አዲስ አበባ፡- የሰላም ጥሪውን ተከትለው የገቡትን በአግባቡ የመያዙ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ የቀሩትም ቢሆኑ የመረዳቱ ሁኔታ እንጂ የሰላም ጥሪውን ተከትለው እንደሚገቡ እምነት አለኝ ሲሉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ስትራቴጂክ አማካሪ አቶ ኢብሳ ነገዎ አስታወቁ፡፡ የሰላም ጥሪውን ተከትለው የገቡት የቡድኑ አባላት በጫካ በነበሩበት ጊዜም ጉዳዮቼ ናቸው ብለው ሲያነሷቸው የነበሩትን ወደ 17 ያህል አጀንዳዎችን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማቅረባቸውን ገለጹ፡፡
ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ስትራቴጂክ አማካሪ አቶ ኢብሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በመሠረቱ በማንኛውም ዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ጠብመንጃ ቦታ የለውም፡፡ ሥልጣን በጠብመንጃ አፈሙዝ አይገኝም፡፡ አሁን ግን ቀጥታ ከአባገዳዎችና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተደረገውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የገቡ ኃይሎች ብዙ ናቸው፡፡ እየተንጠባጠቡ ያሉ ኃይሎችም አሉ። የቀሩትም ቢሆኑ የግንዛቤ ጉዳይ እንጂ ተጠቃልለው እንደሚመጡ ጥርጥር የለም፡፡
እርሳቸው እንደገለጹት፤ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ያሉት ሳይሆኑ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ራሳቸውን ፋኖ ሲሉ የሚጠሩት ታጣቂዎችም አካባቢ እንዲሁ ብዙዎች እየገቡ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ መንግሥት ጠንከር ብሎ መሥራት አለበት፡፡ በራሱ መካከልና በሚገቡት መካከል ደላላዎች ሳይኖሩ ቀጥታ ውይይት ማድረግ መቻል አለበት፡፡ ምክንያቱም በዚህች ሀገር በርካታ የፖለቲካ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ወሬ ከአንዱ ወደሌላው በማመላለስ ግጭቱ ይበልጥ እንዲባባስ እና እንዲስፋፋ የሚያደርጉ በመኖራቸው ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡
እነዚህ አካላት አንዱን ከሌላው ጋር እያጋጩ መኖር የለመዱ በመሆናቸው ግጭት ከሌለ መኖር አይችሉም ያሉት አቶ ኢብሳ፤ ሥራዬ ብለው በተያያዙት የፖለቲካ ንግድ የሀገሪቱን ወጣቶች ወደ እሳት እንዳይማግዱ መጠንቀቁ መልካም ነው፡፡ የሀገሪቱ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሚመለከታቸውም በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሰላም ጥሪውን ተከትለው የገቡት በአግባቡ የመያዝ ሁኔታ አስፈላጊ ነው የሚሆነው ያሉት አቶ ኢብሳ፤ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ያልመጡ አካላት ጠብመንጃ እንዲያነሱ የገፋፋቸው የፖለቲካ ምክንያት መፍትሔ የሚቀመጥለት መሆን አለበት ብለዋል፡፡
መንግሥት ችግሮችን በውይይት እንዲፈቱ የሚያደርግ ከሆነ ጠብመንጃ የሚያስነሳ ሁኔታ እንደሌለም ተናግረዋል። በመሆኑም ባሉበት የሚያቆያቸው ምክንያት አይኖርም ብለዋል፡፡
በቅርቡ የሰላም ጥሪውን ተከትሎ የገባው ቡድን በጫካ በነበረበት ጊዜ ጉዳዮቼ ናቸው ብሎ ሲያነሳቸው የነበሩትን አጀንዳዎች ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቅረብ ችለዋል ያሉት የኦነግ ስትራቴጂክ አማካሪው፤ በዚህ አጋጣሚም ያቀረቡት ወደ 17 ያህል አጀንዳዎችን ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ኢብሳ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የያዘው አቅጣጫ በጣም ጥሩ ነው የሚባል ነው። በኮሚሽኑ አካባቢ ያስተዋሉት ነገር ቢኖር ገንቢ የሆነ ሁኔታ መሆኑን መናገር ይችላሉ፡፡ እርሳቸውም በግላቸው እየረዷቸው ነው፡፡
በኮሚሽኑ ውስጥ ያሉ ሰዎችም መልካምና ሁሉንም ወገን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተው፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በተሳሳተ መንገድ የሚረዷቸው አካላት ቢኖሩም እኔ ግን እንደዛ አላይም፤ ኮሚሽኑ ብዙ መፍትሔዎችን ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
መመካከርና መስማማት የግድ ይላል፡፡ መስማማት አይቻልም የሚባል ከሆነ ደግሞ የሕዝብ ውሳኔን አሜን ብሎ መቀበል ጥሩ ነው፡፡ ችግሩ ምንድን ነው የሚለውን ሕዝብ ያውቃል ያሉት አቶ ኢብሳ፤ ቅራኔ ካለም ሕዝብ ያንን ቅራኔ መፍታት ይችላል፡፡ በአብላጫ ድምጽ ተለያይቶ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሒደትን በሥራ ላይ ማዋል ተገቢ ነው እንጂ የሃሳብ ልዩነት በተፈጠረ ቁጥር ጠብመንጃ ለማንሳት መሯሯጡ አግባብነት አይኖረውም ብለዋል፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም