የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (IAAF) ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያ (Air Quality Detector Device) በአዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥ ጥቅምት ወር 2011ዓ.ም መግጠሙ ይታወቃል፡፡ በወቅቱም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም፣ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የህክምና ዳይሬክተር ሚስተር ስቴፈን ቤርሞን የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ በተገኙበት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ሥራውን በይፋ ማስጀመሩም ይታወሳል፡፡
ማህበሩ ኢትዮጵያን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት መርጦ መሳሪው እንዲገጠም በማድረጉ በወቅቱ ምስጋና ቀርቦለታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተተከለው የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያ በአሁኑ ጊዜ በፈረንሳይ – ሞናኮና በአርጀንቲና – ቦነስ አይረስ ብቻ ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሆን፤ በአፍሪካ ደግሞ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ መሣሪያው በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተገልጿል ፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአትሌቲክስ ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ቅድስት ታደሰ እንደሚሉት፤ የአየር ብክለት መለኪያ መሳሪያው በዓለማችን ኩናክ በሚባል ስፔን ውስጥ ባለ ብቸኛ ድርጅት አማካኝነት የሚመረት ነው፡፡ በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊተገበርባቸው ከታቀዱት አምስት የመጀመሪያው አገራት ኢትዮጵያ ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ ቀዳሚው አገር ሆናለች፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ካላት የረጅም እርቀት ሩጫ ታሪክ አኳያ ሌሎች የስፖርት መስፈርቶችን ማሟላት በመቻሏ የዕድሉ ተጠቃሚ ሆናለች፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም በጋራ የጀመሩት ፕሮጀክት ነው፡፡ የመሳሪያው ውጤታማነት በየጊዜው እየታየ በሌሎች አገሮች ላይ የሚተገበር ይሆናል፡፡
አትሌቶች ከረጅም ርቀት ጀምሮ እስከ ሜዳ ተግባራት ያሉትን ስፖርቶች ልምምድ ከሚያደርጉባቸው ስፍራዎች ዋነኛው ስታዲየም ነው ያሉት ባለሙያዋ፤ በዚህ ዓመት በተደረጉ ጥናቶች በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አትሌቶች ከልምምድ ጋር ተያይዞ በአስም በሽታ ይጠቃሉ፡፡ የመሣሪያው መተከል እንዲህ የጤና ችግር ላለባቸውም ያግዛል፡፡ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሮጀክቱ እንዲ ጀመር ያደረገው አትሌቶች ንጹህ አየር ባለበት አካባቢ ልምምድ ማድረግ እንዲችሉ ከሚል እሳቤ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ባለሙያዋ እንደሚሉት፤ አትሌቶች ልምምድ ማድረግ ያለባቸው ንጹህ አየር ባለበት አካባቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ልምምድ በሚያደርጉበት ወቅት ሳንባቸው በደንብ ስለሚከፈት የሚስቡት አየርም ንጹህ ካልሆነ ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና ለጤና ችግር እንዳይጋለጡ መሳሪያው የአየር ብክለት መኖር አለመኖሩን በሚሰበስበው መረጃ አማካኝነት ለማወቅ ያስችላቸዋል፡፡ ልምምድ የሚያደርጉበት የአየር ንብረት ምን ያህል ንጹህ ነው የሚለውን ደግሞ አትሌቱ፣ አሰልጣኙ፣ የአትሌቱ ተወካይና ማንኛውም ግለሰብ መረጃን ከመሳሪያው ላይ የሚያገኝበት ቀላል ምልክቶች ተቀምጠዋል፡፡ መሳሪያው በትክክል መስራትና አለመስራቱን ከመግለጽ ጀምሮ ግልጽ የሆኑ መመሪያዎችም አሉት፡፡ መሳሪያው ከተተከለ ጊዜ ጀምሮም ባለው ዳታ አማካኝነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ማንኛውም ሰው በቀላሉ መረጃዎችን ማግኘት እንዲችል አረንጓዴ ቢጫና ቀይ የሚያሳዩ መለያ ሶስት ምልክቶች አሉት፡፡ በዚህም አረንጓዴ ምልክቱ የአየር ሁኔታው ጥሩ እንደሆነ የሚያሳውቅ ሲሆን፣ ቢጫ ምልክቱ ችግር መኖሩን የሚጠቁም ነው፡፡ቀይ ምልክት ደግሞ የአየር ንብረቱ ለልምምድ ሙሉ ለሙሉ አመቺ አለመሆኑን ያረጋግጣል፡፡ አትሌቶችም በእነዚህ መረጃዎች ታግዘው ልምምዳቸውን ለማከናወን ያስችላቸዋል፡፡
መሳሪያው በየአምስት ደቂቃው መረጃ የሚያቀብል መሆኑን፤ ያለፉትን ወቅቶች የአየር ሁኔታም በመረጃ መረብ ማስቀመጥ እንደሚችል፤ ለዚህም በስታዲየሙ ምቹ በሆነ ቦታ ላይ መተከሉንና አትሌቶችም መረጃውን እየተከታተሉ ልምምዳቸውን በተሻለ መልኩ እያከናወኑ መሆናቸውንም ባለሙያዋ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ከሳንባ አልፈው ደም ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ጥቃቅን ብናኞችን ጭምር የመለየት አቅም ያለው መሳሪያ በመሆኑ ከተማው ውስጥ ባሉት እንቅስቃሴዎች ከመኪና ጭስ የሚወጣ ንጹህ ያልሆነና ብናኝ ንጥረ ነገሮችን በመለየት አትሌቱ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይረዳዋል ብለዋል፡፡
ባለሙያዋ አክለውም፤ ጥልቅ የሆኑትን ሙያዊ መረጃዎች በተመለከተ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰሩና አጠቃላይ ክትትሉ ደግሞ በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አማካኝነት የሚከናወን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ መሳሪያው አዲስ በመሆኑ ትኩረት የተሰጠው ለስፖርተኞቹ ማስተዋወቅ ነው፡፡የመሳሪያ ተከላው ለጊዜው አትሌቲክስን ታሳቢ ቢያደርግም ለሌሎች የስፖርት አይነቶችም ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ወደፊት እንዲጠቀሙ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡ የተጀመረው ፕሮጀክት ውጤተማ ከሆነ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሌሎች አገሮች ላይም ለማስፋፋት እቅድ አለው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃም ከፌዴሬሽኑ ጋር በመነጋገር ከአዲስ አበባ ስታዲየም በተጨማሪ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ ለማድረግ ታስቧል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
አዲሱ ገረመው