የስነ ጥበብ ሰዎች አንድ የሚሉት ነገር አለ። ‹‹አርቲስት›› የሚለው ቃል የሚያገለግለው ለሠዓሊ ነው። ‹‹አርት›› የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የቅርጻቅርጽና የሥዕል የፈጠራ ሥራዎችን የሚገልጽ ነው። እርግጥ ነው ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችም የፈጠራ ውጤቶች ናቸው። ምንም እንኳን የዘርፉ ባለሙያዎችንም የሚያከራክር ቢሆንም ‹‹አርቲስት›› የሚለው ቃል ግን ለሠዓሊዎች የሚሆን ነው። በኢትዮጵያ ግን ዘፋኝም ይሁን ደራሲ፣ ሠዓሊም ይሁን ተዋናይ በጥቅሉ ‹‹አርቲስት›› ተብሎ ነው የሚጠራው። ይሄ ጥቅል ስም ሲሆን በተናጠል ግን ሠዓሊ፣ ድምጻዊ፣ ገጣሚ፣ ተዋናይ… እያልን መግለጽ እንችላለን።
እንግዲህ የዘርፉ ሰዎች እስከሚስማሙበት ድረስ ‹‹ሠዓሊ›› በሚለው የአማርኛ ቃል እንጠቀምና ስለ ሥዕል እናውራ። ሥዕል ከጥበብ ሥራዎች ሁሉ የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም የሥዕል ጥበብ ከሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ጋር አብሮ የቆየ ነው። የሰው ልጅ ሥዕልን የጀመረው ዋሻ ውስጥ ይኖር በነበረበት ዘመን ነው። ይሄ ማለት እንግዲህ ከሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሁሉ ይቀድማል ማለት ነው። ለዚህም ነው ሥዕል ልክ እንደ ዘፈን እና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች ባህላዊና ዘመናዊ የሚል ምድብ የለውም። የእጅ ጥበብ ብቻ ስለሆነ ከቴክኖሎጂ ዕቃዎች መቀያየር ጋር አብሮ አይቀያየርም።
የሰው ልጅ ገና ዋሻ ውስጥ ይኖር በነበረበት ጊዜ የሚግባባው በሥዕል ነበር። በአካባቢው የሚያስተውላቸውን ነገሮች አስመስሎ ይስላቸው ነበር። የጽሑፍና የቋንቋ መግባቢያ ከመኖሩ በፊት ሥዕልን የስሜት መግለጫና እርስበርስ መግባቢያ ነበር። የሚመገባቸውን ነገሮች፣ የሚያድናቸውን እንስሳት እያስመሰለ ይስል ነበር። እንስሳትን ከመላመዱ እና የቤት እና የዱር እያለ ከመለየቱ በፊት አስመስሎ ይስላቸው ነበር።
ይህ ዋሻ ውስጥ የተጀመረ ጥበብ የሰው ልጅ ከዋሻ ሲወጣም ሊቀር አልቻልም። ይልቁንም እየረቀቀና የበለጠ ተወዳጅ እየሆነ መጣ። የሰው ልጅ የፈጠራ ሥራውን በሥዕል ጀመረና ወደ ቴክኖሎጂና የማሽን ውጤቶች አደገ። ያየውን ነገር ብቻ ይስል የነበረው የሰው ልጅ በምናቡ እየፈጠረም መሳል ጀመረ። በሰማይ ላይ የሚበር (አውሮፕላን)፣ በመሬት ላይ የሚሽከረከር (መኪና) አይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከመኖራቸው በፊት የሰው ልጅ ሰርቶ ማሳያቸውን (ሞዴላቸውን) የሰራው በሥዕል ነው። በጂኦሜትር የሒሳብና ፊዚክስ ውስጥ ያለው ቀመርም ከመሳል የዳበረ ነው። አንድ ሕንጻ ከመሰራቱ በፊት ንድፉ የሚሰራው ወረቀት ላይ ነው። ሥዕል ረቂቁን የሳይንስ ጥበብ አስጀምሯል ማለት ነው።
ሥዕል የዓለም ቋንቋ ነው። ሲባል የምንሰማው ‹‹ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ›› ሲባል ነው። እርግጥ ነው ሙዚቃም የዓለም ቋንቋ ነው። ሥዕል ግን ከሙዚቃም በላይ የዓለም ቋንቋ ይሆናል። ሙዚቃ ውስጥ ድምጽ አለ፤ ግጥም አለ፤ ግጥሙ ውስጥ መልዕክት አለ። በዜማው የጋራ ስሜት ሊኖር ቢችልም ግጥሙንና መልዕክቱን መረዳት የሚችለው ግን የተዘፈነበትን ቋንቋ የሚችል ሰው ነው። ሥዕል ግን ከዚህም በላይ ነው። እናት ስታጠባ የሚያሳይ ሥዕል በዓለም ላይ ቢዞር ሁሉም የሚያየው እናት ስታጠባ ነው። ይሄ የሥዕል ዓለም አቀፋዊነት ነው።
የሥዕልን ረቂቅነት ካየን ግን ረቂቅነቱ ደግሞ ከየትኛውም የጥበብ ሥራ ሁሉ የተለየ ነው። አንድን ሥዕል ለ10 ሰው አሳይተን የሥዕሉን መልዕክት ብንጠይቅ 10 አይነት ምላሽ ልናገኝ እንችላለን። እዚህ ላይ በሠዓሊዎችና በሥዕል አድናቂዎች (ተመልካቾች ማለት ነው) መካከል የሚነሳ አንድ ክርክር አለ።
ከእነዚህም አንዱ ሥዕል ማብራሪያ ያስፈልገዋል አያስፈልገውም? የሚለው ይገኛል። በሁለቱም ወገን ያሉት የየራሳቸው ምክንያት አላቸው። በተለይም ለሥዕል ጥበብ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ‹‹ሥዕል በማብራሪያ ከሆነ ምኑን ሥዕል ሆነው?›› ነው የሚሉት። ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ሥዕል በጣም ረቂቅ ስለሆነ ለሁሉም ሰው ግልጽ ላይሆን ይችላል፤ ማብራሪያ ቢደረግበት ግን ለሥዕል ቅርብ ያልሆኑ ሰዎችን እያለማመደ ወደ ሥዕል አፍቃሪነት ያስገባል›› የሚሉ ናቸው። የብዙ ሠዓሊዎች ምላሽም ማብራሪያ አያስፈልገውም። ምክንያታቸው ደግሞ ሥዕሉን የሚስሉት ለማስተማር ወይም ለስብከት ሳይሆን በወቅቱ የተሰማቸውን ስሜት ለመግለጽ ነው። ያ ሥዕል ለሠዓሊውና ለተመልካቹ የሚያስተላልፈው መልዕክት የተለያየ ሊሆን ይችላል።
የአገራችንን የሥዕል ጥበብ በተመለከተ የማያከራክር አንድ ነገር አለ። የሥዕል ትምህርት ቤት አለመኖር፣ የሥዕል ትምህርት ትኩረት ማጣት በግልጽ የምናያቸው ናቸው። እንዲያውም መማሪያ ክፍል ውስጥ እንኳን ሥዕል የሚሰራ ተማሪ እንደሰነፍ ተማሪ የሚቆጠርበት አጋጣሚም አለ። ችግሩ እንደ አጠቃላይ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ላይ ቢሆንም ሥዕል ላይ ግን ይብስበታል። የሙዚቃ ኮንሰርት እና የሥዕል ዓውደ ርዕይ ያላቸውን የታዳሚ ልዩነት ማስተዋል በቂ ምስክር ነው።
ጉዳዩን እንድናነሳው ያስደረገን ከሰሞኑ የተከፈተው የሥዕል አውደ ርዕይ ነው። ባለፈው ታህሳስ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ቦሌ መዲሃኒያለም አጠገብ ማማስ ኪችን ሬስቶራንት ያለበት ሕንጻ 3ኛ ፎቅ ላይ ለ2 ወር ያህል የሚቆይ የሥዕል አውደ ርዕድ ተከፍቷል። በአጋጣሚ ይሁን አዘጋጆቹ አስበውበት የገና ሰሞን መሆኑ ከሠዓሊው የጥበብ ጅማሮ ጋር ይገናኛል። መጀመሪያ ሠዓሊውን እናስተዋውቃችሁ (በዚህ ዓውደ ርዕይ ላይ የሚታዩት የእሱ ሥራዎች ናቸውና)
ሠዓሊው ተስፋዬ ኡርጌሳ ይባላል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1983 በአዲስ አበባ ተወለደ፤ አዲስ አበባ አደገ። የሥዕል ሥራዎችን መሥራት የጀመረው የገና በዓል ላይ በሚሰጡ የእንኳን አደረሳችሁ ሥዕሎች ነው። በነገራችን ላይ የሥዕል አጀማመር ታሪክ ውስጥም የምናገኘው ይሄው ነው። የመላዕክትና የቅዱሳንን ሥዕል መሳል። በብዙ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥ ሃይማኖታዊ አሻራዎች አሉ። ሠዓሊ ተስፋዬም በገና ሥጦታዎች ሥዕል ጀመረ።
የተስፋዬ የሥዕል ዝናባሌ እየዳበረ መጣ። ልብ በሉ! ኢትዮጵያ ውስጥ የሥዕል ሙያን የሙሉ ጊዜ ሥራ ይሆነኛል ብሎ የሚያስብ የለም። ምክንያቱም የብዙዎቻችን ምርጫ ከችሎታና ከዝንባሌ ጋር ሳይሆን ከእንጀራ ጋር ነው የሚያያዘው። ‹‹የቱ ቶሎ ቅጥር ይገኝበታል፤ የቱ ጥሩ ደመወዝ ያስገኛል›› ነው እንጂ የሚባለው ፍላጎትና ዝንባሌን መከተል እምብዛም የተለመደ አይደለም። ቢሆን እንኳን በተደራቢነት ነው። ምናልባት ሌላ ትምህርት እየተማሩ ወይም ሌላ ሥራ እየሰሩ እግረ መንገድ ይጠቀሙት ይሆናል እንጂ ከልጅነት እስከ እውቀት ሕይወትን ለሥዕል ብቻ መስጠት ብዙም የተለመደ አይደለም። ተስፋዬ ጋ ግን ይህ ዕውነት ሆነ።
ሠዓሊ ተስፋዬ ተሰጥዖውን በማዳበር ዘመናዊ ትምህርቱንም ሥዕል ተማረ። በአለ ፈለገሰላም የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ። ጥሩ ውጤት በማምጣትም እዚሁ ትምህርት ቤት የማስተማር ዕድል አገኘ። አሁንም በዚሁ በሥዕል ትምህርት ወደ ጀርመን አገር በማቅናት ከስታትልቺን አካዳሚ የማስተርስ ዲግሪ አገኘ። በአገር ውስጥ እና በተለያዩ የዓለም አገራት ከ30 በላይ የሥዕል አውደ ርዕዮችን በማዘጋጀት ሥራዎቹን ለጥበብ አፍቃሪያን አድርሷል።
አሁን በመታየት ላይ ያለው የሥዕል አውደ ርዕይ ሠዓሊው ከአሥር ዓመት በኋላ ወደ አገሩ በመመለስ ያዘጋጀው ነው። የሥዕል ሥራዎች ስደተኞችን የተመለከቱ ናቸው። የአውደ ርዕዩ ርዕስ ‹‹ኖ ካንትሪ ፎር ያንግ ሜን›› ይሰኛል። ለዕይታ ከቀረቡት የሥዕል ሥራዎች አራቱ የወረቀት ሲሆኑ የተቀሩት ግን የሸራ ላይ ሥዕሎች ናቸው።
በአገራችን ለሥዕል ሥራዎች አለመታየትና ተደብቆ መቅረት አንዱ ችግር ጋለሪ (የሥዕል ማሳያ) አለመኖር ነው። ይህን የገና ሰሞን የሥዕል ዓውደ ርዕይ አንድ ዓለም አቀፍ ጋለሪ አዘጋጀው። ይህ ዓለም አቀፍ ጋለሪ ‹‹አዲስ ፋይን አርት ጋለሪ›› ይሰኛል።
አዲስ ፋይን አርት ጋለሪ የተመሰረተው ከአራት ዓመት በፊት ሲሆን መቀመጫውን በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እና በእንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን ያረገ ነው። የዚህ ጋለሪ መሥራቾች አቶ መሳይ ሃይለ እና ወይዘሪት ራኬብ ሰሌ ይባላሉ። ጋለሪው ሠዓሊያን ሥራዎቻቸውን በአውደ ርዕይ መልክ የሚያቀርቡበት ነው። በዚህ ጋለሪም ሠዓሊያን ከአድናቂዎቻቸውና የሙያ አጋሮቻቸው ጋር ይገናኙበታል። በሌላ በኩል ጋለሪው ዓለም አቀፍ እንደመሆኑ ሠዓሊያኑን ከዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር ያገናኛል። ታላላቅ ዓለም አቀፍ የሥዕል አውደ ርዕዮችን በማዘጋጀትም ኢትዮጵያውያን የጥበብ ባለሙያዎችን በዓለም አስተዋውቋል። በዓለም አቀፍ የጥበብ ገምጋሚዎች ‹‹አዲስ ፋይን አርት›› ከ27 ዓለም አቀፍ ጋለሪዎች አንዱ ሆኖ ተመርጧል።
እንዲህ አይነት ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ ሠዓሊዎቻችንም ሆኑ ጋለሪዎች አገርን በማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል። አገርን የሚያስተዋውቀው ጥበብ ነው። በእነዚህ ሠዓሊዎችና ጋለሪዎች የሚቀርቡ ሥራዎች ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ ናቸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሁነት የሚያሳዩ ናቸው። ሥዕል ደግሞ የዓለም ቋንቋ ነው።
ከጥበብ ሥራዎች ሁሉ ሥዕል ላይ የተለየ መዘናጋት ያለ ይመስላል። ዓውደ ርዕይ እንኳን ተዘጋጅቶ በቂ ውይይትና ሙያዊ ክርክር አይደረግባቸውም። አውደ ርዕይ ይከፈታል፤ ማንም ሳይሰማ ይዘጋል። ምናልባት ችግሩ ከባለሙያዎች ሳይሆን ከታዳሚዎችም ሊሆን ይችላል። ባለሙያዎችንና ጥበበኞችን ጠርቶ ማወያየትና ሙያዊ ግምገማ ማድረግ ግን የራሳቸው የአዘጋጆችና የባለሙያዎች ድርሻ ነው።
ኪነ ጥበብ ላይ የሚሰሩ የመገናኛ ብዙኃን ላይም ችግር አለ። እስኪ በምን ያህል ጊዜ ነው ስለሥዕል ሲወራ የሰማነው፣ ያየነውና ያነበብነው? ለነገሩ ትዝ የሚለን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሸልማት ካገኙ በኋላ ነው። ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ምንጭ ጠቅሰን ስለአገራችን አርቲስቶች የሕይወት ታሪክ ሰርተናል። ሥራዎቻቸውን እነ ቢቢሲን እየጠቀስን ተናግረናል። የአገራችንን ጥበበኞችና ሥራዎቻቸውን ልናውቅ ይገባል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ዋለልኝ አየለ