የቀትሩ ጸሀይ ‹‹አናት ይበሳል›› ይሉት አይነት ነው። ድካም እያዛለን ቢሆንም ያለማቋረጥ መጓዛችንን ቀጥለናል። እርምጃችን እምብዛም የተጣደፈ የሚባል አይደለም። ወበቁ ግን ድካም ቢጤ ለሰውነ ታችን ያቀብል ይዟል።አብዛኞቻችን ስለወ ቅቱ መለዋወጥ እያነሳን አሳሳቢነቱን ጭምር እናወጋለን። ከአመታት በፊት የነበረው ንጹህ አየርና አሁን እየተነፈስነው ያለውን እያወዳደርንም በግርምታ ተደምመናል።በድንገት ግን በአካባ ቢው ካለ አንድ ቤት ጎራ ስንል ጨዋታችን ልናቋርጥ ግድ አለን።
ከበራፉ ግርጌ ከሚታየው የቁም ምድጃ የትኩስ እንጀራ ሽታ በአፍንጫ ስር ውል ይላል። እሱን አለፍ ብሎ ካለው በረትም የከብቶቹ ድምጽ በጉልህ እየተሰማ ነው።ከወዲያ ወዲህ ውር ውር የሚሉት ዶሮዎች ስፍራውን ያለከልካይ ይሮጡበታል።
ግቢውን አልፈን ወደሳሎኑ ከመዝለቃችን በሁላችንም ገጽታ እፎይታ ሲነበብ ተስተዋለ።አሁን ያረፍንበት የእመት ሽታዬ ገብረመድህን ዕልፍኝ ድንቅ የሚባል አየር እያዘዋወረ ነው።ቤቱ የቀደመውን ወበቅ ሸኝቶ ‹‹እፎይ›› ለማስባሉ ደግሞ የተለየ ማረጋገጫ አላሻንም።እንዲህ ለመሆኑ የሁላችንም ብሩህ ገጽታ በቂ ምስክር ነበር።
ወይዘሮ ሽታዬ እንደእንግድነታችን ተቀብለው ካስተናገዱን በኋላ ጨዋታቸውን ቀጥለዋል።እኛም የቤቱን ጣራና ግድግዳ እየቃኘን በግርምታ ማዳመጡን ይዘናል።እሳቸው የቀደመውን ህይወታቸውን ከአሁኑ እያወዳደሩ በትዝታ ተጉዘዋል።የዛሬን አያድርገውና ከአስራ አራት አመታት በፊት አሁን ባሉበት ሁኔታ እኖራለሁ የሚል ህልም አልነበራቸውም።
የዛኔ ኑሯቸው በአንዲት ጠባብና የፈራረሰች ቤት ውስጥ ነበር። ለመተዳደሪያ በቂ የሚባል ገቢ ያልነበራቸው ወ/ሮ ሽታዬ ለሆድ እንጂ ለስራ ያልደረሱ ህጻናትን ሲያሳደጉም በበርካታ ችግሮች ውስጥ ሆነው ነው። ጠላና አረቄ በሚሸጡበት ጎጆ ችግርና ሕመም ሲያንገላቷቸው ኖረዋል።ይህ እውነት ደግሞ የህይወትን ከባድ ጉዞ በትግል እንዲወጡት ምክንያት ሆኗል።
የዛኔ ወይዘሮዋ በአምቦ ከተማ ያሉ ቤቶችን እያስተዋሉ የራሳቸውን ዕድል ፈንታ ያማርሩ ነበር። የብዙዎቹ መኖሪያ በአካባቢው ድንጋይ ተገንብቶ በጥንካሬ የቆመ ነው።የእሳቸው ቤት ደግሞ ንፋስ ከዝናብ የሚፈራና የክረምቱ ጎርፍ የሚያሰጋው ነበር። እናም ወደ ፈጣሪያቸው እያንጋጠጡ ዘንድሯቸውን ብቻ በሰላም እንዲያወጣቸው ይማጸናሉ።አመት አልፎ አመት ሲመጣ ግን ያለምንም ለውጥ ከነስጋታቸው ሊቀጥሉ ግድ ይላል።
አንዳንዴ ደግሞ ሽታዬ በሀሳብ ርቀው ይሄዱና መልካም ነገርን ያስባሉ።ከዚህ ችግራቸው ተላቀውም ቤት የሚባለውን መኖሪያ በሀሳብ ገንብተው ይጨርሳሉ።ይህኔ በሩን ይዘው በቁልፍ ሲዘጉና መልሰውም ሲከፍቱ ይታያቸዋል። ይህ ሁሉ ምኞት ግን በወቅቱ ከቁም ህልም ያልተናነሰ ቅዠት ነበር።
ወይዘሮዋ ከነበሩበት ተነስተው ወደጓዳ ሲያመሩ ከኋላ ተከተልናቸው። ከመኝታ ቤቱ አልጋ በዕድሜ የገፉና የሚጦሩ አዛውንት ተኝተዋል።ወላጅ እናታቸው እንደሆኑ ነገሩን።ባሻገር ከሚታየው ሳሎን ደግሞ አንዲት ወጣት ህጻን ታቅፋ ተቀምጣለች። የልጃቸው ሚስት መሆኗን ተረዳን። ሽታዬ የትናንቱን ታሪክ አስታወሱና ስለዛሬው ሙሉነታቸው ዳግም ምስጋና አቀረቡ።ለዚህ ታላቅ ጸጋ ‹‹ምክንያቴ ነው›› ያሉትን ቤትም እስከ አጸዱ ዳርቻ አዙረው ያስጎበኙን ያዙ ።
የቤቱን ግርግዳ እየዳሰሱና በሀይል እየደበደቡ ጥንካሬውን ሲፈትሹት አስተውለን በቀለም የተዋበውን ጓዳና ሰፊውን ሳሎን ማድነቅ ጀመርን።በሚያስገርም ጥንካሬ የሚታየውን የቤቱን አቋም ስንመለከት ግን የአሰራሩን ሚስጥር ለማወቅ መጓጓታችን አልቀረም። ግርምታችንን ያስተዋሉት ወይዘሮም የቤቱንና የእሳቸውን የህይወት ትሰስር ለመቃኘት አመታትን የኋሊት ተመልሰው ትርክታቸውን ቀጠሉ።
ከዛሬ አስራ አራት አመት በፊት ነው።በከተማዋ ህይወትን ለማሸነፍ ሲሉ ውሎና አዳራቸውን በድካም የሚገፉ ጎስቋሎቶችን የሚያስተውሉ አይኖች ወይዘሮ ሽታዬ ላይ ሊያርፉ ግድ ሆነ። የነዚህ አይኖች አስተውሎት ማረፊያ ጥግ የሌላቸውን ወገኖች ማፈላለግ ነበርና በድህነት ስር የነበሩ በርካቶች ትኩረትን አገኙ።
በወቅቱ ጥቂት የማይባሉ ቤተሰቦችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ቆርጦ የተነሳው ለም ኢትዮጵያ የተሰኘው ድርጅት እሳቤ በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ ያተኮረ ነበር። ለእነዚህን ቤተሰቦች መኖሪያ የሚሆኑ ቤቶችን ለመገንባት ደግሞ ደን ጭፍጭፎ እንጨት መቁረጥ አማራጩ አልነበረም፡ ድርጅቱ ሰዎቹን ሰብስቦ ጎጆ ሊያወጣቸው እንደሆነ ሲነግራቸው አብዛኞቹ ስሜታቸውን የገለጹት ዕንባ በተሞላ የደስታ ሲቃ ነበር።
ጥቂት ቆይቶ ግን ብዙዎች ጥርጣሬ ገባቸው። ቤቶቹ የሚሰሩት እስከዛሬ ካልተለመደና ተሞክሮ ከማያውቅ የጭቃ ጡብ መሆኑን ሲያውቁ በስጋትና ጥርጣሬ ከረሙ። ቆይቶ የቤቶቹ ግንባታ ሲጀመር ግን ከየቤተሰቡ የተመረጡ አባላት መሳተፍ ጀመሩ። ከሰንቀሌ ቀይ አፈር የተገኘውን ጭቃ በጭድ አቡክተው ጡብ እየቀረጹ ቤቶቻቸውን ማነጽ ሲይዙም በጥንካሬያቸው ተደመሙ። የእጆቻቸው አሻራ ያረፉባቸውና የላባቸው ወዝ የነካቸው አስደናቂ ቤቶች ሲጠናቀቁም በርካቶች እንደገመቱት ሳይሆን ቀርቶ ብዙሀንን ሰብሳቢዎች ሊሆኑ ግድ አለ።
ኑሮ ከተጀመረም በበኋላ አብዛኞቹ በቤቱ ጥንካሬ ስጋቱ ነበራቸው። ያለእንጨት ሲሚንቶና ሚስማር የቆመው ቤት አንድ ቀን በላያችን ሊፈርስ ይችላል በሚል ፍርሀትም ሲጨነቁ ቆይተዋል።አስራ አራት አመታትን ያለአንዳች ችግር የኖሩበት ሽታዬ ግን ልጆች ወልደው የዳሩበትንና፣እናታቸውን የሚጦሩበትን ቤት ዛሬም ድረሰ በስስት እያዩ ‹‹እንዲህ እንኖራለን›› ሲሉ የሚመሰክሩት በተለየ ደስታ ነው።
የቤቱ ነፋሻማ ድባብ የቀደመውን ሙቀት አስረስቶ ድካማችንን እንደተረከብን ወይዘሮዋን ተሰናብተንና ወደሚቀጥለው ግቢ አመራን። ጎረቤታቸው ወይዘሮ ከፈኔ አዱኛ ገና ከበራፉ ሲያዩን በተለየ ፈገግታ ተቀበሉንና ጨዋታችንን ቀጠልን።ከፈኔ ባለቤታቸውን በሞት ያጡት በቅርቡ ነበርና ጥቁር ልብስ ለብሰዋል።ማራኪው ፈገግታቸው ግን ይህን ሁሉ እንዳናስብ አድርጎናል።
የግቢውን ዙሪያ ገባ ስንጎበኝ ከጓሮ የተሰሩትን ኩሽናና መጸዳጃ ቤቶችን ተመለከትን።መለስ ብለንም የቤቱን አያያዝ ታዘብን። ዙሪያውን በአሸዋ የተገረፈው ባለ ሶስት ክፍል ቤት እንግዶችን ሲያስተናግድ እንደከረመ ያስታውቃል። በውስጡ የያዘው የቤት ዕቃም ታስቦበት የተዘገጀ ስለመሆኑ ግልጽ ነው።
ከፈኔ በፈገግታቸው መሀል የትናንቱን ህይወታቸውን በትዝታ እያወጉን ነው። እሳቸው ከአመታት በፊት ከአምስት ቤተሰቦቻ ቸው ጋር በዝናብና ብርድ እየተንገላቱ ከደጅ ያድሩ ነበር። ለነፍስ ብሎ የሚያስጠጋ ዘመድ ወዳጅ አልነበራቸውምና ክረምት ከበጋ በፈታኝ የህይወት መንገድ ሊመላለሱ ግድ ሆኖባቸው ቆይቷል።
ዛሬ ደግሞ በጭቃ ጡብ በተገነባውና በጉልበታቸው በተሳተፉበት የተንጣለለ ቤት እየኖሩ ነው። አብዛኞች የጭቃ ጡብ ብቻውን ቤት ሆኖ ይቆማል የሚል ግምት አልነበራቸውም። እሳቸው ግን በዚህ ጣራ ስር አስራ አራት አመታትን ቆጥረዋል። እንዴት እንደሚኖሩበት ለማስመስከርም ቤቱ ለልጅ ልጆቻቸው የሚተርፍ ቅርስ ሆኖ እንዲቀጥል ጭምር ይሻሉ።
‹‹ለካስ እንዲህም ይኖራል!›› በሚለው ግርምታችን እንደተደመምን ወደሚቀጥለው ግቢ አልፈናል።በዚህ ግቢ ያገኘናቸው ደግሞ አቶ ምትኩ አባጎሬን ነበር። አቶ ምትኩ የስምንት ልጆች አባት ሲሆኑ ህይወታቸውን የሚመሩት በግንበኝነት ሙያ ነው። በአንድ ወቅት ከደርግ ጋር በነበረው ጦርነት መኖሪያቸው በጦር መሳሪያ ሲወድም አባወራው ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ከቀበሌ በረንዳ ወደቁ።
ከዚህ በኋላ ግን ህይወት ለአባባ ምትኩ ቀላል አልሆነም። ልጆችን ማስተማር፣ ቤተሰብን ማስተዳደርና በቀን ስራ ውሎ ጎሮሮን ዘግቶ ማደር ከድካም ላይ ጣላቸው።በወቅቱ ችግረኞችን ከሩቁ የሚለዩት አይኖች እሳቸውንም እኪያይዋቸው በመከራ መንገድ ተመላለሱ። ዛሬ ምትኩ ባለ ጭቃ ጡብ ቤት ባለቤት ናቸው። እንከን የለሽ ነው በሚሉት መኖሪያቸው አመታትን ሲያሳልፉም ያለምንም ስጋት ሆኗል።እንደሳቸው ዕምነት በእንጨት ከሚሰራው ቤት ይበልጥ የጭቃው ጡብ ተመራጭ የሚባል ነው።ዛሬ በአቶ ምትኩ ቤት ያላለፈ ድህነት ቢስተዋልም ባላቸው አቅም ልጅ ድረውና አስተምረው ህይወትን እየመሩ ነው።
ስለነዚህ ጠንካራና ልዩ የሚባሉ መኖሪያ ዎች ስናስብ የሰው ልጆችን ጥበብና የመኖር ዘዴ ከማድነቅ አልተመለስንም።በርካቶች ከት ናንትና አስከፊ ህይወት አምልጠው ማረፊያ ጥግ ያደረጓቸውን የጭቃ ብሎኬት ቤቶችን የመገንባት ዋንኛ ዓላማ ስንሰማ ደግሞ ይበልጥ አድናቆታችን መጨመሩ አልቀረም።
ከዛሬ አስራ አራት አመታት በፊት ቤቶቹን በመገንባት ሂደት ተሳታፊ ነበርኩ ያሉን አቶ ዘሪሁን ኢሮ ደግሞ የግንባታው ዋንኛ ምክንያት የአካባቢውን ደን ከመጨፍጨፍ አደጋ ለመታደግ እንደነበር ያስታውሳሉ።በወቅቱ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርገስ ያስተባብሩት በነበረው የለም ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ስር የሚራመደው ይህ ዓላማ የአካባቢውን ደን ከመጨፍጨፍ ስጋት የሚጠብቅ ሆኖ ቆይቷል።
‹‹ብዙዎች ከተለመዱት ውጭ በጭቃጡ ቦች በተሰሩ ቤቶች የመኖር ልምድ የላቸውም›› የሚሉት አቶ ዘሪሁን አሁን ላይ ግን ከኑሮ ውድነትና ከአሰራር ቅለቱ አኳያ የበርካቶች ፍላጎት ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።ዛሬ እነዛን መሰል ጠንካራ ቤቶች እየተገነቡ አይደለም።እሳቸው ግን በወቅቱ ባገኙትን ሙያዊ ስልጠና ተጠቅመው የቁም ምድጃዎችን በጭቃ ጡቦች እየገነቡ ጠቀሜታውን በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
ከአቶ ዘሪሁን ማብራራያ በመነሳት ስለቤቶቹ የአሰራር ሂደት ይበልጥ ማወቅ ብንሻ ከአቶ ዘሪሁን ቱራ ጋር ወጋችንን ቀጠልን።አቶ ዘሪሁን በለም ኢትዮጵያ የአምቦ ቅርንጫፍ አስተባባሪ ናቸው። ቤቶቹን ለመስራት የሚመ ረጠው አፈር ተገለባብጦ ለቀናት ከተቦካና በጡብ መልክ ከተዘጋጀ በኋላ በጥላ ስር መድረቅ እንደሚገባው ነግረውናል።ይህ መሆኑም የቤቶቹን ዕድሜ በመጨመር በኩል የሚኖረውን ሚና ያልቀዋል።
የአቶ ዘሪሁንን ሀሳብ መነሻ በማድረግ የባለሙያ እገዛ ቢያስፈልገን ከአቶ ዮሀንስ ተሲሳ ጋር ውይይት ያዝን። አቶ ዮሀንስ ሶሊድ ኧርዝ አፍሪካ በተባለ ተቋም የአካባቢ ጥበቃ ተወካይ ናቸው። እሳቸው እንዳሉን እንዲህ አይነቶቹ ቤቶች የእንጨት ቤቶችን የሚተኩ በመሆናቸው ደኖችን በመጠበቅ የአፈር መሸርሸርን ለመታደግ ያስችላሉ።
የጭቃ ብሎኬት ቤቶች በምስጥ ከመበላት አደጋ የራቁ ናቸው። በዕድሜያቸውም እስከ አንድ መቶ አመታት መቆየት ይችላሉ ያሉን አቶ ዮሀንስ ከመኖሪያ በዘለለ ለትምህርት ቤቶችና ለንብ ቀፎዎችም እንደሚውሉ ነግረውናል። እኛም ይህን እውነታ ከዳሌዳዌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተን በጭቃ ብሎኬት ስለመሰራቱ አረጋግጠናል። ቤቶቹ ሙቀትና ቅዝቃዜን በማፈራረቅ በኩል ያላቸውን ጠቀሜታ ሲነግሩን ደግሞ ወይዘሮ ሽታዬ ቤት ስንገባ ያገኘነውን እፎይታ አስታውሰን በጠቀሜታው ላይ ተነጋገርን።
እነሆ! ህይወት በጭቃ ጡቦች ጣራ ስር እንዲህ ቀጥሏል። እነዚህ ቤቶች ዛሬም በቀደመ ጥንካሬያቸው ጸንተው አመታትን እያ ሻገሩ ይገኛሉ። አሁን ላይ በነዚህ ቤቶች መኖር እፎይታን ያገኙ የትናንትና ጎስቋሎች ‹‹እንዲህ እየኖርን ነው›› ብለው የሚናገሩት ከታላቅ ምስጋና ጋር ሆኗል። መልካም ህይወትን ተመኘን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
መልካምስራ አፈወርቅ