ጥር 5 ቀን 2011ዓ.ም ‹‹ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በህብረተሰቡ ሰፊ ተሳትፎ ለላቀ ውጤታማነት›› በሚል መሪ ቃል በሁሉም የክልል ከተሞች የ5 ኪሎ ሜትር እርምጃ ውድድር እንደሚካሄድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።
የስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ የወድድሩን መርሃግብርና ዓላማ አስመልክተው ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ውድድሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ27 ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡ውድድሩ ህብረተሰቡን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በማሳተፍ፣ በአዕምሮና በኣካል የዳበረ ጤናማ ዜጋን ለማበራከት፣ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ግንኙነት ለማጠናከርና ባህሉ እንዲያደርግ ለማነሳሳት ጭምር ታሳቢ ያደረገ መሆኑም አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ፤ ህብረተሰቡን በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለማሳተፍ የተለያዩ የማስፈጸሚያ ስልቶች ተነድፈዋል። በየዓመቱ ንቅናቄ በመፍጠር ህብረተሰቡን በየደረጃው የማነቃቃት ስራ የማከናወን ተግባርም የዚሁ አካል ነው፡፡በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የሚከበረው የእርምጃ ቀን ፋይዳው የጎላ መሆኑንና ውድድሩ ቀጣይነትም እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡
የስፖርት ተሳትፎና ውድድር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በቀለ በበኩላቸው፤ ስፖርቱ ተጀምሮ የሚጠፋ እንዳይሆን ህብረተሰቡ በሚሰራበት፣ በሚማርበት እና በሚኖርበት አካባቢ እንደየፍላጎቱ በግል እና በቡድን ስፖርትን እንዲያዘወትር ከተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል፡፡
በውድድሩ በተለያየ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ከ85 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ጥር 5 ቀን ከጠዋት ጀምሮ እንደ የክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ በተመረጡ ቦታዎች እንደሚካሄድና ለተሳታፊዎች ሰርተፊኬት መዘጋጀቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
ዳንኤል ዘነበ