖ ሳለ ለግብዓትነት የሚፈልጉት ፋብሪካዎች ፍላጎት አነስተኛ ሆኖ ነበር። ሌላኛው ተግዳሮት አካባቢው ላይ የነዳጅ ማደያ ባለመኖሩ የተነሳ ድርጅቱ በናፍጣ የሚሰሩ በርካታ ማሽኖቹን ለማስነሳት የሚያስፈልገውን ናፍጣ ለማግኘት በእጅጉ ሲቸገር ቆይቷል።
የመንገድ ችግር ሌላኛው ተግዳሮት ነው። የድርጅቱ ማምረቻ ቦታው ወደ ጅማ ከሚወስደው ዋና መንገድ 85 ኪሎ ሜትር የፒስታ መንገድ አለው። መንገድ ሲበላሽ የሚጠግነው ሌላ አካል የለም፤ እስካሁንም ድርጅቱ እያስጠገነ እየሰራ ሲሰራ ቆይቷል፤ መንገድ ብልሽቱ በየጊዜው ሊያጋጥም ስለሚችል ለማስጠገን ብዙ ወጪ ይጠይቃል፤ ይህ ሁሉ ወጪው ከድርጅቱ አቅም በላይ እንዲሆን አርጎታል ይላሉ። ይህም በመንግሥት በኩል ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ድርጅቱ በሚያመርተው የድንጋይ ከሰል የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ማሟላት እንደሚችል በመንግሥት የታመነበት መሆኑን የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ፤ የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት ብቻ ሳይሆን ለማስገኘትም ጭምር ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱ ምርቱን ወስደው አጥበው ለውጭ ገበያ እየላኩ ያሉ ላኪዎች እንዳሉም ይጠቁማሉ። ከውጭ የሚመጣው በሀገር ውስጥ ከሚመረተው በዋጋ በጣም ትልቅ ልዩነት እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህም ሆኖ ግን በአንዳንድ ፋብሪካዎች በኩል ባሉት አንዳንድ ብልሹ አሰራሮች ሀገር ውስጥ የሚመረተው የድንጋይ ከሰል ጥራት አውርዶ ለማሳየት የሚሞከርበት ሁኔታ እንደሚስተዋል ያመላክታሉ።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ እያንዳንዱ ፋብሪካ አንደሚጠቀምበት ግብአት የድንጋይ ከሰሉ የጥራት ደረጃ ይለያያል። አላስፈላጊ ማቴሪያሎች ሲቀላቀሉ ጥራቱን ያወርዱታል።
በፋብሪካዎቹ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የታየው የድንጋይ ከሰል ጥራት መውረድ በሁሉም ቦታዎች ላይ እንዳለ አርጎ የመመልከት ችግር አለ። ችግሩ የቱ ላይ ነው? የትኛው ነው ትክክለኛውን ምርት እያመረተ ያለው በሚል በደንብ መመልከት ይገባል፤ ሁሉም ድርጅቶች በወረደ መልኩ እንደሚሰሩ አርጎ መፈረጅ አደጋን ያስከትላል። ጥራቱ እንዲወርድ የሚያደርገው የአሰራር ጉዳይ ነው። ይህንን ሁሉ ችግር ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ ሁሉንም በአንድ አይን ማየት አይገባም።
ድርጅቱ ወደዚህ ሥራ ሲገባ ከፍለጋ ጀምሮ እስከ ማምረት የወሰደው ጊዜና የወጣው ሀብት ቀላል የሚባል አይደለም የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ይህንን ሁሉ ሀብት አፍስሶ የገበያ ችግር ሲያገጥመው እጣ ፈንታው መውደቅ ሊሆን ይችላል ሲሉ አመልከተዋል።
እሳቸው እንዳስገነዘቡት፤ የገበያ ጉዳይ በደንብ ሊታሰብበትና ሊሰራበት ይገባል። የድንጋይ ከሰል የጥራት ደረጃዎችን ጠብቀው የሚያመርቱ ድርጅቶች እንዳሉ ሁሉ ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት የሚያመርቱ እንዳሉ ታውቆ፣ እነዚህን በመለየት ጥራታቸውን የጠበቁትን ምርቶች መግዛት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ሲገባ ሙሉ በሙሉ የዚያ አካባቢ የድንጋይ ከሰል በማለት የአንድን አካባቢ የድንጋይ ከሰል ከገበያ እንዲወጣ ማድረግ አይገባም።
