
በመዲናችን አዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ሴት እህቶች ቡና ለማፍላት ጀበናና ሲኒን ከማጀት አውጥተው ወደ አደባባይ ከዘለቁ ዓመታቶች ተቆጥረዋል። የጀበና ቡና ስራ ከሌሎች የሥራ መስኮች ጋር ሲነፃፀር በተለይ ቦታው ከተገኘ ከ500 ብር ባልበለጠ ገንዘብ ሥራውን መጀመር የሚቻል በመሆኑ፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው እናቶችና ወጣት ሴቶች በየሰፈሩ ሲኒና ጀበና ይዘው ተፍ ተፍ በማለት ስራውን እያቀላጠፉት ይገኛሉ። ይህ የጀበና ቡና ስራ ታድያ ለበርካታ እንስቶች ሰፊ የስራ ዕድልን በመፍጠሩ በርካቶች ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ይታመናል።
ይሁን እንጂ ለበርካታ ሴቶች የስራ ዕድል የፈጠረው ይህ የጀበና ቡና በባለሀብቶች አማካኝነት ከመንደር አልፎ በከተማዋ ባሉ ትልልቅ ፎቆች በረንዳ ላይ ከፍ ብሎ ቦታ ይዟል። አሁን አሁን እነዚህ በፎቆች ላይ የተጀመሩ ቡና ቤቶችም እየተበራከቱ መጥተዋል። በጀበና ቡና ስራ የተጠመዱ ፎቆች መበራከታቸው ደግሞ በየአካባቢው የተኮለኮሉትንና በአነስተኛ ገንዘብ ስራውን የጀመሩትንም ሆነ ለመጀመር ያሰቡትን እንስቶች እያዳከመ መምጣቱ እየተነገረ ይገኛል።
በየፎቆቹ ደረጃ ላይ ከተጀመሩት የጀበና ቡና ስራዎች በፊት ቀድመው ሥራውን ከመንግስት በተሰጣቸው ቦታ ላይ ሸራ ወጥረው በመሐል አራት ኪሎ ለበርካታ ዓመታት የጀበና ቡና እያፈሉ በመሸጥ የሚተዳደሩ እናት ቀደም ሲል ገቢያቸው የደራ እንደነበር ያስታውሳሉ። እኚህ እናት በአነስተኛ ቦታ ላይ ስራውን የጀመሩ ሰሞን ገበያው ብዙ ባይሆንም እየለመደ ሲሄድ፤ የደንበኞቻቸው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ያስታውሳሉ።
ከባንክ አስተዳዳሪ እስከ ቀን ሰራተኛ ቡናቸውን ‹‹ፉት›› ለማለት በሸራ ወደ ተወጠረችው ደሳሳ መጠለያ ጎራ የሚሉት ሰዎች፤ መቀመጫቸው ድንጋይ ቢሆንም አማራጭ ስላልነበራቸው እማማ ጋር ጎራ ማለቱን አይዘነጉትም ነበር፡፡ አሁን አሁን ደግሞ በየቦታው ከእርሳቸው በቅርብ እርቀት ሳይቀር የቡና ስራ መስፋፋት የእርሳቸው ደንበኞች አማራጭ እንዲያገኙ ዕድል በመስጠቱ ሥራቸው ከዕለት ዕለት እየተቀዛቀዘ እንደመጣ ይናገራሉ።
ታድያ እኚህ እናት ፎቅ ላይ ረከቦት ለምታስቀምጥ ቦታ 10ሺ ብር ተከራይተው የሚሰሩት ሰዎቹ የጀበና ቡናን ትተው ሌላ የሥራ መስክ ላይ መሰማራት ይችላሉ የሚል እምነት ቢኖራቸውም ‹‹ እነርሱ ቢሰሩ አልመቀኝም፤ ለእኔ ያለው የትም አይሄድም፤ አንዱ ሲሄድ ሌላው ይመጣል፤ ፎቆቹ ሁሉ የቡና ስራ ቢሰሩም የማውቃቸው አልፈውኝ ሲሄዱ የማላውቃቸው ደግሞ ይመጣሉ። እንግዲህ ስራ እንደዚህ ነው፤ አንድ ቀን ምንም ሳልሸጥ ብገባ ሌላ ቀን ደግሞ 10 ሲኒ ቡና እሸጣለሁ፤ ለቦታው የምከፍለው ግብር በዓመት ስለሆነ ይበቃል›› በማለት ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ።
በተለያዩ ፎቆች ላይ ያለው የቡና ስራ እንቅስቃሴው ጥሩ እና በርካታ ተጠቃሚ ያለው ቢሆንም፤ አንድ ሲኒ ቡና በአምስት ብር እየሸጡ ለመንግስት በዓመት ግብር የሚከፍሉት ቢበዛ 3000 ብር ብቻ በመሆኑ ገበያ ባይኖርም ብዙ እንደማይጎዱ ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳን ፎቆቹ ላይ በርካታ ተጠቃሚ ቢኖርም አቅም ስለሌላቸው፤ ያላቸውን ቦታ ተጠቅመው በጀበና ቡና ላይ የተመሰረተ ህይወትን ከመግፋት ውጪ ሌላ ሃሳብ እንደሌላቸው ይጠቁማሉ፡፡
የጀበና ቡና ንግድ ከፎቆች በረንዳ በተጨማሪ በተለያዩ ሆቴሎችም በርካታ ወጣት ሴቶች የንግዱ ባለቤት ሳይሆኑ ተቀጣሪ በመሆን ይሳተፋሉ። ወጣት ታየች አማረም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሰራተኞች ክበብ ውስጥ በወር ደመወዝ ብር 2000 ተቀጥራ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ የጀበና ቡና ታፈላለች። የጀበና ቡና ስራ በጣም አዋጭ መሆኑን የምትናገረው ወጣት፤ በቀን በጣም ጥሩ ተሰራ ከተባለ 100 ሲኒ ማለትም ከአንድ ኪሎ ቡና በላይ የሚሸጥበት ጊዜ እንዳለና ስራው አዋጭ እንደሆነ ትናገራለች።
አንድ ኪሎ ቡና ከ100 እስከ 140 ብር የሚገዛ ሲሆን፤ አንድ ኪሎ ቡና ከ80 እሰከ 100 ሲኒ እንደሚወጣው የምትገልፀዋ ወጣት ታየች፤ ወደፊት ስራውን የራሷ አድርጋ የመስራት ፍላጎት ቢኖራትም ከገቢው በላይ ከክበቡ ባለቤቶች ጋር ያላት ግንኙነት ቤተሰባዊ መሆኑ አስሮ እንዳስቀመጣት ትናገራለች።
ወጣት ታየች፤ በክበቡ ተቀጥራ ቡና ማፍላት ከጀመረች አራት ዓመታትን አስቆጥራለች። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ሰዎች ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ በስራዋ ላይ የሚያጋጥሟት የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም ሁሉንም እንዳመጣጡ በመመለስ በትዕግስት እየሰራች እንደምትገኝ ትገልፃለች። ወደፊት የራሷን ስራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት በመጠቆም፤ ልምድ ማግኘቷ የሚጠቅማት መሆኑንም ነው የምታብራራው።
በተለያዩ ፎቆች በረንዳ ላይ የተፈጠሩት የጀበና ቡና ቤቶች ውስጥ የምናገኛቸው እንስቶች የንግዱ ባለቤት ሳይሆኑ ለባለ ሀብቱ ተቀጥረው የሚሰሩ ናቸው። ከዚህም በላይ በየመንደሩ በጀበና ቡና ንግድ የሚተዳደሩና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉትን ዜጎች የስራ ዕድል አይጋፋም ወይ?… ብለን የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ተገኝ፤ ይህን ብለዋል።
የጀበና ቡና ስራ ክልከላ ያለው ለውጭ ዜጎች ብቻ በመሆኑ አንድ የውጭ አገር ዜጋ ፍቃድ አውጥቼ የጀበና ቡና ልስራ ቢል አይፈቀድለትም። በተመሳሳይ ደግሞ የጀበና ቡና ስራ ለአገር ውስጥ ዜጋ ብቻ የተፈቀደ የስራ ዘርፍ እንደመሆኑ ማንም ሰው ቡናን በእስታንዳርድ እሰራለሁ ብሎ ከጠየቀ ፍቃድ አውጥቶ መስራት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
እርግጥ ነው አሁን አሁን ትልልቅ ቤቶች ላይ እና ፎቆች ላይ ተከራይተው የጀበና ቡና የሚሰሩት አቅም ያላቸው ነጋዴዎች ቢሆኑም፤ ፍቃድ አውጥተው በእስታንዳርድ አንድ ሲኒ ቡና ከስምንት እስከ አስር ብር የሚሸጡና ለመንግስት ግብር የሚከፍሉ ናቸው። ጥቃቅኖቹ በየመንደሩ ላስቲክ ወጥረው የጀበና ቡና የሚሰሩ ዜጎች ደግሞ መንግስት ጥሪት ማፍሪያ ነው በሚል ፍቃድ የማይጠየቁና እንደውም የሚበረታቱ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ምንም እንኳ ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ፍቃድ አውጥተው የጀበና ቡና መነገድ መብት ቢሆንም፤ በሌላ መስክ ላይ መሰማራት የሚችሉ አቅሙ ያላቸው ሰዎች ቁጥራቸው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ጥቃቅኖቹንና በየመንደሩ በአነስተኛ ወጪ የሚሰሩትን ዜጎች ከውድድር ሊያወጧቸው ይችላሉ። ይህ ደግሞ የበርካታ እንስቶችን የስራ ዕድል በር ይዘጋልና ቢታሰብበት መልካም ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2012
ፍሬሕይወት አወቀ