
በግንቦት ወር መጀመሪያ አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመትና የማስተማሪያ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ተከብሯል:: 22 ፕሮጀክቶችን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ አፅቀሥላሴ በተገኙበት አስመርቆ ስራ አስጀምሯል::
ፕሮጀክቶቹ በምርምር የታገዙ በመሆናቸው የመማር ማስተማር ሂደቱን ከማገዝ ባሻገር በጤናው ዘርፍ የሚሰጡ አገልግሎትን የሚያሻሽሉና የሚያሳልጡ የሆስፒታሉን አቅም የሚያሳድጉ መሆናቸው ተገልጿል:: ፕሮጀክቶቹ በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ ቢሆንም ዩኒቨርሲቲው የመምራት፣ የማስፈጸምና የማጠናቀቅ አቅሙንና የዳበረ ልምዱን ተጠቅሞ የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች ከግብ እንዲደርሱ ባደረገው ጥረት ለስኬት የበቁ ናቸው::
ከእነዚህም 22 ፕሮጀክቶች መካከል የካንሰር ጨረር ህሙማን ማዕከል፣ የኦክስጅን ማምረቻና ህክምና ማዕከል፣ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ማዕከል፣ የቅድመ ህክምና ላብራቶሪ ህንጻ፣ የደረቅ ቆሻሻ ማቃጠያ ማዕከል፣ የሰው ሰራሽ እግር ማምረቻ ማዕከል፣ የድንገተኛ ህክምና ማዕከል፣ የውስጥ ደዌና የጽኑ ህሙማን ህክምና መስጫ ማዕከል፣ የመረጃና ደህንነት ቴክኖሎጂ ማዕከል፣ የማህበረሰብ አቀፍ ሬዲዮ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፣ የእርሻ መካናይዜሽን ፕሮጀክት ተጠቃሽ ናቸው::
ፕሮጀክቶቹን አስመልክቶ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ካሉ ከስምንት አንጋፋ የምርምር ተቋማት መካከል አንዱ ነው:: ከማህበረሰቡ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ስላለው ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች እየሠራ ይገኛል::
ፕሮጀክቶች ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የተጠናቀቁ ቢሆንም የዩኒቨርሲቲውን የ70ና የ100ኛ ዓመታት ምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በአንድነት እንዲመረቁና ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል:: ዩኒቨርሲቲው በጎንደር ከተማና ባሉት ካምፓሶች ያስገነባቸው እነዚህ ፕሮጀክቶች በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው። ፕሮጀክቶቹን ለመገንባት አራት ቢሊዮን ብር ወጥቷል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል አምስቱ ቀደም ሲል ባሉት አመራሮች የተጀመሩ ሲሆን፤ እነዚህ የማጠናቀቅና የማስቀጠል ሥራ ተከናውኗል:: ቀሪዎቹ 17 የሚሆኑ አዳዲስ በመሆናቸው አሁን ባሉት አመራሮች ተጀምረው የተጠናቀቁ ናቸው:: ፕሮጀክቶቹ የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሂደትና በጤና፣ በግብርናና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለማህበረሰቡ ብሎም ለአጎራባች አካባቢዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ናቸው::
አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች በሆስፒታሉ የሚገኙና ዘመኑ የሚፈልገው ጥራት የሚያመጡ በመሆናቸው የሆስፒታሉን የጤና እና የማስተማር አቅም ለመጨመር ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። ይህም ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ከምርጥ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን የያዘውን እቅድ ለማሳካት፤ አገልግሎቱን ለማዘመን፣ ትውልድ ለመቅረጽና በሀገር ግንባታ አሻራውን እንዲያኖር ጉልህ አበርክቶ ይኖራቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ጨምረው እንዳብራሩት፤ በአጠቃለይም ፕሮጀክቶቹ አሁን ላይ የሚፈልገውን ጥራት የሚያመጡ፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማርና ምቹ የሥራ ቦታን የሚፈጥሩ ናቸው::
‹‹አሰራራችንን በማዘመን ወጪ ቆጣቢና ተጠያቂነትን የሚያስፈንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትም ያስችላሉ::›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በሁሉም ፕሮጀክቶች ያለው ድምር ውጤት የዩኒቨርስቲውን ተልዕኳችንን ለማሳካት እንዲሁም በተመሳሳይ የሚሰሯቸው የምርምር ስራዎች ችግር ፈቺና ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል:: የሚሰጧቸው የማህበረሰብ አገልግሎቶችንም የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ እንዲሆኑ ያስችላል ሲሉም ይገልፃሉ ::
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ልጅአለም ጋሻው በበኩላቸው አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ከማህበረሰብ አገልግሎት፣ ከህክምና፣ ከመማር ማስተማርና ከምርምር ጋር የተገናኙ በመሆናቸው የዩኒቨርሲቲውን ተቋማዊ አቅም በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው ይገልጻሉ::
አቶ ልጅአለም እንደሚያብራሩት፤ ዪኒቨርሲቲው በተለይም በህክምናው ዘርፍ የረጅም ዓመታት ልምድ ያካበተ ነው:: ከተገነቡት መካከል አስሩ ፕሮጀክቶች የህክምናው ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው::
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በአማራ ክልል የመጀመሪያውና በሀገር አቀፍ ደረጃም አምስተኛው የካንሰር የጨረር ህክምናን ማዕከል ነው:: ቀደም ሲል በሆስፒታሉ ኬሞና ተመሳሳይ የካንሰር የህክምና አገልግሎቶች ይሰጡ ነበር። የጨረር ህክምና አገልግሎት ባለመኖሩ በርካታ ህሙማን ወደ አዲስ አበባ እና ጅማ ሪፈር እየተደረጉ ሲቸገሩ ቆይተዋል:: የማዕከሉ መገንባት በህሙማኑ ህክምና ለማግኘት የሚያጋጥማቸውን እንግልት የሚያስቀር ይሆናል::
ማዕከሉ የተሟላና ዘመናዊ ጨረር ህክምና መስጫ ማሽን የተገጠመለት በመሆኑ ብቁ ባለሙያዎች በማሰልጠን አገልግሎት መስጠት ጀምሯል:: የካንሰር ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የማዕከሉ መከፈት የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል:: በርካታ ህሙማን ማስተናገድ የሚችል በመሆኑ፤ የሆስፒታሉን አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ከፍ ከማድረግ በዘለለ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
የማዕከሉ ግንባታ በሁለት ዙር የተከፈለ ሲሆን፤ የመጀመሪያው የካንሰር ጨረራ አገልግሎት የሚሰጥ የራዲዮ ቴራፒ ማሽን ያለበትና የራሱ ኢሜጂንግ ሲቲ ስካን ያለው ነው:: ሌላኛው ተኝተው ለሚታከሙ የካንሰር ህሙማን የተሟላ አገልግሎት የሚሰጠው ሲሆን፤ ይህም በቀጣይ ግንባታው እንደተጠናቀቀ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል።
ማዕከሉ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ከትግራይ እና ከአፋር በተጨማሪ ከሱዳን ም ለሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል:: አንዱ ማዕከል ላይ የጨረር ህክምና ብልሽት ቢገጥምና አገልግሎት ቢቋረጥ ከሆስፒታል ወደ ሆስፒታል የመላክ ልምድ ስላለ ሌላ ጋር ሲታከሙ የነበሩትም አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል:: ማእከሉ የህክምና ቱሪዝምን ለማስፋፋትም ይረዳል።
