
የኢንዱትሪው ዘርፍ በለውጥ ውስጥ ይገኛል። ዜጎች ተደራጅተው ወይም በግላቸው ዘርፉን እየተቀላቀሉ ናቸው። ይህ ለውጥ ከሚገለጽባቸው መካከል የአነስተኛ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ይጠቀሳሉ።
የፌዴራል ኢንተርፕራይዝ ልማት በቅርቡ ባወጣው መረጃ የ2017 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት ሁለት ሺ 752 አዳዲስ አምራች ኢንተርፕራይዞች ዘርፉን ተቀላቅለዋል። ሌሎች መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት 3 ዓመታት ብቻ 13ሺህ 800 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ጀምረዋል።
ኢንዱስትሪዎቹ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው። ከእነዚህ መካከል በግብርና ምርት ላይ እሴት እየጨመረ ያለው ቡና ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሸጎ መሸጥ አንዱ ነው። ይህ ኢንዱስትሪ በተለይ ለውጭ ገበያ እሴት የተጨመረበት ቡና እንዲልክ ይጠበቅበታል። ከእዚህ አኳያ ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምትልከው ቡና እሴት የተጨመረበት አንድ በመቶ ቢሆን ነው። ይህ እንዲያድግ የመንግሥት ጽኑ ፍላጎት ነው።
የዘርፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች በባሕላዊ ሥርዓት ታጥሮ የኖረውን የቡና አፈላል ሥርዓት በማዘመን ሰዎች ቡና በቀላሉ አፍልተው መጠጣት እንዲችሉ እያደረጉ ናቸው።
ከእነዚህ አምራቾች መካከል በ2014 የተመሰረተው አልሚ ቡና አንዱ ነው። ድርጅቱ መርካቶ ተክለሃይማኖት አካባቢ ከሚገኙ ሼዶች በአንዱ በ26 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ይሠራል። የድርጅቱ ባለቤት ወይዘሮ አልማዝ ካሕሳይ እንደሚሉት፤ በአነስተኛ ኢንዱስትሪ የጀመሩት ድርጅታቸው፣ አሁን መካከለኛ ኢንዱስትሪ ላይ ደርሷል።
እሳቸው ወደዚህ ሥራ የገቡበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ አንዱ ከቡና አምራች ቤተሰብ መውጣቸው ስለቡና መረጃ እንዲኖራቸው ማደረጉ ነው። በእርግጥ ወይዘሮ አልማዝ ከቡናው በፊት ዶሮ እርባታንም ሞክረዋል። በዚህም የከተማ ግብርና ሞዴል እስከ መባል ደርሰዋል።
ወደ ቡና ቆልቶ ማሸግ ሥራ የገቡት አምስት ሺ ብር ይዘው መሆኑን አስታውሰው፤ ከዚያም ማሽን ሊዝ በሚባለው ተቋም 500 ሺ ብር ተበደሩ። በገንዘቡ የቡና መቁያ፣ መፍጫ ማሽን በመግዛት ሥራውን አሀዱ አሉ።
ሥራቸው ስኬታማ እየሆነ መጣና አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ይዘው ደግሞ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ተሸጋገሩ። አሁን ካፒታላቸው ወደ 10 ሚሊየን ብር ደርሷል። መካከለኛ ኢንዱስትሪ ሲገቡ ሥራው እየሰፋ መጣ፤ የሚጠቀሙት የቡና መቁያ ማሽን ከአንድ ወደ አራት አድጓል።
