ኦሌገነር ሶልሻየር እ.ኤ.አ የካቲት 26ቀን1973 በኖርዌይ ክሪስቲያንሰንድ በተባለ ቦታ ተወለደ። ኳስን ህይወቱ በማድረግ እ.ኤ.አ ከ1980 እስከ 1990 በክሎስኔገን ታዳጊ ክለብ ውስጥ መጫወት ችሏል።እ.ኤ.አ በ1990 ወደ ዋናው ክለብ በማደግ 109 ጨዋታዎችን በመጫወት 115 ጎሎችን ለክለቡ ማስቆጠር ችሏል። ባሳየውም ብቃት በዛው በኖርዌይ ሊግ ወደ ሞልድ ክለብ በመዘዋወር በክለቡ በቆየበት ሁለት ዓመታት 42 ጨዋታዎችን አድርጎ 31 ኳሶችን ከመረብ ማገናኘት ችሏል።
በእነዚህ ሁለት የኖርዌይ ክለቦች አስደናቂ ብቃቱን ሲያሳይ ከቆየ በኋላ እ.ኤ.አ በ1996 ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ በ1 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ ተዛውሯል። እ.ኤ.አ ከ1996 እስከ 2007 በቆየባቸው 11ዓመታት ውስጥ 366 ጨዋታዎችን በማድረግ 126 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። ‹‹በቀያይ ሠይጣኖቹ›› ቤት ‹‹ቤቢ ፌስ›› በመባል በቅጽል ስሙ የሚጠራው ኖርዌያዊው ከተቀያሪ ወንበር በመነሳት በሽርፍራፊ ደቂቃዎች ወሳኝ ጎሎችን በማስቆጠር ይታወቃል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ካስቆጠራቸው ጎሎች ሁሌም በክለቡ ከሚታወስበት መካከል እ.ኤ.አ በ1999 በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ ከባየር ሙኒክ በተገናኙበት የዋንጫ ጨዋታ ነው፡፡ ተቀይሮ ገብቶ በ92ኛው ደቂቃ ላይ ዴቪድ ቤካም ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ኳስ ከመረብን በማገናኘት የማሸነፊያዋን ጎል በማስቆጠር ክለቡ ዩናይትድ ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸንፍ አድርጓል፡፡ በዚህም «ቀያይ ሠይጣኖቹ» ሦስት ዋንጫዎችን በውድድር ዓመቱ እንዲያነሱ በማስቻል ክለቡን ታሪክ እንዲሠራ አስችሏል።
ይህ በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት በቅጽል ስሙ «ቤቢ ፌስ» በመባል የሚታወቀው የፊት መስመር ተጫዋች በአሁኑ ሰዓት እድሜው 45 ዓመት ሲሆን፤ 1 ሜትር ከ78 ሳንቲሜትር ያክልም ይረዝማል። ጎልማሳው ሶልሻየር በአሠልጣኝነት ዘመኑም የኖርዌዩን ክለብ ሞለዴን እ.ኤ.አ ከ2011 እስከ 2014 ማሰልጠን ችሏል። ከዛም እ.ኤ.አ በ2014 ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በማቅናት ካርዲፍ ሲቲን አሠልጥኗል።
በፕሪሚየር ሊጉ የተጠበቀውን ያክል ውጤታማ ባለመሆኑ ወደትውልድ ሀገሩ ተመልሶ እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ እንደገና ቀድሞ ያሠለጥን የነበረውን ሞልድን በማሠልጠን ላይ እያለ ነበር፤ማንቸስተር ዩናይትድ ከሊቨርፑል ጋር ባደረገው ጨዋታ 3ለ1 ከተሸነፈ በኋላ ክለቡ በቅጽል ስማቸው ‹‹ዘስፔሻል ዋን›› በመባል ከሚታወቁት ጆዜ ሞሪኒሆ የጠበቁትን ውጤት ባለማግኘታቸው ያላቸውን ውል ካፈረሰ በኋላ፤ ማንቸስተርም ለቀድሞው የክለቡ ተጫዋች ለነበረው ሶልሻየር ጊዜያዊ አሠልጣኝነት ጥያቄ አቀረበለት። ጥያቄውን ተቀብሎ የሚያሠለጥነውን ክለብ ለምክትል አሠልጠኙ ኧርሊንግ ሞይ በጊዜያዊነት ክለቡን እንዲያሠለጥን ኃላፊነቱን በመስጠት ታሪክ ወደሠራበት ወደ ቀያይ ሠይጣኖቹ መንደር ኦልትራፎርድ በያዝነው ወር ነበር የደረሰው።
በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዘመን ከነበሩ ከዋክብት ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ይህ የፊት መስመር ተጫዋች ማንቸስተርን ካለበት ችግር ለመታደግ ይከብደዋል የሚሉ ጥያቄዎች ከግራም ከቀኝም ይነፍሱ ጀመር። ምክንያቱም በፈርጉሰን ስር ያለፉ ከዋክብት ተጫዋቾች ወደ አሠልጣኝነት ዓለም ብዙ አይቀላቀሉም፤ ወደ አሠልጣኝነት ቢመጡም ስኬታማ አይሆኑም እየተባለ ይታማል። በዚህ ጉዳይ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ይወቀሳሉ። ምክንያቱም በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስር ካለፉ ተጫዋቾች ወደ አሠልጣኝነት ከመጡት ውስጥ እንደነ ሪያን ጊግስ፣ ጋሪ ኔቨል የመሳሰሉት ተጫዋቾች በአሠልጣኝነት ዘመናቸው ስኬታማ ባለመሆናቸው ምክንያት ነው።
በክለቡ ከነበረው የውጤት ቀውስና ከቀድሞ የክለቡ አሠልጣኝና ተጫዋቾች መካከል ከተፈጠረው አለመግባባት አንፃር አሰልጣኙ ጥሩ አጀማመር ይኖረዋል ተብሎ ባይታሰብም፤ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2018 የመጀመሪያውን ጨዋታ ከቀድሞው ክለቡ ካረዲፍ ሲቲ ጋር ባካሄደው ጨዋታ ዩናይትድ 5ለ1 ካርዲፍን ማሸነፍ ችሏል። ይህም ዩናይትድን በፕሪሚርሊጉ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዘመን ባደረጉት የመጨረሻ ጨዋታ እ.ኤ.አ 2013 ወርሀ ግንቦት ላይ ከዌስት ብሮሚች አልቢወን አምስት አቻ ከወጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ጎል ዩናይትድ ማስቆጠር ችሏል። አሰልጣኙም ከዚህ በመቀጠል ከ ሀድረስፊልድ ታወን እና ቦርንማውዝ ጋር ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች በበላይነት ለማሸነፍ ችሏል። በዚህም ሶልሻየር ሶስት ተከታታይ የፕሪሜርሊግ ጨዋታዎች በማሸነፍ ከሰር ማት ቦስቢ እና ጆዜ ሞሪኒሆ በመቀጠል በክለቡ ሶስተኛው ባለታሪክ ሰው ለመሆን በቅተዋል።
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በክለቡ በቆዩበት ሁለት ዓመት ተኩል 2017/18 የውድድር ዘመን የመክፈቻ ጨዋታ ዌስት ሀምንና ስዋንሴን አራት ለባዶ በማሸነፍና ሁለት ለባዶ ሌስተርን በማሸነፍ በሶስት ተከታታይ የፕሪሜርሊጉ ጨዋታዎች 10 ጎሎችን ማስቆጠር ችለው ነበር። የ45 ዓመቱ አሰልጣኝ በአደረጓቸው ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ተጫዋቾቹ 12 ኳሶችን በማገናኘቱ ከሞሪኒሆ በተሻለ በአጭር ጊዜ ታሪክ መስራት ችሏል።
ከሁሉም ነገር በላይ ጆሴ ሞሪኒሆ ከአንዳንድ የክለቡ ኮከብ ተጫዋቾች ጋር የነበረውን የተበላሸ ግንኙነትና እሰጣ ገባ በማስተካከል፤ ከተጫዋቾቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት በመፍጠርና ለተጫዋቾቹ የሚመቻቸውን የአጨዋወት ስልት በመረዳት በሚፈልጉት የአጨዋወት ስልት እንዲጫወቱ በማድረግ፣ ጥሩ ስሜት ኖሯቸው እንዲጫወቱ በማስቻል፣ በክለቡ ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል። በዚህም ክለቡ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ ዳግም እንዲገባ በማድረግ ከአርሴናል ጋር የነበረውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ እንዲል አስችሏል።