ከድርጅቱ ተረክበው ለፋብሪካ የሚያቀርቡ ከ15 በላይ አቅራቢዎች እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ከጥራት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ችግር በርካታ አቅራቢዎችን ከሥራ ውጪ ማድረጉን ተናግረዋል። በሥራ ላይ ያሉት የተወሰኑት ብቻ መሆናቸውን አመልከተው፣ ድርጅቱ ከድሬዳዋ ናሽናል፣ ለሚና ለመሶቦ ሰሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥሮ ምርቶቹን እያስረከበ መሆኑን አመላክተዋል።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከፋብሪካዎች ጋር በመነጋገር የድንጋይ ከሰል ምርቱን የጥራት ደረጃ በፋብሪካዎቹ ስታንዳርድ እንዲሆን እያደረገ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በዚህም ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ወደ ገበያው የተመለሰበት ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል።
በተለይ ፋብሪካዎች የሚያነሱት የጥራት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ የእነሱ ድርጅት የድንጋይ ከሰል ጥራት ጉዳይ ከማዕድን ሚኒስቴር በመጡ አካላት ጭምር ጥራቱ ተፈትሾ የጥራት ችግር እንደሌለበት መረጋገጡን ተናግረዋል። ጦላይ አካባቢ ያለው የድንጋይ ከሰል በአጠቃላይ ጥራቱ ጥሩ የሚባል እንደሆነ ተረጋግጧል ሲሉም ጠቅሰው፤ ድርጅቱ አመራረቱ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ጥራቱን የጠበቀ ምርት እያመረተ መሆኑን አመላክተዋል።
ከኦሮሚያ ክልል ማዕድን ቢሮ ጋር በቅርበት እንሰራለን የሚሉት አቶ እስማኤል፤ ከፋብሪካዎች ጋር ያለውን የገበያ ችግር ለመፍታትም ቢሮው አብሮ ሲሰራ እንደነበር ይጠቅሳሉ።
ድርጅቱ በቀን ከሁለት ሺ ቶን በላይ እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፋብሪካው የቀን ምርት ብዛትና ያለው ፍላጎት አይጣጣምም ሲሉ ተናግረዋል። አንድ ጊዜ ስም በማይሆን መንገድ ከተነሳ መልሶ ማደስና ፋብሪካዎችን አሳምኖ ለመመለስ ጊዜ እንደሚወስድ አመልክተዋል። ያም ሆኖ ድርጅቱ በተቻለ መጠን በጥራት ደረጃ ያለው ምርት እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ የሁሉም ፋብሪካዎች ጥራት ደረጃ ተመሳሳይ ቢሆንም ፋብሪካዎች አሁን የሚወስዱት የምርት መጠን ከፍ ያለ መሆኑን ይገልጻሉ። ከ450ሺ በላይ የካሎሪ መጠን ያለውን የድንጋይ ከሰል እየተጠቀሙ ያሉ ፋብሪካዎች እንዳሉም አስታውቀዋል።
አሁን እየተመረተ ያለው የድንጋይ ከሰል ሳይታጠብ በራሱ የጥራቱ ደረጃ ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹ቢታጠብ ደግሞ ከውጭ ከሚገባው በጣም የተሻለ የጥራት ደረጃ እንደሚኖረው ተናግረዋል። የድንጋይ ከሰል በአመራራት ወቅት በትክክል ከተመረተ የጥራት ደረጃው በጣም ከፍተኛ የሚባል ይሆናል። ያልታጠበው የድንጋይ ከሰል በራሱ ጥራቱ ከፍተኛ ነው። እኛም የምናመርተው ይህንኑ ነው። በቀጣይም የበለጠ ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል በማምረት ለማቅረብ ዝግጁ ነን›› ይላሉ።
ድርጅቱ የድንጋይ ከሰል ከማምረት በተጨማሪ ማጠቢያው ማሽን ለመትከል ማቀዱን አቶ እስማኤል ጠቅሰው፣ በዚህም የሀገር ውስጥ ፍጆታን ከመሙላት ባሻገር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ድርጅቱ 50 ሰዎች በቋሚነትና ከ100 በላይ ለሚሆኑት ደግሞ በጊዚያዊነት የሥራ እድል ፈጥሯል ሲሉ ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም