በሀገር ግንባታ ሂደት ሁሉም ዜጎች የየራሳቸው ሚና አላቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የወጣቱ ትውልድ ተሳትፎ የተጠናከረ ሲሆን እንደ ሀገር የጀመረው ሁለንተናዊ እድገት ፈጣንና የተሳካ ይሆናል። በአንጻሩ ህብረተሰቡን አሳታፊ ያላደረገ ማንኛውም የልማትም ሆነ ሌላ ስራ ውጤታማ የመሆኑ እድል ጠባብ ነው። ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት ሲሆኑ ታይተዋል። ሀገሪቷ ጀምራቸው የነበሩ የሀገር ግንባታ እንቅስቃሴዎችም ከፊሎቹ ሲቋረጡ አብዛኛዎቹ ያለ ለውጥና እድገት ባሉበት ሆነው አመታትን ለማሳለፍ ተገደዋል።
ለእነዚህ ችግሮች መከሰት ምክንያቶች ደግሞ ለረጅም ጊዜያት ሲንከባለሉ የመጡና ያልተቀረፉ በህዝቡ ይጠየቁ የነበሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ያለማግኘት ነው። የህዝቡ ጥያቄዎች ምክንያታዊና ከመሰረቱ ተቀባይነት ያላቸው ቢሆንም ከጥያቄዎቹ ጀርባ የተለያየ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች አጋጣሚውን በመጠቀም አላማቸውን ለማስፈጸም እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በዚህ መሀል በግንባር ቀደምትነት በግብታዊነት ተገቢ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችንና የጥፋት ተግባራትን በአብዛኛው የሚያከናውኑት ደግሞ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑት ወጣቶች ናቸው።
በቅርቡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም የሀገር ግንባታ ከየት ይጀመራል? የቤተሰብ ሚናስ ምን መሆን አለበት? በሚል ከባለሙያዎች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል። በመድረኩ የተሳተፉ የመስኩ ባለሙያዎች እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ብሎም በወጣቶች በኩል የሚታየውን ችኩልነትና ካለማገናዘብ በግብታዊነት የሚደረጉ የጥፋት እንቅስቃሴዎች በማስቆም ወጣቱን ወደ ሀገር ልማት ለማዞር ዛሬ ነገ ሳይባል ቤተሰብ ላይ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያና የስነልቦና አማካሪ የሆኑት ጋዜጠኛ ብሌን ተዋበ እንደሚናገሩት፤ ሀገር የበርካታ ቤተሰቦች ድምር በመሆኑ ለሀገር ግንባታና ብልጽግና የቤተሰብ ሚና ቀዳሚው መሰረት ነው። የሀገር ግንባታ ደግሞ የሚከናወነው ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚተላለፍ ቅብብሎሽ ነው። በመሆኑም የነገዋን ኢትዮጵያ ቀጣዩ ትውልድ መረከቡ የማይቀር እውነታ በመሆኑ ይህንን ትውልድ በበጎ ማነጽ ማስተካከልና ወደቀናው መንገድ መምራት ያስፈልጋል። በመሆኑም ሁሌም የሚቀጥለውን ዘመንና ትውልድ የሚመለከት አዲስ ትውልድ መገንባት ይጠበቃል። ለዚህም ከእያንዳንዱ ቤተሰብ የሚወጡ ልጆች አርቀው የሚመለከቱ ተስፋ የሰነቁና እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ብሎም እንደ ህዝብ የሚያስቡ መሆን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ወላጆች (እናትና አባት) ትልቅ አደራም፤ ኃላፊነትም አለባቸው።
ዛሬ በተለያዩ ቦታዎች እየታዩ ያሉት የእንቢተኝነትና የአመጸኝነት ባህሪያት የሚጸነሱት ቤተሰብ ውስጥ ነው። በአብዛኛው በተመሳሳይ የጥፋት ተግባርና አመጽ ተሳትፈው የሚገኙ ልጆች ያለባቸው ችግር የሚጀምረው ከቤተሰባቸው ጋር በነበሩበት ወቅት ነው። ይሄ ባህሪ ደግሞ ሲያድጉም ይከተላቸውና ከወጣትነት እድሜ አልፈው ቤተሰብ ሲመሰርቱም አንድም ያልተስተካከለ ቤተሰብ ይመሰርታሉ፤ አልያም የመሰረቱትን ቤተሰብ ያፈርሳሉ። ይህ የሚያሳየን አንድ ቤተሰብ በትክክለኛው መንገድ ካልተጓዘና ብቁ ልጆችን ማፍራት ካልቻለ ችግሩ ተሻጋሪ በመሆን እነዛ ልጆች የሚመሰርቱትም ቤተሰብ በአብዛኛው የተበላሸ እንደሚሆን ነው።
ጋዜጠኛ ብሌን ጨምረው እንዳብራሩት ከሚታሰበውና ከሚነገረው ጀምሮ ልጆች ከወላጆቻቸው የሚወስዱት በርካታ ነገር አለ። ለምሳሌ ዛሬ ዛሬ በህክምናው አለም በዲሲፕሊን መጓደል ትልልቅ ስህተቶች ሲፈጠሩ እናያለን። የእነዚህን ችግሮች መሰረት ካየነው መነሻው ቤተሰብ ሆኖ ይገኛል፡፡ ዶክተር መሆን የሚፈልጉ ልጆች የህክምና ትምህርታቸውን በዩኒቨርሲቲና በህክምና ማእከላት ተከታትለው በቂ እውቀት ሊያገኙ ይችላሉ። በእርግጥም የትምህርት ተቋማት ሳይንሳዊውን እውቀት ለማስጨበጥ ትክክለኛ ቦታዎች ናቸው። በተወሰነ ደረጃ ስነ ምግባርንና መልካምነትንም በተመለከተ በየተቋማቱ የሚሰጡ ትምህርቶች ቢኖሩም ውጤት የማስመዝገብ እድሉ ግን ጠባብ ነው። ስነምግባርን ለማስተካከል ዋናው መሰረት ቤተሰብ ነው። ባህሪን ለማስተካከል ለማንኛውም ልጅ ከቤተሰብ የተሻለ ቦታ አይኖርም። ስለዚህ ልጆች ምን መሆን እንደሚፈልጉ እያንዳንዱ ወላጅ በቅርብ ተከታትሎ ማወቅ አለበት። ሀኪም መሆን የሚፈልግን ልጅ እኛ በቤት ውስጥ ሰው መውደድን ለሰው መኖርን ካስተማርነው የህክምናን ስነ ምግባር አሳወቅነው ማለት ነው፡፡ ይህ ሲሆን በትምህርቱም ውጤታማ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው። በሌላውም መስክ የሚታየው ይህው ነው፡፡ ልጆች ከቤተሰባቸው ጀምረው የተገራ ሀሳብ፣ ማንነት፣ ስሜትና አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል።
ሳይንሱ እንደሚያመለክተው ልጆች ስምንት አመት እስከሚሆናቸው እንደ ነጭ ወረቀት ናቸው፡፡ ያዩትን ያደርጋሉ ቤተሰብ በተለይ እነሱ የቅርብ የሚሉት ሰው የሚላቸውን ያምናሉ። በዚህ ጊዜ ጥሩ መሰረት ማስጨበጥ ከተቻለ እያደጉ ሲመጡም በጓደኛ ግፊት ከመስመር የመውጣት እድላቸው ጠባብ ይሆናል። በመሆኑም ቤተሰብ ልጆችን ማረቅ ሀገርን የማዳን ያህል ወሳኝ መሆኑን በማወቅና ጊዜውም ከእነሱ ጋር እያሉ መሆኑን በመገንዘብ መልካሙን መንገድ ማመላከት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
«እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና ውጤታማ ለማድረግ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊውም መስክ ከቤተሰብ ጀምሮ መሰራት አለበት» የሚሉት ደግሞ የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪ የሆኑት አቶ ይመስገን ሞላ ናቸው። እንደ አቶ ይመስገን ማብራሪያ የቤተሰብ ይዘት የሀገርን ሁለንተናዊ እድገትና ሰላም ይወስናል፡፡ በርካታ ቤተሰብ ጤናማ የሆኑባቸው ሀገራት አምራች ዜጋ በመፍጠር ዘላቂና አስተማማኝ እድገት ሲያስመዘግቡ ይታያሉ። በርካታ የፈረሱ ቤተሰቦችን የያዙ ሀገራት ደግሞ እንደ ማህበረሰብም እንደ ሀገርም ለተለያዩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች የተጋለጡ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያም የቤተሰብ ሁኔታ መዛባት እየታየበት እንደሆነ የፍቺ መበራከት፣ የጎዳና ላይ ህይወት መስፋፋትና የባልና ሚስት አለመስማማት አመላካች ማሳያዎች ናቸው። ዛሬ እንደ ሀገር ችግር የሆኑብን ሙስና፣ መልካም አስተዳደርና እርስ በእርስ አለመተማመን መነሻቸው ቤተሰብ ውስጥ ነው። እነዚህ ተግዳሮቶች ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉት ህግ በማስከበር ብቻ ሳይሆን ትውልድ በመቅረጽ ነው። ትውልድ የሚቀረጸው ደግሞ ቤተሰብ ላይ ትኩረት አድርገው በሚሰሩ ስራዎች ነው።
አንድ ልጅ ከቤተሰብ ከወጣ በኋላ በስነ ምግባር ረገድ ማስተካከል አስቸጋሪ ነው የሚሉት አቶ ይመስገን፤ ቤተሰብ ላይ እያሉ ያልተገሩ መጥፎ ባህሪያት እያደጉ ሲሄዱ ከማህበረሰብ አልፈው ግለሰቦች በመንግስት ከፍተኛ የስልጣን መዋቅር ላይ ተቀምጠውም ለተሳሳተ ውሳኔ ሲዳረጉ ይስተዋላል። ለሀገራዊ የሰላም ዋስትና ይሰጣል፡፡ እያንዳንዱ ቤተሰብ ሰላም ከሆነ ሀገር ሰላም ይሆናል። አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት የቤተሰብ ፖሊሲ አላቸው፡፡ ያንን መሰረት አድርገው የሰሩት ስራ ለሀገራቸው ብልጽግናና ሰላም መሰረት ሆኗቸዋል።
አቶ ይመስገን እንደሚሉት በየትኛውም ሃይማኖት የህሊና ህግን ጨምሮ ልጆች ስነ ምግባራቸው የታረቀ ልጆች ለራሳቸውም ለቤተሰብም ለሀገርም ጥሩ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ በአንጻሩ በትክክል ካልተያዙ ወደጥፋት እንደሚሄዱ ይታወቃል። ከዚህም ባለፈ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሰላምን አብሮነትን አንድነትን የሚደግፉ ብዙ ባህልና እሴቶች ያሉን ህዝቦች ነን። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በማህበረሰቡ መካከል የነበሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ፣ አብሮነትን የሚያጎለብቱ እሴቶች እየተናዱ ናቸው። ጉቦ፣ ማጭበርበር፣ መዋሸት፣ በችግር ወቅት አለመረዳዳት የመሳሰሉት እየተስፋፉ መጥተዋል፡፡ ይሄ ሁሉ መነሻውም፣ መቆጣጠር የሚቻለውም ቤተሰብ ላይ እያሉ ልጆች ላይ መስራት ሲቻል ነው።
ስለ ስነምግባር ሲነሳ ብዙዎቻችን ቤተሰቦቻችን ያሳለፉትን ጥሩ ነገሮች ስናወድስ፣ ስናሞግስ እንሰማለን፤ ለመድገም ግን ፈቃደኞች ስንሆን አንታይም። የሃይማኖት አባቶች እንኳ ያላቸውን ተሰሚነትና ተቀባይነት በመጠቀም ስለ ትውልድ ሲሰሩ አይስተዋልም። እነዚህ ሁሉ እንደ ሀገር የተስተካከለ ቤተሰብ በመፍጠር ለሀገር ግንባታ ለማዋል የሚጠብቁን የቤት ስራዎች ናቸው። በመንግስትም በኩል ለቤተሰብ ጉዳይ የሚሰራ ተቋም በየደረጃው ማዋቀር እንዲሁም በየትምህርት ተቋማትም ከካሪኩለም ቀረጻ ጀምሮ በየትምህርት አይነቱ ስነምግባርን ማካተትና ልጆችን ማስተማር፣ በየደረጃው ሀገር አቀፍ የውይይት መድረኮችን ማካሄድ ይጠበቅበታል ሲሉ አሳስበዋል።
በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ትምህርት መምህር የሆኑትና የ«ማይንድ ሞርኒንግ የስነ ባህሪ ማማከርና ምርምር» ድርጅት መስራች የስነባህሪ ተመራማሪና አማካሪ አቶ እድሜአለም ግዛው በበኩላቸው። ልጆችን ከንግግር ይልቅ በተግባር ማስተማር ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ማህበረሰብም መስራት አለብን ይላሉ። እንደ አማካሪው ማብራሪያ በልጆች ላይ ከቤተሰብ ቀጥሎ ተጽእኖ ሊፈጥር የሚችለውና ባህሪን ሊያስተካክልም ሊያበላሽም የሚችለው ማህበረሰቡ ነው። ልጆች ቢበዛ እስከ አራትና አምስት አመታቸው ድረስ ብቻ አብዛኛውን ጊዜ ከቤተሰብ ጋር ያሳልፋሉ። ከዛ በኋላ ግን አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት በትምህርት ቤትና በማህበረሰቡ ውስጥ በመሆን ነው። በዚህም የተነሳ ከወላጆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ አጭር ከመሆኑ ባሻገር ከዛውም ላይ አብዛኛው ሰአት በእንቅልፍ በመመገብና ሚድያ በመከታተል የሚያልፍ ነው። ብዙ ጊዜ ትውልዱ ስነ ምግባር እያጣ ነው፤ ማህበረሰቡ የሚያወግዛቸውን ነገሮች ያደርጋል፤ ለመጤ ጎጂ ባህል ተጋላጭ ሆኗል ሲባል መስማት እየተለመደ መጥቷል።
ነገር ግን እነዚህን ባህሪዎች የሚሰጠውም እንዲያደርግ የሚፈቅደውና በስሩ አቅፎ የተቀመጠውም ራሱ ማህበረሰቡ ነው። በመሆኑም የልጆችን ባህሪ ለማስተካከል ወላጆች ላይ የሚሰራው ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ ማህበረሰቡም ላይ መሰራት ያለበት ስራ አለ። ብዙ ልጆች በቤተሰብ ውስጥ እያሉ በልጅነታቸው በትምህርታቸውም በባህሪያቸውም ጥሩ ይሆኑና ሁለተኛ ደረጃና ከዛ በላይ ሲደርሱ ለበርካታ ደባል ሱሶችና አዳዲስ ጎጂ ባህሪያት ይጋለጣሉ። ይሄ በትክክል የሚያሳየን ቤተሰብ እንደ አንድ አካል የሚሰራው ስራ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችልና እንደ ማህበረሰብ የትውልዱን ባህሪ የሚቆጣጠርና የሚያርቅ ስራ አለመስራቱን ነው። በሌላ በኩል ማህበረሰቡ እንደ ትክክለኛ እያደረገ ጀብድ ጀግንነት አድርጎ የሚመለከታቸው በርካታ መፈተሽ ያለባቸው ነገሮችም አሉ። ከነዚህም መካከል ሰርቶ ከበለጸገው ይልቅ በሙስና ሀብት ያካበተውን ማክበር ማወደስ፤ በመንደር የሚጣሉ የሚያስቸግሩ ልጆችን እንደ ጎበዝ በማየት እውቅና መስጠት፤ ባህላቸውን ሲተውና የሌላ ሀገር ባህል ሲከተሉ እንደ ስልጣኔ እውቀት መመልከት በቀዳሚነት የሚጠቀሱት መካከል ናቸው።
በተጨማሪም አሁን አሁን አብዛኛዎቹ ልጆች ረጅም ግዜ የሚያሳልፉት ፌስቡክና የአውሮፓን ፊልሞች በመመልከት ነው።እነዚህ ደግሞ ከባህላችንም ሆነ ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሚቃረኑ በርካታ አመለካከቶችና እሳቤዎችን የያዙ ናቸው። ልጆች ደግሞ በተፈጥሯዊ ባህሪያቸው ያዩትንና ያስደነቃቸውን አንዳንዴም የወደዱትን ነገር ለመተግበር ስለሚሞክሩ ከማህበረሰቡ ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው አይቀርም። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ መብት የሚጠይቋቸውና እንዲደረግላቸው የሚፈልጓቸው በፊልምና በማህበራዊ ሚድያ የሚመለከቷቸውን ጉዳዮችን ለማሟላት የሚያስችል እንደ ሀገርም እንደ ቤተሰብም የኢኮኖሚም የፖለቲካም ማህበራዊም ሁኔታ የለም። ስለዚህም ከቤተሰብም ከማህበረሰቡም አንዳንዴ ህግን በመጣስም ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ ለመግባት ይገደዳሉ። እዚህ ደረጃ ባይደርሱ እንኳ በሚፈልጉትና በነባራዊው እውነታ መካከል ሃሳባቸው ሲከፋፈል ራሳቸውን ማግለላቸው አይቀርም። በመሆኑም በየወቅቱ እነሱ ያሉበትን ደረጃ ሀገራቸውን ማህበረሰቡን እንዲያውቁ ማድረግ ከሌሎች ሀገራትና ህዝብ ጋር ያለውን ልዩነትና አንድነት እንዲገነዘቡ ማስቻል የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
«ለቤተሰብ ጊዜ መስጠት ቤተሰብን መታደግ ነው» የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዪ ናቸው። ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ እንደተናገሩት ጤናኛ ቤተሰብ ሰላም ያለው ማህበረሰብና ህብረቱና አንድነቱ የተጠናከረ ሀገር ለማቆም መሰረት ነው። የተስተካከለ ቤተሰብ ለመመስረት ደግሞ የቤተሰቡ መስራቾች እናትና አባት ለቤተሰቡ ጊዜ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። ብዙ ጊዜ ከተለያዩ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ የዚህን ኃላፊነት ተሸክመው ለልጆቻቸው ጊዜ ሲሰጡ የሚታዩት እናቶች ብቻ ናቸው። እናቶችም ቢሆኑ ልጆች ትንሽ ካደጉና መንቀሳቀስ ከጀመሩ ብሎም ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላ እምብዛም ጊዜም ትኩረትም ሲሰጡ አይታይም። በዚህም የተነሳ ልጆች በአንድ ወገን ብቸኛ እየሆኑ አካባቢያቸውንም ሆነ አለምን በተለየ መንገድ እየተረጎሙ መኖር ይጀምራሉና በመካከላቸው ብዙ መራራቅና መለያየት ይፈጠራል። አንዳንድ ጊዜ ይሄ ልጅ የእኔ ሊሆን አይችልም እስከማለት የሚያደርስ የሃሳብ የተግባርና የአመለካከት ልዩነት ሲፈጠርም ይታያል። እንደ ሀገርም ለቤተሰብ ለልጆች ጊዜ የመስጠት እውቀት እጥረት አለ። ብዙ የቤተሰብ መሪ ለቤተሰቡ ጊዜ ሰጠሁ ብሎ የሚያስበው ልጆች የሚበሉትን የሚለብሱትን እንዲያገኙ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባት ብቻ ነው። ነገር ግን ከዚህም በላይ አእምሯቸው መንፈሳቸውም ፍቅር ምክርና ሃሳብ እንደሚፈልግ መረዳት ያስፈልጋል።
ልጆች ቅድሚያ የሚሰጡት ለእናትና አባት ነው፡፡ በልጅነታቸው የታረቁ ልጆች ለጥፋት ለእኩይ ስራ የተጋለጡ አይሆኑም። ልጆች በለጋ እድሜያቸው ከቤተሰባቸው ስለሰላም ስለ ፍቅር እየተነገራቸው ካደጉ የሚተገብሩት ይህንኑ ይሆናል፤ ስለስራ እየተነገራቸውና በቤት ውስጥ ስራ ሲሰራ እያዩ አብረው እየሰሩ ካደጉ ለስራ ያላቸው አመለካከት ጠንካራ ይሆናል። ይህንን ሳናደርግ ልጆችን ከተውናቸው በአካባቢያቸው ለሚፈጸሙ ለማይጠቅሙ አጥፊ ተግባራት ተሳታፊ በመሆን ለህብረተሰቡም ለሀገርም ሸክም መሆናቸው አይቀርም።
በተጨማሪ ጊዜ መስጠት ልጅን ለማወቅ ይረዳል። ወላጅ ከልጆቹ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ከቻለ ምን እንዳሰቡ ምን እንደፈለጉ ለማወቅ እድሉን ያገኛል። ይህም ወደተሳሳተ መንገድ እየገቡ ከሆነ በጊዜ ለመቆጣጠር ጥያቄም ካላቸው በጊዜ ለመመለስ እድሉ ይኖራል። በዚህ አካሄድ እያንዳንዱን ልጅ በቤት ውስጥ በማስተካከል ጥሩ ስነ ምግባር ያለው ማድረግ ከተቻለ እንደ ማህበረሰብ ብሎም እንደ ሀገር ዛሬ በየቦታው የምንመለከተው በወጣቶች የሚተገበሩ የተሳሳቱ የጥፋት ስራዎችና ለአንዳንድ ድብቅ አላማ ያላቸው ሰዎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ለመታደግና ብሎም ወጣቱን ኃይል ለጥሩ ነገር ለማዋል ይቻላል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 24/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