በአብዛኛው የሚሠሩት በትዕዛዝ ነው። አልሚ ቡና ሁሉንም ዓይነት ቡናዎች እንደ ትዕዛዙ ሰርቶ እንደሚያቀርብ ተናግረው፣ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሞከሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን ብዙዎች ሥራ የሚሠሩት ተደራጅተው ነው፤ አልሚ ቡና ግን በግሉ እየሠራ ነው። በዚህም ለ25 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የሠራተኞቹ ብዛት አንዳንዴ ሥራ ሲበዛ ወደ 30 ይደርሳል ይላሉ።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ የድርጅቱ ምርቶች ደንበኞች ሱፐር ማርኬቶች እና የሸማች ማኅበራት ናቸው። ለዩኒየኖችም ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገ ነው። ለምርቱ የሚሆነውን ግብአት /ቡና/ የሚያገኙት ከአቅራቢዎች ነው።
በሕብረተሰቡ ዘንድ ካለው ባሕላዊ የቡና አፈላል ሥርዓት ጋር በተያያዘ እሴት የተጨመረበት ቡና ለገበያ ማቅረብ ቀደም ሲል አስቸጋሪ አንደነበር አስታውሰው፤ አሁን በጣም ተለምዷል ይላሉ።
ወይዘሮ አልማዝ የኢንዱስትሪው ማነቆዎች ያሏቸውንም አመልክተዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የማምረቻ አካባቢው መብራት መቆራረጥና መጥፋት ፈታኝ ሆኖባቸዋል። የመብራቱ ችግር የእሳቸው ችግር ብቻ ሳይሆን የዘርፉ ትልቅ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፤ ለ15 ቀናት የጠፋበትን ጊዜ እንደአብነት አንስተዋል።
‹‹የምንጠቀመው ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሶስት ፌዝ ነው፤ መብራት ጠፋ ማለት የትም ሄዶ መሥራት አይቻልም። ቁጭ ብሎ መጠበቅ ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህ ችግር በዚህ ዓመት ብቻ ሁለት ጊዜ እንደገጠማቸው ጠቁመዋል።
ሌላው የማሸጊያ ችግር ነው። ማሸጊያው የሚመጣው ከውጭ ነው። ዋጋው ውድ ነው፤ በሀገር ውስጥ የሚመረተው ማሸጊያ ዋጋም ቢሆን አይቀመስም ይላሉ።
በውሃ በኩልም ችግር መኖሩን አስታውሰው፤ አካባቢው ላይ ውሃ የሚያገኘው በ15 ቀን አንዴ ነው ይላሉ። የቡና ሥራ ውሃ በእጅጉ የሚፈልግ መሆኑን አስታውሰው፤ ሠራተኞች ብዙ በመሆናቸው ለመታጠብ ውሃ ያስፈልጋል ሲሉም አመልክተዋል።
ይሁንና አንዳንድ ችግሮች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተፈቱበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል። በጋራ ለመፍታት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፤ ለእዚህም ታንከር በማዘጋጀት የውሃውን ችግር ለመፍታት የተደረገውን ጥረት አንስተዋል።
ሌላው የኢንዱስትሪው ስጋት ያሉት የጥሬ ቡና መወደድ ነው። የአቅርቦቱ ጉዳይ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከቀጠለ ሥራው አዋጭ እንደማይሆንም አስገንዝበዋል።
የቡና ንግዱን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደሚያውቁት አስታውሰው፤ የቡና ግብይት ሰንሰለት አጥሯል ቢባልም አሁንም በረጅም ሰንሰለት ውስጥ እያለፈ መሆኑን ያስረዳሉ። ለዋጋው ውድነት አንዱ ምክንያት ደላላ ነው ሲሉ ጠቁመዋል። ወደ ውጪ የሚላከው ቡና መጠን እየጨመረ መምጣት ለሀገር፣ ለአምራቹ ወዘተ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ በእነሱ ገበያ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል።
