በማዕድን ዘርፉ የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች

ከአፍሪካ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት አላቸው በመባል ከሚታወቁት ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ሀገሪቱ ተፈጥሮ የለገሰቻት ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ክምችት ያላት ሀገር ብትሆንም፤ ሀብቷ በተለያዩ ምክንያቶች በአግባብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሲደረግ አይስተዋልም። ጥቅም ላይ አለመዋላቸው ብቻ ሳይሆን በቅጡ ስላልተጠኑ ምን አይነት የማዕድናት ሀብቶች በምን ያህል የክምችት መጠን እንዳሏት በውል እንደማይታወቅ መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህን ተከትሎ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሳታገኝ ቆይታለች። ለዚህ ከሚጠቀሱ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል የማዕድን ዘርፉ ለረጅም ዓመታት ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱ እና በቂ ሥራ ባለመሥራት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል።

ኢትዮጵያ ከማዕድን ክምችት አኳያ ስትመዘን በርካታ የማዕድናት አይነቶች ያላት በመሆኑ በሃብቱ ስማቸው በአንደኝነት ከሚጠቀሱት መካከል ትገኛለች። በአይነት ሲገለፁ ወርቅ፣ የከበሩ ጌጣጌጦች፣ ፖታሽ፣ ሊትየም፣ ኮፐር፣ ማንጋኒዝ፣ ክሮማይት፣ የፎስፌት፣ ኒኬል፣ ጨው፣ ለኢንዱስትሪ (ታንታለም ብረት እና ብረት ነክ ማዕድናት እና ሌሎች)፣ ለኮንስትራክሽን (የድንጋይ ከሰል፣ አሸዋና ሌሎችም) ለግብዓት የሚውሉ ማዕድናት፣ የኢነርጂና የጂኦተርማል ማዕድናት ይጠቀሳሉ። በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በዓለም እጅግ ተፈላጊ የሆኑ እና ሌሎች ማዕድናት አይነቶችም ይገኙባታል። በተለይ በዓለም ላይ እጅጉን ተፈላጊ የሆኑ አረንጓዴ ቴክኖሎጂን ለማምረት ከፍተኛ አቅም ያላቸው ማዕድናት መገኛም መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሀገሪቱ ያሏትን የማዕድን ሀብት አይነትም ሆነ ክምችት መጠን በትክክል አይታወቅም። ይህን ሥራ ለማከናወን በየጊዜው ጥናቶች እየተካሄዱ ሲሆን፤ እስካሁን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የክምችት መጠናቸው የታወቁ ማዕድናት አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ወርቅ ነው። በሀገሪቱ ከ517 ቶን በላይ የወርቅ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል። በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ከ40 ያላነሱ ድንቅ እና ውድ ዋጋ ያላቸው ማዕድናት አሏት። ሀገሪቱ ከዓለም ግዙፉ ያልለማ የፖታሽ ክምችት ካላቸው ሀገራትም አንዷ ናት። በደናክል ተፋሰስ ውስጥ በርካታ የፖታሽ ክምችት አላት። የጂኦተርማል አቅሟም ከ10ሺ ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት እንደሚችል ተረጋግጧል። በአሁኑ ወቅት ያላት የድንጋይ ከሰል ክምችትም ከግማሽ ሚሊዮን ቶን በላይ የሚጠጋ እንደሆነ ይገመታል።

በሌላ በኩል ሀገሪቱ ለበርካታ ዓመታት ልትጠቀምበት የምትችለው በቂ ማዕድን እያላት በሀገር ውስጥ በማምረት ሳትጠቀም በመቆየቷ፤ ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ እያስገባች መኖሯ ይታወሳል። በተለይ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ ለብረት፣ ለሴራሚክ፣ ለጨርቃ ጨርቅ እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎችም ለኃይል ምንጭነት የሚውለውን የድንጋይ ከሰል ለማስመጣት ከፍተኛ ወጪ ስታወጣ ኖራለች። ለዚህም በየዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ስታደርግ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ።

እስካሁን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት የተለየውን የማዕድን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋልና በማልማት መጠቀም እንዳልተቻለ ከመጠቆም ባለፈ፤ ይህም ዘርፉ ገና ያልተነካ፣ ብዙ ያልተሠራበትና ብዙ ሥራን የሚጠይቅ ነው። በተለይም ወደ ውጪ የሚላኩ ማዕድናት ላይ ትኩረት ሰጥታ አለመሥራቷ ማግኘት ያለባት ገቢ እንዳታገኝ ሲያደርጋት ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ግን በመንግሥት በኩል የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዘርፉ ትኩረት በመሥጠት ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ ሥራዎች ከመጀመራቸው ጋር ተያይዞ መነቃቃት በመፈጠሩ ለውጦች እየተስተዋሉ ይገኛሉ። ይህም ሆኖ ሕገወጥነትን በመከላከልና ማዕድናቱን ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ሥራዎች እየተሠሩ ቢቆዩም በሚፈለገው ልክ ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም። ነገር ግን ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየተስተዋሉ ነው።

መንግሥት ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በዘርፉ ከፍተኛ እምርታ እንዲመጣ አስችሏል። በተለይ ወደ ውጭ ከሚላኩ ማዕድናት የሚገኘው ገቢ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲጨምር አድርጓል። ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን ከፍተኛ ሆኗል። ወደ ውጭ የሚላኩ የማዕድናት መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምሩና ከፍተኛ ገቢ እንዲገኝ አድርጓል። ከዘርፉ ወደ ውጭ የተላኩት ማዕድናት ሀገሪቱ በታሪኳ አይታ የማታውቀውን ገቢ እንድታገኝ አስችሏታል። ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግሥትን የ2017 የዕቅድ አፈፃፀም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ያላት ሀገር ናት። በአፍሪካ ትላልቅ የማዕድን አቅም አላቸው ተብለው ከሚጠሩ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። እስካሁን በዚያ መስክ በበቂ ደረጃ ያልተሠራበት ምክንያት ባለፉት መንግሥታት የትኩረት ማነስ፣ የአመራር ማነስ፣ የእይታ ማነስ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና የማዕድን ዘርፉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ማገዝ ይችል እንደነበር አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ያለውን እንቅስቀሴ ሲያብራሩ፤ ባለፉት አራት ዓመታት ወርቅ ወደ ውጭ የተላከው በቶን ነው። በዚህ ዓመት ብቻ 37 ቶን ወደ ውጭ ተልኳል ሲሉ ጠቁመው፤ ይህን የሚያህል አቅም እያለ ኢትዮጵያ ስትለምን መቆየቷን በቁጭት አንስተዋል። አምና ሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ከውጭ ምንዛሪ መገኘቱን አስታውሰው፤ ዘንድሮ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱንም ተናግረዋል። ይህ በመንግሥት በኩል የተሰጠው ትኩረት ያመጣው ውጤት መሆኑንም አስገንዝበዋል። በዚህ ጊዜ በየትኛውም መስፈርት በኢትዮጵያ ለማዕድን የተሠጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው፤ ውጤቱም ይናገራል ሲሉ አስረድተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠቀሰው ሌላኛው ማዕድን፤ ጋዝ ነው። ጋዝ ለማውጣት በንጉሡ ዘመን፣ በደርግ ዘመን፣ በኢሕአዴግ ዘመን ሙከራዎች ነበሩ። ከሙከራዎች አልፎ ንግግሮች፣ ስምምነቶች ተካሂደዋል። ከለውጥ በኋላም የግሉ መስክ ተዋናኞች ጋዝ ለማምረት፣ ፋብሪካ ለመትከል ተፈራርመው ሥራ መጀመራቸው ይታወሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በጋዝ ዙሪያ የሚሠሩ የግል ዘርፍ ተዋናኞች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የነበራቸው አቀራረብ ፈቃድ መውሰድና በፈቃዱ ብር ከመፈለግ ውጪ ብር ይዘው የሚሠሩበት ሁኔታ አለመኖሩንም አመላክተዋል።

ይሄንን ተከትሎ አያዋጣም በሚል የነበሩ ኩባንያዎች ተሰርዘው አዳዲስ አቅም ያላቸው ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ መደረጉን አስታውሰው፤ በቅርብ የጋዝ ምርት ለገበያ እንደሚውል አስታውቀዋል። ከጋዝ ምርት ጋር ተያይዞ ሠፊ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሶማሌ ክልል ጋዝ ለማምረት የሚያስችል ሥራ መሠራቱን እና የሥራው የመጀመሪያው ምዕራፍ መጠናቀቁን አብስረዋል፤ በቅርቡ እንደሚመረቅም አመላክተዋል።

