
“ወጣቶች ብልጽግናን ከወደዳችሁት ካርዳችሁን ስጡት፤ በልጽግናን ከጠላችሁት በድምጽ ቅጡት። ህይወታችሁን ለእኛም ሆነ ለየትኛውም ፓርቲ አትስጡ፤ ይሄ ትክክል አይደለም። በድምጽ የምትፈልጉትን ምረጡ የማትፈልጉትን ተው እንጂ ህይወታችሁን ፈጽሞ አትገብሩ! እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ልምድ በእናንተ ዕድሜ እንኳ የምታውቁት ከምርጫ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጦስ ብታዩት ፖለቲከኞች ወንድሞቻቸው፣ ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ምንም አልሆኑም፤ የድሃ ልጅ ግን ተቀጠፈ። ያ የድሃ ልጅ ማንም አያስታውሰውም እናት ናት ያለጧሪ የቀረችው።
በቅርቡም ሁልጊዜ የምታዩት ወጣቱን ገፋፍተው የሚወስዱ ኃይሎች ሲሞቱ አይታዩም ሲያጋድሉ እንጂ። የእናንተም ህይወት የእነሱም ህይወት አንድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ወጣት ስለሆናችሁና ከእነሱም የመሻል ተስፋ ስላላችሁ ለማናችንም ቢሆን ካርዳችሁን እንጂ ህይወታችሁን መስጠት የለባችሁም።” ይህን እጅግ ወሳኝ፣ ወቅታዊና በተለይም ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል በልዩ ሁኔታ በአዕምሮው ውስጥ ሊያሰቀምጠው የሚገባውን ንግግር የተናገሩት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው።
የሩቁን ትተን የቅርብ ጊዜ ትወስታችንን መለስ ብለን ብንቃኝ እንኳ ከላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ንግግር አንገብጋቢነት ግልጽ ይሆንልናል። ለማስታወስ እንኳን በ1997 ዓ.ም የነበረውን አገር አቀፍ ምርጫና ምርጫውን ተከትሎ የመጣውን ጦስ አንዘነጋውም።
የዚያን ጊዜው ምርጫ ቅድመ ሁኔታው እጅግ ያማረ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ዓይን ውስጥ ያሰቀመጠና ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ታሪክ ረጅም ጉዞን ተጉዛለች ያስባለም ነበር። በርካታ ተፎካካሪ ፓርተዎች የውድድር አማራጫቸውን አቅርበው ህዘብ በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጥ ማድረግም ችለው ነበር።
በዚህም ተባለ በዚያ ከምርጫው በኋላ የነበረው ታሪክ ግን እጅግ የሚያሸማቅቅና የብዙ ወጣቶችን ህይወት የቀጠፈ ነበር። ከዚህ ምርጫ ጋር በተያያዘ በተለይም በአዲስ አበባ የበርካታ ወጣቶች ክቡርና መተኪያ የሌለው ህይወት እንደዋዛ ተቀጥፏል።
ለአካል ጉዳት ተዳርገውም ሠርተው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በሚረዱበት ወርቃማው የወጣትነት ዕድሜ ተረጂ የሆኑም በርካቶች ናቸው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩትም ከዚህ ክስተት በኋላ እነዚህን ተጎጂ ወጣቶችና ቤተሰቦቻውን ዞር ብሎ የተመለከተ የለም። ጦሱና ቸግሩ የተረፈው ለምስኪን እናቶቻቸው ብቻ ነበር።
ለርካሽ ፖለቲካዊ ትርፍ የወጣቶችን ህይወት ማሰገበር አሁንም እንዳልቆመ እየተመለከትን ነው። የራሳቸው ፖለቲካዊ ዓላማና ግብ ይሳካ እንጂ በወጣቱ ህይወት መቀጠፍ ቅንጣት ያህል ሐዘን የማይሰማቸው ፖለቲከኞች በአገራችን በብዛት አሉ።
ከታሪክ እንደተረዳነውና ስማቸውን በነፃነት ትግል ዘላለም የምናነሳቸው ታጋዮች ታሪክ የሚያስረዳን የነፃነት ታጋዮች ከትግሉ ፊት ቆመው መስዋዕት ሲከፍሉ እንጂ እንደኛ አገር ፖለቲከኞች በሰው እጅ የእሳትን ኃያልነት ሲሞክሩ አልተስተዋለም።
በእኛ አገር ሁኔታ ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ፖለቲከኞች ራሳቸውንና ቤተሳባቸውን ከአደጋ አርቀው የወጣቱን ህይወት አደጋ ላይ ሲጥሉ እንጂ እነሱ መሰዋዕት ሲሆኑ አይታዩም። ሞት ለሁሉም እኩል ነው ቢባልም የወጣቶች ሞት ግን እጅጉን ያንገበግባል።
አሁንም በዩኒቨርሲቲዎቻን እየሆነ ያለውም ይሄ ነው። በቅርቡ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከሚስተዋለው አለመረጋጋት ጀርባ በስውር የሚሠሩ ፖለቲከኞች አሉ። እነዚህ ፖለቲከኞች ወጣቶችን በብሔር እያጋጩ ሰለማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲስተጓጎልና የወጣቱ የወደፊት ተስፋ እንዲጨልም እያደረጉ ነው።
ለፍቶ፣ ጥሮና ግሮ አሳድጎ የልጆቹን ፍሬ በቅርቡ ለመመልከት ተስፋ ያደረገውን ወላጅም ልጄ ምን ሆነ በሚል ሐሳብ ነጋ ጠባ በሰቀቀን እንዲኖር እያደረጉትም ነው። ተምረው ነገ ለፍሬ እንበቃለን ያሉ በርካታ ወጣቶች በማያወቁትና ባልገባቸው ጉዳይ ህይወታቸው እንደዋዛ ተቀጥፎ ወላጆች በመመረቂያ ጋዋን የሚጠብቋቸውን ልጆቻቸውን በአስክሬን ሳጥን እንደተረከቧቸውም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
እርግጠኛ ሆኖ መናገር የሚቻለው ይህን እኩይ ሴራ የሚሠሩ ፖለቲከኞች ልጆች ከአደጋው ዞን እጅግ የራቁ መሆናቸውን ነው። ስለሆነም በተለይም ወጣቱ ከላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ሂድ፣ በጥብጥ፣ ተጋጭ፣ አጥፋና ተጋደል የሚሉትን ኃይሎች ማንነትና ዓላማ ቆም ብሎ ሊያገናዝብ ይገባል። ማገናዘብ ብቻም ሳይሆን ለእናንተ ርካሽ ፖለቲካ ስንል የእኛንም ሆነ የንፁህ ወንድም እህቶቻችን ህይወት አንገብርም ሊላቸውም ግድ ይላል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2012