
ሴት እናት ናት። እናትነቷ እና አምጣ መውለዷ ከወንዶች በተሻለ መልኩ ለሰዎች እንድትራራ የሚያስገድዳት በመሆኑ፤ አጭበርብራም ሆነ ገድላ ስልጣን ለመያዝ አትፍጨረጨርም። ለዚህም ይመስላል በጦርነትም ሆነ በፖለቲካ አሻጥር በሚገኙ አገር የመምራት ስልጣን ላይ መድረስ ያልቻለችው።
በአለም ላይ ካሉት ከ200 ያላነሱ አገራት በሴት መሪነት ዘመናትን ያስቆጠሩ አገራት ከጣት ቁጥር ያልዘለሉ ናቸው። አገርን በመምራት ብቻ አይደለም፤ ተቋማትን መምራትና ከፍተኛ ኃላፊነት ቦታ ላይ በመቀመጥ በኩል ሴቶች ዕድላቸው እጅግ የጠበበ መሆኑን ባለው የቁጥር መረጃ ማረጋገጥ ይቻላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በፓርላማዎች የሚገኙ ሴቶች 24 ነጥብ 3 በመቶ ያህል ብቻ መሆናቸው ከላይ ላነሳነው ሃሳብ ሰናይ ማስረጃ ነው።
እርግጥ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም በቅርቡ ይፋ ባደረገው ዓለም አቀፍ የፆታ ልዩነት ጥናት “Global Gender Gap Report 2020 ” እንዳመላከተው በስርዓተ ፆታ መካከል ያሉ ልዩነቶችን በመቀነስ ረገድ ከአለም 153 አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ 70 ነጥብ 5 በመቶ አስመዝግባለች። ደረጃዋም 82ኛ ላይ ተቀምጧል። በመረጃው መሰረት በጣም ከተሻሻሉ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ በስርዓተ ፆታ መካከል ያሉ ልዩነቶች በመቀነስ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገቧ ተረጋግጧል። ይህ ይበል የሚያሰኝና የሚበረታታ ነው!
በኢትዮጵያ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት በመንግሥት አካላት ሲታይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 ነጥብ 8 በመቶ፣ በህግ ተርጓሚ አካልነት 20 ነጥብ 6 በመቶ፣ በህግ አስፈጻሚ አካላት ወይም በከፍተኛ አመራርነት 50 በመቶ፣ በመካከለኛ አመራርነት 22 በመቶ ነው።
በተመሳሳይ በክልሎች በአማካይ በህግ አውጪው 40 ነጥብ 3 በመቶ፣ በአስፈጻሚው አካልነት 14 ነጥብ 8 በመቶ፣ በህግ ተርጓሚ 17 ነጥብ 9 በመቶ እንዲሁም በውጭ ዲፕሎማሲ ተልዕኮና አለም አቀፍ ተቋማት የአመራርነት ተሳትፎ 18 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በሌሎች አገሮች እምብዛም ያልተለመዱ የመከላከያ ሚኒስትርነትን የመሰሉ ትልልቅ ኃላፊነቶች ሳይቀር በሴት ከመያዙ ባሻገር አሁንም ድረስ የሰላም ሚኒስትርነቱን የተቆናጠጡት እንስት ናቸው። የአገሪቱ ርእሰ ብሔር ስልጣን የያዙት የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት፣የጠቅላይ አቃቤ ህግ ፕሬዚዳንት እና የምርጫ ቦርድ ኃላፊ ሴቶች መሆናቸው ትልቅ እምርታ መሆኑ አያጠያይቅም። ይህንን ሳያደንቁ ማለፍም ተገቢ አይሆንም!
ነገር ግን ይህ ይቀጥላል ወይ የሚለው ያጠያይቃል። ምክንያቱም አገር የምትመራው በፓርቲ ነው። አሁን ደግሞ ፓርቲ ወደ መንግስትነት የሚመጣው በምርጫ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በ73 የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው በተለይም በተፎካካሪ ፓርቲዎች ደረጃ በአባልነትም ሆነ በአመራርነት ደረጃ የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ ነው።
እውነታው እንደሚያመላክተው እስከ አሁን ካሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አመራር ላይ ያለች ሴት አንድ ብቻ ናት። መቶ በመቶ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር ላይ ያለች ሴት የላቸውም።
የአገሪቱ ፓርቲዎች ግማሽ አካል የሆኑትን ሴቶች ወደ ጎን ትቶ መንግስት መሆን ምን ያህል አዋጭ ነው? የሚል ጥያቄ ሊቀርብላቸው ይገባል። ግማሽ ያህሉ የኅብረተሰብ ክፍል ሴት በሆነበት አገር፣ ሴቶች ወደ ፖለቲካው መሪነትና ውሳኔ ሰጪነት እንዲወጡ ዕድሉን ማመቻቸት የግድ ነው። ፓርቲዎቹ ፖሊሲዎቻቸውን፣ ፕሮግራሞቻቸውንና መተዳደሪያ ደንቦቻቸውን በማሻሻል ሴቶችን በማበረታታት የመጋበዝ ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ፤ ይህን ችግር አቃለው ለምርጫ መቅረብ ግድ ይላቸዋል።
በትምህርት ቢዘልቁም፤ ብቃት ቢኖራቸውም፤ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ሴራን በመፍራት አንዳንዴም ሊፈጠሩ የሚችሉ ጫናዎች ይኖራሉ ብሎ በመስጋት እየሸሹ ያሉ እንስቶችን ማበረታታትና ወደ አመራርነት ማምጣት ያስፈልጋል። የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና አመለካከቶችን በመከተል ሴቶችን ማካተት ከተቻለ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባትም ሆነ ህዝብ የሚማረርባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና ሌብነትን ለመከላከል ያግዛል።
በአገራዊ ምርጫ ላይ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማጎልበት ፖለቲካ ፓርቲዎች ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ነገር ግን በዋናነት ሴቶቹን ወደ አመራርነትና ወደ ነቃ የፖለቲካ ተሳትፎ ከማይጋብዙ እንቅፋቶች መካከል ከወንዶች በላይ ብቃት እንዲኖራቸው መጠበቁ ነው።
ብቃት መነሳት ያለበት ለወንድም ለሴትም ነው። ብቃት ያላት ሴት ስልጣን ስትይዝ እታች የሚፈጠሩ ጉዳዮችን በማንሳት ከእርሷ ብቃት ጋር የማጣበቅ ልምድ በመኖሩ ይህን አጉል ልማድ ማስቆም ይገባል። በአጠቃላይ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ሴት ብቃት የላትም የሚለውን ሰንኮፍ መንቀል የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2012