‹‹ ቡና ላይ እሴት መጨመር እንደ ሌላው ሥራ ቀለል ያለ አይደለም፤ ከባድ ሥራ ነው›› ያሉት ወይዘሮ አልማዝ፤ እንዲያም ሆኖ ኢንዱስትሪው ተስፋ እንዳለው አስታውቀዋል።
በከተሞች እየተፈጠረ ያለው የአኗኗር ልዩነት ለቡና ቆልቶ፣ ፈጭቶና አሽገው ለሚያቀርቡ ሰዎች መልካም እድል ይዞ መጥቷል ሲሉም ጠቅሰዋል። ቡና ቆልተው አሽገው የሚሸጡ ሰዎች ራሳቸውን የበለጠ እንዲያዘጋጁም መክረዋል።
እሳቸው አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ ከአርሶ አደሮች ጋር ተሳስረው ለመሥራት አስበዋል። ከቡና አምራች የትውልድ አካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር ለመሥራት እየተጻጻፉም ይገኛሉ።
ወይዘሮ አልማዝ የተዘጋጀ ቡና ወደ ውጭ መላኩን እንደሞከሩት፣ ይሁንና ከባድ እንደሆነባቸው በማስታወስ፤ ኮፊ ሀውስ መክፈት እንደሚያዋጣ ተረድተው በ2018 ዓ.ም ወደ ሥራው ለመግባት አቅደዋል።
ገበያው በውጪም በሀገር ውሰጥም ጠንክሮ እንዲወጣ በቅድሚያ የቦታውን ስታንዳርድ ማስጠበቅ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል። ለእዚህ ደግሞ ለቡና ማዘጋጃ የሚሆነው ቦታ ሰፊ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።
የመድሃኒትና ቁጥጥር ባለሙያዎች ሥራ ቦታ በተደጋጋሚ የሚመጡ መሆኑን ጠቁመው፤ ምርቱን፣ ሥራውን ያያሉ፤ የጥራት ደረጃውን አረጋግጠው ያሳልፉታል ይሁንና ከቦታ አንፃር ሁልጊዜ ጭቅጭቅ ይነሳል ሲሉ ያብራራሉ።
ለማሽን ግዥ ብድር በማግኘት በኩል ችግር እንደሌለ አንስተው፤ ሌላ የብድር አገልግሎት ለማግኘት ግን ቢሮክራሲው ከባድ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማስፋፊያ የሚሆን ቦታ መጠየቅ ከጀመሩ ሶስት ዓመታት ሊሆናቸው መቃረቡን ያነሱት ወይዘሮ አልማዝ፤ ጥያቄው የቀረበላቸው አካላት እንደውም እየሠሩበት ያለውን ቦታ በተመለከተም፤ ‹‹አምስት ዓመት ሞልቶሻል፤ ትለቂያለሽ›› እያሏቸው መሆኑን ይናገራሉ። ለእርሳቸው ይህ ከባድ መሆኑን ይገልጻሉ።
ወይዘሮ አልማዝ እንዳሉት፤ በዚህ ኢንዱስትሪ ለማደግ ሶስትና አምሰት ዓመት ቀርቶ አስር ዓመት አይበቃም። ምክንያቱም ኢንዱስትሪ ፈተናው ብዙ ነው። ግብአት መፈለግ፣ ሠራተኛ ማብቃትና ማሰልጠን የግድ ነው። ይህ ሥራ ቡና ላይ ሲሆን ደግሞ ይከብዳል።
ቦታ ለማግኘት የሚጠየቀው መስፈርትም ከባድ መሆኑን ጠቅሰው፣ 50 ሚሊየን ብር አስይዞ መሬት ይሰጣል ማለት ግራ እንደሚያጋባ በማመልከት፤ ያን ያህል ገንዘቡ ካለ ለምን በራስ መንገድ ጉዳዩ አያልቅም? ሲሉም ይጠይቃሉ።
አምራቹ እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ አመላክተው፣ እርሳቸው ከዚህ ሥራ ቢወጡ በትንሹ ያበቋቸው 20 ሠራተኞች እንደሚበተኑ ይናገራሉ። በእያንዳንዱ ሠራተኛ ቤት ስንት ሰው እንዳለ ማሰብ ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ኢንዱስትሪው አንደ ሀገር በደንብ ቢታይ መልካም ነው። አድገው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱትንም ማስተዋል ይገባል። ምክንያቱም እዚያ ደረጃ ለመድረስ በጣም ብዙ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል።
ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የነበሩት ሁኔታዎች እየታሰቡ ኢንዱስትሪው በልዩ መታየት አለበት የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ፤ በኮቪድ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የሚያሠሩ ምቹ ሁኔታዎች አልነበሩም ይላሉ።
‹‹ ልቀቂ ስባል እነዚህን ማሽኖች የምወስዳቸው የት ነው? እያልኩ አስባለሁ፤ ከዚህ ከወጣሁ ስሪ ፌዝ ቆጣሪ ያለው ቤት አላገኝም።›› የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ፤ ኃላፊዎች አንዳንዴ ወረድ ብለው ማየት አለባቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ተደራጅተው የሚሠሩ እጅግ ብዙ ናቸው። አምራቾቹ ሞዴል ስኬታማዎችን ማየት ይፈልጋሉ። ለእዚህ ደግሞ ኢንዱስትሪዎች ለቁም ነገር እስከሚበቁ ድረስ መደገፍ አለባቸው። በተለይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሴቶች ማበረታቻ ቢደረግ የተሻለ ይሆናል ብለው እንደሚያስቡም ይናገራሉ።
ሌላኛዋ ቡና ቆልተው ፈጭተው የሚሸጡት፤ ወይዘሮ ጸሀይ ደመቀ ናቸው። በእዚሁ ቡና እሴት ጭመራ ኢንዱስትሪ ላይ ተሠማርተዋል። በ2013 ዓ.ም በአነስተኛ ኢንዱስትሪነት የተቀላቀለው ድርጅታቸው አቦሮ ቡና ይባላል። የማምረት ሥራውን እያካሄደ ያለው ጀሞ አካባቢ በሚገኝ ሼድ ነው።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ጸህይ እንደሚሉት፣ ወደ ኢንዱስትሪው ሲሰማሩ በቅድሚያ የቡና ቅምሻ ስልጠና ተከታትለዋል። ‹‹አቦሮ ማለት ማለዳ ወይም ጎህ ሲቀድ ማለት ነው፤ እኔም ስሜ ጸሀይ ስለሆነ የድርጅቱንም አቦሮ ቡና ብዬ የሰየምኩት›› የሚሉት ወይዘሮ ፀሀይ፣ እሳቸውን ሰው የሚያውቃቸው በአቦሮ ቡና መሆኑን ያብራራሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለው በ300ሺ ብር ካፒታል ነው። ከዚያም ከአዲስ ካፒታል ማሽን የቡና መቁያና መፍጫ ማሽን በብድር ወስዶ ወደ ሥራው ገብቷል። ሥራውን አምስት ሆነው ቢጀምሩትም አሁን ለሁለት እየተፈጸመ ይገኛል።
ቀደም ሲል ቦታ የተሰጣቸው ሀና ቆጣሪ የሚባል አካባቢ ነበር። አካባቢው መሰረተ ልማት አልነበረውም። በኋላም ወደ ጀሞ አካባቢ ሼድ ተዛውረው 120 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቷቸው እየሠሩ ናቸው። የጀሞው መብራት አለው፤ ከመንገድ ግንባታ ጋር ተይይዞ ውሃው ተቋረጦ እንጂ ጥሩ አካባቢ ነው። መንገዱ ግን በጣም አስቸጋሪ ነው ይላሉ።
እንደእሳቸው ገለፃ፤ ሥራው መልቀሚያ፣ ማቀዝቀዣ፣ መቁያ፣ ማሸጋያ ሰፊ ቦታ ይፈልጋል። ይሁንና ነገሮች ባይሟሉም የአቅማቸውን ያህል እየሞከሩ ነው። የጥሬ ቡና መወደድ እሳቸውም ስጋት አሳድሮባቸዋል።
ቡናቸውን በተለይ ድርጅቶች እንዲሁም አንዳንድ ግለሰቦች አዘውትረው እንደሚገዙ ጠቅሰው፣ ከበፊቱ ይልቅ አሁን ጥሩ ገበያ እንዳለ ወይዘሮ ጸሀይ አስታውቀዋል። እንደ ወይዘሮ አልማዝ ሁሉ እሳቸውም በኮንደሚኒየም፣ በሪል ስቴት የሚኖር በርካታ ሕዝብ የቡናው ወይም የኢንዱስትሪው ተፈላጊነት እንዲጨምር እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ቡና በባሕላዊ አፈላል የተዋጠ ነው፤ ሰው ወዲያው ተቆልቶ አሽትቶ መጠጣት ይፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ጸሀይ፤ ይሁንና ሁኔታው እየተቀየረ ነው። ቡና ቆልቶ አሽጎ ለገበያ ማቅረብ ገና ብዙ ሊሠራበት የሚችል ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው ይላሉ። ወደፊትም የበለጠ እየተቀየረ ይሄዳል ብለው እንደሚያስቡ ይናገራሉ።
‹‹ቡና የኛ ነው፤ ይሁንና እኛ ስለቡና ገና ብዙ አላወቅንም። ዓለም ግን ተራቆበታል።›› ሲሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ፀሃይ፤ በደንብ ከተሠራ ወደፊት ከውጪው ባልተናነሰ መልኩ የሀገር ውስጥ ገበያ የተሻለ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ድርጅታቸው ቡናውን የሚያቀርበው ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ነው። ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ቢፈልግም ሂደቱ ላቦራቶሪ፣ ጥሬ ቡና ማስቀመጫ መጋዘን እና እርሻ ጭምር ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ፀሃይ፤ በተጨማሪ ገበያው በአስመጪና ላኪዎች የተያዘ በመሆኑ ለጊዜው ወደ ውጭ የመላክ ሃሳባቸውን ትተውታል።
እሳቸው ራዕይ በአቦሮ ቡና ላይ በቅድሚያ ሀገር ውስጥ በሚገባ መሥራት፤ ከዚያ ለውጪ ገበያ ማቅረብ ነው። ለእዚህም እሳቸውም ተወልደው ባደጉበት ኢሊባቦር ቡና ማልማት ፍላጎት አላቸው።
አሁን የድርጅታቸው ሀብት ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ደርሷል። 11 ሠራተኞች ያሏቸው ሲሆን፤ ገበያው ሞቅ ሲል የሠራተኛቸው ብዛት ይጨምራል። በተለይ ለቡና ለቀማ ብዙ ሠራተኛ ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል።
ምርታቸውን ለማስተዋወቅ ኢግዚቢሽኖችን የሚጠቀሙት ወይዘሮ ፀሃይ ትላልቅ ኢግዚቢሽኖች ተሞክሮ ለመጋራት፣ ልምድ ለመለዋወጥ ጥሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
መንግሥት የሚሰጠው ድጋፍ ለኢንዱስትሪው ልማት በጣም ጥሩ መሆኑን ተናግረው፣ ከብድር ጋር ተያይዞ ያለው ቢሮክራሲ እሳቸውም የተቸገሩበት መሆኑን ጠቁመዋል። ብድሩን ለማግኘት ያለው ቢሮክራሲ እና ውጣ ውረዱ ሌላ አማራጭ እንዳይታይ የሚጋርድ ነው ብለዋል።
ሥራውን ለማስፋፋት የመሥሪያ ቦታ ኪራይ ውድነት ሌላው የዘርፉ ፈተና ስለመሆኑ ወይዘሮ ፀሃይ አመልክተዋል። ‹‹ሥራውን ለማስፋት እናስብና መሥሪያ ቦታ ይወደዳል። የመንግሥት ቤት አይገኝም፤ የግለሰብ ቤት በጣም ውድ ነው። የግል ቤቶች ሥራው ሲለመድ ያስወጣሉ፤ ተረጋግቶ መሥራት ያስቸግራል።›› ሲሉ ጠቁመዋል። መንግሥት በኪራይ ቢያቀርብም አምኖ መሥራት እንደሚቻል አመልክተው፤ በዚህ በኩል የመንግሥት ድጋፍ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም