ከመጋቢት 2010 ጀምሮ አገራችን ለውጥ ላይ ነች። ለእኛ አዲስ ነገር ባይሆንም ለውጥ ምን ጊዜም “ሰርክ አዲስ” ነውና ሁሌም ይወራለታል። በክፉም ይሁን በደግ ስሙ ይነሳል፤ ይወድቃል።
በአገራችን እየተካሄደ ያለው ለውጥ እንዲሁ በቀላሉ እንዳልተገኘ ተደጋግሞ ተገልጿል። በመሆኑም የለውጡ እውን መሆን ለብዙዎች ብስራት ከመሆን አልፎ የእርካታ ምንጭም ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ፤ የመጣው ለውጥ የፈጠረው መነቃቃትና የመለወጥ ፍላጎት አፍታም ሳይቆይ እራሱ ለውጡ በወለዳቸው እድሎች ለተሻለና ለበለጠ ለውጥ መትጋት ሲገባ፤ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነና “መንግስት ነኝ” የሚል በዛ። ውል በሌለው አጀንዳም ወዳልተፈለገ ነውጥ ተገባ። ባጭሩ ግጭትና ሁከት በየቦታው ሆነ። ቡድኖችና ግለሰቦች በተከበረው አገርና በተከበረው ህዝብ ላይ ለያዥ ለገናዥ እስኪያቅት ድረስ ሸለሉበት። ሽለላው አሁንም አልቆመም። ሁከቱና ሰላም መንሳቱ የእምነት ተቋማት ተማፅኖ፣ የምእመናን ፆም ፀሎት፣ ያገር ሽማግሌዎች ተግሳፅና ምክር፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ውትወታ፣ የመንግስት ደንብና መመሪያ … ሳይገድበው እዚህ ድረስ ዘልቋል።
እንዳልነው ለውጥ የትም አለ። ይኖራልም። ችግሩ የለውጥ ባህርያትን ካለመረዳት የተነሳ በርካቶች ቡድን መስርተው፣ ዘርና ወገን ለይተው እንዲቧቀሱ፤ ጦሳቸውም ለሀገርና ለህዝብ እንዲደርስ መደረጉ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናቶችን እያጣቀሱ ሰፋ አድርጎ ማየቱ ጥሩ ነው።
በዓለም አቀፉ የሰላም ተቋም (IPI) አማካኝነት የተጠናው “Strategies for Political Transition Planning” እንደሚለው በየትኛውም መንገድ የሥርዓትም ይሁን የአመራር ሽግግር ይደረግ ወይም ምርጫ ሁለቱም ለውጥ/ቼንጅ ናቸው። በሁለቱም መንገድ ነባሩ ዞር ብሎ አዲስ ሃይል ወደ አመራር ይመጣል። ሆኖም አንዳንዶች፤ በተለይም ነባሩ አመራር ይህን አምኖ ለመቀበል ሲቸገር ይታያል።
ሌላውና በጥናቱ የተገለፀው በለውጥ ጊዜ ለሚፈጠር ችግር እንደ መንስኤ የተቀመጠው የቀድሞው አመራር አዲሱን አመራር ለምን በእኔሐ ጊዜ ተግባራዊ ሲደረጉ የነበሩ ደንብ እና መመሪያዎችን ብቻ አታስቀጥልም፤ ለምን አዳዲስ አሰራር ታመጣለህ የሚል ቆሞ ቀር አስተሳሰብ ነው። እንደ ጥናቱ ከሆነ ይህ ስህተት ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ወደ መንግስታዊ አመራርነት ሲመጣ ሊያስፈፅመውና ሊያከናውነው የሚፈልገው ዓላማ አለው። ያንን ነው ተግባራዊ ሊያደርግ የሚጥረው እንጂ የቆዩ ስህተቶችን ሊደግም አይደለም። በመሆኑም ለዚሁ አጀንዳው በአግባቡ ተፈፃሚ መሆንም አላማዬን ያስፈፅሙልኛል ያላቸውን ከጎኑ ማድረጉ የማይቀርና የሚጠበቅ ፖለቲካዊ እርምጃ ነው። ዋናው ነገር ይህ ሁሉ ሲሆን ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ መሆኑ ላይ ነው።
ችግሩ ያለውና ለውጡ በተፈለገው መንገድና አቅጣጫ እንዳይሄድ ወይም እንዲሰናከል የሚያደርገው የቀድሞው አመራርም ሆነ ሌሎች በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ አለን የሚሉ ወገኖች ይህን አምነው መቀበል ሳይችሉ ሲቀሩና ለውጥ ጠል ሲሆኑ ነው።
የጠቀስነው የሰላም ተቋም ጥናት ይህንኑ የለውጥና የሽግግር ጊዜ ትኩረቱን ያሳረፈው በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ አገራት ላይ ሲሆን፤ በእነዚህ አካባቢዎች የተደረጉ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን፣ የተቃውሞዎቹ መሰረታዊ መነሻዎችን፣ የመጡ ለውጦችን ነባሩ አመራር ለውጡን ለመቀበል ያለመፈለግ እምቢተኝነት አቋምና ይህም ያስከፈለውን የከፋ ዋጋ መረጃዎችን ጠቅሶ ይተነትናል። ግብፅ፣ ቱኒዚያና ሊቢያን ከመሳሰሉት አገራት ተገቢውን ልምድ መውሰድና ለውጥን ተቀብሎ የለውጡ አካል በመሆን አብሮ መስራትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስፈን እንደሚገባም አስረግጦ ያብራራል።
ሌላውና ርእሰ ጉዳዩን በዚህ ዙሪያ ያደረገው “The Problem of Political Transitions in Africa: The Cameroon Question” (2012) እንደሚያስረዳው አፍሪካ፤ በተለይም ከሰሀራ በታች ያሉ አገራት ምን ጊዜም ሁከት ያልተለያቸው ሲሆን ከእነዚህ ሁከቶችም አንዱ ለውጥን መቀበል ካለመቻል (ለውጥ ጠል መሆን) ምክንያት የሚከሰተው ነው።
እንደዚህ ጥናት መዘርዝር ከሰሀራ በታች ባሉና ቀደም ሲል በፈረንሳይ ቅኝ የተገዙ የአፍሪካ አገራት ብዙ ጊዜ ለፖለቲካ ለውጥ ወይም ሽግግር የተጋለጡ ናቸው። ለዚህ ደግሞ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ስልጣንን ዘላለማዊ አድርጎ ለመያዝ መሻት፣ ለዚህም ህገ-መንግስትን እስከ መቀየር ድረስ መሄድ፣ አምባገነንነት፣ ስር የሰደደና ቅጥ ያጣ ሙስና፣ የከፋ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት፣ የመሳሰሉት መሆናቸውን ያስረዳል። መንግስታት ከዚህ ዘመን ከተጠየፈው ተግባራቸው ካልራቁ በህዝባዊ አመፅ መገፍተራቸው እንደማይቀርም ያስጠነቅቃል።
ኮትዲቯር፣ ጋቦን፣ ቶጎና ጊኒን እስከ እለተ ሞታቸው ድረስ ከመሯቸው አምባገነን መሪዎች ጋር እየዘረዘረ የሚያቀርበው ይህ የጁሊየስ አግቦር እና የጆን ሙኩም ኢምባኩ የጋራ ጥናት በርካታ አስገራሚ ፖለቲካዊ ክስተቶችን በማስረጃነት ያቀረበ ሲሆን ከሁሉም አስደማሚው ግን እነዚህ መሪዎች ስልጣን ከጉያቸው እንዳይወጣ ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ማሳየቱ ነው። በተለይ የካሜሮንን ከሁሉም የከፋ የሚያደርገው ህገ-መንግስታዊ ምክር ቤትም ሆነ ሌላ ውሳኔ ሰጪ አካል የሌላት መሆኑ መንግስት ምንም አይነት ሀይ ባይ አካል እንደሌለው ያሳያል።
ይህ ባለአስራ ሶስት ገፅ ጥናት ከሸፈናቸው መካከል “የተሻለና ሰላማዊ ሽግግር ተደረገ” ሲል “ያሞገሳት” አገር ያለች ሲሆን እሷም ጋቦን ነች። በጋቦን ስልጣን ከአባት ወደ ልጅ ሲተላለፍ ሰላማዊ እንደነበር “Except in Gabon, where the death of President Bongo resulted in a peaceful transfer of power to his son” ሲል የሚሳለቀው ጥናት በሌሎች አገራት ደም አፋሳሽ የስልጣንና የሥርዓት ሽግግር የሚካሄድባቸው መሆናቸውን ይገልፃል። በአፍሪካ ለውጥም ሆነ ሽግግር ያለ ሁከት፣ ብጥብጥ፣ ሰብአዊ ቀውስና ቁሳዊ ውድመት ውጪ እንደማይታሰብ የሚናገረው ጥናቱ አፍሪካ ከዚህ ወጥታ የሚያይበትንም ጊዜ ይናፍቃል።
“Challenges of democratic transition in Africa” በሚል የቀረበው ጥናትም ከላይ በዋቢነት የጠቀስናቸውን ከማጠናከር ባለፈ ጉዳዩን ሲያቀለው አይገኝም። ለየት የሚያደርገው ቢኖር በአፍሪካ ሽግግርና ተግዳሮቶቹ አይነተ-ብዙና እጅግ ውስብስብ መሆናቸው ላይ ማተኮሩ፤ አምባገነን መሪዎች ለስልጣናቸው እስከ እለተ ሞታቸው ብቻ ሳይሆን ግብአተ ምድራቸው ድረስ ለማቆየት የቀድሞ ቀኝ ገዥዎችን ህግጋት መልሶ ወደ ህጋቸው ማምጣት ድረስ መዝለቃቸውን ማሳየቱ ነው። እንዲሁም አፍሪካን ካለችበት አዘቅት ለማውጣትና ወደ ፊት ለማራመድ ከተፈለገ አዳዲስ የዴሞክራሲ ሃይላት ወደ መንግስት አመራርነት መምጣት እንዳለባቸውና በቀድሞዎቹ፤ ብቃት በሌላቸውና በሙስና በተጨማለቁ መንግስታት አማካኝነት የተንሰራፉ ድህነትን፣ መሃይምነትን፣ ጦረኝነትን እና ኋላ ቀርነትን በመታገል ማስወገድ እንደሚገባቸው ምክር ይሰጣል።
እኛም እንላለን፤ እባካችሁ የተጀመረው ለውጥ ይቀጥል ዘንድ ሁላችንም ሃላፊነታችንን እንወጣ። ለውጡ የህዝብ ብሶት የወለደው፤ አገራችን እየተከተለች ያለችውም አቅጣጫ የህዝብ ነውና በጥቂቶች እንዳይቀለበስ እንከላከል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፤ በጊዜያዊ ጥቅምም ይሁን ባልተገባ ጀብደኝነት፣ በስልጣን ጥምም ይሁን በስልጣን ጉጉት የተጀመረውን ህዝባዊ ለውጥ ለማደናቀፍ አንጣር። ባጭሩ በአፍሪካችን ተምሳሌት እንሆን ዘንድ ለውጥ ጠል አንሁን።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 24/2012
ግርማ መንግሥቴ