ሌላኛው አሰልጣኙ በዩናይትድ ቤት ያሻሻሉት ትልቁ ነገር የፖል ፖግባ የአጨዋወት ስልት መቀየራቸውና ከተጫዋቹ ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠራቸው ነው። ሞሪኒሆ ከተጫዋቹ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በጣም የሻከረ ነበር። ምክንያቱም ተጫዋቹን በጥልቀት ተመልሶ እንዲከላከል ጫና ያደርጉበት ስለነበር፤ በዚህም ተጫዋቹ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ለመጫወት ስላልተመቸው በአሰልጣኙና በተጨዋቹ አለመግባባት እንዲፈጠር ሆኖ ነበር። ይህ ክለቡ በከፍተኛ ዋጋ ከጁቬንቱስ በ95 ሚሊዮን ፓውንድ ያዛወረውን የመሀል ሜዳ ተጫዋች በተቀያሪ ወንበር ላይ ቁጭ እንዲል በማድረግ ለክለቡ የሚጠበቅበትን ግልጋሎት እንዳይሰጥ ማድረጉ ይታወሳል። እንደ ስፖርት ተንታኞች አስተያት ተጫዋቹ ለወደፊቱ ለከፍተኛ ያቋምና የብቃት መውረድ የሚያጋልጠው ነበር። ታዲያ ኖርዌያዊው አሰልጣኝ ለተጫዋቹ ከ ሄሬራና ኔማኒያ ማቲች ፊት በመሆን ያጥቂ ክፍሉን እንዲረዳ አጥቅቶ እንዲጫወት በማድረግ ይህ ፈረንሳዊ ኮከብ ሀንደርስ ፊልድን 3ለ1 እና ቦርንማውዝን 4ለ1 ክለቡ ባሸነፈበት ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል።
ፈረንሳዊው ኮከብ ለቡድን አጋሮቹ ዩናይትድ ካርዲፍን 5 ለ1 ሲያሸንፍ ለሊንጋርድና ለሄሬራ ኳሶችን በማቀበል ጎል እንዲያስቆጥሩ አስችሏል። በተጨማሪም ለሮሜሎ ሉካኩ ከቦርንሞውዝ ባደረጉት ጨዋታ ጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ በማቀበል ጎል እዲያስቆጥር በማድረግ በውድድር ዓመቱ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ያቀበለውንም ብዛት በእጥፍ አሳድጓል።
‹‹የክለብ አጋሩ ሊንጋርድ ይህ ፈረንሳዊ የመሀል ሜዳ ፈርጥ ከኋላ በመከላከል ሚና ግራ ሲጋባ ነበር። አሁን ላይ በዩናይትድ አካዳሚ ወደ አደገበት የአጨዋወት ፍልስፍና መመለስ እንደቻለ አምናለሁ በማለት ሀሳቡን ገልጿል፡፡ የሱ የእግርኳስ አጨዋወት በጣም ያዝናናል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ክለቡ ከ18 ዓመት በታች የታዳጊዎች ዋንጫ ሲያነሳ ይህ ፈረንሳዊ ኮከብ እንዴት ለክለቡ ግልጋሎት እንደሚሰጥ አውቅ ነበር። በአሁኑ ወቅት ተጫዋቹም እርሱ በሚፈልገው በሜዳው ወደግራ በኩል አድልቶ በነጻነት ሜዳውን አካሎ እንዲጫወት ነጻነት አግኝቷል። በዚህም ወደፊት ተጭኖ በመጫወቱ ጎሎችን አስቆጥሯል። ተጫዋቹ ይህን ማድረግ እንዲችል የ45 ዓመቱ አሰልጣኝ ሶልሻየር ሙሉ በሙሉ አግዞታል። ኖርዌያዊው አሰልጣኝም በራስ መታማመኑን በመጨመር ነጻ ሆኖ እንዲጫወት በማድረግ ከአሁን በፊት ሲያሳየው የነበረውን ምርጥ አቋም ዳግም እንዲያሳይ እየረዱት ነው›› በማለት ሊንጋርድ ጨምሮ ተናግሯል፡፡
‹‹ይህን ፈረንሳዊ ኮከብ ከአሁን በፊት አጨዋወቱን በሚገባ ስላየሁት በጥሩ ሁኔታ እንደሚጠቀምበት እርግጠኛ ነኝ። እርሱ እንዴት በድንቅ ሁኔታ እግርኳስን ይጫወት እንደነበር ከአሁን በፊት አይቻለሁ፡፡ አሁን ሁላችንም ወደምናውቀው ምርጥ አቋሙ በመመለስ ላይ ነው። ባደረግናቸውም ሶስት ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። ለወደፊትም ቡዙ ጎሎችን ለክለቡ እንደሚያስቆጥርም አልጠራ ጠርም›› በማለት የቀድሞው «የቀያይ ሰይጣኖቹ» አጥቂ ያሁኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሶልሻየር ስለተጫዋቹ ተናግሯል።