በሌላ በኩል ከማዕድን ጋር በተያያዘ ስለማዳበሪያ አንስተው፤ የግብርና ዘርፍ የተሟላ ውጤት የሚያስገኘው የማዳበሪያ ፋብሪካ ኢትዮጵያ ካላት ብቻ መሆኑንም አመላክተዋል። በማዳበሪያ ምክንያት ምርታማነት ሊወርድ ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም ከተለያዩ ኃይሎች ጋር መንግሥት ሲነጋገር መቆየቱንም አብራርተዋል። በመጨረሻ የአፍሪካን ልማት የራሱ ልማት አድርጎ የሚያስብ በኢትዮጵያም በተለያዩ አፍሪካ ሀገራትም ብዙ ኢንቨስትመንት ያለው የናይጄሪያ ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ ጋር ድርድር የተካሔደ መሆኑንም ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጋዙ ምርት ለገበያ እስከሚውል ሲጠበቅ ነበር ብለዋል።

እንደእሳቸው ማብራሪያ፤ በቅርቡ ኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ መሥራት ትጀምራለች። የማዳበሪያ ፋብሪካ መሥራት ትጀምራለች ብቻ ሳይሆን፤ ከ40 ወራት በኋላ ጨርሳ ታስመርቃለች። ወርቅ ለማምረትም ሦስት እና አራት ፋብሪካዎች እየተሠሩ ነው። ምናልባት ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ፋብሪካዎቹ ያልቃሉ። እነሱ ካለቁ በከፍተኛ ደረጃ የወርቅ ምርት ያድጋል።

ታንታለምን በተመለከተም፤ ከትላልቅ ኩባንያዎች ጋር ንግግር መጀመሩን አመላክተዋል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማዕድን አቅም አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለምሳሌ ጋዝን በመጥቀስ የኢትዮጵያ መንግሥትና የቻይና መንግሥት ኩባንያዎች በጋራ የሚያመርቱት መሆኑን አስረድተዋል። ማዳበሪያውን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥትና ዳንጎቴ በጋራ የሚያመርቱት መሆኑን ተናግረዋል። ትክክለኛውን ኢንቬስተር በመምረጥ ከመንግሥት ጋር ማዕድንን በጋራ ለማልማት እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ ፈቃድ እየወሰዱ ሰዎች እንዳይጠፉ እንዲሁም፤ ለግል ዘርፉ በመተማመን ሰጥቶ መተው ሳይሆን እውቀትና ካፒታል የሚገኝበትን መንገድ ለመከተል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከማዕድን በተለይም ከወርቅ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከሀገሪቱ ዕቅድ በጣም ከፍ ብለው የተፈጸሙ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል። በአጠቃላይ ሀገሪቷ በማዕድን ዘርፉ ካላት ሰፊ ክምችት አንጻር ብዙ ሥራዎች የሚጠበቁ ቢሆንም፤ በተለይ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ወዲህ የታዩ ለውጦችና የተመዘገበው ውጤት አበረታች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል። ይህም በቀላሉ የመጣ ሳይሆን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱና የማስተካከያ እርምጃዎች በማድረጉ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ አስረድተዋል። በመጨረሻም ከማዕድን በአጠቃላይ በጋዝ፣ በወርቅ፣ በማዳበሪያ እየመጣ ያለው እመርታ ትኩረት አልተሰጠውም የሚያስብል ብቻ ሳይሆን የሚጨበጥ ውጤት ያለው ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

የማዕድን ዘርፉ ለኢኮኖሚ ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር ዘርፍ ነው። በዘርፉ አሁን ላይ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ለማስቀጥል በመንግሥት ብቻ የሚከወነው ተግባር ሊሆን አይችልም። በመሆኑም እየታዩ ያሉ ጅምሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ሀገሪቱ ከሀብቱ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል። ለዚህም በዘርፉ የተሠማሩና መሠማራት የሚፈልጉ አካላትና የሚመለከታቸው ሁሉ የየድርሻቸውን በመወጣት በዘርፉ የሥራ እድልን ከማስፋት ባሻገር ሀገሪቱ ከሀብቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ያስፈልጋል የሚለው መልዕክታችን ነው ።

በወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You