ሌላው በአቶ ልጅአለም የተገለፀው፤ የኦክስጂን ማምረቻ ማዕከል ነው:: በሆስፒታሉ በዓመት ከ500መቶ በላይ ህሙማን የህክምና አገልግሎት ያገኛሉ። በመሆኑም ለጽኑ ህሙማን ታካሚዎች፣ ( ለህጻናት ፣ ለአዋቂዎችና ለእናቶች የወሊድ ህክምና) ጋር የተገናኙ የኦክስጅን አገልግሎቶች እንደሚያስፈልጉ ይታወቃል:: ቀደም ሲል ኦክስጂን አዲስአበባ ወይም ከባህርዳር በግዥ በማምጣት ጥቅም ላይ ይውል ነበር:: የሆስፒታሉ የአገልግሎት ስፋት የታካሚዎች ቁጥርና የኦክስጂን አቅርቦቱ የተመጣጣነ ስላልነበር የራሱን ኦክስጅን ማምረቻ በመገንባት የኦክስጅን አቅርቦቱን ሙሉ በሙሉ መሸፈን ተችሏል:: ማዕከሉ 13 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሕዝብ አገልግሎት እንደሚሰጥ ይታመናል::
እንደእሳቸው ገለፃ፤ ማዕከሉ የማምረት አቅም በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ለሆስፒታሉ ብቻ ሳይሆን በሙሉ አቅም ሲያመርት ለሌሎች በአጎራባች ለሚገኙ የጤና ተቋማት ጭምር ኦክስጅን የማቅረብ አቅም ፈጥሯል:: ኦክስጅን ለታካሚዎች በሲሊንደር ከቦታ ቦታ ተደራሽ ማድረግ እንዳለ ሆኖ በመስመር ተደራሽ በማድረግ ህክምና አገልግሎት አሰጣጡን ከፍ ለማድረግ ተችሏል:: ይህም አገልግሎት አሰጣጥን ከማሳደግና የህክምና ጥራት ከፍ ከማድረግ አኳያ የራሱ አስተዋጽኦ አለው።
በዚህ ፕሮጀክት ሥር ሌሎች ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፣ የደረቅ ቆሻሻ ማቃጠያና የንጹህ መጠጥ ውሃ ማጣሪያ ናቸው:: ቀደም ሲል የፈሳሽ ውሃ ማስወገጃ ችግር ስለነበረ ፍሳሽ ወደ ማህበረሰቡ እየተለቀቀ የአካባቢ ብክለት ሲያስከትልና ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲነሳበት ነበር::
ፕሮጀክቱ የሆስፒታሉን ፍሳሽ በዘመናዊ መንገድ በማጣራት የተጣራውን ውሃ ለላውንደሪ፣ ለአትክልት እንዲሁም ለኩላሊት እጥበት አገልግሎት ጭምር እንዲውል የሚያስችልና የመጠጥ ውሃ እስከማምረት የሚደርስ ሆኗል። በተጨማሪ ራሱን የቻለ የመጠጥ ውሃ ማጣሪያ ተገንብቷል። በተመሳሳይ የደረቅ ቆሻሻ ማቃጠያ አወጋገድም ዘመናዊ ስላልነበረ ከአካባቢ ብክለት ጋር በተገናኘ ችግር ሲያስከትል ቆይቷል። አሁን ላይ ግን ዘመናዊ የአካባቢን ብክለት የሚቀንስ የቆሻሻ ማቃጠያ ተገንብቶ ሥራ ጀምሯል ።
ሌላኛው ፕሮጀክት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የተገነባው የሰው ሰራሽ እግር ማምረቻ ማዕከል ነው:: ማዕከሉ በጦርነት፣ በመኪና አደጋ፣ በተለያዩ ጉዳቶች ምክንያት የአካል ጉዳት የደረሳባቸው ሰዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያስችላል:: ሥራውን በጀመረ አጭር ጊዜ ውስጥ ከ80 በላይ ለሚሆኑ ሰው ሰራሽ እግር ለሚፈልጉ ህሙማን ሰው ሰራሽ አካል የመተካት ሥራ ተሰርቷል:: ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ለአንድ ሺ ታካሚዎች የተሟላ አገልግሎት መስጠት ይችላል:: ብዙ ሰው ሰራሽ እግር የሚፈልጉ ሰዎች አሉ:: በመሆኑም ማዕከሉ የተሟላ ግብዓትና ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ በቂ ባለሙያዎች ስላለው የአገልግሎቱ ፈላጊዎች በተመጣጠነ ክፍያ ህክምና እንዲያገኙ የሚያደረግ ይሆናል።
የንጹሕ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም ከእነዚሁ ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀስ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ በጎንደር ከተማም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እጥረት ፈተና ሆኖ ቆይቷል:: ለመማር ማስተማር፣ ለምድረ ግቢ ውበት እንክብካቤ፣ ለተማሪዎች የምግብና የመጠጥ አገልግሎት የሚውል በጣም ከፍተኛ የውሃ ፍላጎት አለ:: ለምርምር ሥራዎችና የሆስፒታል አገልግሎት ከፍተኛ የውሃ አቅርቦት ያስፈልጋል። የተማሪዎች አገልግሎትም ከፍተኛ የውሃ ፍጆታ ስላለው ይህንን የውሃ አቅርቦት ከከተማዋ ማግኘት ፈታኝ ነበር።
ይህን ችግር ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው በራሱ ፕሮጀክት አምስት የውሃ ጉድጓዶችን በማልማት ማዕከል ላይ በተገነባ የውሃ ማከፋፈያ ለማራኪ፣ ለአጼ ቴዎድሮስ፣ ለፋሲል ግቢ በቂ የውሃ አቅርቦት ማድረስ ተችሏል:: ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲው ከተማዋ ከሚያቀርበው 20 በመቶ ያህል ውሃ ይጠቀም ነበር። ይህንን ውሃ በማስቀረት ዩኒቨርሲቲው ራሱን እንዲችል አድርጓል:: ውሃው የጉድጓድ ውሃ እንደመሆኑ በየጊዜው በላብራቶሪ ምርመራ በማድረግ ይፈተሻል፤ ጉድጓዶችን የማጠብና የማጣራት ሥራ ስለሚስራ ምንም አይነት የጥራት ችግር አይገጥምም።
የውሃ ፍጆታው እንደአቅርቦቱ መጠን እየጨመረ መጥቶል የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ የምድረ ግቢ ውበት ሥራ በከፍተኛ ደረጃ የውሃ ፈጆታን ይጠይቃል:: ይህ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ሲሆን ሁለተኛው ዙር ላይ ሌሎች ውሃ ማልማት የሚያስችሉ ጥናቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም አስገንዘበዋል::
ሌላው የገለፁት የፕሮጀክቱ አካል የድንገተኛ ህክምና ማዕከልና የጽኑ ህሙማን ህክምና መስጫ ማዕከላት ግንባታ ነው:: እነዚህ ማዕከላት ቀደም ሲል በአነስተኛ ህክምና ባልተደራጀ ሁኔታ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ነበሩ:: በተለይ የድንገተኛ ህክምና ማዕከል ከፍተኛ የህሙማን ጫና የነበረበትና ለማስተናገድ አስቸጋሪ የነበረ ነው።
የጽኑ ህሙማን ህክምና መስጫ ማዕከልም ከፍተኛ ጥንቃቄና እንክብካቤን የሚፈልግ ነው:: ይሄ ማዕከል የተደረጃና በዘመናዊ ቁሳቁሶች የተሟላ ደረጃውን የጠበቀ የህሙማን ፍላጎትን በማከለ መልኩ ተገንብቶ ሥራ እንዲጀምር ተደርጓል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጨምረው እንዳብራሩት፤ ሌለኛው የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ ሥርዓት ከፕሮጀክቶቹ መካከል ተጠቃሽ ነው:: በዚህ ረገድ የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማሳለጥ የሚያስችሉ የኤሌክትሮኒክ ሜዲካል ሪከርድ ዲጂታል ሥርዓት መዘርጋት ተችሏል። ይህም የታካሚዎችን መረጃ በመሰነድ፣ ለሚመለከታቸው የህክምና ክፍሎች የህሙማኑን መረጃ ለማድረስ የሚያስችልና የህሙማን መረጃ ደህንነቱ የተጠበቀና ሚስጥራዊነቱም እንዲጠበቅ የሚያስችል ነው:: በዚህ መንገድ አብዛኛው የህክምና አገልግሎት በዲጂታል እንዲሆን ማድረግ ተችሏል::
ከፕሮጀክቶች መካከል ሌላኛውና ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት የማህበረሰብ አቀፍ ሬዲዮ አገልግሎት ነው:: ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኤፍ ኤም 92 ነጥብ አንድ የማህበረሰብ ሬዲዮ በመገንባት በቀላሉ ለጎንደርና አካባቢዋ ማህበረሰብ ተደራሽ እየሆነ ይገኛል:: ይህም በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በንቃተ ህግ ማህበረሰቡን ለማንቃትና ከማህበረሰብ ግብዓት መስብሰብ ያስችላል ::
በሌላ በኩል ደግሞ ከጋዜጠኝነትና ብሮድካስት ጋር ተያያዥ የሆኑትን ትምህርት ክፍሎች የተግባር ትምህርት የሚሰጥበት ይሆናል:: ይህም ጥራት ያለው ባለሙያ እንዲወጣ ሆስፒታሉ ለጤና ምሩቃን እንደሚሰጠው አይነት አገልግሎት እንዲሰጥ ያግዛል። በአጠቃላይ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተገነቡት 22ቱም ፕሮጀክቶች ለዩኒቨርሲቲውና ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ናቸው ሲሉ ተናግረዋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም