በክርስትና በድምቀት ከሚከበሩት አበይት በዓላት መካከል የገና (የልደት) በዓል አንዱ ነው። ይህ በዓል ሰማይና መሬት የታረቁባት፣ ሰው እና መላእክት በአንድነት የዘመሩበት ፣ ከሁሉም በላይ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲጠበቅ የነበረው የአዳም ተስፋ የተፈፀመበት፣ የተወለደበት ታላቅ የደስታ ቀን ነው።
አባ ዳንኤል በጽሑፋቸው እንደሚሉት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው ይህ በዓል በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች በብሔራዊ በዓልነቱ ቢታወቁም በጥንቷ ሮሃ በዛሬዋ ላሊበላ ከተማ ያለው አከባበር ግን እጅግ የላቀ ፣ የደመቀ እና የተለየ ነው። የቅዱስ ላሊበላ ከተማ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን አቅጣጫ በ 800 ኪሜ ርቀት አካባቢ የምትገኝ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩት ንግስናን ከክህነትን አጣምረው ከያዙት “አራቱ ቅዱሳን” መካከል አንዱ በሆነው በቅዱስ ላሊበላ ስም የተሰየመች፣ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጧም ቀይ መሬት በሆነ ኮረብታ የምትታወቅ እና ከአንድ አለት ተፈልፍለው የተሰሩ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሙዚየም ነች ።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ከ 800 ዓመት በፊት ድንቅ በሆነ የአሠራር ጥበብ ታንፀው በዘመናችን በትንግርት ማዕከልነታቸው የሚጠቀሱ እንደሆኑ አባ ዳንኤል በጽሑፋቸው ጠቅሰው እንደ ሰንሰለት ተያይዘው ከተማዋን ያደመቁት አብያተ ክርስቲያናቱ ዮርዳኖስ ተብሎ በሚጠራው አነስተኛ ሸለቆ ተለያይተው በሦስት ምድብ ተከፍለው እንደሚገኙ ይናገራሉ።
እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ከመሠረት እስከ ጣራ፣ ከመቅደሱ እስከ ቅኔ ማህሌት ድረስ ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የተሰሩ ፣ በልዩ ልዩ ቅርጾች ያጌጡና አንዱ ከሌላው ጋር የማይመሳሰሉ ናቸው። ከመደበኛዉ የህንፃ አሠራር ሁኔታ በተለየ መሠረታቸው የተጣለው ከጣራቸው ላይ መሆኑ ደግሞ የተለየ አግራሞት የሚፈጥር ነው።
የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን በ1520 ዓ.ም በመጎብኘት የመጀመሪያ የሆነው አውሮፓዊ የፖርቱጋል ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ጉብኝቱን “እጅግ በጣም አስደናቂ እና ከፍተኛ የጥበብ ችሎታ የሚታይበት ዕፁብ ድንቅ ሥራ በመሆኑ ያየሁትንና የተሰማኝን ነገር ሁሉ ብጽፍ የሚያምነኝ ስለማይኖር በእግር ተጉዘው ሄደው በአይናቸው ለሚያዩት ትቻለሁ“ በማለት አጠቃሎታል። የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የአህመድ ግራኝንም የጭካኔ ልብ የሰበሩ የጥበብ መዶሻዎች ናቸው። አህመድ ግራኝ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወረራው አብያተ ክርስቲያናቱን አድንቆ ሳይነካቸው ትቷቸው እንደሄደ የጽሑፍ መረጃዎች እንዳሉ አባ ዳንኤል ጠቅሰዋል።
ልደት በልዩ ሁኔታ ለምን በላሊበላ ይከበራል
ወደ ተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ ከሌላው አካባቢ በተለየ ሁኔታ የገና በዓል በቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የሚከበርበት ዋና ምክንያት ቅዱስ ላሊበላ የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት በታህሳስ 29 ቀን እንደሆነ የላሊበላ ከተማ አስተዳዳር የባህልና ቱሪዝም ስፖርት ፅህፍት ቤት ኃላፊ መሪጌታ መልካሙ አለሙ ይናገራሉ። በሌላ አባባል የንጉስ ላሊበላ ልደት ከኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን ጋር በመግጠሙ የልደት በዓል በቦታው በድምቀት እንዲከበር ምክንያት እንደሆነም ያስረዳሉ።
በገድሉም እንደተጻፈው ቅዱስ ላሊበላ የተወለደው ታህሳስ 29 ቀን በ1101 ዓ.ም እንደሆነ የሚናገሩት የፅህፍት ቤት ኃላፊው መሪጌታ መልካሙ አለሙ ከአባቱ ከንጉስ ዛም ስዩም እና ከእናቱ ከኪርወርና ነው። ኪርወርና በጥንቱ የአገውኛ ቋንቋ ቤተ ክርስቲያን ማለት እንደሆነም ይታወቃል። በተጨማሪም ቅዱስ ላሊበላ በተወለደ ጊዜ ነጫጭ ንቦች ስለከበቡት እናቱ ይህንን አይታ ልጇን ንብ በላው ለማለት በአገውኛ ላል በላ እንዳለችውና በሂደትም ስሙ ላልይበላ ተብሎ መጠራት እንደጀመረ በገድሉ ተገልጿል።
የት ይከወናል
ድንቅና ማራኪ የሆነው የገና በዓል ሥርዓት የሚከናወነው በቤተማርያም ቤተክርስቲያን ዙሪያ እንደ አጥር ከቦ ከሚገኘውና በተለምዶ ማሜ ጋራ ተብሎ በሚጠራው ኮረብታማ ዓለት ላይ ነው። በዚህ ዕለት ካህናቱ ከላይ ከኮረብታውና ከታች ከቤተክርስቲያኑ ዙሪያ ሆነው በመላእክትና በእረኛ ምሳሌ የሚያመሰግኑት ‹‹ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ›› የሚለው ዝማሬ ልብን የሚመስጥና ከ2 ሺህ ዓመት በፊት የተከናወነው መንፈሳዊ ታሪክ በምናብ የሚያስቃኝ ነው።
በገና በዓል ሰሞን ላሊበላ ከተማ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪው ዓለም በሚመጡ አማኞችና ጎብኚዎች ትጥለቀለቃለች። በዚህም ምክንያት ይላላ መሪጌታ አቢያተክርስቲያናቱ የገና በዓልም የከተማዋ ዋነኛ መታወቂያ ሆኖ ይገኛል።
ዳግማዊ ኢየሩሳሌም
ላሊበላ ከተማ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ዳግማዊ ኢየሩሳሌም በመባል ትታወቃለች። የመጀመሪያው ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ለመሳለም ይሄዱ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ሥቃይ ለመቀነስ ቅዱስ ላሊበላ ኢየሩሳሌም በሚገኙ ቅዱሳን መካናት አንፃር በቦታው አብያተ ክርስቲያናቱን ማነፁ የሚናገሩት ኢትዮጵዊያን ያመሪጌታ መልካሙ ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌም ሄደው የሚያገኙትን መንፈሳዊ በረከት ብዙ ችግር ሳይገጥማቸው አገራቸው ለማግኘት እንዲችሉ ታስቦ አብያተ ክርስቲያኑ እንደታነፁ መረጃዎችም ይጠቁማሉ።
ሌላው ምክንያት ደግሞ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያንን ተሳልሞ በቀጥታ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ሄዶ እንደተሳለመ ይቆጠርለታል በማለት ለቅዱስ ላሊበላ በገድሉ የተሰጠውን ቃል ኪዳን መሠረት ያደረገ እንደሆነም መሪጌታ ይነገራሉ። በቅዱስ ላሊበላ በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የልደት በዓል መንፈሳዊ በረከት የሚታፈስበት ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ትምህርት የሚገኝበት ትእይንት፣ ለጭስ አልባው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሰፊ ድርሻ ያለው እና ለአገር ገፅታ ግንባታ የላቀ ሚና የሚጫወት የቅርስ ሀብታችን ነው። ስለሆነም ይህ ለቤተክርስቲያኒቱ ሆነ ለአገራችን የማይተካ ሚና ያለው መንፈሳዊ ሀብት በአግባቡ ተጠብቆና ታውቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ይጠቁማሉ።
አባ ዳንኤል ስለዚህ ድንቅ ቦታ በጽሁፋቸው እንዲህ በቅኔ ተቀኝተዋል ፡-
በለሰ ገነት ለአዳም ወሔዋን መቲሮቶሙ
መንክረ ልደት አምላከ መንገሌሆሙ ሰሐበ፤
ወገብርኤልሀ ዜናዌ ቀጸበ፤
እንተ ከመ ዝሰ ግብር እምከመ ለአዳም ተውህበ
ወረከበት ሔዋን ዘኢተረክበ፤
ካዕበ ይስሐብ ኀቤሆሙ አበ
ለበለስ ይምትርዎ ካዕበ።
እንደ አባ ዳንኤል የቃል በቃል ፍችውም እንዲህ ነው። የገነትን በለስ አዳምና ሔዋን መቁረጣቸው ከሄደን ገነት ተባረሩ፤ በዚህም ምክንያት አስደናቂ የሆነውን የአምላክ መወለድ ወደእርሱ ሳበ። የምሥራች ነጋሪን “ገብርኤልንም” የጠቀሰው እርሱ ነው። እንዲህ ያለውን ነገር ምሥጢር ለአዳም እንደተሰጠ ሔዋንም ያልተገኘውንና ያልተመረመረውን ምሥጢር አገኘች። ታላቁ ኢትዮጵያዊ የስድስተኛው ምዕት ዓመት “ቲኦሎጂያን” ቅዱስ ያሬድ እንዳተተው፣ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ ሕይወት፤ ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አስካለበረከት፤ ወማየ ባሕርኒ ኮነት ሐሊበ ወመዓረ። ይህም ማለትም ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተራሮች የሕይወት እንጀራ ሆኑ፤ የበረሃ ዛፎችም የበረከት እሸትን አፈሩ፤ የባሕር ውኃም ወተትና ማር ሆነች ይላል።
በምዕራብም ሆነ በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንዳለው ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በአንዳንድ ዓበይት በዓላት እንደ ሆሣዕና፣ ስቅለት፣ ያሉት ከቅዳሴ በኋላ የሚደረጉ ሥርዓቶች እንዳሉ የሚጠቅሱት አባ ዳንኤል አያይዘውም አንዱ በበዓለ ስቅለቱ ከስግደት በኋላ የሚደረገው በወይራ ቅጠል ካህናቱ፣ ‹‹ይኸን ያህል ስገድ›› እያሉ የሚያደርጉት ጥብጠባ ይጠቀሳል። ሊቃውንቱ ስለ በለሶን፣ ስለገና ዛፍ አንድምታ አፍታተው እንደሚገልጹት ይጠበቃል። የሶርያው ካህን አባ ዳንኤል እንደጻፉት፣ ገና ታላቁ ምሥጢረ ሥጋዌ የሚከበርበት ነው። በዚያም ምሥጢር እግዚአብሔር ቃል፣ሰው ሆነ (ቃል ሥጋ ኮነ) በእኛም ዘንድ አደረ እንዲል።
የዘንድሮ የልደት በዓል ዝግጅት
የዘንድሮ የገና እና ቅዱስ ላሊበላ ክብረ በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅቱ እያጠናቀቅ መጠናቀቁንም የሚናገሩት መሪጌታ መልካሙ አለሙ የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ማህበረሰብ እና የላስታ ላሊበላ ህዝቦች የገና በዓል እና የቅዱስ ላሊበላ ክብረ በዓልን ለማክበር ወደ ስፍራው የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በጉጉት እና በፍቅር እየተጠባበቁ እንደሚገኙም አክለዋል።
የላሊበላ ከተማ አስተዳደር እና የላስታ ላሊበላ ማህበረሰብ ወደ ላሊበላ የሚመጡ አንግዶችን ለመቀበል እና ለማስተናገድ ኮሚቴዎች እና ንዑስ ኮሚቴዎች በማቋቋም ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት መሪጌታ መልካሙ አለሙ በአንድ በኩል እንግዶቹን ተቀብለው እግር አጥበው እና ማረፊያ አዘጋጅተው የሚያስተናግዱ፤ በሌላ በኩል ስለ ላሊበላ እና አካባቢው ታሪካዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ትውፊታው መረጃዎችን ለእንግዶች የሚያደርሱ ግለሰቦች በኮሚቴው መለየታቸውንም አስታውቀዋል ።
ወቅቱ የጾም ጊዜ በመሆኑ እድሮች እና ማህበራት ተደራጅተው የገንዘብ መዋጮ እንዲያደርጉ በኮሚቴው እየተዘጋጀ ሲሆን በዚህም ረገድ ከእድሮቹ በተገኘው ድጋፍ ምዕመናን ጾም እንዲፈቱ እንደሚደረግም ገልጸዋል ።የጸጥታ ሀይሎችም ከላስታ ወረዳ እና አካባቢው ነዋሪዎች ጋር በጥምረት የእንግዶችን ደህንነት ለመጠበቅ ዝግጅት ላይ ናቸው። በደብሩ ውስጥ የሚከናወኑ ስርዓቶችን ለማካሄድ የአድባራቱ ካህናት የጽዳት እና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶችን በመጨረስ እንደሆኑ የሚናገሩት መሪጌታ መልካሙ ሆቴሎች ከፍተኛ ቁጥር ያለውን እንግዳ ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል ። አብዛኞቹ ሆቴሎች አልጋዎችን ለውጭ ሀገራት እና ለሀገር ውስጥ እንግዶች አስቀድመው ዝግጅት እያደረጉ ነው።
በግቢያቸው ውስጥም ድንኳን ጥለው የአልጋ እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚሰጡ በተለመደው ሁልጊዜ አገልግሎት እደሚሰጡ ሆቴሎች ቅድመ ዝግጅት ላይ ናቸው። በውጭ እና ሀገር ውጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በድምቀት የሚከበረውን የገና በዓል እና የቅዱስ ላሊበላ ክብረ በዓል በላሊበላ ከተማ ተገኝተው እንዲያከብሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ። የቅዱስ ላሊበላ የልደት በዓልና የገና በዓል የሚከበረውና ሊቃውንት ‹ቤዛ ኩሉ› በተባለው ሥርዓት ዝማሜና ወረብ የሚያቀርቡት ዙሪያውን እንደ አጥር በክበባት ‹ማሜ› ጋራ ተብሎ በሚጠራው ክፍታ ቦታ ላይ እደሚከብር እና የቅዱስ ላሊበላ አገልጋይ ካህናት እና በላስታ ላሊበላ ዙሪያ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህና አብረው በአሉን በደምቀት እዲያከብሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
እንደ መሪጌታ መልካሙ ኢትዮጵያ የበለጸገ ባህል የደረጀ ባህላዊ እውቀት ያላት አገር ናት። ስለዚህም እነዚህን እውቀቶች በመጠቀም የአገር አንድነት ማስጠበቅ ተገቢ እንደሆነ ገልጸው እኛም ያሉንን በእያንዳንዱ ክልሎች እና ብሔረሰቦች የራሱ የሆነ በሀይማኖታዊና በባህላዊ ዕወቀት የደረጀ ድንቅ የመቻቻል የሰላም እና የፍቅር እሴቶች አሉ፤የመጣብንንና የሚመጣብንን ሰይጣናዊ የጥፋት ውሃ ለመከላከል ለመግታት ከመርዳት አልፈው ለአገሪቱም ሆነ ለእያንዳንዱ ግለስብ ጥቅም ያስገኛሉ። ስለዚህም ልክ እንደ ላሊበላ ከተማ በሌሎችም ከተሞች እና ብሔር ብሔረሰቦች ድንቅ ባህላዊ ዕውቀት ከአገር አልፎ ለዓለም ምሳሌ እንዲሆን ማበልጸግ እና ለአገራዊ ጥቅምና መግባባት መጠቀም አስፈላጊ ነው።ኢትዮጵያ የፍቅር የመቻቻል አገርና ምድርነቷ ይቀጥላል።
መልካም በዓል!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2012
አብርሃም ተወልደ