ፖግባም ሞሪኒሆ ከከለቡ አሰልጣኝነት በመነሳታቸው ከፍተኛ ተጠቃሚ ከሆኑ ተጫዋቾች የመጀመሪያው ነው። ዩናይትድ በሶልሻየር እየተመራ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ይህ ተጨዋች የሁሉም ጨዋታዎች የልብ ምት መሆን ችሏል። ተጨዋቹም ወደ ቀድሞ ብቃቱ በመመለስ ከነበረበት ድብርትና ጭንቀት በመውጣት ወደቀድሞ ደስታውና ሳቁ መመለስ ተመልሷል።
ከእርሱ በተጨማሪም ራሽፎርድና አንቶንዮ ማርሻል በሶልሻየር የአሰልጣኝነት ዘመን የፊት መስመሩን የማጥቃት ፊታውራሪነት በመሰጠታ ቸው፤ ዩናይትድ ከቦርነማውዝ ጋር ባደረገው ጨዋታ በተጋጣሚ ግብ ክልል አካባቢ ባደረጉት አሰፈሪና አደገኛ እንቅስቃሴ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ በመሆን ሁለቱም ጎል አስቆጥረው መውጣት ችለዋል። አሠልጣኙ ክለቡ ቀድሞ ወደ ማይታወቅበት ተጋጣሚ ክለብን ተጭኖና አጥቅቶ መጫወት ፍልስፍና እንዲመለስ በማድረጋቸው እነርሱም ደስተኞች ናቸው። ምክንያቱም ሁለቱም ተጫ ዋቾች ከመከላከል ይልቅ ወደፊት ተስበው የሚጫወቱ በመሆናቸው ነው።
በትናንትናው ዕለት በሴንት ጀምስ ፓርክ እስታ ዲየም ኒውካስትል ከማንቸስተር ዩናይትድ ባደረጉት የቦእሲንግ ደይ የመጨረሻ ፍልሚያ ዮናይትድ ሁለት ለባዶ ኒውካስትልን ማሸነፍ ችሏል። ዮናይትድ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ እ.ኤ.አ በ1946 ሰር ማት ቦስቢ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ካሸነፉ በኋላ፤ ሶለሻየር ዳግም አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የቦስቢን ገድል በመድገም ከሳቸው በመቀጠል ሁለተኛው ታሪካዊ አሰልጣኝ ለመሆን በቅቷል። አሰልጣኙም የምሽቱን ጨዋታ በማሸነፉ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ደረጃ ከተቀመጠው ቸልሲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት ዝቅ እንዲል አስችሏል። «ለቀያይ ሰይጣኖቹ» የማሸነፊያዎቹንም ጎል ሮሜሎ ሉካኩ በ64ኛው እና ማርኮስ እራሽፎርድ በ80ኛው ደቂቃዎች ማስቆጠር ችለዋል። እራሽፎርድም ባደረገው ድንቅ እንቅስቃሴ የዕለቱ የጨዋታው ኮከብ ለመሆን በቅቷል።
ተጫዋቾቹ ውጤታማ ባልሆነ የአጨዋወት ፍልስፍና ታስረው ከነበሩበት የጆሴ ሞሪኒሆ ዘመን መፈታት ችለዋል። ክለቡ ማንቸስተር ዩናይትድ ዳግም ወደ ቀደም አስፈሪነቱ በኖሮዊያዊ አሰልጣኝ አማካኝነት በመታገዝ በመመለስ ላይ ነው። ይህ ኖሮዌያዊ አሰልጣኝ ክለቡ ጊዜ ሰጥቶ እንዲያያቸው ፍላጎት አላቸው።እንዲሁም ሆስፒታል የቆዩት የቀድሞው የክለቡ የምንጊዜውም ምርጥ አሰልጣኝ የሆኑት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን አሰልጣኙ ያደረጉአቸውን ጨዋታዎች ስታዲየም በመግባት ጨዋታዎችን በማየትና በክለቡ የልምምድ ሜዳ በመሄድ ልምምዳቸውን መመልከት ችለዋል። ለክለቡ የቦርድ አባላትም አሰልጣኙን ጊዜ ሰጥተው እንዲያዩአቸውም ጠቁመዋል። ክለቡ ግን እኚህ ኖርዌያዊ አሰልጣኝ በትንሽ ጊዜ ይህን ሁሉ ስኬት ቢያስመዘግቡም ያለፉት አምስት ዓመታት የዋንጫ ድርቁን የሚቀርፍለት አሰልጣኝ በማማተር ላይ ተጠምድዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
ሰለሞን በየነ