የመርሐቤቴ ህዝብ የሚታወቅባቸው የተለያዩ ባህላዊ ስርዓቶችና ወጐች አሉት፡፡ እነዚህም ልማዶች ጥንት የነበሩ፣ አሻራቸው ሣይጠፋ ዛሬም ያሉ ናቸው፡፡ በተለይም በክብረ በዓላት የሚከወኑ የመርሐቤቴ ወረዳ ቃል ግጥሞች ማህበረሰቡ መጥፎ የሚለውን ምግባር በመንቀፍ መልካም የሚለውን በማወደስ ጠቃሚ የሚላቸውን እሴቶች ለማስጠበቅ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ቃል ግጥሞች የአካባቢውን ማህበረሰብ ስሜቱንና ፍላጐቱን ማንፀባረቂያ በመሆንም ያገለግላሉ፡፡ በአንድ ወቅት በመስክ ቆይታዬ ከዚሁ አካባቢ የሰበሰብኳቸውን ቃል ግጥሞችና አካባቢያዊ አንድምታቸውን እንደሚከተለው ላስቃኛችሁ፡፡
የገናን በዓል ከታህሣሥ 27 እስከ 29 ለተከታታይ 3 ቀናቶች በመርሐቤቴ ዓለም ከተማ ኦፍና አማኑኤል ቤተክርስቲያን የወረዳዋ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎችና ሌሎችም ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት ባህላዊና ሀይማኖታዊ ስርዓቶችን ይከውኑበታል፡፡
በዚህ ክብረ በዓል ልጃገረዶች እጃቸውን እንሶስላ በመሞቅ ሽንሽን ቀሚስ ለብሰው ነጠላ በመደረብ ተውበው ይውላሉ፡፡ ወጣት ወንዶችም ቁምጣና ጃኬት ለብሰው ሸበጥ በመጫማት በዓሉን ያከብሩታል፡፡
በቃል ግጥም በክዋኔው ወቅት ወጣት ወንዶች ክብ በመስራት ያ ሆ፣ አይናማ፣ ሆይ መላ የሚባሉ ዘፈኖችን ሲጨፍሩ ከ50 እስከ100 ተቀባዮች ፣ ከ5እስከ10 ጨፋሪዎች ፣ ከ1 እስከ 6 አውራጆች (ድምጻውያን) ይሳተፋሉ፡፡ ሴቶች ወጣቶች ሸሙናዬ፣ ሆይ መላ፣ ደርባባ የመሣሠሉትን ጨዋታዎች ሲጫወቱ ከ50 እስከ 100 እና ከዚያ በላይ በመሆንና ክብ በመስራት ከ2 እስከ 4 አውራጆችና ከ2 እስከ 6 ጨፋሪዎችን ያሣትፋሉ፡፡
በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ ባለሙያነትን ለመግለፅ፣ ቁንጅናን ለማጉላት እንዲሁም ቁምነገረኝነትን ለማወደስ የሚገጠሙ ግጥሞች አሉ፡፡
አውራጅ ተቀባዮች
ዘምባባ ዘምባባ………….……………ማሪ ዘንባባ
ዘምባባዬ ……………………………ማሪ ዘንባባ
ጓዴ ባልንጀራዬ ……….…………….ማሪ ዘንባባ
ልዙር ከኋላሽ ……………..…………ማሪ ዘንባባ
ዘንባባዬ ……………………………..ማሪ ዘንባባ
ለመልክሽም አይደል………………….ማሪ ዘንባባ
ዘንባባዬ ……..……………………….ማሪ ዘንባባ
ለቁምነገርሽ ………………………….ማሪ ዘንባባ
በዚህ ማሪ ዘንባባ በተሰኘ ጨዋታ ውስጥ ያሉት ግጥሞች ባልንጀራሞች የሆኑ ሴቶች እርስ በርስ የሚወዳደሱበት ነው፡፡ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ዘንባባ እጅግ ተወዳጅ የሆኑ ነገሮች የሚመሰሉበት በመሆኑ ጓደኞቻቸውንም በዘንባባ በመመሰል ስለቁምነገርና መልካምነት የሚያወድሱበት ይልቁንም ከመልክ በላይ ውስጣዊ ማንነት ወይም መልካም ስብዕናን የሚያጐሉበት ጨዋታ ነው፡
የውዳሴ ቃል ግጥሞች
አይንና ጥርሷ የእግዚአብሔር ስራ ነው
እኔን የገረመኝ አረማመዷ ነው
ይህ ቃል ግጥም መልኳ በተፈጥሮ የሚያምር ቆንጆ ደምግባት ያላትን ሴት በተፈጥሮ አምላክ ያደለሽ ቁንጅናሽ ላይ የአንቺ የአረማመድ ለዛ ተጨምሮበት ውብ አድርጐሻል በማለት ወጣት ወንዶች የመረጧትን ሴት የሚያወድሱበት ነው፡፡
የፈተለች እንደሁ አስመስላ ጭራ
የጋገረች እንደሁ አስመስላ ሞራ
አትወዳደሩ ሴቶች ከርሷ ጋራ
ፈትልና እንጀራ መጋገር በማንኛውም ሴት ሊከወን ቢችልም፣ ግጥሙ የተገጠመላት ሴት ግን ከሌሎች ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዳሸጋገረችው ይገልፃሉ፡፡ በመሆኑም ከባለሙያዎቹ የምትበልጥ ባለሙያ እንደሆነች የሚያቀነቅኑበት ግጥም ነው፡፡
የፍቅር ቃል ግጥሞች
በዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ቃል ግጥሞች በተቃራኒ ፆታ መካከል ወዳጅነትን ለመግለፅ፣ የመፈላለግ ስሜትን ለማንፀባረቅ እንዲሁም በፍቅር በመጐዳት የደረሰባቸውን ወዘተ… መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡ ቃል ግጥሞችም በዚህ ድንበር ውስጥ የሚቀነቀኑ ናቸው፡፡
እቴ ባንቺ ነገር ባንቺ የተነሣ
ቅዳሴውም ቀረ ዳዊቱም ተረሣ
በሴቷ ፍቅር የተነደፈው ወጣት የፍቅሩን ጥግ መድረስ ሲገልፅላት የተጠቀመበት ቃል ግጥም ነው፡፡ በዚህ ቃል ግጥም እሷን እሷን ብቻ እያሰበ ስራ መፍታቱን የሚገልፅበት መንገድ ነው፡፡ ወጣቱ ከሀይማኖታዊ ተግባራቶች መቆጠቡ የቱን ያህል ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ይገልፃል፡፡
አባትሽ በጡጫ ሰንዝረው ሣቱኝ
ወንድምሽ በአንካሴ ወርውረው ሣቱኝ
እናትሽ በድውይ ወርውረው ጣሉኝ
አንቺን ስል ነው እንጂ ሊጥ አልደፋሁኝ
ወጣቱ የወደዳትን ልጃገረድ ከቤተሰቧ ተደብቆ ለማየት ሲሞክር አባትና እናቷ ወንድሟም በጥላቻ አይን ሁልጊዜ ሲመለከቱትና አሳሩን ሲያሣዩት እሱ ደግሞ ምሬቱን በግጥም ይገልፅበታል፡፡ የደረሰበት እንግልት እሷን ወዶ ባደረገው እንቅስቃሴ እንጂ ሌላ ምንም አለማጥፋቱን ሲገልጽ ‹‹አንቺን ስል ነው እንጂ ሊጥ አልደፋሁ›› ብሎ ይዘፍንላታል፡፡
ፍቅርህና ፍቅሬ አንድ ላይ ሲቃና
በአየር እንሄዳለን እንኳን በመኪና
በዚህ ቃል ግጥም ደግሞ ሴቷ ልጃገረድ ወዳጇን እኛ ከተዋደድንና ፍቅራችን በሚገባ ከሰመረ ፣ ሰምሮም አንድ ላይ ከሆን እንኳንስ ትንሽ ነገር ይቅርና ትልቅ ነገር እናሟላለን ትለዋለች፡፡ እዚህ ላይ አየር ያለችው አውሮኘላንን ነው፣ አውሮኘላን ደግሞ ከመኪና የበለጠ የጐላ ፋይዳ ስላለው በፍቅራቸው ስኬት ትልቅ እንሆናለን የሚለውን ለመግለፅ ትጠቀምበታለች፡፡
ገለባ በሆንኩኝ /2/ የደጇን ግብስብስ /2/
አርጋኝ እንድገባ ግብስብስ /2/
አርጋኝ እንድገባ ግብሶ በሆንኩኝ
በማህበረሰቡ ሴቶች ማገዶ ለቀማ ላይ ይሣተፋሉ፡፡ ታዲያ ወጣቱ የወደዳትን ልጅ ራሱን ከማገዶ ጋር እያመሳሰለ እኔም ማገዶውን ሆኜ ከማገዶው ጋር ለቅማና አግበስብሣኝ ይዛኝ ብትገባ በማለት ምኞቱን በዚህ ቃል ግጥም ይገልፅበታል፡፡
በቀልን የሚያነሳሱ ቃል ግጥሞች
በመርሐቤቴ ወረዳ የሚኖር ገበሬ አብሮ መስራት፣ ችግርን በጋራ መወጣት ባህሉ እንደሆነ ሁሉ ‹‹ባለቤቴን ለምን አየሃት? አዝመራዬን ከብት አስበላህብኝ፣ የእርሻ ድንበሬን ገፋህ›› በማለት ዕሰጥ ገባ ውስጥ ገብቶ ለመበቀል ራሱን ያዘጋጃል፡፡ በዚህ መሀል መገዳደልም አይጠፋም፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን የተመለከቱ ቃል ግጥሞች በፉከራ እና በሽለላ መልክ ሲቀነቀኑ ይስተዋላል፡፡ በምሣሌነት የሚከተሉትን ቃል ግጥሞች እንመልከት፡፡
አባቱ አረዳ የተኛውን በሬ
ጐትጉተው ጐትጉተው አደረጉት አውሬ
አባቱ በሰው እጅ ተገድሎ የአባቱን ደም ባለመወጣቱ በበሬ ተመስሎ የነበረው ልጅ የአባቱን ደም በመመለሱ ከአውሬ ጋር ተነፃፅሯል፡፡ ኃይለኝነቱን ፣ አይበገሬነቱን መግለፃቸው ነው፡፡ በዚህም ግጥም ሰው መግደል እንዴት እንደሚያስከብር መገመት ይቻላል፡፡
ያቺ ሱሪ ጨርቄን ጠቅሜ ጠቅሜ አስቀምጫታለሁ
ወንድነቱ ሲገኝ እታጠቃታለሁ
ደም መመለስ እንደ ጀግንነት በሚቆጠርበት ማህበረሰብ ውስጥ ለሚኖር ግለሰብ ደም ባለመመለሱ በደረሰበት ተፅዕኖ የተነሣ የሚደርስበትን መገለል በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ሲባል ግጥም መግጠም ይጀምራል፡፡ ‹‹ይዋል ይደር እንጂ መግደሌ አይቀርም›› እያለ ያቅራራል፡፡ አንድ ቀን ተሳክቶለት ወንድ ለመባል እንደሚበቃ ከግጥሙ እንገነዘባለን፡፡
ሣምባውና ልቡ እየተሟገቱ
አሸንፏል ሳንባው እየሞተ ልቡ
ይህ ግጥም ደግሞ ‹‹ለመግደል ፈርተህ እንጂ ጊዜና ቦታ እየጠበቅህ አይደለም፡፡›› የሚል ነው፡፡ ሣምባና ልብ ዕሰጥ አገባ ገጥሞ እናገኛለን፡፡ ልግደል አልግደል የሚል ሙግት ይዘዋል፡፡ ፍርሀት ወይም ወኔ ቢስነት በሣምባ፣ ጀግንነት ደግሞ በልብ ተመስለዋል፡፡ የልቡ መሞት ሲነግረን የፍርሀቱን ልክ እንድናጤን ይረዳናል፡፡
የስድብ ቃል ግጥሞች
በዚህ ቃል ግጥም ዘርፍ ውስጥ የሚሰደቡ ወይም የሚተቹ ሰዎች ምን ያህል ሆዳም እንደሆኑ ፣ ምን ያህል መልከ ጥፉ እንደሆኑ ወይም ምን ያህል ፅዳታቸውን የማይጠብቁ እንደሆኑና ስንፍናቸውንም ለመግለፅ ወዘተ… ጉዳዮችን በማንሣት ይቀነቀናል፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡ ቃል ግጥሞችም ይህንኑ የተመለከቱ ናቸው፡፡
የእንቅልፍ አጀቡ ልጅ እግዚአብሔር ጥሎብኝ
አገላብጣለሁ ምስጥ እንዳይበላብኝ
ተሳዳቢዋ ሴት እጅጉን ሰነፍና እንቅልፋም በመሆኗ ከእንቅልፏ እንኳን የምትነሣው ተቀስቅሣና ተጐንትላ በመሆኑ ይህንን ተግባሯን ደግሞ በእንዲህ አይነት ቃል ግጥም ይገልፁላታል፡፡
ወዘፍ ወዘፍ ያለ የግራር አጥር
እኔ ለባላገር እጅግም አልጥር
በአካባቢው ማህበረሰብ ሰነፍ ሰው ስለማይወደድ በተለይ ሰነፍ የሆነ ወንድ በሴቶች ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ በመሆኑም በቃል ግጥሙ የተጠቀሰው ተሰዳቢው መቀመጥን የሚያበዛና ስራ የማይወድ ስለሆነ ሴቷ እኔ ላንተ ለመሆን አልጥርም በማለት ስንፍናውን ትነግረዋለች፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
አዲሱ ገረመው