- የማሻሻያ ጥያቄ ቢያቀርብም መልስ አላገኘሁም ብሏል
አዲስ አበባ፦ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ መዋቅሩ ለስራው ማነቆ እንደሆነበት አስታወቀ፡፡ መዋቅሩ እንዲሻሻል ጥያቄ ቢያቀርብም መፍትሄ እንዳላገኘ ጠቅሷል፡፡
በኤጀንሲው የዕውቅና አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ አብይ ደባይ እንደገለፁት፤ የኤጀንሲው መዋቅር ለስራቸው ማነቆ በመሆኑ ይህንኑ ለማስተካከል ባለፉት አራት ዓመታት አጥንተን ማስተካከያ ለማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም መፍትሄ አልተሰጠንም ብለዋል።
በአገሪቱ ላለው የትምህርት ጥራት ችግር በህዝብና በመንግስት መግባባት ተደርሶበታል ያሉት አቶ አብይ፤ ከችግሩ ምክንያቶች መካከል ባለፉት ዓመታት በትምህርት አግባብነትና ጥራት ላይ በሚፈለገው ደረጃ ቁጥጥርና ክትትል አለመደረጉ አንዱ ነው ብለዋል።
ችግሩን ግዙፍና ውስብሰብ ያደረገው ቁጥጥርና ከትትል የሚያደርገው ኤጀንሲው በአዲስ አበባ በጥቂት ሰራተኞች በመደራጀቱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ከ2ሺ በላይ የትምህርት ተቋማትን በሚፈለገው ደረጃ ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ እንዳላስቻለው ተናግረዋል።
ኤጀንሲው ችግሩን ለመቅረፍ እስከ ሁለት መቶ ባለሙያዎች እንዲኖሩትና በክልሎች ሰባት ቅርንጫፎችን ለመክፈት የሚያስችል መዋቅር አጥንቶ አቅርቧል ያሉት አቶ አብይ፤ በሲቨል ሰርቪስ ኮሚሽን ጥናቱን በማስገምገም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ልኳል ብለዋል።
እንደ አቶ አብይ ገለፃ፤ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ችግሩን ቢረዱትም ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ግን እንዳልቻሉም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም በሚፈለገው ደረጃ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ችግር ተፈጥሮባቸዋል፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ በበኩላቸው፤ ተቋሙ እራሱን የቻለ በመሆኑ ጉዳዩን በእራሱ ማስፈጸም እንዳለበት ገልጸዋል። በስራቸው በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማት ስላሉ እያንዳንዱን ነገር እነሱ እንደማያስፈጽሙም አንስተዋል፡፡
ለረጅም ዓመታት ህግን በማስከበር ረገድ ችግር ነበረ የሚሉት አቶ አብይ፤ይህን ለማስተካከል በተለይም በአዲስ አበባ 167 የግል ትምህርት ተቋማት ላይ የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡
በዳሰሳ ጥናቱም 46 ካምፓሶች ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ግድፈቶች እንደተገኘባቸውና ኤጀንሲው ከግንዛቤ ማስጨበጫ እስከ ከፍተኛ የማስተካከያ እርምጃም መውሰዱን ተናግረዋል።
በታዳጊ ክልሎች የማስተካከያ እርምጃዎች ለመውሰድ ጥረት መደረጉን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ከፍተኛ ችግር በታየበት የጋምቤላ ክልል ቡድን ተዋቅሮ ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን የማስተካከያ እርምጃ እንደተወሰደም ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በተደረገው ክትትል በጋምቤላ ክልል አስራ ሁለት ህገ ወጥ የትምህርት ተቋማት መገኘታቸውንና በዘንድሮ ዓመት በድጋሚ በተደረገው ክትትልም ናፒየር ኮሌጅ፣ ዌስተርን መካነየሱስ የትምህርት ተቋም፣ ሶቢል ኮሌጂ እና ኮትራን ፒሪንተቨ የሚባሉ ህገ ወጥ የትምህርት ተቋማት ተገኝተዋል ብለዋል።
ትምህርት ቤቶቹ ምንም አይነት የማስተማሪያ ቁሳቁሱና ቤተ ሙከራ ሳይኖራቸው የጤና ትምህርትን ጨምሮ በሌሎች ሙያዎች ሲያስተምሩ መገኘታቸውንና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በሌሎቹ ታዳጊ ክልሎች ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ቢገምትም ባለባቸው የአቅም ውስንነት በሚፈለገው ደረጃ ክትትል አለማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በሱማሌ፣ በአፋር፣ በቤንሻንጉል ጉምዝና በሌሎችም ክልሎች ከክልል መንግስታት ጋር በመሆን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስዱ አመልክተዋል።
ኤጀንሲው የወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ተገቢ አይደለም በማለት ሁለት ተቋማት በኤጀንሲው ላይ ክስ መስርተው ክርክር እየተደረገበት እንደሆነም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