ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግራቸው፣ ሃሳብን በነፃነት ስለመግለፅና ስለ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የሚከበረውም ሆነ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን የሚሆነው ጠንካራ የመገናኛ ብዙኃን ሲኖሩ እንደሆነ አይካድም፡፡ እርሳቸውም ቢሆኑ ይህን ጉዳይ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ከተመዘገቡ ለውጦች መካከል አንዱ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የታየው መሻሻል ተጠቃሽ ነው፡፡
ሃሳብን በመገናኛ ብዙኃን የመግለፅ ነፃነት መሻሻል አሳይቷል፡፡ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አመለካት ላላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እድል በመስጠት ሃሳባቸውን እንዲገልፁ የማድረግ ጅምሮችን አሳይተውናል፡፡ ይህም እርምጃቸው ህገ-መንግሥታዊ እውቅና ያለው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲከበርና የሃሳብ ብዝሃነት እንዲኖር ያደርጋል፡፡
መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ያደረጉ እንደ ኢሳት (ESAT) እና ኦ.ኤም.ኤን ያሉ (OMN) መገናኛ ብዙኃን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንም እነዚህን ጣቢያዎች እያጣቀሱ ዘገባዎችን መስራት መጀመራቸው ሊበረታታ የሚገባው ትልቅ የእርምጃው ፍሬ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ታግደው የነበሩ በርካታ ድረ-ገፆችም እገዳው ተነስቶላቸው ወደ ቀድሞ ስራቸው ተመልሰዋል፡፡
በሕትመት መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እየታየ ያለው መነቃቃት ደግሞ ለሁሉም የሚታይ የዶክተር ዐቢይ አስተዳደር የለውጥ እርምጃ ውጤት ነው፡፡ ብዙ አዳዲስ ጋዜጦችና መጽሔቶች ገበያውን ተቀላቅለዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ‹‹ኢትዮጲስ፣ አዲስ ማለዳ፣ በረራ፣ ፍትሕ፣ ጉለሌ ፖስት» እና ሌሎችም የሕትመት ውጤቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ጋዜጣዎችና መጽሔቶች የተለያየ አመለካከት ላላቸው ኅብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ በመሆንና አማራጭ ሃሳቦችን ወደገበያው በማቅረብ ሁሉም ዜጋ በአገር ግንባታ ሂደት ላይ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ እድል ይሰጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው አስተማማኝ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግም በዋጋ የማይተመን ሚና ይጫወታሉ፡፡
ሲ.ፒ.ጄ (Committee to Protect Journalists – CPJ) የተባለው ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ቡድን የቦርድ ሊቀመንበር ካትሊን ካሮል በኮሚቴው የ2018 ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ሽልማት (International Press Freedom Award) መርሃ ግብር ላይ ሲናገሩ ‹‹በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰረ ጋዜጠኛ የለም፤ ይህ ሲሆን በአገሪቱ ከ13 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው›› ብለዋል፡፡ ለዚህም የኮሚቴው ቦርድ ትልቅ አድናቆት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በእውነቱ ይህ ትልቅ ስኬትና ኩራት ነው! ለወትሮው በዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ቡድኖች ስሟ በክፉ ሲነሳ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬ በነዚሁ ተቋማት አድናቆት ሲቸራት መስማት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይና ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም (UNESCO) የ2019 የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን (International Press Freedom Day) በኢትዮጵያ እንዲከበር መወሰኑ እንደቀላል ነገር የሚታይ ውሳኔ አይደለም፡፡ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ያለው ልምድ እንደሚያሳየው ቀኑን እንዲከበርባቸው እድል የሚሰጣቸው አገራት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት እንዲከበር ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩና በዘርፉም ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ የቻሉ ናቸው፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያም ከእነዚህ አገራት ተርታ የሚያሰልፋትን እድል ያገኘችው እንዲሁ በስጦታ ነው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡
የተቋሙ የኢትዮጵያ ተወካይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር እየወሰዳቸው ያሉትን የለውጥ እርምጃዎች በተለይ ደግሞ የአገሪቱን የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ለማሻሻል የሚከናወኑትን ተግባራት እንደሚደግፉና እንደሚያደንቁ ገልጸው ነበር፡፡ በአጭሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃዎች ተቋሙ በአገሪቱ ላይ ተስፋ እንዲጥል ስለማድረጉ አመላካች ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት አዎንታዊ እርምጃዎችና ለውጦች ሁሉ ለውጡን ዘላቂ ለማድረግ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡
ይሁን እንጂ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እነዚህ በጎ ለውጦች ቢታዩም፣ አሁንም ዘርፉ መሻሻል ያላሳየባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ላብራራ፡፡ ለውጡ ያልቀየረው የዘርፉ ዋነኛ ችግር የሙያዊነት (Professionalism) ጉዳይ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃኑ (በተለይ የራዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች) ርዕሰ ዜናዎች፣ ጉዳይ መረጣና ተያያዥ ሙያዊ ጽንሰ ሃሳቦች ከትናንቱ ያልተለወጡ ሆነው ይታያሉ፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ራሳቸው አጀንዳ ቀርፀው ከመስራት ይልቅ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ መነጋገሪያ የሆኑ ጉዳዮችን በመውሰድ ብዙ እሴት (Value) ሳይጨምሩባቸው ያቀርቧቸዋል፡፡
ግጥም ጽፎ ሬዲዮ ላይ ቀርቦ ግጥሙን ያነበበና ፌስቡክ ላይ መረጃ የሚለጥፍ (ምናልባትም መረጃው የውሸት መረጃ ሊሆን ይችላል) ሰው ሁሉ ‹‹ጋዜጠኛ›› ተብሎ በሚጠራበት አገር ትክክለኛውን የጋዜጠኝነት ሙያ ደንብ ለመተግበር እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የጋዜጠኛውም ሆነ የተቋማቱ አመራሮች የየራሳቸው ሚና አላቸው፡፡ እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለስልጣኖቻቸው ተቋማቱ ስራቸውን በነፃነት እንዳይሰሩ ከሚደረግባቸው ጫና እንዲላቀቁ መንገዶችን ያመቻቻሉ እንጂ፣ ለእያንዳንዱ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያ ጠንካራ ሥራ አስኪያጅ የመሆን አልያም ለእያንዳንዱ ጋዜጣና መጽሔት ጥሩ ዜና የመፃፍ ኃላፊነት የለባቸውም፡፡
ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ‹‹በአንድ ራስ ሁለት ምላስ›› የሆነው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ገዢ ሲቀያየር ውዳሴውንና ኩነኔውንም እየለወጠ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ‹‹ሰማይ አይታረስ፤ንጉስ አይከሰስ›› በሚለው ብሂል ‹‹አንበሳ አጉራሹ ግርማዊ ጃንሆይ›› ብለው ያሞገሷቸውን ንጉሥ በሌላ ጊዜ ‹‹ስልጣናቸውን ለግል ዝናቸውና ክብራቸው ያዋሉ››፣ ‹‹ከጓድ ሊቀ-መንበር መንግሥቱ አመራር ጋር ወደፊት›› ብለው የዘመሩላቸውን ሰውዬ ደግሞ ከጊዜ በኋላ ‹‹አምባገነን፣ ጨቋኝ፣ ነፍሰ በላ…›› የማለት አባዜ የተጠናወታቸው ተቋማት ናቸው፡፡
ዛሬም ቢሆን መገናኛ ብዙኃን ከዚህ መጥፎ ባህሪያቸው ተላቀዋል ማለት አይቻልም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አስተዳደር የሚተቹ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን (በተለይ የራዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች) በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ በአስተዳደሩ ላይ ትችት ሲያቀርቡ የሚስተዋሉት በውጭ አገራት የነበሩና ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እየሰሩ ያሉ ጣቢያዎች ናቸው፡፡መቼም እውነተኛ መሰረት ያላቸው ትችቶች ለአስተዳደሩም ሆነ ለለውጡ መጠናከር ትልቅ ጥቅም እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገባ ያውቃሉ የሚል ሙሉ እምነት አለኝ፡፡
እዚህ ላይ ‹‹መገናኛ ብዙኃኑ መተቸት ያለባቸ
ውን ጉዳዮች የማይተቹት በማን ድክመት/ችግር ነው›› የሚለው ጉዳይ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡
እኔ በበኩሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፉ እንዲያድግ ፍላጎት ያላቸው ሰው እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊትም ያደረጓቸውን ንግግሮች ብንመለከት የንግግሮቻቸው ትኩረት ምክንያታዊ ኅብረተሰብን መፍጠር ላይ ያተኮሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ምክንያታዊ ማኅበረሰብ ሊፈጠር የሚችለው ደግሞ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ባሕል ሲዳብርና ይህን የማስፈፀም ብቃት ያላቸው እንዲሁም በኅብረተሰቡ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስሪት ላይ በጎ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ ጠንካራ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ሲኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ለመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ማደግ የሰጠውን ትኩረት መጠቀም አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አማራጭ የሌለው አስገዳጅ ተግባርም ጭምር ነው፡፡
ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እንዲያድግ ትልቅ ፍላጎት ቢኖራቸውና ጥረት ቢያደርጉም ይህ ጥረት በየደረጃው ባሉ የአመራር አካላት ካልታገዘ ፍላጎታቸውና ጥረታቸው ሊሳካ አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ከመተግበራቸው የተነሳ ስህተት ሆነው ሳለ ሕግ ሆነው የቀሩ አሰራሮች አሉ፡፡ ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት ለኅብረተሰቡ አለመስጠት የተለመደ መንግሥታዊ አሰራር ሆኖ በመቆየቱ መረጃ አለመስጠትና መዋሸት እንደትክክለኛ አሰራር ተቆጥረው ቆይተዋል፡፡
በእኔ አመለካከት ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ከዳረጓት ምክንያቶች መካከል አንዱ ጠንካራ የሆነ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አለመኖሩ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ካላቸው መረጃ የመስጠት፣ የማስተማርና የማዝናናት ሚና በተጨማሪ ተፅዕኖ የመፍጠርና የማሳመንም ሚና አላቸው፡፡ ጠንካራ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ባሉበት አገር የሕዝብ ንቃተ ህሊና ያድጋል፤ሙስና ይዳከማል፤ሕዝብ የመንግሥትን አሰራር እንዲያውቀው ይደረጋል፤መንግሥትና ባለስልጣናት ይወቀሳሉ/ ይተቻሉ፡፡ በዚህም የተበላሸው ይስ
ተካከላል፤የተስተካከለው ይጠናከራል፡፡ ጠንካራ የመገናኛ ብዙኃን የሌሏት ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ዘርፈ ብዙ ችግር ውስጥ እንደገባች የችግሩን ገፈት በየቀኑ እየቀመስነው ነው፡፡ ጠንካራ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መገንባት ካልቻልን ጉዟችን ሁሉ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡
አሁን እድሉ ተገኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍን ተዘፍቆበት ካለው ችግር ውስጥ ማውጣት አገሪቱ ካለችበት ዘርፈ ብዙ ችግር እንድትወጣ ትልቅ አስተዋፅዖ ስለሚያበረክት እድሉን በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2011
አንተነህ ቸሬ